ከደርግ ወደ ጎሣዊ ደርግ- “ግንቦት 20” (ክፍል ፫)

በህገ-ወጥ መንገድ ከሚሰደዱ ዜጎች ውስጥ 60% የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። እንደ UNHCR (2013፣ 2014፣ 2015፣ 2016) ሪፖርት የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ ሄዷል። ስደተኞቹ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ የዘለቀ የትምህርት ደረጃ ያላቸው፣ አነስኛ የሙያ ክሂል ባለቤት የሆኑ፣ የሚሰደዱበትን አገር መዳረሻ በቅጡ ያልለዩ፣ ከውጪ አገር ዜጎች ጋር የመግባቢያ ቋንቋ ችግር ያለባቸው መሆኑ የስደተኞቹን መከራ አብዝቶታል።
በደቡብ አፍሪካ፣ በሊባኖስ፣ በኩዌት፣ በቤሩት፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ … ወዘተ በመሳሰሉ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አረብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በግፍ ተገድለው በአደባባይ መጣላቸውን፣ በመኪና አደጋ ህይወታቸው ማለፉን፣ ከፎቅ ላይ ራሳቸውን በመፈጥፈጥ ህይወትቸውን ማጥፋታቸውን … መሰል አሰቃቂ የዜና ዘገባዎች እንደ ሜትሮሎጂ ዘገባ በየዕለቱ መስማት ከጀመርን ውለን አድረናል። የዜጎቹ የመከራ ዜና ግድ የማይሰጠው ህወሓት/ኢህአዴግ በብዙ ጭንቀትና መከራ ስደተኞቹ የሚያገኙትን ገንዘብ ለቤተሰብ መደጎሚያ ወደ አገር ውስጥ መላካቸው የምንዛሬ እጥረቱን የሚሸፍንለት በመሆኑ ህገ ወጥ ስደቱንም ቢሆን በበጎ ጎኑ ይመለከተዋል። የአገዛዙ ጭንቀት የምንዛሬ እጥረት እንጅ የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የመከራ ህይወት ግድ አይሰጠውም።
ምዕራባዊያኑም ቢሆን ለራሷ ዜጎች መሆን አቅቷት በወደቀ አገዛዝ ስር የምትከላወስ አገር መሆኗን እያወቁ “ኢትዮጵያ የስደተኞች ቤት” ሲሉ ከደቡብ ሱዳን የምንሻል መሆናችንን በምፀት ይነግሩናል። ራሱን ከሱማሌያ እና ከኤርትራ ፈራሽ “መንግሥታት” ጋር የሚያወዳድረው ህወሓት/ኢህአዴግ የራሱን ዜጎች አሰቃቂ የስደት ገመና ደብቆ ስለጎረቤቶቹ ያወራል።