ምድርን የመረገጥ እምነት

ምድርን የመረገጥ እምነት

Click to read in pdf

ህጻኑ ከተወለደ ፮ ወር ቢሆነው ነው፡፡ ከመዳሁ ለመገላገል አንድ የዘየደውን መላ በመለማመድ ላይ ይገኛል፡፡ የአልጋ፣ የወንበር.. ሌላም ቁስ በመያዝ የመቆምና ለመሄድ የመውተርተር ፍላጎት አዕምሮውን ሞልቶታል፡፡ ስለዚህም ይጥራል አሁንም ይጥራል፡፡ በዚህ ሙከራ ውስጥ የተረዳው አንዳች እውቀት ቢኖር ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ነው፡፡ ምርኩዝ የሚሆነው የማይታጠፍ እጅ ወይም እቃ ካገኘ ሀሳቡን ይጥላል፡፡ በእምነት መላውን መለማመድ ይጀምራል፡፡ በተለይ የወላጆቹን እጅ ካገኘ ከሌላው ሁሉ የበለጠ ብርታትና ልበ ሙሉነት ይሰማዋል፡፡ እናም ይውተረተራል የእግሩን ልፍስፍስነት እስኪረሳ ድረስ፡፡ የወላጆቹ እጅ ተንቀሳቃሽ በመሆኑ ለመራመድ ለሚያደርገው ጥረት ወሳኝ አጋዦች ይሆኑለታል- ከቁሶቹ ይልቅ፡፡

የህጻኑ ድርጊት የታወሰኝ የሰው ልጅ መቼ እምነትን ማዳበር እንደሚጀምር ማሰብ በጀመርሁ ወቅት ነው፡፡ ስለሰው ልጅ የጸና እምነት እንዳስብ ያደረገኝ ደግሞ ይህ ጥያቄ ነው

“የሰው ልጅ መቼ ነው ምድር ልትገለባበጥብኝ ወይም ልትንሸራተት አሊያም አንዳች ነገር ልትሆን ትችላለች” ብሎ ሳይረግጣት የሚቀር? አይደለም ሳይረግጣት ሊሸሽ ቀርቶ ስለዚህ ጉዳይ ለማሰብ’ኳ እድሉን ያገኘ አይመስለኝም፡፡ የመሬት ስበትን ህግ በመርሳት አይደለም- ቁልቁል የመሳቡን፡፡ ግን በልበሙሉነት ሳይፈራና ሳይጠራጠር የቆመባትን ምድር ይረግጣታል፤ ይዘልባታል፡፡ ምድሯ ምንም እንደማትሆን የጸና እምነት በልቡ ተስሏል፡፡

አንድ ሰው በምንገድ ሲጓዝ ዝናብ ቢዘንምበትም ጥላውን ዘርግቶ ለመጠለል አያመነታም፡፡ ምክንያቱም ከዝናቡ እንደሚያስጥለው በጣሙን እርግጠኛ ነው፡፡ የዝናቡ ጠብታ ሊቀደው ይችል ይሆን? ጨርቁ ከላዩ ላይ ተገንጥሎ ይጠፋ ይሆን? ወይም ድንገት የወጠሩት ሽቦዎች ውልቅልቅ ይሉ ይሆን? የሚሉ ፍራቻዎችና ጥርጣሬዎች አይነሱበትም፡፡ ያውቀዋላ! ይሄ የገዛው ጥላ’ኮ ነው! ሊያውም ስንት ብር አውጥቶ በዛ ላይ ጨርቁ አዲስ ሽቦዎቹ ጠንካራ ናቸው፡፡ እናም እምነቱን በጥላው ላይ ይጥላል፡፡ ይዘረጋዋል፡፡ ይጠለላልም፡፡

የምድርን እርግጠኛ አይሁን እንጂ ጃንጥላን ሰው እንደሰራው ማንም ያውቀዋል፡፡ የሰው እጅ ሥራ ደግሞ ሊበላሽ ይችላል፡፡ አዲስ ነው ጠንካራ ነው እየተባለ ድንገት ስብር፤ ደርሶ ቅድድ ሊል ይችላል፡፡ ይሄ በሕይወታችን ያጋጠመን ጉዳይ ነው፡፡ ይቆያል ያልነው ቁስ ያለጊዜው ሲበላሽ፤ ያደርሰናል ያልነው ከመንገድ ሲጥለን በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡ የሰው ልጅ የሰራው በመሆኑ ብዙም አይደንቀን፡፡ ያው መልሶ ሰው ይሰራዋላ! ካልሆነም እንጥለዋለን፡፡ እኔን የደነቀኝ ግን ውጤቱ ሳይሆን የመነሻው እምነታችን ነው፡፡ የሙጥኝ፤ ወይም እፎይ የሚል የመደገፍ ፍላጎት የፈጠረው እምነታችን፡፡

ያ ህጻን ልጅ እኛን ባከለና በመሰለ ወቅት ጉድጓድ ትመስለው የነበረች ምድር ሜዳ፣ የምትገለብጠው የመሰለችው መሬት አስተማማኝ መረገጫ እንደሆነች ይረዳል፡፡ ስለዚህ የወላጆቹ እጅ ወይም ደጋፊ ቁሶች አያስፈልጉትም፡፡ በራሱ መቆምና መራመድ እንደቻለ እርግጠኛ ነውና፡፡ ግን የመደገፍ እምነቱን አሁንም አውልቆ አልጣለውም፡፡ መደገፊያውን ቀየረ እንጂ፡፡ ከወላጆቹ እጅና ከቤት ቁሶች ወደ ምድር ቀየረው፡፡ አሁን የሚረግጣት ምድር እንደማትገለብጠው እርግጠኛ ሁኗል፡፡ ስለዚህም እምነቱን ሰጥቷታል፡፡

በአንዳች ነገር እምነት ውስጥ መኖር የሰው ልጅ ሰው የመሆኑ ጠባይና ባህርይ ነው፡፡ ያለ እምነት መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ሰው እምነቱን ባጣ ወቅት ይሞታል፡፡ የለበሰው ልብስ ገላውን እንደሸፈነው ባያምን ኑሮ ከቤቱ ባልወጣ ነበርና፡፡ ስለዚህም ልብሱን እየለበሰው’ኳ ገላውን እንደማይሸፍንለት ካመነ ብቻውን መሆኑ ነው አሊያም መለመሎውን በአደባባይ መዞሩ ነው፡፡ ይሄም ያለማመን እምነቱ ከሌላው ስለሚለየው የመኖሩን እድሜ ያሳጥርበታል፡፡

ልብ ብለን በአንክሮ ሰብእና ካሰብነው እኚህ የሚያያቸውና ሊደገፋቸው የሚከጅላቸው ነገሮች ሁሉ አንዳች ደጋፊ እጅ አላቸው- እነሱንና እሱን እንዲገኙ ባደረገ፡፡ ፈጣሪ በሰው ልጅ ልቡና ውስጥ እምነትን መሳሉ እርሱ የእምነት ሁሉ ራስ መሆኑን ለማስተማር ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሰው ሁሉ ደግሞ በፈጣሪው ላይ እምነት አለው፡፡ የበለጠ እጅ የበረታ ክንድ እንዳለው ሁሉም ያምናል፡፡ ይሄ እምነታችን በልቡና ህጋችን የተረዳነው እውነትና ያገኘነው እውቀት ነው፡፡

ይሄን ሁሉ ባሰብሁ ጊዜ ለፈጣሪ ያለን እምነታችን ምድርን እንደመረገጥ ካለ እምነት በላይ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ኑሮና ህይወታችን ግን ይሄን አይገልጹም፡፡ ፈጣሪን እንደ ምድር ሳንጠራጠረው ብንደገፈውም’ኳ በእርሱ ያለን እምነት ለሌሎች አናሳ ድጋፎች ያሻማነው እምነት ነው፡፡ ሌሎች ትናንሽ ድጋፎች ላይ እምነታችን የበረታውን ያህል በእርሱ ያለን እምነት ይቀንሳል፡፡ መደገፋችን ይዛነፋል፡፡ እኚያ ሰዋዊ ድጋፎች በተመቹን ቁጥር ይበልጡን በእርሱ ያለን የመደገፍ ምቾት እያጣነው እንሄዳለን፡፡

ነገሩ’ኮ ቀላል ነው ምድርን ከፈጠረና ከፍጡሩ ማን የበለጠ ድጋፍ የበለጠ ክንድ ይሰጠናል? ለምድርና ሌሎች ድጋፎቻችን ያለን እምነት ጽኑዕና የበረታ ሲሆን ፈጣሪ ላይ ያለን እምነት ግን የላላ ነው፡፡ ባይላላማ ምድርን የምንረገጣት ስላመናት ሳይሆን ፈጣሪ እንደማይጥለን ስላመንን በሆነ ነበር፡፡ ምድርን አምነዋት የከዳቻቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ለብዙዎች የረገጧት ምድር ከድታቸው ከሆዷ ገብተዋል፡፡ ማን ያኔ አተረፋቸው? ያኔ ማነው ከነዚያ መዓት የሰወራቸው? የተረፉትም የሄዱትም በፈጣሪ ላይ ባላቸው እምነት ልክ ተመዝነዋል፡፡

እግዚአብሔርን እንዲህ ብለን ከእገሌ ጋር ልናወዳድረው የማይቻለን ጌታ ነው፡፡ ሸክላ ከሰሪው ጋር አይነጻጸርም፡፡ ለእርሱ ያለን እምነት እጅግ በበረታ መጠን የመደገፋችን ምቾት ይሰማናል፡፡ በእርሱ ላይ ያለን እምነት ይበልጡን በጸና ጊዜ ሁሉን ማድረግ እንዲቻለን እናውቃለን፡፡ የምናምናትን ምድር አንስተን እስከማሸሽም ቢሆን፡፡ በማናምነው ውቂያኖስ ላይ እስከመራመድም ቢሆን፡፡ ማለፊያ በተዘጋብን ወቅት ባህሩን እንደ ግድጊዳ አቁመን እስከመውጣትም ቢሆን፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት የመኖራችን ጣዕም የሕይወታችን መዓዛ ነው፡፡ እምነቱ (እሱን ማመን) በፍቅሩ ውስጥ የምንዋኝበት እስትንፋሳችን ነውና፡፡ ይቆየን

 

ኅዳር ፳፻፭ ዓ.ም

አዲስ አበባ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑