ትላንት….
ነብያት ተመኙ ከምላሳቸው ቃል ምድር ላይ ‘ዲያዩ
መባዘኑ ቀርቶ ባርነት አብቅቶ ተስፋ ‘ዲገበዩ
ግና.. ስቃያቸው በዝቶ ጽድቃቸው ዋጋ’ቶ የመርገም ጨርቅ ሆነ
ኃጢአትን ተዋልደው በውርስ ተቀባብለው ነፍሳቸው ጣመነ፡፡
ያኔ.. እንባን ማበሻ የተስፋ ቀን ሲደርስ አርያም ተከፈተ
በበረትም ሲገኝ ነጻነት አውጆ ሰላምን አተተ
ምድር በይቅርታ በም’ረት ተከድና ፍቅር በረከተ
ዛሬ….
እኒያ ደስታዎች ለታሪክ ተትተው ዘመናት አለፉ
እኚህኛው ትውልድ አሮጌውን ጥለው አዲስ ውርስ ታቀፉ፤
በጉያቸው መሃል ክፋት ተወሽቆ ከበጎነት ወጡ
ሃሳባቸው ነጥፎ ግብራቸው ተራቁቶ በክፋት ተዋጡ፡፡
ነፍስና ሥጋን ማስታረቅ ከብዷቸው እመሃል ቤት ዋሉ
ምድርን አጸይፈው መልካም ፊቷ ዞረ ዓለምን በከሉ፡፡
ግና.. ነብያቶቻቸው ከትንቢት ቢጣሉ
ይህን እየጠየቁ ይ’ን ይሞግታሉ
ግን ጽድቅ ምንድር ነው በምድር ላይ ላሉ?
ጽድቅማ-በጎነት!!
መልካምን ወዶ መልካሙን መናፈቅ ለበጎ መሰዋት
በመልካምም ሥራ ነፍስና ሥጋን ማዋደድ ማስታረቅ
ያኔ.. ላ’ርያም ክንድ ማደሪያ ልብ በረት ይሆናል
ዳግም ልደት የለም በትውልድ ትንሣኤ ተስፋ ይፈጸማል
ምድርም.. በይቅርታ አጊጣ ሰላም ይሰበካል ፍቅርም ይዘራል!!

ጽድቅማ-በጎነት!!
መልካምን ወዶ መልካሙን መናፈቅ ለበጎ መሰዋት
በመልካምም ሥራ ነፍስና ሥጋን ማዋደድ ማስታረቅ