ለራስ ብቻ
የቀደሙ መሪዎቻቸውን ጥላና ዳና ተከትለው ይነጉዳሉ፡፡ በዚህ ወደ ተስፋ ቀዬ ለሚደረግ ጉዞ የሁል ጊዜ ትጋታቸው አብሮ ነው፡፡ ጉምም፤ ጉትልትል ማለት ነው ገብረ ጕንዳን፡፡ በረዥሙ የተስፋና የተሻለ ፍለጋ ጉዞ ብዙ ጕንዳናውያን አልቀዋል፡፡ አለቃና አዛዥ በሌለበት በዚህ ጉዞ ሁሉም ራሱን ሰጥቶ ይጓዛል፡፡ ገዢ በሌለው አነዋወራቸው ክረምቱ የችግር ዘመን ሳይመጣ በበጋ መብላቸውን ሲያዘጋጁ ይሰነብታሉ፡፡ መከር በባተ ወቅት መኖዋቸውን ይሰበስባሉ፡፡ መንገዳቸው ሁሉ ጥበብን የተሞላ ነውና በደኅንነት ይኖራሉ፡፡ ሊያከማቹ ወጥተው በዛው የቀሩትን በየመንገዳቸው ሲያገኙ ተስፋ መቁረጥ ልባቸውን አይሞላም፡፡ ድካም መንፈሳቸውን አይወርሰውም፡፡ ይጓዛሉ፡ ይተጋሉ፡ ይሰራሉ ሳይደክሙ ሳይሰለቹ፡፡ ያለ መሪ፣ ያለ አለቃና ናዛዥ በአንድነት ለአንድነት፤ በራስ ለራስ፡፡
ከፊት ያለው ተጓዥ የደሴቱን ጉዞ አልፎ ወንዙን መሻገር ጀምሯል፡፡ ወንዝ የማይገታው ጕንዳን፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘውና እግር ለእግር ተቆላልፈው አንዱ በሌላው ላይ ተደርቦ በጕንዳን መረብ (ድልድይ) ሌላው ጕንዳን ወንዙን ይሻገራል፡፡ የገጠሩ በደቦ እህል የመሰብሰብና የመውቃቱ አንድነት አይገልጸውም፡፡ አንድነትና ኅብረታቸው ነፍሳቸውን ለአደጋ እስከማጋለጥና እስከ መረሳት የሚደርስ ነው፡፡ በዚህ በድልድይ ጉዞ ብዙዎች ተንጠባጥበው ከስር ከሚጮኸው ወራጅ ወንዝ ይጠልቃሉ፡፡ ይሄ ግን ማንንም አያስቀርም፡፡ ወደ ኋላ የሚያደርግ ምንም ምክንያት አይሆናቸውም፡፡ ይቀጥላሉ ይሻገራሉ- በኅብረት ዜማቸው ታጅበው፡፡
አንድ ጕንዳን ከወንዙ ደርዝ ሲደርስ ከተቆላላፊዎቹ ድልድዮች ተርታ ነበር የደረሰው ግና ለመግባት አመነታ፡፡ ከዚህ በፊት ከማኅበረ ጕንዳን ባህል የተለዩ የደረሰባቸውን ያስታውሳል፡፡ ማኅበሩ ህይወቱን ቀጥሏል፡፡ መሐል በሚፈጠሩ ታካቾች የማይሰናከል ጽኑ አንድነትና ባህል ተፈጥሯልና፡፡ ግን ሲያስበው እርሱ እጁ እስኪገነጠል ከሌላው ጋር ተጣብቆ እየተሳበ ሲጓዝ ሌላው በእርሱ ላይ እየፈነጠዘ ሲንገዋለል ታሰበውና ልቦናው በቅናት ታወረ፡፡ ማንም መሪ ከታች እንዲሆን አላዘዘውም፡ ማኅበራዊ ህጉ መራው እንጂ፤ በደመነፍሳዊ ጉዞው፡፡
“ቀጥል እንጂ ጌታው!” አለ ከኋላው ተራውን በጉጉት የሚጠብቅ ጉንድ፡፡
የሚሻገሯት ደሴት በጸጥታና አርምሞ ተውጣ ህይወቷን ቀጥላለች፡፡ በሌላው ዓለም የሚነፍሰው የለውጥ እስትንፋስ የኑሮ ትርምስና ሁካታ በእርሷ የተፈጠሩ አይመስሉም ዝም ብላ ታዘግማለች፡፡ ነዋሪዎቿ ከአንድነትና ኅብረት ይልቅ የግል ሩጫ በልጦባቸዋል፡፡ የግል ሯጮቹ ሲመዘብሯትና ሲበዘብዟት እንጂ ሲያስጌጣትና ሲሸልሟት አይታይም፡፡ ሌሎቹም የተደፈረ ገላና የተመዘበረ ጎተራ ታቅፈው በዝምታቸው ያለቅሳሉ፡፡ ሌላው ሃገር የወጣች ፀሐይ እዚህ 13 ወራት ብትሞቅም አልባሳት የተራቆተ ገላቸው ይበርደዋል፡፡ በፀሃይዋ ምግባቸውን የሚያበስሉት ጥቂቶችና አድርባዮች ሁነው ለሌላው አልተረፈውም፡፡ ስለዚህም በርሃብ ይሰቃያሉ፡፡ ግን አሁንም ደሴቷ በጸጥታና በእርምሞ ተውጣ ህይወቷ ቀጥሏል፡፡
“ምንነካህ? ወዳጄ ፈጥነህ ግባና ጉዞአችንን እናፍጥነው እንጂ” ሌላኛው ከተሻጋሪዎቹ ተራ የደረሰው በስሱ አንባረቀበት፡፡ የተገተረው ጕንዳን ያሰላስላል፡፡ ‘ለምንድነው ግማሹ ተቆላልፎ ድልድል ሰርቶ ሲንፏቀቅ ሌሎቹ በላዩ እየዘለሉ የሚቦርቁት?’
“አንተ ጕንድ! ወይ እኔን አስቀድመኝና ላሻግራቸው ምንድነው መፍዘዝ?” ከእርሱ መስመር አራተኛ ላይ የተሰለፈችው ጮኻ ጠየቀችው፡፡ የተቆላለፉት ድልድይ ሰሪ ጕንዳኖች እየተንፏቀቁ ከወንዙ ጠርዝ እየሸሹ ነው፡፡ ሌላው ተከትሎ መጥቶ ድልድዩ ካልቀጠለ ሌሎች መሻገርም አይችሉም እነርሱም ተንጠባጥበው ማለቃቸው ነው፡፡
የደሴቲቷ ባህል እየተጋባባቸው ይመስላል፡፡ በደሴቲቱ ነዋሪዎች ዘንድ አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መስራት ነውር እየሆነ መጥቷል፡፡ በጋራ የሠሩት የሚኮሩበት ሥራ ለማሳየት በመቸገራቸው የእገሌ ሀውልት የእገሌ ህንጻ የእገሌ መኪና እያሉ መመጻደቅ ጀምረዋል፡፡ የቀደሙት የሥልጣኔ አሻራዎችም በጣም ከመራቃቸው የተነሣ እየተረሱ ይገኛሉ፡፡ አዲሱ ትውልድ ስለነዚያ ታሪኮች ምንም አያውቅም፡፡ ስለ እርስ በእርስ ደም መፋሰስ ታሪክ እንጂ ስለ ደሴቲቷ ታሪካዊ ጀግንነት ማንም አያውቅም፡፡ ትንሣኤዋ የምድርን ማለፍ የሚጠብቅ ይመስላል፡፡ ድህነቷና ኋላ ቀርነቷ ከመብዛቱና ከመርዘሙ የተነሣ ለድሮ ታሪኳ ሌላ አዲስ ታሪክ እያበጁላት ይገኛሉ፡፡ ደሴቷን እየተሻገሩ የሚገኙት ጕንዳኖች ያለመሪ ሲጓዙ ደሴቲቷ በመሪ መጓዝ አቅቷት ታዘግማለች- በጸጥታና በአርምሞ፡፡
“ለምንድነው ሁሌ እኛ ተጨቁነን የምንኖረው? እኛ እየተሸከምናቸው ሌሎች ይሻራሉ፡፡” እንቢተኛው ጕንዳን ዞሮ ጠየቃቸው፡፡ በብዙ መደነቅ ተሞልተው
“በአጋጣሚ ይሁን በእድል ተደጋጋሚ ጊዜ ድልድይ ሆነህ ታውቅ ይሆናል፡፡ ግን ሌላው የሚሻገረው’ኮ ያንተ ልጅ ወይም ዘመድ ነው” አዛውንቱ ጕንዳን መለሱለት፡፡
“አንተ ታካች ስማችንን ስለምን ታጠፋለህ?” ሌላው ወጣት ተቆርቋሪ ተንጫረረ
“አሁን ተራው የእኛ ዘር ነው፡፡ ተሻጋሪ ብቻ መሆን ይኖርብናል፡፡ የእናንተ ዘር ለዘመናት ሲሻገርብን ኖረ አይበቃውም?”
“ዘር ሁሉ የተፈጠረ በብሔረ ጕንዳን ነው፡፡ ሃገራችን የምንኖርበት ሁሉ ነው እንጂ የዘራችን ቀዬ ብቻ አይደለም፡፡ አንተም ጕንዳን እኔም ጕንዳን ነን፡፡ በኅብረት መኖሩን አባቶቻችን አስተማሩን በኅብረት ስለኖሩ ጠንካራና የማይገረሰስ ታሪክ ሰሩልን፡፡ እስቲ ወጣ ብለህ ከብሔረ እንስሳት ጠይቅ ጕንዳኖች እንዴት የሚያስቀና ታሪክ እንዳላቸው ይነግሩሃል፡፡ እጃቸውን ለድካም ሰጥተው አያውቁም፡፡ እንቅልፍ ባይናችን ዞሮ አያውቅም፤ ለሽፋሽፍቶቻችን እንጕልቻን ሰጥተን አናውቅም፡፡ እንደ ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ እንደ ወፍ ከአጥማጅ እጅ እንደሚድኑት እኛም ከድኅነት ለመላቀቅ የተሻለ ደሴት የተሻለ መሬት ፍለጋ ስንባዝን አንደክምም”
“ግን አሁንም ተጓዦች ነን፡፡ መቼ ነው የምናርፈው? አሁንም ታሪክ እናወራለን መቼ ነው ታሪክ የምንሰራው? አሁንም ተቅበዝባዥና ተንከራታቾች ነን” እንቢ ባዩ ጕንዳን መለሰለት
“ ይኸው ታሪክ ለመፍጠር በምናደርገው ጉዞ እንዳንተ አይነት እንቅፋት አናጣም፡፡ የዘር የጎሳ የብሔር ጠባብ አዕምሮ የጸነሰው፡፡ ስለ ብሔረ ጕንዳን ህልም ሳይሆን ስለ ዘርህ ድካም ታወራለህ፡፡ ከእኛስ ዘር ድልድዮች አልነበሩም? ከእነገሌ ዘርስ ተሻጋሪ አልነበሩምን? ገና ሰርተን ሳንጨርስ ስለ እረፍት ታወራልህ፡፡ በየቤቱ ግድግዳ ባለ ካፌ ውስጥ በወንዝ ዳር መጠጥ ቤታችንም ሆነ በየዛፉ ላይ ባለ መቃረሚያ ቤቶች የሞላው ስንት ሰነፍ ህዝብ አለን አይደለም እንዴ! መቼ ሰርቶ ነው የሚያርፈው? መቼ አከማችቶ ነው የሚበላው? ክረምት በመጣ ቁጥር የሚያልቀው ህዝብስ የእኛ አይደለም? ያኔ ታታሪ አባቶቻችን በገነቡት ስም አይደለም ተገንብተን ያለነው? ለሌሎችስ ምሳሌ የሆነው በእነርሱና ተከታዮቻቸው ጥረት አይደለምን! ታዲያ አንተ በኅብረት መስራትን ምነው ጠላህ? ብቻ መሮጥ ምነው አማረህ? ያ ከወንዙ ሊንጠባጠብ የደረሰው ድልድይ ያንተ ወገን አይደለም ሮጠህ ለመደገፍ ለምን አትደርስለትም?”
ከኋላ የነበረ ጕንዳን ተሽቀዳድሞ ሮጦ ወደ ወንዙ ሊገባ የነበረውን ድልድይ ጕንዳን ደረሰለት፡፡ ሌሎቹም ተከተሉት፡፡ የጕንዳናውያን ጉዞ ሲቀጥል እንቢ ባዩ ጕንዳንና ተከታዮቹ ወደኋላ ተመለሱ፡፡ በደሴቲቷም ላይ ኑሮአቸውን ቀጠሉ፡፡በየኑሮአቸውም መሐል አንዱ እየተነሣ በሆነ ባልሆነ የራሱን ቡድን ይዞ መገንጠል ወይም የኔን ሃሳብ ብቻ ስሙ በሚል አምባገነንነትን አቀነቀነ፡፡ የቀደመው ጕንዳን ወንዙን ተሻግሮ ሌላ የሥልጣኔ ህይወት ሲቀጥል የቀሩት የደሴቲቷ ጕንዳኖች በየፊናቸው ቀድሞ የተከማቸውን እየበሉና ጥቂት እየሰሩ ስለኖሩ በድህነት ተሰቃዩ፡፡
የሚኖሩባትም ደሴት ነዋሪዎቿ ገና ከእንቅልፋቸው ስላልነቁ ለጕንዳኖቹ የሚተርፍ ሊሰሩላቸው አልቻሉም፡፡ እስከመቼ እንደሚተኙና መቼስ እንደሚነሱ ከመጠየቅ በቀር አላወቁም፡፡ የዘመናት ልምላሜ ረገፈ፤ ድህነት እንደ ወንበዴ እየመዘበረ አሰቃያቸው ችጋርም እንደታጠቀ ሰው በሰይፍ ብዙውን ጨረሰ፡፡ ሌላ ዓለም የወጣው የሥልጣኔ ፀሐይ በዚች ደሴት እንደጠለቀ ቀረ፡፡ የደሴቷም ህይወት በጸጥታና በአርምሞ በዝግታ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡
ኅዳር /፳፻፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ
Leave a comment