በእንተ ጾም

በ pdf ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

  • ጾም ከኃጢአት ወይስ ከምግብ መከልከል?
  • የጥሉላት ምግቦች ርኩሳን ናቸውን?
  • ሥጋ በፍላጎቱ ላይ ልጓም ያስፈልገዋልን?
  • ሁሉን እንበላ ዘንድ አልተፈቀደምን?
  • የጾም በያይነቱ- እንደመካሻ?
  • መጠጥ፣ ሩካቤ ሥጋና ጾም
  • ጋድ፣ ቅዳሴና በዓል በነብያት ጾም

እንደ መግቢያ . . ..

የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ መቀየር፣ የባህል፣ ልማድና ትውፊት መወራረስ፣ የቄሳር ዐለም ርዕዮት መለዋወጥና የመሳሰሉት ጉዳዮች የአስተሳሰባችንን አቅጣጫ፣ እይታና አረዳድ ይሞርዱታል፣ ያርሙታል። የዚህ ለውጥ ቀጥተኛና የመጀመሪያ ተጠቂ ደግሞ የሃይማኖት ትምህርት ነው። ትምህርቱ እንዲስተካከል አሊያም እንደየሰብዕ ምልከታ እንዲገራ ፍላጎት ይበረታል። እርግጥ ነው የሰው ባሕርይ አላዋቂ ነውና ሁልጊዜ በመማርና በማወቅ ላይ ይገኛል። ስለዚህም ይህን ዓይነት ለውጥ የሚጠበቅና ጤናማም ነው። በተጨማሪም ሃይማኖት የሰውን ጸባይ የማነጽ ድርሻው ተነጥቆ ስላልጠፋ የለውጡን ሰሪነት ሚናም ይወስዳል።

በሰው ልጅ ታሪክና አስተሳሰብ አድማስ እስካሁን ሰው ከእምነት ነጻ መሆን አልቻለም። አይችልምም። ለዚህም ድካም ማስታገሻ እምነትን ከሃይማኖት የመነጠሉን ሥራ አጥብቆ በመስራቱ የነጻ ፈቃዱ አማኝ የሆነ ሰውን ማግኘት አዳጋች አይሆንም። ይህም እምነቱ ልቡ የሚመርጠውን መንፈሱ የሚከተልበት ከቆይታ በኋላ ልቡ ባይሻው ሊቀይረው ወይም ሊተወው ነጻ ምርጫው (ለልቡ ምኞት ህግና ትዕዛዝ ስለሌለው- [አለው ግን ራሱ የሚያወጣው ራሱ የሚፈጽመውና ራሱ የሚቆጣጠረው መሆኑ ነው’ጂ]) የሚፈቅድለት ሕይወት ነው።

ለዘመናት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ስትናገር እስከዚህኛው (እኛው) ትውልድ ድረስ የጸናችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን የመምስል ሕይወት እንዴት እንደሆነ በሕጎቿና ስርዓቷ ውስጥ ታስተምራለች በዚህ ሕይወትም ለመኖር ታድ’ላለች። ከዚህም ሕይወት አንዷ ጾም ናት። ፍትሐ ነገስት[2] የጾምን ትርጉም ባብራራበት አንቀጽ እንዲህ ይላታል “ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀ ጊዜ የሰው ከምግብ መከለከል ነው በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሰራለት እየታዘዘ የፈቲውን [ኃይለ-ፍትወት] ኀይል ያደክም ዘንድ ለነባቢትም ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ”[3]። ለዝንጉ አዕምሮ ንቃት፣ ለደከመ መንፍስ ብርታት፣ ለጠያቂዎችም ምላሽ ይሆን ዘንድ አቤቱ ድኩማን ለምሆን እውቀት ለሌለኝ እምጽፍበት ኃይለ ቃልህን ግለጽልኝ።

ጾምና መጽሐፍ ቅዱስ

ለአንዳንድ አማንያን ለሚያምኑበት ነገረ ጉዳይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ከመቀበል ይልቅ ለነጻ ፈቃዳቸው ትርጉም ደጋፊ ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስን እማኝ ማድረግ የቀለለ ይመስላል። መጽሐፍ ቅዱስ ሲጠቀስም ሰፍሮና ቆጥሮ ትዕዛዛትና ሥርዓትን አልሰጠም የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ።  ለዚህ አይነት መከራከሪያ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ለተመሳሳይ ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት መጻሕፋቸው የጻፉትን እንጠቅሳለን።

እግዚአብሔር አድሮ ቅዱሳት መጽሕፍትን ያጻፋቸው የሚያጽፋቸው ቅዱሳን ሰዎች ፫ ክፍል ናቸው በ፫ ይከፈላሉ። የጽሑፋቸው ዓላማም ፫ ዐይነት ነው። እኒኽውም ጸሓፍቱ ነቢያት፣ ሐዋርያት ሊቃውንት ናቸው። ዓላማቸውም የነቢያቱ ትንቢት የሐዋርያቱ የነብያት ትንቢት መፈጸሙን መስበክ ሲሆን የሊቃውንቱም ብሉያትና ሐዲሳትን እያስማሙ የተሰወረውን እየገለጹ አስፋፍቶ ከብሉያትና ሐዲሳት ግብ ሳይወጡ መተርጎም ነው።

ኹለተኛም የሊቃውንት ትርጓሜ መጻሕፍት ዓላማ ጌታ መጽሐፈ ኪዳንን እና ሐዋርያት ሲኖዶስንና ዲድስቅልያን[4] እንደጻፉ ሊቃውንትም ጉባኤ እያደረጉ ጌታ በመጽሐፈ ኪዳን ሐዋርያት በሲኖዶስ ከወሰኑት ግብ ሳይወጡ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት የሚ’ሾሙበትን የሚሻሩበትን ሕግ ማገግ የአጽዋማትን የበዓላትን ሥራት መደንገግ በጠቅላላው ቤተ ክርስቲያን የምትተዳደርበትን ውስጠ ደንብ መወሰን ነው።[5]

እዚህ ላይ የመጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁን ምሳሌ ለአጽኖት መጋበዝ የብሉይ፣ ሐዲስና የሊቃውንት መጻሕፍትን[6] በምሳሌ ለማስረዳት ይጠቅም ይሆናል። አንድ ቅቅል፣ ወይም ክትፎ ለመብላት የሚፈልግ ሰው የሥጋው የትመጣነት ከበሬ እንደሆነ ይረዳዋል። የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሬ እንደማለት ነው። የበሬ ሥጋ ለመብላት መታርድ ይኖርበታል። የሀዲስ ኪዳን መጻሕፍት የታረደ የበሬ ሥጋ እንደማለት ነው። መ’በለቱ ብቻውን ለምግብነት አያበቃውም። የሊቃውንት መጽሐፍት ደግሞ ከተበለተው ሥጋ በዐይነት የተሠራውን ምግብ ይመስላሉ።[7]

ሁሉም የሚያስፈልጉ ናቸው። ሂደታቸው የሚያስረዳን ማኘክና መዋጥ እንዲቀል የሚያደርጉ መሆናቸውን ከቅዱሳት መጻሕፍቱ አንጻር ለመረዳትና ለመገንዘብ ደግሞ እንዴት እንዲከብዱና በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ እንዴት እንደሚጠቅሙ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል”[8] ዳሩ ግና ቅዱስ ጴጥሮስ “በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።”[9] ያለውን ማስተዋል ይገባል።

የሚከተሉት ጥቅሶች በሕግ እና በፍቃድ መጾም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በውል የታወቀ እንደሆነና የእግዚአብሔርም ትዕዛዝ እንደሆነ ያስረዱናል። የመጀመሪያውስ የፈጣሪ ትዕዛዝ ‘አትብላ’ም አይደል። “ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ”[10]

ዘጸ ፳፬፥ ፲፰፣ ዘዳ ፱፥ ፱ና ፲፰-፲፱፣ ፪ኛ ሳሙ ፲፪፥ ፲፮-፪፣ ፩ኛ ነገ ፲፱፥ ፮-፰፣ ዕዝ ፰፥ ፳፩፣ ነህ ፩፥ ፬ (፩-፲፩)፣    አስ ፬፥ ፲፮፣ ዮና ፫፥ ፩-፲፣ ማቴ ፮፥፲፮፣ ፬፥፪፣ ማር ፱፥ ፳፱፣ ፩፥ ፲፫፣ ሉቃ ፮፥ ፳፩፣ ፪፥ ፴፯፣ ፬፥፪

በ፹ወ፩ መጻሕፍት ውስጥ ለይቶ በዚህ ወር ጹሙ ቅቤና ሥጋም አትብሉ የሚል አምላካዊ ትዕዛዝ የለም ለምትለውም ቢሆን ሰማንያ አሐዱ መጻሕፍት ሲኖዶስ ዲዲስቅልያ ጭምር ናቸው። ከ፹ወ፩ መጻሕፍት አንዱ የታወቀ ደዌ ካደረበት ሰው በቀር ጾመ ፵ንና ረቡዕን ዐርብን የማይጾም ካህን ቢሆን ይሻር። ሕዝባዊ ቢኾን ይለይ ይላል። ረሰጠጅ ፷፣ ረሰጠብ[11] ፵ወ፰[12]

ጾም ከኃጢአት ወይስ ከምግብ መከልከል ነው?

“ጾም ከእህልና ከውኃ መከልከል አይደለም። ከእግዚአብሔር ፊት የሚደርስ ጾምስ የልብ ንጽህና ነው። ሥጋ ቢራብ ቢጠማ ነፍስ ግን ፍቃዷን ብትፈጽም ልብም ከጣዕሙ የተነሣ ደስ ቢለው የጾምህ ጥቅሙ ምንድን ነው?”[13] ኢትዮጵያዊው ካህን ቅዱስ ያሬድ በ ጾመ ድጓው የሚጾመው ኃጣውእ የሚጾም ረቂቁ ሕዋሳት መኾኑን ዐውቆ “ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ወንትፋቀር በበይናቲነ. . . . . …. ዓይን ይጹም እምርእየ ሕሱም፣ ዕዝን ይጹም እምሰሚዐ ሕሱም፣ ልሳንኒ ይጹም እምተናግሮ ሕሱም”[14]  ጾምን ስንጾም ወንድማችንን በመውድድና እርስ በእርስ በመፋቀር ይሁን። እንዲሁም ስንጾም ሕዋሳቶቻችን ሊጾሙ ይገባል። እንደምን ነው ቢሉ ዓይናችን ከሚያየው፣ ጆሮአችን ከሚሰማውና አንደበታችንም ከሚናገረው ሊቆጠቡና ሊጾሙ ይገባቸዋል። ይህ ቢራዘም እጆቻችን ከሚዳስሱት፣ እግሮቻችን ከሚዳክሩበት፣ አፍንጫችን ከሚያሸቱትና ባጠቃላይ የሰውነታችን ክፍሎች አዕምሮና ልቡናን ጨምሮ በጾም ወራት ከለመዱት ውሎ ሊለዩ ይገባቸዋል።[15]

ከላይ ፍትሐ ነገስት ጾም ከእህል ውኃ መከልከል አይደለም ሲል ለረቂቅ ህዋሳትና ለኃጢአት መከልከል አጽንኦት ለመስጠት ነው’ጂ በመግቢያ ላይ እንደጠቀስነው “ጾም በሕግ ውስጥ በታወቀ ጊዜ የሰው ከምግብ መከለከል ነው” ብሎ ደንጓል።[16] በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱትም ጸዋሚዎች ከእህል ከውኃ ከሥጋ ከቅቤ ተከልከለው ማቅ ምንጣፍ ለብሰው እንደጾሙ ይነግሩናል።

ከጥሉላት ምግቦች ስለመከልከል

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መሆኑን አምነው ለሚከተሉት ልጆቿ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት የራሷ የሆነ ሥርዓት እንደየሁኔታው እያየች ለምዕመናን ታዘጋጃለች፡፡

ሥርዓት /ቀኖና/ የአማናንያንን መንፈሳዊ አኗኗር አንድ ለማድረግ፣ በጽኑዕ ሥጋና የአጋንንት ፆር ተሸንፈው ከሕይወት እንዳይባዝኑ ለማድረግ በአባቶች አማካይነት መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ሕግ ነው፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በአባቶች አማካይነት ታይቶ ሊሻሻልና ሊለወጥ የሚችል ቢሆንም ተቀባይነት ያለው ምክንያት ተገኝቶ በይፋ እስካልተገለጸ ድረስ ለሚጥሰው ሰው በደል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲናየናችን ይህንን መሠረት አድርጋ ከደነገገችው ሥርዓት አንዱ የጾም ሥርዓት ነው።

አስቀድመን እንዳልነው ጾም ሥጋን በማድከም የሥጋን ፍላጎቶች በመግታት የነፍስን ሥራ መሥራት ነው፡፡ ለዚህም ነው በጾም ወቅት ለሥጋ ምቾት ከሚሆኑና ሥጋዊ ፍላጎቶችን ከሚያነሳሱ ነገሮች ሁሉ የምንቆጠበው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ይህንኑ ያስረዳናል፡፡ የእሴይ ልጅ ንጉሥ ዳዊት በጾም ወራት ሥጋና ቅቤ እንዳልበላ እንዲህ ሲል ገልጿል፡፡ “ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፣ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ. . . ነፍሴንም (ሥጋዬንም) በጾም አስመረርኳት”[17] በተጨማሪም ራሱን በጾም በመወሰን ታላላቅ ራዕይ ለማየት የበቃው ነብዩ ዳንኤልም በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም።”[18] በማለት በጾም ወራት ፈቃደ ሥጋን ከሚያበረቱ ምግብና መጠጥ በሙሉ መቆጠብ እንዳለብን ያስተምረናል። የጾም ጊዜም የኃዘን ጊዜ እንደሆነ ይናገራል “ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ”[19] በዚህ መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን በጾም ወቅት ለተወሰነ ሰዓት ከምግብና ከመጠጥ ከመቆጠብ በተጨማሪ የጥሉላት ምግቦች ከሆኑት ሥጋና ቅቤ ከመሳሰሉት ምግቦች መከልከል እንዳለብን ታስተምራለች፡፡

ለሚጠራጠሩ ስለጾም የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያደርጋቸው ትልቁ ምክንያት ጾም የታዘዘበትን መሠረታዊ ዓላማ አለመረዳት ነው፡፡ አባቶች ምጽዋት የገንዘብ ስጦታ እንደሆነ ጾም ለነፍሥና ለፈቃደ እግዚአብሔር የሚቀርብ የሥጋ ግብር ነው ይላሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ መብል በእግዚአብሔር ዘንድ ግዳጅ አይፈጽምልንም፣ ብንበላም አይረባንም አይጠቅመንም ብንተወውም አይጎዳንም[20] እንዳለው።

ነብዩ ኢሳይያስ ጾማችንን እንዲህ እየፈተሸ ምላሽ ይሰጠናል ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን? እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል። የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም፦ እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ብትተው፥ ባታንጐራጕርም፥ ነፍስህንም ለተራበ ብታፈስስ፥ የተጨነቀውንም ነፍስ ብታጠግብ፥ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል። እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። ከዱሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሠራሉ፥ የብዙ ትውልድም መሠረት ይታነጻል፤ አንተም፦ ሰባራውን ጠጋኝ፥ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ ትባላለህ። ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፥ ሰንበትንም ደስታ፥ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው፥ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፥ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፥ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ፤ የእግዚአብሔር አፍ ተናግሮአልና።[21]

ጥሉላት እንደረከሱ?

ከዚህ ሌላ በጾም ወቅት ሥጋና ቅቤ መብላት ሰውነትን ያረክሳል ብላ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምር የሚመሰላቸው አሉ፡፡እዚህ ላይ በግልጽ መታወቅ ያለበት ክርስቶስ የቀደሰውን ነገር ሁሉ ቤተ ክርስቲያን አታረክሰውም፡፡ ክርስቲያን በጾም ሥጋ የማይበላው ያረክሰኛል ብሎ አይደለም፡፡ የሥጋን ፈቃድ በማድከምና ቀደመን የጾም ዓላማ ብለን የጠቀስናቸውን ለማሳካት እንጂ፡፡ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን አይጠቅመኝም”[22] በማለት እግዚአብሔር የነፃነት አምላክ መሆኑንና የሚጠቅመንንና የማይጠቅመንን ለይተን በነፃነት በሥርዓተ መመራት እንደምንችል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያስተምረናል፡፡ አንድ ክርስቲያን በጾም ሥጋ ቢበላ የሚነቀፈው የበላው ሥጋ ስለአረከሰው ሳይሆን ከወንድሞቹ በገብር በማነሱ የአባቶቹን ትእዛዝ በመጣሱና ሥጋን መብላት በመተው ከሚያገኘው ማዕረግ ስለተዋረደ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ሥጋ በመብላት ያሳየውን ስንፍና ይኹውም ቀኖናን በመተው የሠራውን ስህተት ሃይማኖቱን/ዶግማውን በመተው የርኩሳን መናፍስት ሲሳይ እንዳይሆን አስቀድሞ ለማስገንዘብ ነው፡፡

የጾም በያይነቱ- እንደመካሻ?

ቀድመንም እንዳስቀመጥነው ነቢዩ ዳንኢል ማለፊያ እንጅራ አልበላሁም አዝንም ነበር ያለው አነጋገር ለብዙ ቅዱሳን ለጾማቸው ፊለግ ሆኖአቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከዕፅዋት ፍራፍሬና ከአትክልት ወገን አንኳን ዘይትን አብዝቶ ጣዕምን አጠንክሮ ከሥጋና ከቅቤ የሚገኘውን እርካታና ጥቅም ተክቶ መውሰድ የማይገባና ለህሊናም ደስ የማያሰኝ ነው። ጾም ምግብ መቀየርና ማመጣጠን አይደለም፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ይህንን መሰል የተሳሳተ አስተሳሰብ ላላቸው ወገኖች እውነታውን ታሰተምራለች፣ ትመሰክራለች ከቅቤና ከሥጋ መከልከልን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በምዕመናን ላይ ጫና አድርጋ የቆየች የሚመስላቸው ወገኖች አሉ። ከላይ እንደተጠቀሰው የጾም መሠረታዊ ዓላማ ሥጋን ማድከም መሆኑን የተረዳ ለምን ሥጋና የእንስሳት ተዋፅፆ በጾም ወራት ይከለከላል የሚል ጥያቄ በህሊናው አይመላለስም፡፡ ይልቁንም ከላመ ከጣመ ምግብ ራሳቸውን ገትተው በጸሎትና በስግደት በመትጋት ለራሳቸው ጽድቅና ቅድስና ለሌላው ወገንም በረከትና ድህነት ማግኘት ምክንያት የሆኑትን ቅዱሳን አባቶችን በማሰብ ራሱን ለዚያ ያዘጋጃል እንጂ፡፡

የሚያሰክር መጠጥና ተራክቦ በጾም

እርግጥ ነው ስካር ሰውን የሚያዋርድ ከሕገ እግዚአብሔር የሚያወጣ በሕግ የተጠላ ነው። ስለዚህ መጠጥ ርኩስ ነው ብሎ መተው አይገባም እንጂ ከጠጣሁ ራሴን መግታት አይቻለኝም ብሎ መተው የተሻለ ነገር ነው። መጻሕፍት ስካርንና ጥጋብን ይነቅፋሉ እንጂ ማናቸውንም ነገር ርኩስ ብለው አይነቅፉም። ይህን መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ በመጻፋቸው እንዲህ ያስረዳሉ። ስካርና ጥጋብ በሐሊበ አዝርዕት በጠላ ባርቄ፣ [በወይን በቢራ] ብቻ አይደለም። በሐሊበ እንስሳትም ይመጣል። ይህን ለመረዳት ጥጃ ከማሰሪያው በተፈታ ጊዜ ሜዳ እስቲጠበው ድረስ በመፈናጠዝ ጥጋቡን የሚገልጸው ከእናቱ ጡት ያገኘውን ወተት ብቻ ተመግቦ ነው። እንደዚሁ ፈረስና በቅሎም አውታራቸውን በበጠሱ ጊዜ ሰማይን በአርግጫ ለመምታት እስኪቃጡ ድረስ የሚፏልሉ ሣርና ጥሬ በልተው ነው’ጂ በመጠጥ አይደለም። ስለዚህ ማንኛውም ዐይነት ምግብ ቢኾን ሕግ በማይፈቅደው ጊዜ መከልከል በሚፈቅድበት ጊዜ በመጠን መመገብ ይገባል እንጂ ይህ ዐይነት ምግብ ንጹሕ ነውና ሰዓት ሳልወስድ እመገባለሁ ይህ ዐይነት ምግብ ያረክሳል ማለት አይገባም።[23]

እንደዚሁም ፍትሐ ነገስት ስለ ጾም በደነገገበት አንቀጹ እንዲህ ይላል “ሴቶችም ጌጣቸውን ይተዉ ሁሉም ለእያንዳንዱ በ፵ ጾምና [ዐብይ ጾም] በሰሙነ ሕማማት መጠበቅ ይገባዋል። ድኅነታችንና የኃጢአት ሥርየት በእርሱ ነውና። ይኸውም ሥራ አንዱስ እንኳ በ፵ ጾም ወራት በምንጣፍ ፈጽሞ እንዳይገናኝ ከጋብቻ ሕግ የወጣ ነው። ክብርት በምትሆን በሕማማት ወራት ይህችን ኃጢአት የሚሠራ ሰው ወዮለት። በተድላ በደስታ ፈቃዳችንን ካደረግን ትንሣኤውን ባየን ጊዜ ተድላ ደስታችን ወዴት አለ?[24] አዋጁ እንደሚለው በዐብይ ጾምና ይልቁን (ካልተቻለ) በሰሙነ ሕማማት ክልክል ነው። ጠንካራና የበረቱ ክርስቲያኖች በሁሉም አጽዋማት ምንጣፍ ለይተው ይጠናቀቃሉ።

ሥጋ ልጓም ይፈልጋል

አምላካችን በአምሳሉ ለፈጠርው የአዳም ልጅ ኹሉ በመጠን ሊበላና ሊጠጣ ሊለመልም በልቶ ጠጥቶም ለሰጪው ሊያመሰግን ፈጠርው እንጂ የእግዚአብሔር መቅደስ ሊኾን የተመደበውን ሕይወቱን ሊያመነምነው ሊያበላሸው አላዘዘውም በማለት ለጻፈ ተጠራጣሪ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ሲመልሱ “ሰው በመጠን ተመገብ ማለት በጾም ልጓም ይዞ ነው እንጂ የጾም ልጓም አውልቆ ስድ ለቆ በመጠን ተመገብ ማለት አጋሰስን ከመስክ ማሃል ያለልጓም ለቆ በልክ ተመግበሽ ተዪ እንደ ማለት ያለ ነው”[25] ብለዋል።

እግዚአብሔር የሚመርጠው አገልጋይ ኾዱ የሞላ፣ ደረቱ የቀላ፣ ሰውነቱ የፋረሰና ገላው የለሰለሰ ቢሆን ከዳዊት ይልቅ ኤልያብ በተመረጠ ነበር።[26] በመቆምና በስግደት በትጋህ ሌሊት በረሃብ በጽምዕ በውርጭ በብርድ መከራ የተቀበለ ጳውሎስም ከንቱ በቀረ።[27] ጌታም ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው ያለው በከንቱ በሆነ።[28]

ይልቁን ያዕቆብ በልቶና ጠግቦ ሆዱ በሰፋ፣ አካሉ በገዘፈ፣ ልቦናው በሞራ በተደፈነና ጥጋብ ባቀናጣው ጊዜ ፈጣሪውን እግዚአብሄርን ተወው፣ ሕይወቱም ከእግዚአብሔር ራቀ ተለየ።[29] ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “በምድር ላይ ተቀማጥለሃል”[30] ለሥጋ የጾምን ልጓም አበጅቶ አለመኖር ልጄ ሆይ፥ አንተ በምድር ላይ ተድላ ደስታ ስታደርግ ደኃው ይሠቃይ እንደነበረ እወቅ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ የሚል ፍርድ ከማሰማት በቀር ምንም አይረባም አይጠቅምም።[31]

አጫጭር ጥያቄና መልሶች

ገና እና ጥምቀት ዓርብ እና ረቡዕ ቢውሉ ይበላባቸዋል ወይስ ይጾማሉ?

በዓለ ሃምሳ፣ የልደት እና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር በየሳምንቱ ዓርብ እና ረቡዕን መጾም ይገባል።[32]

የገና እና የጥምቀት ቅዳሴ ስንት ሰዓት ነው?

በዚያ ዘመን በኒቂያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት የልደትና ጥምቀት ቅዳሴው በሌሊት ይሆን ዘንድ አዘዋል።[33]

ልደት ጋድ አለው?

የልደት እና የጥምቀት በዓላት ጋድ አላቸው።[34] የገና ጾም ፵፬ ቀናትን ይይዛል፡፡ ፵ ጾመ ነቢያት፣ ፫ ጾመ አብርሃም ሶርያዊ፣    ፩ ጋድ በድምሩ ፵፬ ይሆናል። የገና ጋድ ከጾሙ ተያይዞ የተቀመጠ እንጂ ለብቻው የተቀመጠ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰሙነ ሕማማት ለብቻው የሚቆጠር ጾም ነው፡፡[35] ነገር ግን አንድ ሰው ዐቢይ ጾምን ሳይጾም ከርሞ ሕማማትን ለብቻው መጾም አይችልም፡፡ የገናም ጋድ እንዲሁ ነው፡፡

ይህንን ጋድ የልደትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች እንዲጾሙት የተሠራ ነውን?

በቤተ ክርስቲያን ላልተጠመቁ፣ ለማይቆርቡ፣ ንስሐ ለማይገቡ፣ ለማያስቀድሱ፣ ለማይጾሙ ሰዎች ተብሎ የተሠራ ልዩ ሥርዓት የለም፡፡ በፍትሐ ነገሥት[36] እንደተገለጠው ሰባቱ አጽዋማት «ለክርስቲያን ሁሉ» የታዘዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም የገናን ጾም ክርስቲያን ሁሉ ጾመው በበዓለ ልደት ሊገድፉ ይገባቸዋል፡፡

እንደመውጪያ. . ….  

ጾማችንን የተሟላ የሚያደርገው ከጸሎት ጋር ሲሆን ነው ለክርስቲያን ጾም ጸሎትና ምፅዋት የማይነጣጠሉ ጽኑ የዲያብሎስ ድል መነሻ መሳሪያዎች መሆናቸውን ጌታ ለሐዋርያቱ እንዳስተማረ ቤተ ክርስቲያንም ለልጆቿን ታስተምራለች፡፡

ጾም ለጸሎት እናቷ ለአርምሞ እኅቷ ለአንብዕ መፍለቂያዋ ለበጎ ትሩፋት ኹሉ ጥንት መሰረት ናት[37]

ጾሙን ጾመን ድኅነተ ሥጋ ፣ ድኅነተ ነፍስ ፣ በረከተ ሥጋ ፣ በረከተ ነፍስ የምናገኝበት እንዲሆንልን የተወዳጅ ልጇ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት ፣ የእመቤታችን የድንግል ማርያም አማላጅነት ፣ የቅዱሳኑ ሁሉ ተራዳኢነት ከሁላችን ይሁን፡፡ አሜን ???


[1] አረጋዊ መንፈሳዊ ገጽ ፪ [ይህ መጽሐፍ ከሶስቱ የመነኮሳት መጽሐፍ አንዱ ነው። የቀሩት ደግሞ ማር ይስሐቅና ፊልክስዩስ ይባላሉ።]

[2] ፍትሐ ነገሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምትመራበት የእምነቷ፣ የሥርዓቶቿና የሕጎቿ መደንገጊያ መጽሐፍ ሲሆን ቃለ አዋዲ ደግሞ የአስተዳደር መጽሐፍ ነው።

[3] ፍት ነገ ገጽ ፩፻፶

[4] ሲኖዶስንና ዲዲስቅልያን ቤተክርስቲያን ከምትቀበላቸው ፹ወ፩ መጽሐፍ ቅዱስ መሐል የሚካተቱ ናቸው።

ከ፳፯ቱ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር የሚደመሩ ፰ መጻሕፍት አሉ። ፩. ትዕዛዝ ሲኖዶስ ፪. ግስው ሲኖዶስ ፫. አብጥሊስ ሲኖዶስ ፬. ሥርዓተ ጽዮን ሲኖዶስ ፭. መጽሐፈ ኪዳን ቀዳማዊ ፮. መጽሐፈ ኪዳን ካልዕ ፯. ቀለሚንጦስ ፰. ዲድስቅሊያ

እነዚህ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት አሁን በእጃችን በሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተካተቱም፡፡ይህም የሆነው እያንዳንዳቸው በጣም ትልቅ መጻሕፍት በመሆናቸው ለማካተት አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፡፡ግን ከሰማንያ አንድ መጻሕፍት መድበን ነው የምንቆጥራቸው።

[5] ኰኲሐ ሃይማኖት ገጽ ፩፵፰- ፩፻፶፮

[6] ብሉይና ሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ማለት ፹ወ፩ መጽሐፍ ቅዱስ ከያዛቸው መጻሕፍት መሐከል ናቸው። የሊቃውንት መጻሕፍት ደግሞ አዋልድ መጻሕፍት ከሚባሉት የሚካተቱ ናቸው።

[7] በቃል ትምህርት ጸሐፊው ከሰማው በራስ አገላለጽ የተጻፈ ነው።

[8] ፪ ጢሞ ፫፥ ፲፮ ተጨማሪ ሮሜ ፲፭፥ ፬ ላይ “የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል” ይላል

[9] ፪ኛ ጴጥ ፫፥ ፲፮

[10] ዘፍ ፪፥ ፲፯

[11] ረሰጠአ (የመጀመሪያው ሲኖዶስ ወይም ቀሌምንጦስ ቀዳማዊ ወይም ትዕዛዝ ሲኖዶስ ማጣቀሻ አጽሮት ነው)

   ረስጠብ (ሁለተኛው ሲኖዶስ ወይም ቀሌምንጦስ ዳግማዊ ወይም ግጽው ሲኖዶስ ማጣቀሻ አጽሮት ነው)

   ረስጠጅ (ሦስተኛው ሲኖዶስ ወይም ቀሌምንጦስ ሣልሳዊ ወይም አብጥሊስ ሲኖዶስ ማጣቀሻ አጽሮት ነው)

[12] ፍት ነገ ፭፻፹፱ ገጽ ፻፶፬

[13] ፍት ነገ አንቀጽ ፭፻፴፰

[14] ጾመ ድጓ ዘወረደ ዘሰንበት ገጽ ፭

በቅዱስ ያሬድ የተደረሱት የዜማ መጻሕፍት አምስት ናቸዉ፡፡እነርሱም ድጓ፣ጾመ ድጓ፣ዝማሬ፣ መሥዋዕትና ምዕራፍ ናቸዉ፡፡

ድጓ፡-የቅዱስ ያሬድ ትልቁ የዜማ መጻሕፍ ነዉ፡፡ድጓ ማለት ስብስብ ማለት ነዉ፡፡በዉስጡ የዓመቱን በዓላትና የሳምንታት መዝሙራት ሰብስቦ የያዘ ነዉ፡፡ይህ መጽሐፍ በዐበይት በዓላት በዜማ የሚቀርበዉን ምስጋና ሰብስቦ የያዘ የዜማ መድብል ነዉ፡፡ ድጓ በአራት ትልልቅ ክፍሎች ይከፈላል፡፡ይኸዉም፡-የዮሐንስ ድጓ፣ አስተምህሮ ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ የፋሲካ ድጓ ተብሎ ይታወቃል፡፡

ጾመ ድጓ፡-ሁለተኛዉ የዜማ መጽሐፍ ሲሆን የሚጠናና ለመምህርነት የሚያበቃ ነዉ፡፡ድጓ ቁጥሩ ከአስተምህሮ ሲሆን በዐቢይ ጾም የሚደርስ ራሱን የቻለ መጽሐፍ ነዉ፡፡

ዝማሬ፡-ሦስተኛዉ የዜማ መጽሐፍ ነዉ፡፡ዝማሬ ምስጋና ማለት ነዉ፡፡ዝማሬ በጸሎተ ቅዳሴ ከድርገት በኋላ በቅዳሴ ማብቂያ አካባቢ የሚዜም የሚዘመር የጸሎተ ቅዳሴዉን ዓላማ ተከትሎ የሚሔድ ማለት ነዉ፡፡መጽሐፈ ዝማሬ በይዘቱ አምስት ነገሮች አሉት፡፡እነርሱም ኅብስት፣ ጽዋ፣መንፈስ፣ አኮቴት እና ምስጢር ናቸዉ፡፡

መሥዋዕት፡-አራተኛዉ የዜማ መጽሐፍ ነዉ፡፡መሥዋዕት የቃሉ ትርጓሜ ሁለት ዓይነት ነዉ፡፡አንደኛዉ ምልልስ ማለት ነዉ፡፡በግራና በቀኝ እየተመላለሰ ወይም እየተቀባበለ የሚባል ስለሆነ ነዉ፡፡የመሥዋዕት ሁለተኛዉ ትርጉሙ ደግሞ የነፍስ መመላለስ (መሸጋገሪያ) ማለት ነዉ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀትን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤዉንና ዕርገቱን የሚያስረዳ ነዉ፡፡ የመሥዋዕት አገልግሎት ለሙታን ጸሎተ ፍትሐት ለማድረስ በበዓላትና በአጽዋማት ደግሞ ስብሐተ ነግሕ ለማድረስ ነዉ፡፡

ምዕራፍ፡-የቅዱስ ያሬድ አምስተኛዉና የመጨረሻዉ የዜማ መጽሐፍ ነዉ፡፡የምዕራፍ ቀጥተኛ ትርጉሙ ማረፊያ ወይም ማሳረፊያ ማለት ነዉ፡፡ምዕራፍ ከመዝሙረ ዳዊት የተዉጣጣ ድርሰት ሲሆን የዳዊት መዝሙራትን በመስመር (ምዕራፍ)እየከፋፈለ የዜማዉን አይነትና ማሳረፊያ ይገልጻል፡፡

[15]  ዘካ ፯፥፭፣ ስንክ ታኅ 13፣ ፊለክ ፪፻፵

[16] ፍት ነገ ገጽ ፩፻፶

[17] መዝ. ፻፰ (፻፱)፥ ፳፬። ፷፰ (፱)፥ ፲

[18] ዳን ፲፥ ፪-፫።

[19] ዳን ፱፥ ፫

[20] ፩ ቆሮ ፰፥ ፰። ፯፥ ፴፩-፵

[21] ኢሳ ፶፰፥ ፫-፲፬

[22] ፩ኛ ቆሮ ፮፥ ፲፪

[23] ኰኲሐ ሃይማኖት ገጽ ፫፻፱

[24] ፍት ነገ ፭፻፺፯ ገጽ ፻፶፭

[25] ኰኲሐ ሃይማኖት ገጽ ፫፻፲

[26] ፩ሳሙ ፲፮፥ ፮-፲፬

[27] ፪ቆሮ ፲፩፥ ፳፫-፴። ፲፪፥ ፲

[28] ማቴ ፭፥ ፮

[29] ዘዳግ ፴፪፥ ፲፫-፲፮

[30] ያዕ ፭፥ ፭

[31] ሉቃ ፲፮፥ ፳፭

[32] ረስጣ ፳፰። ፍት ነገ ፭፻፹፯

[33] ፍት ነገ ፭፻፺፭

[34] ፍት ነገ ፭፻፷፯

[35] ፍት ነገ ፭፻፷፭

[36] ዝኒ ከማሁ

[37] ኰኲሐ ሃይማኖት ገጽ ፫፻፲፯

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑