መተዛዘል

( click to read pdf ) ጠቢቡ (ጠቢቡ ስል ከእሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ እርሱ በዚህ ስም የተጠራበትን ያህል ጥበብና እውቀት ያሟሉ እንደሌሉ ልብ ይሏል-ስሙን ወረሱት’ጂ) ይህ ጠቢብ በምድር ላይ በቆየበት እድሜው እጅግ ብዙ የዓለም ክንውኖችና ድርጊቶችን፣ስሪቶችና ሂደቶች፣ቅዠቶችና ምኞቶች… ወዘተ ሁሉን አሰሰ፤ የምድር ጥበባት፣ፍልስፍናዎች፣ ምስጢራትና ህላዌዋን ሁሉ መረመረ፤አመሠጠረ፡፡ በጥበቡ ቃልም መሐል ይኽን የሚደንቅ ምስጢር አረቀቀ፡፡ “ከፀሐይ በታች ሁሉ ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካም ነገር ከማድረግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ” መክ ፫፥፲፪

     ጠቢቡ ዓይኑ ከንስር የረቀቀና አጉልቶ የሚያይ፣ ልቡናው ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ኃይል ፍሰት የተነሣ ከሚመጣ ንዝረት የበለጠ ውስጥን የሚቦረቡርና የሚያርገፈግፍ አርቆ መርማሪ ብቻ እ’ሱ እ’ሱ ነበር፡፡ ሲጀመር ‘እርሱ ብቻ ጠቢብ’ አላልንምን?! እስቲ ጥያቄ ላንሣ “እርስዎ በሕይወትዎ ምን መስራት ያስደስትዎታል?” እርካታ የሚያመነጭልዎትን ደስታ ማለቴ ነው፤ ያን ፍጹም እርካታ፣ የደስታዎች ሁሉ ጉብታ፣ በሕይወት የመኖርዎን የእርካታ ጣራ ማለቴ ነው፡፡

     ብዙዎች የተለያየ ምላሽ እንደሚኖራቸው የታመነ ነው፡፡ የአንድ ወዳጄ ምላሽ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው “ሰው ተቸግሮ (ችግር ሲባል የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሐሳብ መዋዠቅ፣ የጭንቀት፣ የመላና ደስታ የማጣት፣ የብቸኝነት፣ ረዳት ሰው ያለማግኘት፣ የብርታትና ድጋፍ የሚሆን ሰው የማጣት ወዘተረፈ ሊሆን ይችላል) እናም ሰው ተቸግሮ በችግሩ ስደርስ እጅግ እደሰታለሁ፡፡ ከችግሩ ወጥቶ ልቡናው በሀሴት ሲሞላ አእምሮው ረፍት ሲጎበኘው በመጽናናት ውስጥ ሲደሰት ሳየው በጣሙን እረካለሁ፡፡ ኦ! እናንተ ለሰው ልጅ ሰው ሲደርስ ከማየት የዘለለ ምን ደስታ አለ!” በማለት በጓደኝነት ጨዋታ ውስጥ አካፍሎን ነበር፡፡

    ሁላችንም የምንወደው ምላሽ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ ምናልባትም በውስጣችን ሞልቶ እንዴት እንደምናወጣው መንገዱን ያጣንለት ሐሳብም ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ግን በሐሳቡ ላይ ሳይሆን ሐሳቡ ከመጣበት መነሻ ላይ አተኩራለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምላሽ ለመስጠት ምን ዓይነት የአመለካከት፣ የአስተሳሰብና የእይታ እርከን ውስጥ መግባት ይጠይቃል? ይህ ሐሳቡ በልባቸው ሞልቶ ያተረፉትን ይመለከታል፡፡

     መጽሐፍ እንዲህ ይላል “ዝንቱ ትእዛዝየ ውእቱ አፍቅር ቢጸ….ትእዛዜ ይህቺ ናት ባልጀራህን እንደነፍስህ ውደድ የምትለዋ” ማቴ ፳፪፥፴፱  ወንድምን መውደድ እንዳለብን እናምናለን፡፡ መውደዳችንን እንዴት እንገልጻለን ነው ጥያቄው? እስቲ ይህን እንጠይቅ እኛ በምድር ላይ ምን አለን? የቱ የኛ ነው? ቤታችን ነው? ቁሳዊ ንብረቶቻችን? ዘመዶቻችን? ስልጣናችን? ገንዘባችን? ክብር ዝናችን ነው? ስጦታዎቻችን? ማዕረጋችን? ….. ጥሩ ማንን ነው እነኚህን አጥቶ ሲያገኛቸው፤ አግኝቶ ሲያጣቸው ያላየነው? የኛ ከሆኑ ምን ወሰዳቸው? ይህንን መጠየቃችን ሁሉ የኛ እንዳልሆነ ልክ ሸክላ በውስጡ ስለያዘው ውኃ አስገኚዬ ወይም ክፋይ አካሌ ነው እንደማይለው ሁሉ–እ’ሱ ራሱ የሸክላው ሰሪ ነውና! እኛም ሁሉ የ’ኛ እንዳልሆኑ በሥጋዌ ዘመናችን መጥተው እንደሚያልፉ ክረምትና በጋ ከቆጠርናቸው ስለምን ከወንድማችን ጋር በሰላም እንኖር ዘንድ አንናፍቅም? ምክንያቱም አንድ ሰው ያለሌላው እርዳታ ስለማይኖር፡፡ አሊያማ የብቻችን ዓለም የቱ ነው? የብቻችን ደሴት ወዴት ነው? ይቺ ምድር የሰው ዘሮች በሙሉ ናት፡፡ የጋራችን ዓለም–እንዳደረግናት ልትሆን የተዘጋጀች፡፡

     ይህን ባሰብን ጊዜ እውነትም ከትእዛዛት ሁሉ በላይ የሆነ ትእዛዝ መሆኑን እንረዳለን–ወንድምን እንደነፍስ አድርጎ ማፍቀር፡፡ ይህ ከብዙ ልምምድና ከመንፈሳዊ ብስለት የሚመነጭ ጣፋጭ እውነታ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ጣፋጭ እውነታ ውስጥ ለመኖር በፍቅር ውስጥ ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ቂም በቀልነት፣ ለራስ ብቻ ማለት…. እንደሌለ ስለምንረዳ ልቦናችንና መንፈሳችን ሁሉ በመልካም ጸጋዎች ይሞላሉ፡፡ ዓለሙ ሁሉ መልካም መስሎ ይታየናል፡፡ እኛም ለዚህ መልካሙ ዓለም በጎውን እናበረክትለት ዘንድ እንጥራለን፡፡ እንግዲህ በዚህ ጥረት ውስጥ ነው ወንድማችንን እንደራሳችን አድርገን እየወደድን እንዳለን የሚገባን፡፡ ይህ ሐሳብ ሲጠቃለል ቀና አመለካከት ከማዳበር የተገኘ በጎ ልምድ ወይም ጸጋ ነው፡፡

     ከላይ ወዳልተቋጨው ሐሳቤ ስመለስ ትኩረቴን በወዳጄ ሐሳብ ላይ ሳይሆን በሐሳቡ መነሻ ላይ በማድረጌ ነው በጎ አመለካከት ስለማዳበር ለመዘርዘር መሞከሬ፡፡ ስለዚህ የዚህ ሰው ሀሳብ መነሻ በልቦናው ካነገሠውና በበሰለ አእምሮው ጎዝጉዞ ካስቀመጠው የቀና አመለካከት በጎ ልምድ የመነጨ መሆኑን እንረዳለን፡፡ የተናገረውን ሐሰብ ሲያደርገው ይህን ልማድ ሲለማመደውና በውስጡ ሲቀርጸው ይኖራል ያኔም ወንድሙን እንደነፍሱ ከመውደድ በላይ ነፍሱን አሳልፎ መስጠትን ይማራል “ነፍሱን ስለወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” ዮሐ ፲፭፥፲፪ እንዳለ መጽሐፍ፡፡

     ለዚህ ነው ጠቢቡ ሰለሞን ሰው ልቡን ደስ የሚያሰኘው ይህ ‘መልካም ማድረግ’ ብቻ መሆኑን የገለጸልን፡፡ መልካም ማድረግ ድርጊት ነው ለዚህ መልካም ማሰብ ይቀድማል፡፡ ለመልካም ማሰብና መልካም ማድረግ ደግሞ በቀና/በበጎ አስተሳሰብ (positive thinking) የተሞላ ልቡና፣ አእምሮና መንፈስ ሊኖረው ይገባል ሲል ነው ከመጨረሻው ድርጊቱ ላይ አተኩሮ መናገሩ፡፡

    ሌላ አንድ ምስጢር ላክልና መጣጥፌን ልቋጫት፡፡ ርዕሴን ‘መተዛዘል’ ማለቴ የእንግሊዘኛውን interdependence የሚለውን ለመተካት በማለት ነው፡፡ ሐሳቡም የሰው ልጅ ብቻውን ኑሮ ብቻውን የሚያድግና የሚሞት ፍጡር አይደለም፡፡ በመተሳሰብ፣ በመከባበር፣በመረዳዳትና በመተጋገዝ በኅብረት መኖር ግድ ይለዋል–ማኅበራዊ ፍጡር እንደመሆኑ፡፡ ለአንድ ሰው ውድቀትም ሆነ ስኬት የሌላ ሰው ተጽእኖ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይኖራል፡፡ ምሳሌ እንዲሆናችሁ እስቲ የምታውቁትን ሰው ሁሉ መርምሩ፡፡ ተሳካለት የምንለው ያለማንም ሰው ድጋፍ ብቻውን ቆመን? እዚህ ደረሰን? በሕይወቱ አልተሳካለትም የምንለውስ በጥረቱ ወይም በውድቀቱ ውስጥ የሌላ ሰው እጅ የለበትምን? ቀላሉ መልስ’ኮ ይህ የብቻ ዓለም አ’ደለም ነው!! እናንተ ባትሰሙት ወይም ባታነቡት ይሄን እንዴት እጽፋለሁ?! ስለዚህ የሰው ልጅ እርስ በ’ርሱ የተዛዘለ ነው፡፡ ለአንዱ ጉዞ የአንዱ ጀርባ የግድ የሚያስፈልገው፡፡ ስለዚህ ይህን መተዛዘል ለበጎ እንጠቀምበት፡፡ ጀርባው ላይ ቆመን መርፌ ለመውጋት ወይም ለመቧጨር ሳይሆን በርታ እያሉና በፍቅር እየሳሙ ለመሄድ ቀና አመለካከቱን እናዳብር፡፡ በዚህ ቀና አመለካካት ውስጥ ዓለምን በበጎ ዓይን እናያታለን፡፡ የምድርን በጎ መዓዛዋን እናሸታለን፡፡ ጣዕሟን እንቀምሳለን ያኔ ወንድማችንን እንደወደድን እንረዳለን፡፡ ወንድሙን የሚወድ አምላኩን እንደሚወድ ምስክር ይሆንለታል፡፡ “ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን አምላኩን ሊወደው እንዴት ይችላል?” ፩ዮሐ ፬፥፳፩

      ወዳጆቼ ሆይ ይህ ሀሳብ ሳያደርጉት በማሰብ’ኳ የሚረኩበት ነው ሲያደርጉትና በውስጡ ሲኖሩበትማ አቤት! ያኔ ይቺ ዓለም ለ’ኛ የተፈጠረች መሆኗን እኛም ጌቶቿ እንደሆን እንረዳለን፡፡ ይህ ሐሳብ ሽቱ ነው ለራስ ሲያርከፈክፉት ለሌላው የሚሸት እናም ለሌሎች እናካፍለው እናዳብረው፡፡

                                               ፲፰/፰/፳፻፪ ዓ.ም

                                                  አዲስ አበባ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑