ለእግረኛ የተከለከለ
ፎቶ ማንሳት የተከለከለ ነው፡፡ መግባት የተከለከለ፡፡ ማየት የተከለከለ መናገር የተከለከለ ማድመት የተከለከለ መንዳት የተከለከለ ማቆም የተከለከለ መቀመጥ የተከለከለ…. ወዘተ ብዙ የተከለከሉዎች፡፡ የሕብረተሰባችን የአኗኗር ህግ በብዙ ክልከላዎች የተሞላ ነው፡፡ እናትና አባት ‘አታድርግ’ የሚል የክልከላ ህግ አለው፡፡ አካባቢው ‘አስነዋሪ’ የሚል መከልከያ ያወጣል፡፡ ቀበሌ ባለሥልጣን መንግስት ብዙ የክልከላ ህጎች አሏቸው፡፡ በሰው በራፍ /ደጅ/ ላይ እንዳይቀመጡ የተቃጠለ ዘይት /ኦሊዮ/ በማፍሰስ ከመከልከል አንስቶ የታጠቀ ደንብ አስከባሪ በመሳሪያው አስፈራርቶ እስከሚከለክለው ድረስ ታግደንና ተመርተን ኖረናል እየኖርንም ነው፡፡
እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቶ አንድዬ የነበረው አዳምም ክልከላው እስኪነሳለት መጠበቅ አልተቻለውም ‘ብላ ብላ’ ይለው ነበርና፡፡ የሥነ-አዕምሮና የሥነ-ልቡና ባለሙያዎችም ከዚህ በመነሳት ይመስላል የሰው ልጅ ብዙ በተከለከለ ቁጥር ብዙ ያን የተከለከለውን ነገር የማግኘት ፍላጎቱ ያይላል የሚሉት፡፡
ይህ ተጣብቶን ያደገው የክልከላ ባህላችን ህግ አውጪ ስንሆንም አይለቀንም፡፡ ህጋችን ከጥቂት ፍቃዶች ጋር ብዙ ክልከላዎችና ማስጠንቀቂያዎች እናጥቅበታለን፡፡ አስተዳደሪም ስንሆን አይተወንም ሰራተኞቻችንን በገደብና በክልከላ ከእኛ በሩቁ እናግዳቸዋለን፡፡ ወደ’ኛ እንዲቀርቡ በጎ ፈቃዳችን መጠ’የቅ ይኖርበታልና፡፡ ሰራተኞችስ ብንሆን አገልግሎታችን ግልጽና ክፍት ከመሆን ይልቅ ስውርና ክልከላ አይበዛውም? መቀመጥ አይቻልም፡፡ ከዚህ ርቃችሁ እዛ ቁጭ በሉ፡፡ ቦርሳ አስቀምጡ፡፡ ቀበቶ ፍቱ፡፡ ሞባይል አጥፉ፡፡ ሻርፓችሁን ግለጡ፡፡ ሞባይል አይገባም፡፡ ላፕቶፕ በር ላይ አስቀምጡ፡፡ አትደገፉት፡፡ አትቁሙ ወዘተ በየአገልግሎታችን ውስጥ የምንናገራቸው አሊያም የለጠፍናቸው ክልከላዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ የልዩ ባህል፣ ታሪክና እምነት ባለቤት ነች፡፡ እዚሁ የምንኖር ልጆቿ ታሪኳን፣ እምነትና ባህሏን በሚገባ አናውቅም፡፡ ትላንት ከውጭ የመጣ እንግዳ ለእኛው ያስረዳናል አሊያም ሃገሩ ሲመለስ ጽፎ ይልክልናል፡፡ ለዚህ የወንድሜ ገጠመኝ ጥሩ ማስታወሻ ይሆናል፡፡ 5 ኪሎ ብሔራዊ ሙዚየም ለጉብኝት ገብቶ አስጎብኚው እንዳይቀር ነካ ነካ እያደረገ በግርፍ ይሸኘዋል፡፡ ታዲያ እንኳን ተጨማሪ እውቀት ሊያገኝ ያወቀው የነበረው እስኪማታበት ድረስ ቢጨንቀው ሰብሰብ ያሉ የውጭ ሃገር /ፈረንጆች/ ዜጎች ያሉበትን ምድብ ተቀላቀለ፡፡ አቤት የአስጎብኚው የማስረዳት ጉጉት፡፡ አቤት የዝርዝር መረጃው ፍትፍት! እርሱም ተፋሰሱን የጠበቀና የተንሰላሰለ እውቀት ገብይቶ ተመለሰ፡፡
ፎቶ እንዳናነሳ ስንቱን ታሪካችንን ተከለከልን? ገብተን እንዳንጎበኝ ስንት ክልከላ ተለጠፈብን፡፡ እኛ እንዳናየው ታግደን ለውጭ እንግዶች ስንቱ ተፈቀደ፡፡ ይሄ የእንግዳ የመቀበል ባህላችን ወይስ የክልከላ አዚማችን ይመስላችኋል? የእንግዳ መቀበሉን’ኳ ዜግነት እየመረጥን መሆኑን እያየን በመሆኑ ለሌላ ጊዜ እንተወው፡፡ የክልከላ ጠኔያችን በማሳየትና በመፍቀድ ልናገኛቸው የሚገቡን የነበሩ ብዙ ሀብትና በረከት አሳጥቶናል፡፡ ብዙ ልናሳካው ያሰብናቸው የጋራ መንፈስና አንድነት ርቀውና፡፡
ዋና ጉዳዬ’ኳ ይሄ አልነበረም፡፡ የእግረኛ ክልከላ መቼ እንደሚነሳ አሳሰበኝ’ጂ፡፡ መቼም ይቺ አዲስ አባችን አቶ እገሌና እገሊት በከተማው ውር ባሉ ቁጥር ተንቀሳቃሽ የክልከላ ማስታወቂያ ይዞ መዘሩ የተለመደ ሆኗል፡፡ በተለይ በስብሰባ ወቅቶች፡፡
ያለን አፍንጫ ያለው አውራ ጎዳና ጥቂት ሆነው እርሱኑ ሊቀራመቱን የበላይ በትር በፊታችን ይገሸራል፡፡ ባለመኪኖች እስከ አንድ ሰዓት ቆመው እንዲጠብቁ ማዕቀብ ተጥሎባቸው ወይም ከደረሱበት መዳረሲያቸው በሌላ መስመር እንዲዞሩ ተገደው የአዙሪት ሲሽከረከሩ መዋል የሹፌሩና የተሳፋሪው እሮሮ ነው፡፡ እግረኞች ከደረሱበት በራቸው አሊያም ከሩቅ ጉዟቸው ዥጉርጉር ቱታ በለበሰ፣ ወገቡን በውኃ መጠጫ ኮዳና ዝናር በታጠቀ፣ በትከሻው የእርሱን ቁመት የሚያህል መሳሪያ ባነገተ የባለሥልጣን ጸጥታ አስከባሪ ታግቶና ከጉዞው ተከልክሎ ገና የመንገዱን መግቢያ ያልረገጡ ጋላቢ መኪኖችን ጥበቃ ይቆማሉ፡፡
ይገርመኛል፡፡ በምድራችን ላይ ከፍተኛ ከበሬታ፣ ጸጥታና ልዩ ድጋፍ የሚሰጣቸው ብቸኛ ሰዎች ቢኖሩ ባለስልጣናት ይመስሉኛል፡፡ ይህቺ ዓለም ለእነርሱ ብቻ እንደተሰራች ያህል፡፡ ይሄን ሃሳብ እንድናጎላውና እንድንጨክንበት የሚያደርገን የዘቦቹ ድንፋታና ቁጣ ነው፡፡ አይቶት ከማያውቀው መኪና ውስጥ ካለ የአንድ ሃገር ባለስልጣን ይልቅ ፊቱ የቆሙት ብዙዎቹ እሱን የሚመስሉ ዜጎች ክብርና ጥበቃ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ በዚያ ቀውጢ ሰዓት ማን ትንፍሽ ይላል፡፡ ሰሚ የሌለው ጩኸት፤ አድማጭ ያጣ ልቅሶ ነውና፡፡ ኦሆ! አባዬ ለነፍሴ! የህዝብን በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት በሚጋፋ መልኩ በየእግረኛ መንገድ አለፍ አለፍ ብለው መሣሪያ ባነገቱ ሰራዊቶች መሐከል መንቀሳቀስ እጅግ ከባድና አስቀያሚ ነው፡፡
ለነዚህ የስብሰባ ወቅቶች የሥራ ሰዓት ቢስተካከሉ ጥሩ መፍትሄ ይመስለኛል፡፡ የመግቢያ ሰዓት ወደ አራት ሰዓት ከፍ ብሎ መውጪያው ከአስር ሰዓት በፊት ተደርጎ ቢስተካከል መንገዶች ከመጨናነቅ አስተናባሪዎች ከመቸገር የሚድኑ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ሰራተኞች ጠዋት በመጓጓዣ /ታክሲ/ እጥረት ከመንገላታትና ማታ አምሽቶ ከመግባት የሚታደግ ይመስለኛል፡፡
ለባለከልካዮችም ለዜጎች ክብርና ጥበቃ ማድረግን የተካኑ ፀጥታ አስከባሪዎች እንዲኖራችሁ ተገቢውን ሥልጠና ስጡልን፡፡ ባለስልጣናቱንም በመስቀለኛ መንገድ ለመጠቀም እንዲችሉ አሊያም አቋራጭ (ማስተንፈሻ) መንገዶችን እንዲጠቀሙ ብታበረታቱልን፡፡ እኛንም በመሣሪያ ብቻ መከልከልን እንድንማር ሳይሆን በእውቀት እንድንመራ አስለምዱን፡፡
ሠላም ያለማንገቻ!
: አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ ነው፡፡ጥር ፯/፳፻፬ ዓ.ም
አዲስ አበባ


Leave a comment