የትዳር ገጾች
የህይወት እንቆቅልሽ ለመፍታት
አጋር ረዳት መፈለጉ
ከአቻ ተጓዳኝ ጋር መጣመር
ከብቻ ህይወት ማፈግፈጉ
ምኑ ላይ ነው ወጉ?
ያለመተማመን ቅመም የበዛበት
የመውደድ ሽታ ‘የታጠኑ
ለአብሮነት ህይወት ማዕድ
ከአንድ ገበታ መስፈኑ
ምንድር ነው እርባኑ?
እኔነትን ከፍሎ ለተሰጠው
የ’ርሱነትን ጣእም ማጣጣሙ
መተሳሰብ ባልከበረበት
ለአንድነት ኑሮ መታመሙ
ምን ይሆን ጥቅሙ?
ስሜትን መካፈል ያልነገሰበት
የጥምረት ካባ መደረቡ
ክብርን መሙላት ካልቻለ
የልብ መጥመጃ መረቡ
ምን ይሆን ግቡ??
ለትዳር ነፍስ ሥጋና መንፈስ
ፍቅር እምነትና መተሳሰቡ
እነኚህ መሰረት ናቸው
ዘር ማብቀያ መደቡ
በግልጽ ውይይት ከሰለጠነ….
በፈሪሃ እግዚአብሔር ከታጠረ
በእርካታ ፍሬው ይለቀማል ከዛፉ
ረፍት ሠላምና ተስፋ
ከቅርጫት ሞልተው እየተረፉ፡፡
ኅዳር ፪/፳፻፩ ዓ.ም
አዲስ አበባ
Leave a comment