ኦቦ ለማና ህወሃት

አቶ ለማ መገርሳ የመንግስት ባለስልጣን ሆኖ በቆየበት ጊዜ ሁሉ ሲያስገድል፣ በሀሰት ሲያስወነጅል፣ ሕዝብን ከሕዝብ ሲያባላ እና በድህነት እንድንሰቃይ ለሙስና ሲያጋፍር ነው የኖረው። ሌላውን የኢህአዴግ ባለስልጣን አስኮንኖ፣ አቶ ለማ እና ዶ/ር ዐብይን ነጻ የሚያስወጣ ምንም ዓይነት ምክንያት የለንም።

ማሽሞንሞን ሳያስፈልግ፥ አቶ ለማ መገርሳ የኢህአዴግ ሽንት ጨርቅ ነው። የአምባገነን ስርዓት ሽንት እንዳይታይ በማድረግ ረገድ የሚጫወተው የዳይፐርነት ሚና ከደረሱብን ጉዳቶችም የሚልቅ እና፣ ለዚህ ግብሩ መጨፈር እና መቀኘታችን ወደፊት ብዙ የሞራል ዋጋ የሚያስከፍለን ነገር ነው የሚሆነው።

ኢህአዴግ በሽንት መጨማለቁን ስላወቀ እና በሕዝብ ጠንካራ ተቃውሞ ስለተናጠ፣ እሱን የሚሰበስብለት እና የሚያቋቁመው ‘poker face’ ሲፈልግ ነው አቶ ለማን ያገኘው። በተቃውሞ ወቅት በታዩ ምልክቶች መሰረት፥ የሽንት ጨርቅ የሚሆነው እና የዘረኝነት ሀፍረቱን የሚጋርድለት የኢትዮጵያዊነት ጨርቅ መሆኑን ስለሚያውቅ፣ እሱን እያወሩ በተለይ ተቃውሞዎቹ ጠንክረው በነበረበት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችን ልብ የሚያሸፍትለት ሲፈልግ ነው አቶ ለማን ከጉያው ፈልቅቆ፥ ፊት ያዋለው።

መንግስት ከወጣበት ማቅ ለመውጣት እና ዕድሜ ለመግዛት ያለውን ብቸኛ አማራጭ፥ ኢትዮጵያዊነትን ለማቀንቀን ፍላጎት እንዳለው ያየነው ቀደም ብሎ ሽንት ጨርቅ ኀሠሣ ላይ ሳለ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በደነገጉ ማግስት እንኳን “ኢትዮጵያዊነት ላይ አልሰራንም” ብለው በይፋ መናገር ጀምረው እንደነበረ አውስተነዋል። እሱን ተከትሎ፥ ከሌላ ጊዜው በተለየ መልኩ የአድዋ ድል በዓልን በመንግስት ደረጃ በሰፊው ለማክበር ላይ ታች መባሉ እና፣ አድዋ ድረስ ተሂዶ የእምዬ ሚኒልክ ፎቶ በሌለበት በእቴጌ ጣይቱ ፎቶ ብቻ መከበሩም አይዘነጋም።

በኢቲቪ እና ኤፍኤም ሬድዮዎች፥ ዘመቻ በሚመስል መልኩ፣ ሰዎችን ስለብሔራዊ የድል በዓላት እየጠየቁ ከመለሷቸው አሳቃቂ መልሶች ጋር ሳያፍሩ ማስተላለፍ እና በራሳቸው ጊዜ የቦረደሱትን ክፍተት ለመሙላት ፈቃደኝነት ያላቸው እስከማስመሰል ድረስ፣ የተላለፉትን ዝግጅቶችም ተመልክተናል። የነአቶ አባዱላ መግባት እና መውጣት፣ የወ/ሮ አዜብ መታገድም እንዲሁ ካለምክንያት አይደለም። ካለስሌት የሚያደርጉት ምንም ነገር የለም! እኛ ግን በዚህ ሁሉ ሂደት አልፈንም ሣሩ እንጂ ገደሉ እንዳይታየን በ“ኢትዮጵያዊነት” ስም መጥተው በእነሱ ጊዜ ይዘውሩናል።

አሁን ሰሞንኛ ሽውታ እና ትኩሳት ላይ ስላለን፥ ይህን መስማት የሚያስከፋቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ግን እውነቱ ባለበት ነው። የሚናፈቀው ለውጥ እና ከሰቆቃ አኗኗር ለመላቀቅ የሚደረገው ጥረት ለመጓተቱ እና እያንዳንዱ ተስፋ ብላሽ ለመቅረቱ፥ የእኛው ሚና ከፍተኛ ነው።

አቶ ለማ እንዴትም አድርጎ በንግግር ቢራቀቅ ኢህአዴግ በፈቀደለት ልክ ነው የሚንቀሳቀሰው። ገመዱን እነሱ ይዘውት ሲለቁት በረዥሙ ይሄዳል፣ ሲሰበስቡት ደግሞ ይሰበሰባል። ምክንያቱም ታማኝ ወዳጃቸው ነው። አቶ ለማን የመለመለው፣ ያሳደገው እና ጡት እያጠባ ጎኑ ያኖረው ኢህአዴግ ነው። ስለዚህ እሱ የሚናገረው ነገር በሙሉ ኢህአዴግ የሚያውቀው እና ክትትል የሚያደርግበት ነው እንጂ እኛ በገራገርነት እንደምናስበው መንግስት ላይ ነጥብ እያስቆጠረ እና ነጥብ እያስጣለ አይደለም። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ምንም ነውር የማያውቁ ስለሆኑ፣ የፈለገውን ያደርጉ ነበር። እሱም ያንን እያወቀ የምር ኢትዮጵያዊ ስሜት ካለው ደግሞ፥ አብዮት ለማቀጣጠል እና ተጽህኖ ለመፍጠር ሽቁጥቁጥ የሚሆንበት ነገር የለም።

ሆኖም ግን፥ ለመንግስት ገጽታ ጥሩ ሽፋን ስለሆነ ከእኛ በላይ መንግስት ይወደዋል። (ኮካዎች ቢሰድቡት ለመላ ነው እንጂ ባለውለታዎቹ እንደሆኑ ግልጽ ነው። ሚሚ አባ ዱላን እንዴት እንዴት ስታብጠለጥል እና ወንጀለኛ መሆኑን ስትናገር እንደነበር አይረሳም።) እሱም እዚያ ያለው በስሌት እና በተልእኮ ነው እንጂ ሕዝብ አፍቅሮ ለውጥ ለማምጣት አይደለም። መፍትሄው በኢህአዴግ ዘንድ መሆኑን ለሕዝብ ለማስመስከር የሚተጋ ሀዋርያ ነው። ኢህአዴግ ጠላቱን አይንቅም። በግለሰብ ደረጃ ኑሮውን የሚኖር ጸሐፊ እንኳን እንደ ትልቅ ቁም ነገር አስልኮ ሲያስጠብቅ፣ አፉን ሲለካለት እና ሲያሰቃይ ነው የሚኖረው። የዚያኑ ያህል ደግሞ ከሂሳቡ የሚዛነፍ ወዳጅነት ቢኖርም አይራራም። “አብዮት ልጆቿን ትበላለች” ይሰራል። “ደማችን ፈሶለታል” ብለው በይፋ የሚናገሩለት ወንበር ዙሪያ መዝነው ያላከበዱትን ከፊት አያሰልፉም።

ሰፊው ሕዝብ ግን፥ ባህርዩ ሆኖ ንግግር ያስደምመዋል። ሲሰድቡት እና ሲያንገላቱት ኖረው “የኔ ጌታ” ሲሉት ልቡ በኀዘኔታ እና ፍቅር ትርክክ የሚል ሩህሩህ ሕዝብ ነው ያለን። ከዚህ ቀደም የነበሩ እምነት የተጣለባቸው ሰዎችን ታሪክ ብናይም እንዲሁ በንግግር ተማርከንባቸው ነው እንጂ… ሰው ተቀምሶ አይታይም መቼስ። እንዳንተባበር እና በጋራ እንዳንመክር፥ በአጀንዳቸው ለያይተውን ዞረን እንዳንገናኝ፣ በንግግር ያምታቱናል። ከዚህ ጉድ ይውጡ እንጂ፣ በኢቲቪ በቀጥታ የሚተላለፍ የጠንቋይ ማምለክ እና የድንጋይ ቅቤ መቀባት መርሀ ግብር ከማድረግ እንኳን ወደ ኋላ የማይሉ አፍረተ ቢሶች ናቸው።

መንግስት በእኛ የሆይሆይታ ድጋፍ እና ተቃውሞ ተደጋግፎ ከጉድ እየተረፈ፣ ሲጎነጉን የጎለመሰው ሴራ እንዳይጠልፈው ደርሰን እየፈታንለት አይዞህ እያልነው ነው ያለው እንጂ ከበቃው ድሮ ነበረ። ባልበሰለ እርካታ አባዜያችን (premature ejaculation) ተይዘን፣ በንግግር እየተማረክን ተባብረን አለን። ጠላትን መናቃችን፣ አሳንሰን ማየታችን እና ማጣጣላችን ይበልጥ እንዲፈነጭብንና እንዲያላግጥብን ነው የሚያደርገው።

ጠብ ገጥሞ የቆሰለ አውሬ ይበልጥ ይቆጣልና፥ “አያ በሬ ሆይ ሣሩን አየህና፣ ገደሉን ሳታይ” እንዳይተረትብን፥ በእነሱ ዘንድ የሚወደስ፣ የሚገጠምለት እና የሚሳልለት መልካምነት ካላቸው እሱን ለእነሱ እንተውላቸውና እርስበርሳችን እንተያይ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያችንን ይጠብቅልን!

ከዮሐንስ ሞላ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑