የተማረ ይግደለኝi

(click to read pdf)

የተማረ ይግደለኝi

መሞትስ በተማረ እጅ ማለት እንዳልሆነ የምሳሌ አነጋገር ትርጉም ያስረዳን ይመስለኛል፡፡ የተማረ፡ እጁ ለመግደል የተባረከ ማለት አይደለምና እርግጥ አለማወቅን ለማጥፋት፣ ድንቁርናን ለመግደል፣ ፈዛዛነትን ለመንቀል የተባረከ ይሆናል፡፡ አዎ መሞትስ በተባረከ እጅ! ልቤን የሞላውን ሕይወት አልባ ጥበብ ይደምስስልኝ፡፡ እውቀት አልባ ቀኔን አብዮታዊ-የመማር እርምጃ ይውሰድበት፡፡ ብልሃት የጠፋውን የአኗኗሬን ድንበር ይድፈረው፡፡ ብሩህ ቀንን ያሳየኝ፣ የሠለጠነ የኑሮ ዘይቤን ይግለጽልኝ፡፡ የመሻሻል የመለወጥ ተስፋን ይፈንጥቅልኝ፡፡ ብንልም መልካሙን ብለናል፤መማር እንዲህና ለእንዲህ ካልሆነ ለምኑ!!

የተባረከ እጅ የጠፋቸው ብዙ ‘የተማሩ’ ምሁራን እየበዙልን ይገኛሉ፡፡ እኔ እስከሚገባኝ መማር የአካል የመንፈስና የአዕምሮ ለውጥ ማምጣት ይመስለኛል፡፡ የተማረ ሰው አካሉ የዳበረ፣ መንፈሱ የጠነከረና አዕምሮው የበለጸገ መሆን ይኖርበታል፡፡ ትምህርት ደግሞ ከሁለት መንገድ ይገኛል ከትምህርት ቤትና ከልምድ፡፡

አካል ስንል ፈጦ የሚታየው ቁመና መልካችንን የሚገልጸውን ማለታችን ነው፡፡ አንዲት ህጻን ልጅ ሰውን ስትጨብጥ ከአንገቷ ጎንበስ በአንድ እጇ ሌላውን ጨብጣ በአክብሮት መጨበጥ እንዳለባት ብናስተምራት እርሷም እንዳልናት ብታደርግና ብትለምደው ተማረች ማለት እንችላለን፡፡ የህጻኗ ትምህርት ሶስት ነገሮችን የለወጠ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ አካሏ መታዘዝን ለምዷል፤ ማጎንበስ እጅን በእጅ መጨበጥ የማያስቸግራትና ለሰላምታ ጊዜ የሚታዘዝ አካል ኖሯታል፡፡ መንፈሷ ማድረግ በመቻሏ ኩራት፤ እውቀቱን በማዳበሯ ልበሙሉነት አዳብሯል፡፡  ከሰው ጋር የምትግባባበት ትልቅ እውቀት ቀስማለች፡፡ ይህ ተጨማሪ ለውጥ ነው፡፡ ስለዚህም መማር የአካል ለውጥ ያመጣል፡፡ ትምህርት አካልን የሚያፈዝ ሳይሆን የሚያነቃ ያደርጋል፡፡ ለመታዘዝ የሚያዘግም ሳይሆን ፈጣንና ጤናማነት እንዲበዛ ይረዳል፡፡ ልክ አንዳንዶች ከትምህርት ቤት ሲወጡ አካላቸው በምግብ ብቻ ደልቦ ለሥራ የሚታዘዝ ሳይሆን ለምግብ ወፍራም ትዕዛዝ የተገዛ ይሆናል፡፡ ኃላፊነትና ጫና ሲሸከም የሚዝል የሚርበደበድና ፈጥኖ የሚደክም አካል ይኖራቸዋል፡፡ የአካል ለውጥ እድሜን ተከትሎ የሚመጣ የተፈጥሮ ሂደት ቢሆንም ትምህርት ጤናማና የተስተካከለ ማድረጊያ አንዱ ገበታ ነው፡፡ እንደው እንደ ህጻን ልጅ ራሳቸውን መሸከም የሚያቅታቸው ‘የተማሩ’ ትልልቅ ሰዎች አላጋጠመዎትም?

መማር መንፈስን በማጠንከር ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል፡፡ ይሄ ወሳኙ የትምህርት ጠቀሜታ ነው፡፡ የት/ት ገበታ የተለያዩ ሰዎች ባህል፣ እምነት፣ ልምድ፣ ተሞክሮ፣ ሕይወት፣ ስኬት፣ ሕልምና ምኞት…. ደባልቆ መመገቢያ ማለት ነው፡፡ ብዙዎች አዲስ ባህል ይለምዳሉ፡፡ ልምዳቸውን ያካፍላሉ፣ ምኞት ይሰርቃሉ፣ እምነት ይጋራሉ ወይም ተሞክሮ ይኮርጃሉ፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ግን በጠመኔ ተጽፈው የሚረዱት ሳይሆን ከአብሮት ሕይወት የሚቀዷቸው መጠጦች ናቸው፡፡ አማራጭ ቤተ መጻህፍት ሳይሆኑ የእለት ተእለት የንባብ ገጾች፡፡

ተማሪው በእነዚህ ት/ቶች ሲሞላ  የጠነከረ መንፈስ ይገዛል፡፡ ሥነ-ምግባሩ የታረመ ይሆናል፡፡ የጸና እምነት ወይም ሕይወትን የሚመለከትበት ብዙ መነጽሮች ያሉት ዓይናማ ይሆናል፡፡

በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ናቸው በሥነ-ልቡና (sychology) ክፍለ ጊዜ መምህራቸው አንድ ጥያቄ እንደዚህ ይጠይቃቸዋል፡፡ “እናታችሁ በጠና ታማለች ለሞት በሚያሰጋ ህመም ግን ለህክምና በቂ ገንዘብ የላችሁም፡፡ በሥራ ቦታችሁ አንድ ባለጉዳይ አንድ ጉዳይ ታስፈጽሙለት ዘንድ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ማማለያ አቅርቦላችኋል፡፡ እንናንተ ብትሆኑ ምን ትወስናላችሁ? ገንዘቡን ተቀብሎ እናታችሁን ማዳን ወይስ ገንዘብን ትቶ እናትን ማጣት?” መምህሩ በክፍል ውስጥ ያሉትን ከሰላሳ በላይ ተማሪዎች እያንዳንዳቸውን እየዞረ መልሳቸውን ተቀበለ፡፡ በአብዛኛው ተማሪ ምላሹ ገንዘቡን ተቀብሎ እናቱን ማትረፍ ነበር፡፡

ገንዘቡን መቀበል ሙስና ነው፡፡ ሙስና ደግሞ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ወንጀል ነው፡፡ ትምህርት መንፈሳችንን አድሶ ለወንጀል የተጋበዘ ሳይሆን በሥነ-ምግባር የታነጸ፣ ለሆዱ የሚያድር አድር ባይ ሳይሆን ለህሊናው የሚያድር፣ እንዴት በልቼው ልደግ ሳይሆን እንዴት በላቤና ትረቴ ልደግ የሚል መንፈስ ሊሞላን ይገባል፡፡ ይህቺ ዓለም የቆመችው መንፈሳቸው በበጎ በጠነከረ ሰዎች እርዳታና እገዛ ነው! ሌሎችማ ተጠፋፍተው ባጠፏት ነበር፡፡ ካልተማረው መለየታችን እንዴት ይገለጻል? ለሕይወት ባለን አመለካከት፣ ጥቅመኝነት ባልዘመዘመው እምነታችን፣ ከተሞክሮዎች በምናመጣቸው ችግር ፈቺ መፍትሄዎቻችን፣ ላልተማረው ባለን ክብርና ይልቁንም ሕይወት ላስተማረችው ልምድ በመንበርከካችን፣ የሌላውን ወግና ባህል አክብረን የራሳችንን በማስጠበቃችንና ለማኅበረሰባችን አለኝታ በመሆናችን አይመስላችሁም?!

የመጨረሻው መማር የአዕምሮ ለውጥ ነው፡፡ ይህ ለውጥ አብዛኛው ‘የተማርኩኝ’ ነኝ የሚለን መማሩን ሊያሳየን የሚገለጥበት መንገድ ነው፡፡ አዲስ ቋንቋ በማውራት፣ ጥራዝ ነጠቅ እውቀቱን በመንዛት፣ ሊያግባቡን በማይችሉ ት/ታዊ (accadamic) ቋንቋዎች በመናገር፣በማወናበድ ‘መማሩን’ና መለየቱን ሊያሳየን ይጥራል፡፡ ለእኔ ከላይ የተባሉት ለውጦች አብረውት ካሉ ይህን ቢያደርግ አይከፋኝም፡፡ አሊያ ግን ቀለም (ደረቅ ት/ት) ብቻውን ፍቅር አይገዛም፣ አብሮነትን አያዳብርም፣ ክብርን አይለግስም፣ ሞገስ ጸጋ አያላብስም፡፡

ይህ የአዕምሮ ለውጥ በአዳዲስ የንድፈ ሀሳብና የተግባር እውቀቶች መሞላት ሲሆን እነዚህ እውቀቶች ሕብረተሰቡ ውስጥ ለተፈጠረን ችግር መፍትሄ ለማመንጨት፣ ነገ የተሻለ ሥልጣኔ ፈጥሮ ኑሮን ለማቅለልና ለማገዝ፣ አርቆ በማሰብ ለነገ ለማቀድ፣ አዳዲስ ዘዴዎች እይታዎችና መንገዶች ለማበጀት ሲችል፣ ለማያውቁት ለማዳረስ (በተቋማት ወይም በሚዲያ)ሲጥርና ተተኪ ማፍራት ሲቻል የተገለጠ የእውቀት ለውጥ እንዳለና የተማረ እንዲጎበኘን መረዳት ይቻላል፡፡ እኛም እጁ የተባረከ በመሆኑ ና የተማርከው ግደልልን እንለዋለን፡፡

እንደአለመታደል ሁኖ ተቋሞቻችን ተማሪዎቻቸውን አንጸው ለማውጣት የሚሞክሩት በት/ት ቀለም ሞልተው ብቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው የተማሪው ጥረት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የተጠበቀ ቢሆንም ተቋማት ትምህርታቸው በእውቀት የበለጸገ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ የጠነከረና በአካል የዳበረ ተማሪ ማፍራት እንዲቻለው ሁኖ መቅረጽ ይኖርባቸዋል፡፡ ነገ ለዚች ሃገርና ህዝብ ተስፋ  የሚመርቋቸው ተማሪዎች የቁጥር ማሟያ ሳይሆን የለውጥ ሐዋርያ እንዲሆኑ ሊተጉ ይገባል፡፡ ሕልምና ርኦት አልባ መምህር እንዴት ለተማሪው ተስፋ ሊዘራ ይችላል? የቀለሙስ ትምህርት ከኑሮና ከሕይወት ጋር ምን ዝምድና አለው? መምህራን ወላጆች ሌሎች ብርቱዎች ልምዳቸውን እንዴት ማካፈል ይችላሉ? ተማሪው ከቀለሙ ጎን ህይወቱን መምራት እንዴት ይችላል? ወዘተ ለዚህም እንዴት ተማሪዎቻቸውን በመንፈስ ማጠንከርና አካሎቻቸው ንቁና የዳበሩ እንዲሆኑ  እንደሚችሉ ያሏቸውን ተሞክሮ በመጠቀምና በማስፋት የትምህርት አሰጣጡ መንገድ፣ ሥርዓተ ትምህርቱና የተማሪ አስተማሪ ወተማሪ ግንኙነት ፖሊሲ መከለስና መንደፍ ይኖርባቸዋል፡፡

አይደለም ሌሎች ለውጦች ተጓድለው የቀለሙን ት/ት ብቻማ እያየነው ነው የመልቀቅና የመንጠባጠብ ችግር!! ሕብረተሰቡም ይህን እያየ የተማረ ይግደለኝ የሚለውን የክብርና የሞገስ ስማቸውን ቀይሮ ተማሪ ገደለኝ እንዳይባሉ!!

:  አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ ነው፡፡

ሐምሌ ፲፰/፳፻፬ ዓ.ም

አዲስ አበባ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑