‘የጥራት አምባሳደሮች’ ዩኒቨርስቲ ኮሌጆቻችን

‘የጥራት አምባሳደሮች’  ዩኒቨርስቲ ኮሌጆቻችን

click to Read in pdf

‘የጥራት አምባሳደር’ የሚለው ሐረግ ምናልባት የቅ/ጊዮርጊስ ቢራ ማስታወቂያን ያስታውሰን ይሆናል። ጥራት የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ሁሌም አሻሚና አነጋጋሪ ቢሆንም እንደየሙያው አግባብ ትርጓሜ ተሰጥቶት ፤ቢተገበርም ባይተገበርም ጥቅም ላይ ውሎ ይገኛል። አልኮልና ለስላሳ ድብልቅ ምሩቃን እያመረቱ የሚገኙት የትምህርት ፋብሪካዎቻችንም መፈክራቸው ይሔው ሀረግ ነው።

‘የልቀት ት/ት ቤት’

‘ጥራት ላለው ት/ት ….’

‘ዓላማችን በዝቅተኛ ክፍያ ጥራት ያለው ት/ት….’

‘ጥራት ላለው ት/ት የተሠጠን ነን’

‘ጥራት…ጥራት..

ሌላም ሌላም እነሱን የሚገልጽ መጠሪያ ወይም ደንበኛ መሳቢያን የማስታወቂያ ቃል የዓላማቸው ክበብ አድርገውት ይገኛሉ። የግልና የመንግስት ተቋማት በየወቅቱ ለሚፈበርኳቸው ወጣቶች የነገ ጥቅምና ጉዳት ተጠያቂዎች ናቸውና ‘ጥራትን’ ባያነግቡ ነበር የሚደንቅ። በተለይ በዚህ ወቅት ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ የዚህን ትውልድ ተመራቂዎች በሚነቅፉበትና አሣንሰው በሚያዩበት ወቅት ምጣድ ሆነው ለሚጋግሯቸው ወጣቶች ተቋማቱ የሰፋና የበዛ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል።

መንግስት ለቴክ/ሙያ ተቋማት የእውቅና ማግኛ ተመራቂዎቻቸው በሙያ ብቃት ምዘና (COC) ባለፉት መጠን ላይ ማንጠልጠሉ ተገቢና ሲያንስባቸው ነው ያስብላል-ምንም’ኳ በሙያ ምዘናው ላይ ጥያቄ ቢኖረኝም። ለከፍተኛ ት/ት ኮሌጆነት፣ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅነትና (ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ መባሉ አሁን ባለው አግባብ /context/ሊገባኝ የማይችል ስያሜ ነው) ዩኒቨርስቲነት እውቅና የሚያያቸው ብዙ መስፈርቶቹ ጋር ተቋማቱ የራሳቸውን የውስጥ ጥራት ኦዲት (Internal audit and quality assurance) እንዲያቋቁሙ እያበረታታና እያስገደደ ይገኛል። ጥቂቶቹ በመምሪያ (department) ደረጃ የጥራት ማረጋገጫ ክፍል አቋቁመዋል፡፡ ብዙዎቹ በሰዎች በጎ ፈቃድ ላይ ተንጠልጥለዋል።

የተማሪ ትምህርት የመቀበል አቅምና ፍላጎት፣ የተቀበለውን የመተግበር ችሎታ ሲመዘንና ሲወረፍ ያስተማረው አስተማሪ፣ የተማረበት ተቋምና የእርሱ ጥረት ዋነኛ ተጽዕኖ አድራጊ ተደርገው ሊነሱ ይገባል-እውቅና ሰጪው ተቋምም ሳይዘነጋ። የሚገርመው ግን የዘንድሮ ተማሪዎች ሲወቀሱ አጨብጫቢና አባሪዎቹ እኚሁ አካላት መሆናቸው ነው። በተለይ መምህራን የሚቀድማቸው አልተገኘም። እንደ እኔ የተማሪውን ሸክም ሊሸከሙለትና እንደ የኃላፊነታቸው ተጠያቂ ቢሆኑ የመጀመሪያ ተጠያቂ ተቋማቱ ሊሆኑ ይገባል። መምህራኖቹ ሲቀጥሉ ተማሪው የቀረውን ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል። የት/ት ቢሮው በሶስቱም ውስጥ ድርሻ ያለበት አካል ነው።

በዚህ ጽሑፍ ተቋማቱ ውስጥ የሚታዩና ሃይ የሚላቸው የጠፉ ጉዳዮችን ለማንሣት እሞክራለው። ብዙ የሚባልባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም የተወሰኑትን ሁለት ቅርቤ በሆኑ ተቋማት አማካኝነት ለመዳሰስ እሞክራለው። ሁለቱን ተቋማት ማንሣቴ ለመሟገት ሳይሆን በቅርብ ያየኋችው በመሆናቸው ነው። ከተቋማቱ ጋር ወዳጅነትም ሆነ ጠላትነት ስለሌለኝ በንጹህ ልቡናና በቅንነት የምነቅፍባቸው ጉዳይ ነው። ሌሎቻችሁ ደግሞ የሌሎች ተቋማትን ተግዳሮት ታሳዩናላችሁ፣ ጻፉልን።

በአደረጃጀቱ፣ በስፋቱና በሚደርጋቸው ጥረቶቹ ከማደንቃቸው ተቋማት አንዱ ነው አድማስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ። ለሌሎች ሊያካፍላቸው የሚገቡት ብዙ ልምዶችና ተሞክሮዎች ያሉት ትልቅ ተቋም ነው። በብዙ ተማሪዎች ልብ ውስጥ የሚጉላላና መፍትሔ ያጣ ጉዳይ ቢኖረው የሚመድባቸው መምህራን ችግር ነው። እጅግ የሚደነቁ፣ የሚያስተምሩትን የሚያውቁ፣ እውቀትና ክህሎት ብቻ ሳይሆን የአመለካከት ለውጥም ለማምጣት የሚጥሩ የተመሰገኑ መምህራን ቢኖሩትም አብዛኛዎቹ ግን አስተማሪነትን ከገንዘብ ማግኘት በላይ ለማየት ያልታደሉ ይመስለኛል።

መጀመሪያ የሚያስተምሩትን የማያውቁ ብቻ ሳይሆን ያልገባቸውን እንደመሞከሪያና አማራጭ ማጣት ይጠቀምባቸዋል። እነዚህ  ደግሞ የሚያስተምሩት እውቀት ሳይሆን የሚያወጡት ፈተና ይበዛላቸዋል። ሌላው ማስተማር የሰለቻቸው በየተማሪው እጅ የተበተነውን ሃንዳውት ቆሞ በማንበብ (ሊውም ሃንዳውታቸው ከብዙ ዓመታት በፊት ተዘጋጅቶ/ከመጻህፍ ተቀድቶ-copy/ በፎቶ ኮፒ ቤት የተቀመጠ ነው) የተማሪውን ገንዘብና ጊዜ ሲያነክቱ፤ ጥሩ መሆናቸውን ካመነ በሥልጠና ስሜታቸውን ለማሣሣት ወይም የማስተማር ዘዴ በየጊዜው ለመስጠት ሲጥር አይታይም- ቢያንስ ለውጡን መገንዘብ ስለምንችል። የመምህራኑን ፈተናና ሃንዳውት ወይም ሌላ የማስተማሪያ ዘዴ የጥራት ማረጋገጫ መምሪያው በየጊዜው ቢፈትሸውና ማስተካከያ እንዲያደርጉበት አሊያም ሥልጠና እንዲሰጣቸው ቢያደርግ ወቅቱን የዋጀ ት/ት ለመማርና ያወቅነውን ብቻ ለመመዘን በተፈተንን ነበር።

በተለይ መምህራንን መመዘን እንደ ዓለም ዋንጫ በዓመታት አንዴ የሚመጣ ይመስላል። ምንግዜም አስተማሪ ለያስተማረበት ት/ት ሊመዘንና ሊገመገም ይገባዋል፡፡ ሌላው የመምህሩ ክፍል መግባት ተቋሙ ለሚመድባቸው ሰዓት ተቆጣጣሪዎች በቂ ነው። ክፍል ገብቶ የት/ቱን ሽፋን አለማዳረሱን (course coverage) የሚያረጋግጡት ግን ተማሪ አልተማርኩም ብሎ ከመጣ ብቻ ነው። አሊያ ግን በሁለት ምዕራፍ ት/ት የ6-7 ምዕራፍ ት/ት ይፈተናል። እድሜ ለ ኮፒ ሃንዳውት- አንብበህ ግባ ነው። ስለዚህ አስተማሪን የመቆጣጠሪያ ዘዴያቸውን በየጊዜው ሊያስተካክሉትይገባል።

ሌላው የአቤቱታ አቀባበል መንገዱ መፍትሔ የሚሰጥ ሳይሆን ተደርጓል ለማለት ያህል ብቻ ነው። የውጤት አቤቱታ (complain) ይሞላል፣ አስተማሪው አይቶ ተገቢ አቤቱታ አይደለም ብሎ ይጥለዋል። አስተማሪው ተገቢ ነበር ቢልማ በፊቱንም ባስተካከለው ነበር። ስለዚህ ያስተማሪ ስልክ በመውሰድ በግል መፍትሔ ለመፈለግ ይሞክራል። ምንም ያህል አቤቱታ ቢበዛ አቤቱታ ሊከበርና መፍትሔ ሲፈለግ ተማሪው ካስተማሪው ጋር ተገናኝቶ ካልሆነም በሶስተኛ ወገን ሊሆን ይገባዋል።

ሁለተኛው ተቋም ዩኒቨርሳል ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ነው። በአሁን ሰዓት በከተማው ውስጥ አንድ ግቢ (campus) ብቻ ሲኖረው ጥሩ መምህራን በንጽጽር አሉት የሚባልለት ነው። የዚህ ተቋም መሰረታዊ ችግር በእቅድ የመመራት ችግር ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የፈተና መርሀ ግብር ይወጣል። ጠዋት ወጥቶ ከሰዓት፤ ዛሬ ወጥቶ ነገ ሊቀየር ይችላል። በተደጋጋሚ ተማሪዎች ፈተና ሲያመልጣቸው ታይቷል። ፈተናው ሲቀየር ቀኑ፣ ሰዓቱ ወይም ቦታው ሊሆን ይችላል። ማን ከማን ጋር ተነጋገሮ እንደሚቀይረው ግልጽ አይደለም። ለፈተና መዘጋጀት ብቻውን በቂ አይደለም በየጊዜው እየደወሉ መቼቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል- ፈተናን ያህል ነገር እንዳያጡ።

ተማሪዎች የወሰነ ት/ቱን (semester) ውጤት ሳያዩ ሌላውን ይቀጥላሉ። አንዳንዴ ፈተና ሳይጨርሱ የቀጣዩ ወሰን ት/ት ይጀመራል። ውጤት በጊዜ ለምን እንደማይገባ ከገባ የውጤት ዘገባ (grade report) ለምን እንደማይሰጡ እነሱም የሚያውቁት አይመስለኝም። በክፍያ ላይ ግን ድርድር የለም። በምዝገባ ወቅት የተሞላ ት/ት ላይማሩት ይችላሉ ወይም ወሰነ ት/ቱ ሊያልቅ 3 ሳምነት ሲቀረው አዲስ ት/ት ሊጀምሩ ይችላሉ። አስተማሪ በተገኘበት ሰዓት። ለምንድን ነው ተማሪ የምታስተምሩት? ተብለው ሊጠየቁ ይገባል። ባገኘው ወቅት መምህር እያመጣ የሚያስጀምር ከሆነ ስለተማሪዎቹ ሳይሆን እያሰበ ያለው ኮርሱ መሸፈኑንና ገንዘብ መቀበሉን ነው ያስብላል።

በሁለቱም ተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎች የመጨረሻ አማራጫቸው ለት/ቱ ቸልተኛ መሆን ወይም/ እና ለፈተና እየተዘጋጁ መምጣት ብቻ ይሆናል። የሁለተኛው ተቋም የጤና እንደመሆኑ የመተግበሪያ ጊዜ ስለማይኖር የመርፌን ስም እንጂ የመውጋት ዘዴውን ማወቅ መመረቃቸውም አያረጋግጥላቸውም።

አዎን የዚህ ዘመን ተማሪ እውቀት ይዞ ሳይሆን ወረቀት ይዞ ይወጣል። ይሄ እንዲሆን እየፈቀዱ ያሉት ግን ራሳቸው ተቋማቱ ናቸው። በዚህ መልክ በማወቅም ባለማወቅም እንዲቀረጽ አድርገውታል። ስለተማረው ት/ት ሳይሆን ስለአስተማሪው የበለጠ ያውቃል። ስለዚህ እንደሚፈልገው ይሆንለታል። ተቋማቱም መፍትሄ ይኖራቸዋል ብሎ ስለማያስብ ለራሱ መፍትሄ ይፈይዳል። በመፍትሄ እጦት ዊዝድሮ የሞሉ ብዙ ተማሪዎች ይኖራሉ። ጭንቅላቱ ውስጥ ‘A’ ለመሙላት ሳይሆን በወረቀት ‘A’ ለመጻፍ ለሚሸክት ተቋም ተማሪው ጥቅሙ ምኑ ነው? በዝምታ ወረቀቱን ሰብስቦ መውጣት እንጂ። ነገ ቢሰራውም ባይሰራውም’ኳ ይወዳደርበታል።

ተቋማቱ አትራፊ ነጋዴዎች በመሆናቸው ገንዘብን ማሰባቸው ተገቢ ነው። በገንዘባቸው ህንጻ የመገንባትን ያህል ግን ቀላል አይደለም-ሰዎችን መገንባት። ይሄ የዜግነትና ለሐገር የማሰብ ኃላፊነት ተቆንጥሮ የሚሰጥ ሳይሆን ሁሉ ባለበት ኃላፊነት ልክ የተሸከመው የሁልጊዜው እዳው ነው። ተቋማቶቻችን ‘የመከኑ’ ተመራቂዎችን የሚያመርቱ ‘የመከኑ’ ተቋማት እንዳይሆኑ በሃላፊነት ሊያስቡበት ይገባል። ገንዘብን ብቻ ሲያሯሩጡ የሚረሷቸው ህንጻዎች ማርጀታቸው፣ ሲስተሞች መዛጋቸውና ሠራተኞችም መንቀዛቸው አይቀርም። የነቀዘ ተቋም ደግሞ….. የሚያመርተው ያንኑ ነው፡፡ ይሄ የእንቁላሏና ዶሮዋ ጨዋታ አይደለም።

ይቆየን-ጤና ከሰጠን እንመለስበታለን

የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም

አዲስ አበባ

ማስታወሻ: * በከተማችን የሚገኙ የግል ዩኒቨርስቲ ኮሌጆች ብዛት ሁለት ብቻ መሆኑን በቅርብ ከየከፍተኛ ትምህርት ጥራት አግባብነት ኤጀንሲ  የወጣ ድብዳቤ ያመለክታል፡፡ እነሱም አልፋ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅና  አድማስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሲሆኑ ብቸኛው ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ፡፡ (update መጋቢት ፳፻፭)UNIvrs

3 thoughts on “‘የጥራት አምባሳደሮች’ ዩኒቨርስቲ ኮሌጆቻችን

Add yours

  1. ተቋማቱ አትራፊ ነጋዴዎች በመሆናቸው ገንዘብን ማሰባቸው ተገቢ ነው። በገንዘባቸው ህንጻ የመገንባትን ያህል ግን ቀላል አይደለም-ሰዎችን መገንባት። ይሄ የዜግነትና ለሐገር የማሰብ ኃላፊነት ተቆንጥሮ የሚሰጥ ሳይሆን ሁሉ ባለበት ኃላፊነት ልክ የተሸከመው የሁልጊዜው እዳው ነው። ተቋማቶቻችን ‘የመከኑ’ ተመራቂዎችን የሚያመርቱ ‘የመከኑ’ ተቋማት እንዳይሆኑ በሃላፊነት ሊያስቡበት ይገባል። ገንዘብን ብቻ ሲያሯሩጡ የሚረሷቸው ህንጻዎች ማርጀታቸው፣ ሲስተሞች መዛጋቸውና ሠራተኞችም መንቀዛቸው አይቀርም። የነቀዘ ተቋም ደግሞ….. የሚያመርተው ያንኑ ነው፡፡

  2. ተቋማቱ አትራፊ ነጋዴዎች በመሆናቸው ገንዘብን ማሰባቸው ተገቢ ነው። በገንዘባቸው ህንጻ የመገንባትን ያህል ግን ቀላል አይደለም-ሰዎችን መገንባት። ይሄ የዜግነትና ለሐገር የማሰብ ኃላፊነት ተቆንጥሮ የሚሰጥ ሳይሆን ሁሉ ባለበት ኃላፊነት ልክ የተሸከመው የሁልጊዜው እዳው ነው። ተቋማቶቻችን ‘የመከኑ’ ተመራቂዎችን የሚያመርቱ ‘የመከኑ’ ተቋማት እንዳይሆኑ በሃላፊነት ሊያስቡበት ይገባል። ገንዘብን ብቻ ሲያሯሩጡ የሚረሷቸው ህንጻዎች ማርጀታቸው፣ ሲስተሞች መዛጋቸውና ሠራተኞችም መንቀዛቸው አይቀርም። የነቀዘ ተቋም ደግሞ….. የሚያመርተው ያንኑ ነው፡፡

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑