አለሁኝ ባይ

አለሁኝ ባይ

Click to Read in pdf

ሰናይት እባላለሁ፡፡ እድሜዬና አካለ ቁመናዬ ለየትኛውም ደረጃ ይመጥናል፡፡ ብዙ ጓደኞች አሉኝ፡፡ ከአንገት፣ ከልብ፣ ከእግር…. ወዘተ የሚወዱኝና የምወዳቸው፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር ስሆን የምኖረው የአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰራተኛ ነኝ፡፡

ጥቂት ገላጭ የሆኑ እውነታዎች የነገርኩህ ይመስለኛልና ትረዳኛለህ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሰናይትን ላታውቃት ትችላለህ እንደእውነቱ እኔም አላውቅህም ብቻ በውስጤ የታፈነውን በአንድ ወቅት ያጋጠመኝን ልተነፍስልህ ይሄን ጽፌዋለሁ፡፡

አየሩ ከጠዋት ጀምሮ አኩርፏል፤ ቀኑም እንደዚያው ይመስለኛል፡፡ ትንሽ ትንሽ ያነባሉ፡፡ ሥራ ከወትሮው በተለየ ፈጠንና ነቃ ብዬ የገባው ሲሆን መልካም ጤንነት ይሰማኛል፡፡ በእርግጥ ሰው ሁሉ በውስጡ የሚይዘው አንዳች ጉዳይ/ሐሳብ ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ፤ እኔም ያዳፈንኩት ሐሳብ ነበረኝ፡፡ ጠዋት ከሻይ ሰዓት መልስ ከአለቃዬ የተሰጠኝ ደብዳቤ ግን በውስጤ አዳፍኜ የተምተወው ነገር አላስቀረልኝምና ውስጤ ተረበሸ፡፡ ሰው በሕይወቱ ስንት ያልጠበቀው ነገር ያጋጥመዋል? በዚህ ጭንቀት፣ ንዴትና እልህ ውስጥ እያለሁ በስልክ የሰማሁት ደግሞ ቁስል ውስጥ ስንጥር እንደመሰንቀር ሆነብኝ፡፡ ጥዝጣዜው በዛ፡፡ የዳመነው ውስጤ መዝነም ጀመረ-እንደደጁ፡፡

መቼም ምን ቢያጋጥማት ነው ማለትህ አይቀርም፡፡ ያጋጠመኝን ለመንገር ከስር መሰረቱ መተረክ ያስፈልገኛልና በዚህ ጊዜህን አልሻማም፡፡ አንድም የእኔ ዓይነት ችግር ምናልባት የብዙዎች ላይሆን ስለሚችል ሁሉም የራሱን ቁስል እንዲያስብበት ስል ከችግሩ መዝነም በኃላ ስለሆኑት ብቻ ልነግርህ እወዳለሁ፡፡

በጣሙን ከመንደዴና ከመንገብገቤ በላይ ባዶነት ተሰማኝ፡፡ የተጣልኩ ብቻዬን የቀረሁ መሰለኝ፡፡ አዎ ከሥራ ባልደረቤቼ ጋር በደህና ጊዜ አግባብ ያለው የጠነከረ ወዳጅነት የለኝምና ቅርቤ መስለው አልታዩኝም፡፡ ይህን ሳውቅ ይበልጡን ሰው ናፈኩ፣ተራብኩኝ፡፡ ከአንድ ሰው ጋር የግድ መገናኘት እንዳለብኝ አመንኩ፡፡ ከሥራ ወጥቼ እግሬ ወደመራኝ መጓዝ ጀመርኩ፡፡ ደግነቱ እጅግ የተመረጡ ጓደኞች አሉኝና ከአንዳቸው ጋር በመገናኘት ብሶቴን እንዲጋሩኝና እንዲያበረታቱኝ፤ አለሁሽ አይዞሽ ከአንቺ ጋር ነን እንዲሉኝ ማድረግ ስለምችል በደስታ ፈካው፡፡ ስልኬንም አንስቼ ምንተስኖት ጋር ደወልኩ፡፡ ምንቴ የጋራ ልብ ያለን እስኪመስለኝ ቅርቤ ያለ ነውና መረጥሁት፡፡ “አሁኑኑ ላገኝህ እፈልጋለሁ!”

“ምን አጋጠመሽ ሰኒ?”

“እሱን ስትመጣ! አሁን ፍጠን እባክህ እንዳትዘገይብኝ” ያለሁበትን ልነግረው ስጣደፍ

“ሰኒዬ በጣም ይቅርታ አድርጊልኝ ከከተማ ወጣ ብያለሁ….. አሁን አልደርስም…” እና ሌሎችንም ነገሮች ነገረኝ የቀረውን ባልሰማውም፡፡ ለማስተዋል ጊዜ አላገኘሁምና ሃይሚ ጋር ስልኬን መታው

“አሁኑኑ ላገኝሽ እፈልጋለሁ ቶሎ ነይልኝ….”

“ሰኒ የኔ ቆንጆ ምን ሆንሽብኝ?”

“ሃይሚ ከሌግዠር ሆቴል ፊት ለፊት ካለው ማደያ……..”  አቋረጠችኝ፡፡ ፈጽሞ ያልጠበኩት

“ …ሰኒ ምንድነው የሆንሽው ንገሪኝ? …. ይኸውልሽ… እኔ..” ባጭሩ ልትመጣልኝ አልቻለችም፡፡ ነፍሷ ሰውን ለተራበች አንዲት ሴት ይሄ ዜና ምን ያህል ቅስሟን ሊሰብራት እንደሚችል መገመት አይከብድህም፡፡ መራመዴን አቁሜ ከአንድ ግድጊዳ ተደገፍኩ፡፡ በግንባሬ በኩል አንዳች ነገር ተፈትልኬ ካልወጣሁ ሲለኝ አፍኜ ያዝኩት፤ በሌላኛው እጄ ቁጥር እየመታሁ፡፡ ስለኩ ተጣራ፡፡ ተነሣም፡፡ ልታገኘኝ ባለመቻሏ ማዘኗን ነገረችኝ፡፡ ከዚህ በላይ ጉልበት ያለኝ አልመሰለኝም እንደምንም ብዬ አራተኛ ጓደኛዬ ጋር ስልኬን አስጮኹክ፡፡

“እባክህን …. አሁን ላገኝህ እፈልጋለ..ሁ”

“እንዴት!” ጮኹኩኝ ለራሴ፡፡ የአጋጣሚዎች መደራረብ ነው ብዬ ለማመን ተቸገርኩ፡፡ እርሱም አልቻለም፡፡ አራት የቅርብ ጓደኞቼ በዚህ በጭንቀቴና እጅግ ሰው በሚያስፈልገኝ ሰዓት ሊያገኙኝ አልፈቀዱም ወይም አልቻሉም….. ምን ሊሰማኝ እንደሚችል አንተ መገመት ትችላለህ፡፡

እግሬ እንደሚራመድና እጆቼ ግድጊዳ እየተደገፉ ጉዞ መቀጠሌን አስታውሳለሁ፡፡ ‘ሳይደግስ አይጣላም’ እንደሚሉት ይመስለኛል በጉዞዬ መሐል ከቅርብ የቤተክርስቲያን ጉልላት ይታየኛል፡፡ አንዳች ስበት ጎትቶኝም ደርሼ ገባሁ፡፡ ከዛፍ ስር ተቀምጬ የአንገት ልብሴ እስኪርስ ድረስ አነባሁ፡፡ አይኖቼን አላዘዝኳቸውም ዝም ብለው ያፈልቃሉ-ትኩስ ውኃ፡፡ እስኪበቃው ድረስ አይኔ ማንባቱን ቀጠለ፡፡ አዕምሮዬ ውል ያለው ነገር ባያስብም ቅሉ እያነባሁ በሐሳብ እከላወስ ነበር፡፡ በእንባዎቼ ታግዞ ተዝቆ የወጣለት ይመስል ቀለል ሲለኝ ይሰማኛል፡፡ ፊት ለፊቴ የሚታየኝ የመቅደሱ ጉልላትና መስቀሉ ነበር ከዛ በላይ ሰማይ………… በሰማይም አንድ ኃይል…..የማይተው የማይረሳ ፈጽሞ የማይዘነጋ ዘወትር አለሁኝ የሚል ልዕለ ኃያል አምላክ፡፡

እግዜርን በአካል እጠብቀው እንደሆን’ጃ፡፡ በብዙ የሕይወት ጉዞዎቼ አብሮኝ መኖሩን ቢነግረኝም ቅሉ ዛሬ ግን ፍንትው ብሎ ታየኝ፡፡ ለካስ እግዚአብሔር የሚገለጠው ሰው በሚረዳውና በሚገባው መጠን ነውና፡፡ ውስጤን ተስፋ ሲሞላ፤ አካባቢዬን ሠላም ሲያውደው አየዋለሁ፡፡ ጊዜ፣ አካባቢና ሁኔታዎች የማይከለክሉት ወሰን ድንበር አልባ ነው ለካ! እየቆየሁ የተረዳሁት በፊቱንም ቅዱስ መንፈሱ በውስጤ መኖሩን እኔ ሌላ እርዳታ ሌላ መጠጊያ ፍለጋ መባዘኔን ነው፡፡ ይኸውም አሁን እዚህ ተቀምጬ የመጣ ሳይሆን በውስጤ የነበረ መንፈሱ ሲሞላኝና ሲያድሰኝ ተሰምቶኛል፡፡

እውነቴን ነው የምልህ ወዳጄ! ከቅጽሩ ስወጣ ያቺ ተንከላዋሽ መጠጊያ ያጣችው ሴት ፈጽሞ አልነበረችም፡፡ አጠገቧ ሁኖ እንደሚያጫውታትና በትከሻው ደግፎ እንደሚያባብላት ዓይነት በብዙ ምቾትና በብዙ ሠላም ውስጥ ሆና ነው ስትወጣ የምታያት፡፡ የአጋጣሚ ይሁን የትእዛዝ ባላውቀውም ብዙም እንዳልራኩ ከደወልኩላቸው ጓደኞቼ አንደኛውን አገኘሁት፡፡ አብረን እየተጫወትን አዘገምን፡፡ ምን እንዳለኝ ግን ታውቃለህ?

“ሰኒ ሙች! እንደዚህ የተጎዳሽ አልመሰለኝም እንጂ’ኮ እምጣ ነበር”

ገርሞኝ አይደለም የጻፍኩልህ፡፡ እግዚአብሔር ምን እንዳስተማረኝ እንድትረዳኝ ብዬ’ጂ፡፡ አለሁኝ ባይ ማን መሆኑንና እንዴት ያለ መጠጊያ መሆኑን ትረዳ ብዬ ነው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ያበዛልኝ ሠላሜ ሁሉ ይሙላልህ፡፡

ያንተው ሰናይት፡፡”

የሰናይት ማስታወሻ ከደረሳቸው አንዱ በመሆኔ ለእናንተ አካፍለው ዘንድ ወደድሁ፡፡ እናንተም ለወደዳችሁት አካፍሉት፡፡

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑