የሰልፍ ሃገሯ ወዴት ነው?

የሰልፍ ሃገሯ ወዴት ነው?

  • ቢፒአር ሆይ ወዴት አለህ?
  • ዘመናዊ ‘ሬሽን’ /ክፍፍል ተጀመረ እንዴ?

(click to read in pdf )

ከሥራ ወጥቼ በሃይገር ባስ ወደቤት እየተመለስኩ ነው፡፡ ከጎኔ የተቀመጠው ወጣትና ሹፌሩ ወሬ አሙቀዋል፡፡ እኔ የጆሮዬን ቀልብ ወደነሱ ጣል እያደረኩ በዓይኔ ቀልብ ከባቢዬን እየዳሰስኩ እጓዛለሁ፡፡

“ወይ ጉድ ደ’ሞ ምን ተፈጠረ?” ወጣቱ ይጠይቃል

“ጋዝ ሊገዙ ነዋ!” ሹፌሩ ይመልሳል፡፡

አይናቸውን ተከትዬ አማተርሁ፡፡ የነዳጅ ማደያው በሰዎች ሰልፍ ተሞልቷል፡፡

“በቃ ያለሰልፍ የሚሆን የለም?”

“ምን ታደርገዋለህ!”

ግን ቆይ ምንም ማድረግ አንችልም እንዴ? በቃ ለሁሉ ነገር ካልተሰለፍን የንግድም ሆነ የኑሮ ሕይወት አይተነፍስም ማለት ነው?

ትዝ ይለኛል የሞባይል ሲም ለማውጣት የተሰለፍኩት ሰልፍ ርዝመትና የወሰደብኝ ጊዜ-ሊያውም በመከራ የተገኘ ሰልፍ ነበር፡፡ ተሰልፎ ውሎ ነገ ኑ ወይም የለም አልቋል ከመባል የተሻለ ነበር ምክንያቱም የሰልፍ ተራ ደርሶኝ ገዥቼ ነበርና፡፡ ሲም ያወጣሁበት ያ የዑራኤል ቴሌ መንደር በቅርብ ጊዜ ሌላ ረዥም ሰልፍ አይቼበት ተገርሜ ነበር፡፡ ለካ ሰልፉ ወደ ውጭ ሃገር ለመሄድ የሚሰናዱ ሰዎች ሰልፍ ነበር፡፡ ከኃይሌ ዓለም ህንጻ በላይ የጀመረ ርዝመቱ ተጠማዞ ፍትህ ሚኒስቴር ደርሶ ነበር፡፡ ያው አካባቢ ዛሬ ሃይገሩ በካሳንቺስ አዙሮ/አቋርጦ አመጣን እንጂ ከመኪና ሰልፍ የማይጸዳ መንገድ ነው፡፡ የዑራኤል ትራፊክ ፖሊስ (መቼም መብራቱ ለመውለቅ የተተከለ ነው) ያቆመው መኪና ሰልፍ ባምቢስን ያልፋል፡፡ የባንቢሱ በተራው እስጢፋኖስ ላለመድረስ ይንፏቀቃል፡፡

“ምን ሰዉ’ኮ ጠፋ የተባለ ጊዜ ነው ሊገዛ የሚሻማው”

“ምን በሄድክበት ሁሉ ሰልፍ ነው፡፡ አንዲት ወረቀት ለማግኘት ስንት ባዝነህ ነው የምታገኘው”

“እሱስ ልክ ነህ” ሹፌሩ የገጠመው ነገር ያለ ይመስል ፈጥኖ ተስማማ፡፡ እውነትም ያጋጠመው ነገር ነበር፡፡ የአንድ ትራፊክ ክስ/ቅጣት/ና ለመክፈል የደረሰበትን እንግልት እያወጋው ነበር፡፡

በእርግጥ በሰልፍ የተወለደ (የመውለጃ ተራ በመጠበቅ ቦታ አጥቶም ሊሆን ይችላል)፣ በሰልፍ ያደገ፣ በሰልፍ የተማረና በሰልፍ ያወቀ ህዝብ ‘ሰልፍ’ ለሁሉ ነገሩ መገለጫ ባይሆን ነው የሚገርመው፡፡

ባ’ንድ ወቅት ጨው ተወደደ ተብሎ በየሱቁ የነበረ ሩጫና ትግያ ሳስታውስ ብዙ ሕይወታችን ስክነትና እርጋታ ያልተሞላ ነገን በመጠራጠርና ተስፋን በመታረዝ የተሞላ ይመስለኛል፡፡ እስኪ ይለፍ እስኪ ይቆይ ወይም እስኪ ይረጋጋ የሚል ጠባይ አልሰራብንም፡፡  ሩጫችን ‘ነገ ሁሉ ይዘጋል፡ ነገ ሁሉ ያልቃል፡ ነገ ሁሉ ይራቆታል..’ ወዘተ የተባለ ዓይነት ነው የሚመስለው፡፡ እርግጥ የምንሰማቸውን ሁሉ በጥርጣሬና በዚህ መንፈስ ለውጠን የምንሰማቸው ይመስለኛል፡፡ ልክ ነገ ነዳጅ ይጨምራል ከተባለ የመጓጓዣ አገልግሎቱ ይዛነፋል፡፡ ዛሬ በሞላት ነዳጅ ነገ ታሪፍ/ተመን/ ጨምሮ ለመጫን ሌላው ደግሞ ከዋጋ ጭማሪ ቀድሞ ለመሙላት በየማደያው ይሰለፋል፡፡ ነዳጅ ማደያዎች ደግሞ ነገ አትርፎ ለመሸጥ ይቆጥባሉ ወይም ያሳልቃሉ፡፡

በዚህ ሁሉ ውስጥ የሚታየኝ ነገር ቢኖር ኑሮአችን በሰከነና በተረጋጋ ሃገር ምጣኔ ሃብት/ኢኮኖሚ/ ውስጥ አለመሆኑን ነው፡፡ በተገኘው ጭላንጭል ማትረፍና መዝረፍ ወይም ማጋበስና መሰብሰብ፡፡ ቅንጣት የምጣኔ ሀብት ልውጥ ኑሮአችንን ያናጋል፡፡ ስለዚህም እንሰጋለን፡፡ ነገ የባሰ እንዲመጣ እንጅ የተሻለ እንዲኖር አይታየንም፡፡ እድሜና ልምድ ያስተማረንም ይሄንኑ ነውና፡፡

ስንዴ ጠፋ፣ ስኳር ጠፋ፣ ዘይት ጠፋ… ስንሰማቸው የሚያሸብሩ ዜናዎች ናቸው ለነጋዴውም ሆነ ለሸማቹ፡፡ ሸማቹም እንዲህ ያስባል “ይህ የምጥ ጣር ምልክት ነው፡፡ በጊዜ አልሞላ ያለ ጎተራዬን ሳይራቆት ላከማችበት” ይላል፡፡ ስለዚህ ፍጆታዎቹ አሉ የተባሉበት ቦታዎች ሁሉ አሳዶ በመሄድ ይሸምታል፡፡ ሁሉም ወዳለበት ስለሚጓዝ ከአንድ ይሰባሰቡና ረድፍ ይሰራሉ-ተርታ ሊይዙ፡፡ ነጋዴውም እንዲህ ይላል “ይቺ የትርፍ ማዋቀሪያ ምልክት ናት፡፡ በጊዜ ሌሎች ሳይቀድሙኝ ሰብስቤ ላከማች…ነገ መጨመሩ አይቀርምና አትረፌ እሸጠዋለሁ” ይላል፡፡ ስለዚህ እርሱም ሊገዛ ይሰማራል፡፡ የሚገርመው ሸማች መሳይ ነጋዴ እንደመኖሩ ነጋዴ የመሰለ ሸማች መኖሩ ነው፡፡ ሸማች መሽሎ ነጋዴ ይሸምታል-ሊሸጥ፡፡ ሸማች የነበረውም ሰብስቦ ከቤቱ ጎተራ ይልቅ ለነጋዴ ይሸጣል-ይነግዳል፡፡

እነዚህ የንግድ ሥርዓት ክፍለ አካላት ቢሆኑም’ኳ እንደ አንድ ጤነኛ የንግድ ሥርዓት የሚታይ አይደለም፡፡ የንግድ ሥርዓቱ ጤነኛ አለመሆን በንግድ ሥርዓቱ ተሳተፊ የሆኑት ህዝቦች ጤንነት አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡ የህዝቦቹን ጤንነት ከተጠራጠርን በእርግጥም ሃገሪቷ ታማለች፡፡ ስለዚህ ህመምተኛ ሃገር ውስጥ ስላለን መድኃኒታችንን በሰልፍ ውስጥ እንፈልጋለን፡፡ ቀድመን ለማግኘትና ቀድመን ለመግዛት፡፡ ከዚህ በላይ መግዛት አልችልም ጭማሬው በዛ ብሎ ከመጮኽ ይልቅ አብዝቶ መግዛት የህመማችን ምልክት ይመስለኛል፡፡ በየቤት ቁጥሩ በተከፈቱ ካፌዎች ውስጥ ማነው ተጠቃሚው? በውድ እቃዎችን የሚሸምተው ማነው ያጠራቀመው ወይስ የተጠራቀመበት (ማጣቱ)?

ሌላው ሃገር የዳቦ ዋጋ ጨመረ ሲባል  …..ኡኡኡ…..

የነዳጅ ድጎማ ቀረ  …..ኡኡኡ…..

የምግብ ዋጋ ናረ  …..ኡኡኡ…..  ይላሉ ኡኡታቸውን በቁጣ እንደኛው በሰልፍ ይገልጻሉ፡፡ ያድማሉ፡፡ ይታደማሉ፡፡ ታዲያ ካልጮኸ ማን ይሰማዋል፡፡ ጮኾም’ኳ እንደሱ ካልቀመሱት በቀር የጩኸቱን ዋጋ አይረዱለትም፡፡ የመሪዎችና የሰሚዎች ጩኸት ሌላ ጆሮአቸው የደለበው በሌላ ነውና..

እውነት ነው ኑሮ በጣሙን ተወዶብናል በኪነጥበቡ እንጂ መኖር ካ’ቆምን ቆይተናል፡፡ ግን ደፍረን በቃን ካላንነው በቀር ይባሱን በቁማችን እንቀበራለን፡፡ የሚመሩን መፍትሄ ካላበጁልንና ረፍት ካልሰጡን ኑሮና ሕይወታችንን በስጋትና በጥርጣሬ ከሞሉት መመራታችን ጥቅሙ ዜጋ መሆናችን ፋይዳው ምንድነው? መጮኽ በቃኝ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የተወደደውን ዳቦ ገዝቶ ከመብላት ይልቅ በቃን መብላት አልቻልኩም ብሎ መጮኽ ያስፈልጋል፡፡ እነሱ አይሰሙም የዳቦ ዋጋ ምን ማለት እንደሆነ አያውቁትምና፡፡ ምግብ ለመኖር መሠረታዊ ፍላጎት መሆኑን ለመረዳት አይሹም፡፡ የሥልጣናቸውን እድሜ ለማራዘሚያ መድኃኒትነት ይጠቀሙበታል እንጂ፡፡

መሰለፍን ለባለሥልጣኖቻችን የኃያልነታቸውና የኃይላቸው መገለጫ አድርገው ይገልጹታል፡፡ ተራ በመጠበቅ ተሰልፈን ሁኑ የተባልነውን ሁነን የእነርሱን ድራጎት እንድናገኝ ይፈልጋሉ፡፡ ቢፒአር በየመስሪያቤቱ ከሰለጠነ ከብዙ ዓመታት በኃላም አሁንም አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ሰልፍና መንከራተቱ አይቀንስም፡፡ ታች ያለው ባለሥልጣን መሐል ካለው ጋር አይግባባም፤ የመሐሉ ከላዩ ጋር አይቀናጅም ለምን ቢባል አገልግሎቱን ስለመስጠቱ ሳይሆን አለቃውን ስለማስደሰቱና የ’ሱን ትዕዛዝ ስለመፈጸሙ ይጨነቃል፡፡ ትዕዛዝና አሰራር ቀጥና ከላይ ትወርዳለች ለሌሎቹም ዶግማና ጸሎታቸው ትሆናቸዋለች፡፡ ተገልጋዩም እንግልትና ሰልፍ መፍትሄ ከሰጠኝ ብሎ ይቀላቀላል፡፡ ይህን የተለመደ ተግባር ትተን በቅርቡ የመጣው 40/60 የቤት እቅድ ጥሩ ማሳያችን ነው፡፡ የበላይ ባለሥልጣናት በዚህ ቀን ይጀመራል ይሄና ይሄ ያስፈልገዋል አሉ፡፡ ተጻፈም (ምሳሌ፡ ከቀበሌ ቤት አለመኖሩን ማስረጃ..) ነዋሪውም በየቀበሌው ሥራውን አሳታጉሎ ተሰለፈ፡፡ ቀበሌዎች ግን ስለጉዳዩ አያውቁም፡፡ ለተሰለፈው ህዝብ የሰልፍ ቦኖ (ኒብራ) እየሰጡ ሲበትኑና ሲያሰልፉ ዋሉ፡፡ ላልተወሰነ ጊዜ ተሸጋገረ እስኪባል ድረስ፡፡

መጀመሪያ ላይ ያነሳሁላችሁ የሞባይል ሲም ሰልፍ የሚያሳየው የአገልግሎት አቅራቢው ለነዋሪው የነበረው ዝቅተኛ ግምትና አገልግሎቱን ያለሰልፍና ያለ እንግልት እንዳይሰጡ የዳረጋቸው መሆኑን ነው፡፡ ሌሎቹም አገልግሎቶች ግልጽነትና የአንድ ፈጻሚ አካል እጥረት ለሰልፍና ለእንግልት ይዳርጋሉ፡፡ አሁን አሁን ሳስበው የሚያስፈልጉንን የዜግነት አገልግሎቶች በሙሉ እንደ ሬሽን በእደላ ተሰልፈን ካልሰጡን በቀር ያገለገሉ አይመስላቸውም መሰል፡፡

እንደ ጉምሩክ የመሰሉ መስሪያ ቤቶችን ያየ ደግሞ የነዋሪውን ችግር መረዳት ይቻለዋል፡፡ ነጋዴው ሂሳቡንም ሆነ ቫት ለማሳወቅ የወሩ መጨረሻ ትዝ የሚለው ይመስለኛል (ሆነ ብሎ ቸል/ይደርሳል በማለት ሳይሆን አይቀርም) የጉምሩክን ግቢ በሰልፍ ይወሩታል፡፡ መስሪያ ቤቱም አገልግሎት ለመስጠት ትንፋሹ እስኪሰልል ይታትራል፡፡ ሲያሰልፉ ሲበትኑ ቁጥር  ሲያድሉ ሲቀይሩ፡፡

የሰልፍ ሃገር ሰልፈኞች መሆናችን እርግጥ ነው፡፡ ከሰልፍ ለመገላገል የቀረበ እድል ያለን አይመስለኝምና ሰልፋችንን ሰልፍን ለማስቀረት’ኳ ብንምጠቀምበት አይሻልም ትላላችሁ?! “አንሰለፍም!” ብለን ብንሰለፍ! ወይም ከማጉረምረም ለመጮኽ ብንሰለፍ!! ቸር ይግጠመን

ጥቅምት ፳፻፭ ዓ.ም

አዲስ አበባ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑