ሞት ታላቅ መጽሐፍ ነው……..

ሞት ታላቅ መጽሐፍ ነው……..

Click here to read in pdf ብጹእ አቡነ ቄርሎስ በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያርክ ረፍት “ሞት ታላቅ መጽሐፍ ነው እኛ ግን አናነበውም” ማለታቸውን ተጠቅሶ ማንበቤ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ሆነኝ፡፡

መጽሐፍን ገልጠው ቢያነቡት እውቀትና ት/ት ይሰጣል፡፡ ትዝብትን ያካፍላል፡፡ ልምድ ይለግሳል፡፡ ምሥጢር ይገልጣል፡፡ ሕይወትን ይቀኛል፡፡ ሞትም እንዲሁ ነው ድምጹን ከሰሙት ቀለሙን ከለዩት የመጽሐፍ ያህል ነው፡፡ የግለሰብ ሞት ለሟቹ ማረፊያ ነው፡፡ የመሞታቸውን ምስጢር ለሚመረምርና በመሞታቸው የመጣና ሊመጣ ያለውን ጥበብ ለሚጠናቀቅ ማለፊያ እውቀት አዝሏል፡፡

የሰው ልጅ መሆን በቂ ነው—በሰዎች ሞት ለማዘን፡፡ የሃይማኖት ራስ የሆኑ አባትን ማጣት ለእምነቱ ተከታዮች ሃዘን ነው፡፡ ሥራቸው ከሃይማኖት ህግጋት ቢመነጭም ለማኅበረሰብ ከተረፈ ለሃገርና ለወገን የተሻለና የተገለጠ አሻራውን ከጣለ የዚህ አባት መሞት ከእምነቱ ተከታዮች በላይ ዓለሙን የሚያጎድል የከፋ ሀዘን ይሆናል፡፡

የሃገር መሪ—አስተዳዳሪና የሕዝብ ሁሉ ራስ ሲያርፍ፤እራስ የተሆነለት ህዝብ ልቅሶ ማበሻ የለውም፡፡ የመሪው ከሃገር የዘለለ ድርሻውና አስተዋጽኦው ለዓለም ከተረፈ ለመላው ህዝብ ሁሉ ሀዘኑ ጥልቅ ነው፡፡

በሃገራችን የነሐሴ ወር መግቢያ ሳምንታት ሀዘኗን ያከበዱ፣ ጭንቀቷን ያጎሉ በተለይ ለተከታዮቻቸው መሪርና ከባድ ሃዘን የፈጠሩ ነበሩ፡፡ ናቸውም፡፡ እነሆም ቅዱስ ፓትሪያርካችንን ሸኝተን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን (የቀደሙትን) ለመሸኘት በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡

ሁለቱም ያጣናቸው የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገር ያላቸው ይመስለኛል፡፡ የሥልጣን እድሜያቸው በተመሳሳይ ወቅት ጀምሮ እንዲሁ ተፈጽሟል፡፡ ለ21 ዓመታትም አቶ መለስ አገሪቷንና ህዝቧን ገዝተው ሲያስተዳድሩ አቡነ ጳውሎስም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክንና ምዕመኗን ለሃያ ዓመታት ገዝተው አስተዳድረዋል፡፡ ሁለቱም ከሥልጣናቸው ሞት ረፍት ሆኖ ለይቷቸዋል፡፡በየአስተዳደራቸው ክብርና ሞገስ ሲያገኙ የመሰማትና የመደመጥ እድሉንና ኃይሉን ፈጥረዋል፡፡ ሁለቱም የሚነቀፉበትና የሚወቀሱበት ግብር ነበራቸው ሲያስተናግዱትም ሰንብተዋል፡፡ ይመሩበትና ይመ’ሩበት ከነበረው ህግና ሥርዓት ሁለቱም በማፈንገጥ ታምተዋል፡፡ በተለይ ሁለቱም ኃይልና ሥልጣን በራሳቸው ዙሪያ በመሰብሰብ ራሳቸውን ልዩ ኃይል አድርገው ስለዋል ወይም እንዲሳል አድርገዋል፡፡

ሞትን እንደመጽሐፍ ገልጸን ከየገጸ ንባቡ ተተኪዎቻቸው ሊያነቧቸውና አስተውሎት ሊሰጧቸው የሚገቡ ርዕሶችን በደማቁ እናስምርባቸው፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ሁለትና ዋና አርዕስት (ርዕሶች) ማጣት በተፈጥሮ ግዴታ እንደመጣ ዑደት ብቻ ልንቆጥረው ይከብደናል፡፡ ይልቁንም ሃገሪቷ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ስናየው በቀላሉ ዝም ብሎ ማለፍ አይገባም፡፡ በተለይ ተተኪ ከመሰየም ጎን ለጎን ተተኪውም ሆነ ሰዩማነ መላዕክ (አለቃ ሿሚዎች) ጥሩ የማሰቢያ፣ የማገናዘቢያና የመጸለያ ወቅት ያገኙ ይመስለናል፡፡ በኃላፊነት ላይ የሚቀመጥ ማንም ሰው ፈጣሪ ሲፈቅድለት እንደመሆኑ ክፋት ሆነ በጎነት የገለጻቸው መሪዎች የፈጣሪ ምርጫ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግና በተመሳሳይ ወቅት መሪዎችን መነጠቅ የፈጣሪን ፍላጎት የማስተዋያ እድል ይመስለኛል—የሃገራችን ህዝብ ሃይማታዊ እንደመሆኑ፡፡

   ከአቡነ ጳውሎስ የተረከብነው…….

የኢትዮጵያ ቤ/ክ በዓለም ስሟ የታወቀና የተከበረ ሆናለች፡፡ ቅርንጫፎቿ እየበዙ ሥሯ እየረዘመ ይገኛል፡፡ ካህናተ ወአድባራተ ብዙ ሆናለች፡፡ የብዙ ት/ቤቶችና የጥቂት ከፍተኛ ተቋማት ባለቤት ነች፡፡ አጥቢያ ቤ/ክናት ራሳቸውን እንዲችሉበት በሚል ብዙዎቹ የህንጻና ሱቅ ባለቤት ናቸው፡፡ መምህራነ ወንጌልና ዘማሪያን ባይበቃትም’ኳ ብዙ አፍርታለች፡፡

በሌላ በኩል በሃገር ውስጥ ያላት የመሰማት ኃይሏ በተለያዩ ምክንያቶች እያነሰ መጥቷል፡፡ አስተዳደሯ እየላላ ዘመኑን ያልዋጀ በመሆኑ ፈጣን እርምጃ ያለመውሰድ፣ተፈጻሚነት መጉደል በተለይ የበላይ ውሳኔዎችን ያለመታዘዝና አንዱ የሌላውን የሚሽርበት መሆኑ በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ በቤ/ክኗ መዋቅር ስር ያሉ ኃላፊዎች (ከራስ እስከ ጥፍር) በዝምድና፣ በጎሰኝነትና ጥቅማጥቅም በመታለል እየደረሰ ያለ የአስተዳደር በደል እሮሮና እሰጥ አገባዎች እንደበዙ ከራሷ ከቤ/ክኗ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህም ዘመን ቤ/ክኗ በየአድባራትና ገዳማት የሚገኙትን የቤተክርስቲያንና የዓለም ቅርጽ የሆኑ መጻህፍት ታሪካዊና ትውፊታዊ ቅርሶች ለመመዝገብና ተገቢውን መረጃ ለመያዝ ጊዜው የበቃት አትመስልም፡፡

በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ የሚሾማቸው አባት ትልቅ የኃላፊነት ሸክም እንዳለባቸው እንረዳለን፡፡ የሚመጡት አባትም ሆኑ ሌሎች ኃላፊዎች (በተለይ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት) የሥጋዊ ጠባያት የታየበት የአስተዳደር ዘይቤና ግለሰባዊ ጠባያት ከመንፈሳዊው አገልግሎት እንዲወገዱ ማድረግ ያስፈልቸዋል፡፡ ከምንም በላይ ከግላዊ ጥቅምና ራስን ከማግለል ተለይቶ የቤ/ክኗን መዋቅር በመጠበቅና የአስተዳደር መዋቅሯን ዘመኑን የዋጀ (ጊዜው የሚፈልገውን) እንዲሆን መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህም የምዕመኗን አቅም፣ የጊዜና እውቀት አስተዋጽኦ በሚገባ ለመጠቀምና አንድነትን ለማጠናከር ሲረዳ ቤ/ክኗና አባቶችም ያላቸውን የመሰማትና የመከበር ኃይል ማደስና መለወጥ ይቻላቸዋል፡፡

ተረፈ መለስ (ሃገሪቷ ከአቶ መለስ በኋላ)……

የሚታዩና ሊለኩ የሚችሉ ብዙ አንጻራዊ ለውጦች ውስጥ ትገኛለች— ሃገራችን፡፡ ቀድሞ ከነበሩ ስርዓቶች በተሻለ ብዙ የት/ት ተቋማት ተከፍተውላታል፡፡ የ1ና የ2 ደረጃ ት/ት ሽፋን ብዙ ተመንድጓል፡፡ በየዓመቱም ከመቶ ሺህ በላይ ተማሪዎች ከፍተኛ ተቋም ይገባሉ፡፡ እየተመረቁም ነው፡፡

ሃገራችን ኢኮኖሚዋ ሽቅብ እየገሰገሰ ሞገስና ብርታት አስገኝቶላታል፡፡ ዓመታዊ የሃገር ምርቷ ቁጥሩ ጨምሯል፡፡ የፍጆታና ግብዓ ፍላጎቷ ከመብዛቱ በላይ የግል ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ የጤና መርሐ ግብሯ ምስጋናን ካሰጧት ዋነኛው ነው፡፡ ብዙ የህክምና ተቋማትና መሳሪያዎቻቸውን እያሟላች ትገኛለች፡፡ የከተማ ልማቷ በዓይናችን የምንመሰክርለት ነው አዳዲስ መንገዶች እየተዘረጉ ህንጻዎች እየተገሸሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ከ 1997 በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት ብዙ ለውጦች እየተገኙ ናቸው፡፡ አባይንና የለውጥ ና እድገት እቅዱን ሳንዘነጋ መሆኑ ነው፡፡

ከ21 ዓመታት በኋላ የተረከብናት ኢትዮጵያ ከላይ በተዘረዙት መስኮች ላይ ከተገኙት ለውጦች ጋር ያልተሟሉላት ችግሮች ነበሯት፡፡ ኢኮኖሚዋ ይደግ እንጂ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረገ አልነበረም፡፡ በቀን ከ3 ጊዜ በላይ የመብላት ተስፋዋ ቀርቶ አንዱንም አተው በተዘረጋው መንገድና ህንጻ ውስጥ ሳይሆን በደሳሳ ጎጃቸው አንጀታቸውን ታቅፈው የሚበሉት ስለሚያስቡ ዜጎቿ ጉዳይ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡ በሌላ በኩል መቆጣጠርና መፍትሔ ሊመጣለት ያልተቻለው የዋጋ ንረትና የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እጥረት ህብረተሰቡ መሰቃየቱን ለምዶት በዝምታ ተውጧል፡፡ መንግስትም ዋና የንግድ መስኮችን አላካፍልም በማለቱ የቴሌን አገልግሎት ከነችግሮቹ የመብራትና ውኃ እጥረትም ሳይቀረፉላት እዚህ ደርሳለች፡፡ 85% ገበሬዋ አሁንም የሚበቃውን ለማምረት አልተቻለውም ኢንዱስትሪዋ አድጎ የሥራ እድልና የምጣኔ ሀብት እድገት ጥንካሬ ሊፈጠር አልቻለም፡፡

ከ21 ዓመታት በኋላ የተረከብናት ሃገር አሁንም በመልካም አስተዳደር እጦትና ብልሹነት ተውጣ ነው፡፡ የፍትህ ስርዓቷ በተረጋጋና በተደላደለ መሠረት ላይ የሚያቆሙ ተቋማት አልተዘረጉላትም፡፡ በዚህም ሀሳብን በነጻ የመግለጽ የመጻፍና የመናገር እንዲሁም በህግ ፊት እኩል የመቆም መብቶች እየተዳፈኑ ይገኛሉ፡፡ ፓርቲዎች የመደራጀትና የመንቀሳቀስ ሚዲያን እኩል የመጠቀም መብት በ 97 ያየነው ይደገማል ብለን ተስፋ ከመጠበቅ ውጪ አሁን በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ተዳፍኖ መዝጊያው ላይ የደረሰ ይመስላል፡፡ የሃገሪቷን ባህል ትውፊትና ልማድ አክብሮ እንዲከበር ባለመደረጉ ማኅበረሰቡ የባህል ቀውስ ውስጥ ለመግባት ከጫፍ ላይ ይገኛል፡፡

በ21 ዓመታት ውስጥ የተፈጠረው ትውልድ ይህን መንግስት ብቻ የሚያውቅ ነውና እድሜውን ከሥራው ጋር ያነጻጽራል፡፡ በመሆኑም አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትራችን የተገኙትን ብዙ ተግባራዊ ለውጦችና ድሎች ከማስጠበቅና ከማስቀጠል ጎን ለጎን መንግስት የሚወቀስባቸውንና ያላሟላቸውን ጉዳዮች ለመዳሰስና ማስተካከያ ለማድረግ ጥሩ ወቅት ላይ ያሉ ይመስለናል፡፡ በተለይ በአቶ መለስ ሞት ብዙ ህዝብ ሀዘኑን መግለጹ ህዝቡ በእሳቸው ፍጹምና የተሟላ አስተዳደር አግኝቷል ማለትን አያመለክትም፡፡ ለሥራዎቻቸው ሁሉ ማጽደቂያ አድርጎ መውሰድ ተገቢ አይመስለኝም—የህዝቡን ጨዋነትና አዛኝነትን እንጂ፡፡ መንግስትም ሆነ አዲሱ መሪያችን የሚባለውን ለመስማት ለዜጎች ሃሳብ ክፍትና አምኖ ለማስተካከል የቀኑ ይሆኑ ዘንድ ወቅቱ ይጠይቃቸዋል፡፡

ስለዚህች ሃገር ሁሉም ባለሙያ፣ምሁር፣ ዜጋና ኃላፊ ይመለከተዋልና በጋራ መስራትን አዲሱ መሪ ሊያሳዩን የሚገባው ነው፡፡ ኃላፊነት እሳት ነው፡፡ ቀድመው ለመጪው ሊጠቅም በሚችል፣ ትውልድን በመገንባትና በማነጽ ሥራ ላይ ከተሰማሩ እሳቱን ህዝቡ ይታደጋቸዋል፡፡ ስለዚህም ልዩ ቃል የመግቢያና መሐላን የማደሻ ወቅት ነው—ለነገዋ ኢትዮጵያ፡፡ ፈጣሪ የሙታንን ነፍስ ይማርልን፤ ለመጪዎቹ እርሱን መፍራትን በልባቸው ይሙላልን፡፡ አሜን!

 : አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ ነው፡፡

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑