ክረምት ከሌለ ሁሉ ቤት…..

ክረምት ከሌለ ሁሉ ቤት…..

ክረምትን ከረመ ይለዋል ሥርወ ግሱ፡፡ አንዴ የሚወጣ የሚደርስ ማለትን ይመስላል፡፡ እርግጥ ነው ሶስቱ አፈ ለምለም የሚባሉት ወራት በዓመት አንዴ ይወጡና ልምላሜን፣ ንጽህናንና ተስፋን አብስረው ይመለሳሉ–በአብሳሪ አበባቸው አደይ ታጅበው፡፡

ክረምት መታደስን የሚጠይቅ ወቅት ነው–ራስን በማዘጋጀት መለወጥን፡፡ በበጋ ወይም በሌላ ወቅት ዝግጅታችን እንቀበለው ካልን የአሻዋ መሠረታችንን ሊጠራርገው፣ ጥንካሬ አልባ ድንኳናችንን ሊቀደውና ሜዳ ልናድር ፈቀድን ማለት ነው፡፡ የሚደፍሩ ካሉ ቤታቸውን በአለት ላይ የሠሩ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

የክረምት ውኃ ሙላት በበጋ ወቅት በተሰራለት ቦታና በተቀየሰለት መንገድ ብቻ ተጓዥ አይደለም፡፡ ለዚህ የድሬዳዋው የ’98ቱ የጎርፍ መጥለቅለቅና ጥፋት አንዱ ማሳያ ይሆናል፡፡ ይሄ ማለት ግን መቆጣጠር ፈጽሞ አይቻልም ማለት አይደለም፡፡ የጎረፉ መጠን እንደሰፋና የዝናቡ መጠን እንደበዛ እያዩ የዓመታት መንገዱን ይከተላል ብሎ በተስፋ ከተቀመጡ በ’ርግጥ ጥፋቱ ‘ሩቅ ሳይሆን ሁሉም ቤት ሊያንኳኳ ይችላል፡፡

የድሬዳዋን ነገር ድሬዳዋ ያነሣዋል እንዲሉ አንድ መንደር ውስጥ አምስት መደዳ የተገጠገጡ የቀበሌ ቤቶች ያሉበት ግቢ አለ፡፡ በፊትለፊቱም ሌሎች መደዳ ቤቶች ይገኛሉ፡፡ ታዲያ የዚህ ግቢ ነዋሪ መንቀሳቀሻ በቤቶቹ መሐከል ያለው ረባዳ ስፍራ ነው፡፡ አስገራሚው ነገር ክረምት የመጣ ጊዜ መሐል ያለው መንገድ ግቢውን አቋርጦ በሚያልፍ የሰፈር ጎርፍ ይወረራል፡፡ ነዋሪው ቤቱ ይከትማል አሊያም ጀልባ መፈለግ ይኖርበታልi ለጊዜው ያለው ጀልባ ግን ጎረፉ ሲያልፍ ትቶት የሄደው ጭቃ ላይ ተዳልጦ መውደቅ ይሆናል፡፡ በተለይ ጎረፉ ኃይሉ የበዛ ‘ለት በሰላም ከመሄድ ይልቅ የየበራፉን ደፍ ተዳፍሮ እቤት ጎራ ማለቱ አይቀርም፡፡ ለዚህ እኔ እማኝ እሆናለሁ፡፡

ብዙ እንደዚህ ዓይነት መንደሮች በየከተማው ይኖራሉ፡፡ እዚህ አዲስ አበባችንም፡፡ ምንም የክረምት ዝግጅት ሳያደርጉ ወይም ሳይደረግላቸው እንደማይቀር እዳ ክረምቱን የሚገፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሄ ምናልባት የጓዳ ውስጥ ችግር ነውና ጓዳ ለማደስና ለማስተካከል አልደረስንም ይሆናል፡፡ ግና አደባባይን ያስዋቡ መንገዶቻችንስ ብንል ‘ሞልተው’ ማለታችን አይቀርም፡፡ ሌሎቹን መንገዶቻችንን ትተን’ኳ አውራ የሚባሉትንና የቀለበት የሆኑትን ብናይ ምንድነው ነገሩ ያሰኛል፡፡ ክረምት ከሌለ ሁሉ ቤት ብቻ ሳይሆን ክረምት ከሌለ ሁሉ መንገድ የሚል መጨመር ይኖርበታል፡፡

መናኸሪያ አካባቢ፣ አዋሳ-ኢትዮጵያ

በዝናብ ወቅት ለአደጋ መንስኤ ከሆኑ የትራፊክ ሥጋቶች አንዱ ጎረፍ ነው፡፡ በተለይ የተንጣለለ አስፋልት ላይ የሚተኛ ጎርፍ፡፡ መኪናዎች የተንጣለለውን ጎርፍ ተዳፍረው ማለፍ ስለማይችሉ ጥጉን የተረፈውን አስፋልት ለመጠቀም ይገደዳሉ፡፡(ለአብነት የመገናኛ አደባባይ፣የቦሌ-ሳሪስ መንገድ….. መውሰድ ይቻላል) አደባባዩን ለመዞርና መንገድ ለመሻገር ሰዓታት ይፈጃሉ፡፡ እኔ ልቅደም እኔ ልቅደም የሚለው ስግብግብነት ሲጨመር ወደግጭት አደጋ ይቀየራል፡፡ እግረኛው’ማ ምን ተስፋ አለው፡፡ እንደሃገሬ ገበሬ ወንዙ እስኪጎድል መጠበቅ አሊያም መኪና እየተንጠላጠሉ ለመሻገር መጣር፡፡

የአስፋልት ላይ ጎርፍ መጠራቀም ችግር ሁለት ምክንያቶች ያሉት ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪው የንድፍ ሥራው (Design) ረባዳውን የማጥፋት (level) ሥራ ሳይገልጽ ሲቀር ወይም ተገልጾ ሳይሰራ መቅረት ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት የፍሳሽ ማስወገጂያ (sewerage) ችግር፡፡ ይህ የከተማዋ መሠረታዊ ችግር ቢሆንም በተለይ አዲስ እየተሰሩ የሚገኙ መንገዶች ሰፊና በቂ የፍሳሽ ማስወገጃ ተገቢ ከሆነ የማስተንፈሻ ቦታ ጋር አለመስራት ለነገ ያለማሰብ ችግር ነው፡፡ ለነገ በዝቶ ሊመጣ ለሚችል ፍሳሽ ማስገጃነት ሊውሉ ቀርቶ የዛሬን ፍሳሽ ሜዳ ላይ ከዘረገፉት የአሰሪያቸው ባለስልጣን አርቆ የማየት እጥረት እንዳለበትና በዛሬ እፎይታ የሚደሰት መሆኑን አመላካች ይመስለኛል፡፡

የአስፋልት ላይ የጎርፍ ችግር በተደጋጋሚ የሚነሳ ቢሆንም የሚወስዱት ማስተካከያ ግራ የገባቸው ይመስላል እንደ ድሬዳዋ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች፡፡

ሠናይ ወርኃ ክረምት

:  አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ ነው፡፡

ሐምሌ ፩/፳፻፬ ዓ.ም

አዲስ አበባ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑