ምን ታህል ፴፩ ዓመት?
የትውልድ እድሜ ናፍቆት
የዑራ ታሪክ ድምሰሳ
ዘመኑ ጥቅምት ባተ
ደስታን ጠግቦ ‘ያጋሳ
ከ 31 ዓመታት በኋላ የአንድ ሰዓት ዘገባ
ዛሬ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአህጉራዊ እግር ኳስ ጨዋታ ውድድር ዳር ቆማ ከመመልከት የሚገላግላት የ45 ደቂቃ ውድድር ብቻ ይቀራት ነበር፡፡ ከቀኑ ፲፩ ሰዓት ላይ፡፡
ይህቺ 45 ደቂቃ ከሁለት በላይ ጎል እንዲቆጠርባት ትፈለጋለች፡፡ ከዛማ ትኬት መቁረጥ ነው፡፡ ሁለት ዓይነት ትኬት፡፡ የመጀመሪያው የአውሮፕላን ደቡብ አፍሪካ የሚወስድ ሲሆን ሌላኛው የ31 ዓመት ተመልካችነትን ፍቆ የዚህ ዘመን ተሳታፊ የሚያሰኛት የታሪክ ትኬት፡፡
ግን እንደው 31 ዓመት ምን ያህላል? በምድር እድሜ እንቁጠረው ከአስር ሺህ ውስጥ እንደሚነሣ 31 ቁጥር? ወይስ በሰው እድሜ እንቁጠረው ከ 50 ላይ እንደሚነሣ 31? የሰው እድሜ ይቀላል 31 ዓመት ማለት የአንድ ትውልድ እድሜ ማለት ነው፡፡ የ30 ዓመት ወጣት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ስትሳተፍ አይቷት አያውቅም እድሜውን በሙሉ፡፡ ስለዚህ ምንአልባት
ታሪክ ነው መስራችነት
ታሪክ ነው ተሳትፎ
ዐይን ያየውን ያምናል
ከመስማት ለፈፎ…..
በማለት ያላየውን ላለመስማት ሲጥር ይሄ 30 ዓመቱ ሳይቋጭ የሚያየውን ዐይኑ አመጣለት፡፡ ስላየው ሊያወራም የታሪኩ ባለድርሻ ተሳታፊ ሆነ፡፡ እድሜ ለሁለት ጎል፡፡ ለሁለገብ ተጫዋቹ (በእለቱ ጨዋታ) አዳነና አንድያው ፕሮፌሽናል አጥቂያችን ሳላሃዲን፡፡
እንኳን የዚህ ታሪክ ተካፋዮች ሆንን ማለት ታላቅ ነገር ነው፡፡ ቢያንስ የእኛ ዘመን ለስፖርት ታሪካችን መነሻ(reference) ሆኗልና፡፡ በታሪክ ውስጥ እናብባለን፡፡ እንሰማለን፡፡ ያየነውን እንናገር ዘንድ እንዘግባለን፡፡
ከቤቶ ውስጥ የደስታ ጩኸትና ሁካታ በኋላ ወደ አደባባይ ወጣሁ የአካባቢውን ስሜት ለማየት፡፡ የጉርድ ሾላ አደባባይ ከቤቱ ተገልብጦ በወጣ ህዝብ ተሞልቷል፡፡ መኪናዎች ሲያልፉ በአጀባ በፉጨትና ሆሆታ ታጅበው ነው፡፡ እነርሱም በድርሻቸው ሁለት የፍሬቻ መብራቶቻቸውን ቦግ ድርግም እያደረጉ፣ ጡርባቸውን እየጠሮምቡ፣ የመኪና አካሎቻቸውን እየደበደቡ ቆሞ የሚሸኛቸውን ህዝብ ይሰናበቱታል፡፡
“የእርግብ አሞራ…የእርግብ…” በምሽቱ የተሳካለት ዘፈንና ምናባትም በእለቱ በከተማዋ ሪከርድ በሚሆን መልክ የተዜመ ነው(ተደጋግሞ በመዜምና በብዙ ህዝብ በመዜም)-የእርግብ የእርግብ… አሞራ- የድሮ ጨዋታ!!
ክፍት መኪናዎች ላይ ተጭነው እየጮኹ የሚያልፉ ወጣቶች ለቆመው ወጣት እሳት ናቸው ማንደጃ-ምድሪቷ ትናጣለች፡፡ ባንዲራ እያውለበለቡ የሚያልፉ ባለመኪናዎች የሸኚውን ወጣት ልብ ወኔ የሚዘሩ እንግዶች ነበሩ፡፡ በእግሩ እየጨፈረ ባንዲራ ይዞ የሚመጣ ተጓዥ ካለ አቀባበሉ ጆሮን ይሰውራል ልብል ይሰልባል፡፡ ተጓዡም ተቀላቅሎ ደስታን ተቀባብሎ ጮኾ …. ሳይበቃው ይጓዛል፡፡
የቆመውን ሰው ደስታ ለመካፈል ፖሊስ የጫኑ የፖሊስ መኪናዎች ሆኑ የፌዴራል (ተመላሾች ይመስላሉ) መኪና አልከለከለ፡፡ መኪናውን ንጠው የቆመውን ያስንጡታል፡፡ በተለይ ባለታክሲዎችና ሃይገር ባሶች ከስታዲየም ተመላሽ በመያዛቸው ጭፈራውና ጩኸቱ የተለየ ነው፡፡ ረዳቶች (ወያላዎች) መምጣታቸውን ያበስራሉ በሆሆታ ይቀበሏቸዋል፡፡ እንደጉድ ይቀወጣል…….. የመኪና የመያዝ ልኩ በመቀመጫ ብቻ የተገጣ አልነበረም፡፡ ታክሲዎች’ኳ ሳይቀሩ ከኋላቸው የተንጠለጠለ ወጣት አዝለዋል-ያለምንም መያዣ!! ታዝሎ ከመጣ ወጣት አንዱ መውደቁንና መርዳታችንን ሳልረሳ መሆኑ ነው (ሲወድቅ የጫነው አይሱዙ’ኳ አላወቀውም)፡፡
ከሞባይል መሸጫ ቤት የሚወጣው ሙዚቃ ለአካባቢው የደስታ ግለት ወሳኝ ድርሻ ነበረው፡፡ ወጣቱም ሲያሻው ሞባይል ሱቅ በራፍ ሆዶ በሙዚቃ ይጨፍራል ሲያሻው አስፋልት እያቋረጠ ተጓዦችን ይሰናበታል፡፡ በጨፋሪዎች መሐል የሚያልፍ ባለመኪና ጽዋው ይሄ ነበር- በሰዎች ተከቦና ጎኑ ሆነ ላዩ ላይ በሰዎች ተሞልቶ ተንጦ ተንጦ ይለቀቃል፡፡ ወቸ ጉድ!! አንዱ ፖሊስ ከመኪና የወደቀውን ልጅ “ከሃገሪቷ ደስታ አንጻር ምንም ማለት ነው” ብሎት ነበር የጉዳቱን መጠን እያየ…. ቅልጥ….. ወቸ ጉድ!!
የ31 ዓመት ናፍቆት ምን ያህል ነው? የ31ዓመት ተመልካችነትስ? አሁን የዘገብኩት ያህልስ ይሆን እንዴ? የ፴፩ ኣመት ሰንሰለት መበጠስ ከተቻለ ሌሎች እስራቶችንስ መበጠስ አይቻለን ይሆን እንዴ? እኚያ በታሪክ የታሰርንባቸው ሀብቶቻችን ዛሬ ሰርተን የታሪክ ባለቤት መሆን ይቻል ይሆን እንዴ?
አቦ! እንኳን ደስ አላችሁ!! እስቲ የእናንተን አካባቢ ምሽት አካፍሉን፡፡





Leave a comment