አትቀስቅሷቸው!

አትቀስቅሷቸው
በሰላም ይረፉ፡ አትቀስቅሷቸው
 አትዘኑላቸው
 አታልቅሱላቸው። 

 ራሄልም የለች፡ ዕንባዋ 'ሚሻገር
 ሙሴን 'ሚጠራ፡ ከጸባዖት ቅጽር
 ለእኛው እናልቅስ
 ልጅነት ህሊና፡ ላስጨነገፈ
 ነፍስ እናትነትን፡ ላዘነፈ
 ሀዘን እምነትን፡ ለዘረፈ። 

 ለ'ኛ ፈርዖኖች
 ለልበ ደንዳና
 ለጭካኔ ጀግና
 ከጎጥ ሰው ፈንካች
 ለአዛኝ ቅቤ አንጓች
 ለሚወድ በጭፍን፡ ሚጠላ በድፍን
 ለአዞ እ'ባ አፍላቂ፡ መርጦ ለሚያዝን። 

 ይሂዱ ይተኙ፡ እነሱስ አረፉ
 በእኛው ኃጢያት ለጽድቅ ተሰለፉ
 ልመናስ በነርሱ፡ ምስክር ለሞሉ
 ለ'ውነት ለቀረቡ፡ ሕይወት ለታደሉ። 

 ለ'ኛ ለከንቱዎች 
 ለበላዔ ሰዎች
 አስብቶ አራጆች
 ከእርዳችን መሐል፡ ጽድቅ ፈላጊዎች
 ሰብአ ነውረኞች!!!!

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑