ያልሞተው ሟች

(CLICK HERE TO READ IN PDF)ያልሞተው ሟች

ቅድመ አግድም……

ከቁሙ አፈር ላይ አፈር አልባ ወዙ

ተራ ላብ እንዳይሆን ጨው ጨምሮበት

ለቁልሉ አፈር ጣይሙን ‘ዲጣፍጥ

ሕይወት ‘ዲዘራ ወዙን ቢቀዳለት

አፈር ውኃ ወሰደው አፈር አፈር በላው

‘ሚሉት ትርጓሜ ዘመኑ አለፈ

ሲፈጠር ከአፈር ሲፈርስ ወደአፈር

እርባን የለሽ ትረጉም የቀድሞ ታጠፈ፡፡

አፈር ወዝ አውጥቶ አፈር ላይ ሲጨመር

የወዙ መዓዛ ሰፈሩን ያውዳል፡፡

ቢጋደም ይቀናል በቁሙ ቁልሉን

እንደናርዶስ ሽቶ ጣዕሙን አካፍሎታል

ድህረ አግድም….

ተድቦልቡሎ ሲቆም ያለ የነበረ

ማገር ተበጣጥሶ ቋሚውም ወደቀ

ያ’ፈር ቤት ተረስቶ ትዝታ እስኪሆን

አፈር አፈር ገባ ታሪኩ አለቀ፡፡

ቁማሙ ተጋድሞ አፈር አፈር ሆኖ

ቆየ ከተረሳ ያ መዋቴ ሥጋ

ሲባል….. በቁመቱ ጊዜ ያንጠባጠበው ወዝ

ሚዛኑ አዘንብሎ ለጣእሙ ዋጋ

አፈር ይወለዳል አፈርም ይሰራል

መዋቴነቱ ቀርቶ በሥራው ያብባል

ቁሙ ቢጋደምም አግድሙም ይቆማል

የተወለደ’ጂ የሰራ መች ሞቷል!

ሕያው ሥራ……

’ሥጋ ሳይበሰብስ የቁም አፈር ሳለ

በመኖሩ እድሜ ሀብቱን ከገለጠ

ለኖረበት ትውልድ አሻራውን ጥሎ

ወዝ-ባሉት ሥራ ጣዕሙን ከሰጠ

ህያውነት ለ’ርሱ መንታ ገጽ ተላብሶ

መኖርና መሞት ከአንድ ተደባልቋል

በሥጋው እያለ ከመኖሩ በላይ

ህይወት ያለው ሥራው ኖረ ያሰኘዋል!

ህያው ሞት….

የሥጋነት ኑሮው ‘ረፍተ ዘመን ገቶት

ከቁምነት ተርታ ወዳግድም ቢሰለፍ

ዓይኑ ባያማትር ጆሮውም ባይሰማ

መናገሪያ ልሳን አንደበት ቢቆለፍ

በአካል ተገልጾ ለቁልሉ አፈር

አለሁልህ ባይል ሞት በ’ሱ ሰልጥኖ

ከመቃብር ውስጥ ካ’ግድምነት ኑሮ

ቃሉ ያስተጋባል ለዘመናት ገኖ፡፡

መቃብር ያልገባው ያ የ’ጁ አሻራ

ሞት መቼ ነካው ህያውነት ለብሶ

ስሙን ያስወድሳል ክብሩ ይዘከራል

ሞቷል ሲሉት ኖሯል በሞት ጀርባ ነግሶ

እናም….

እናማ! ሥጋው አፈር ሁኖ መቃብር ሲውጠው

ካ’ፈር በላይ ሆኖ ሥራው ከሸተተ

ቁሙ ቢጋደምም አግድሙም ይቆማል

የተወለደ’ጂ  የሠራ መች ሞተ!!

ጥር ፳/፳፻ ዓ.ም

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑