

በውጤቱም አገሪቱን ወደብተና የሚገፉ ህዝባዊ አመፆች እዚህም እዚያም ገንፍለው ወጥተዋል። ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ
መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የኃይል አማራጭን የሙጥን ያለው አገዛዝ መንግስታዊ ፍጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። አገዛዙ የመጣበትን መንገድ ምርጫቸው ያደረጉ የነፃነት ኃይሎች በሚያደርሱት ጥቃት አገሪቱን “መንግስት” አልባ አስመስሏታል። በጎንደርና ባህርዳር አካባቢ በየጊዜው እየፈነዱ ያሉ ቦምቦች የጋዛ ሰርጥን ውጥረት የሚያስታዉስ ሆኗል። የፖለቲካ ነፃነት እጦት እና የሰላማዊ ትግል መጨፍለቅ ወደ ህዝባዊ አመጽ እና የህብዑ ጥቃት እንደሚገፋ የህወሓቷ ኢትዮጵያ ከበቂ በላይ ምሳሌ ነች።
የኢትዮጵያን ማህበራዊ ስሪት በቅጡ መረዳት ባልቻሉት የትግራይ ሽፍቶች የሚመራው ህወሓት በበረሃ በኩል በምዕራባውን አንጋሾቹ ተረድቶ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የሰላማዊ ትግል ጀምበር ለአፍታ ፈንጥቃ ተመልሳ በማዘቅዘቋ ብረት ማንሳት ብቸኛ የነፃነት መንገድ ሆኖ ቀርቧል። አሁን ባለው ዘውጋዊ መካረር ኢትዮጵያን ለርስ በርስ ጦርነት የቀረበች አገር አድርጓታል። የችግሩ መውጫ ጫፍ ከነፖለቲካዊ ልዩነቶቻችንም ቢሆን የጋራ ጠላት የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ ላይ ሙሉ ኃይልን ማሳረፍ ያልተፈተሸው የትግል መንገድ ነው በማለት በርካታዎች ይከራከራሉ። ነውጥ አልባ ትግልን በፍጹም ልባቸው የሚደግፉና የሚያምኑበት ደግሞ በትክክለኛው አልተሞከረም እንጂ ነውጥ አልባው መንገድ ለኢትዮጵያ ችግር ፍቱን ነው ይላሉ፡፡ እስካሁን በኢትዮጵ የተካሄደውን ትግል ሰላማዊ የፓርቲ ምርጫ ትግል እንጂ እውነተኛ ነውጥ አልባ ትግል አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡