ምንትኑ ጌጋየ ለዝ ብእሲ

To read in pdf click

ምንትኑ ጌጋየ ለዝ ብእሲ

የጲላጦስ ነገር የሚደንቅ ነው! የዘመኑ ድንቅ አሳቢ ነበርና፡፡ ዓለም ሁሉ የሚጠይቀውን እርሱ ደፍሮ ጀምሮት ተመዝግቧል–እውነት ምንድነው? ብሎትም የለ፡፡ የረቀቀና እጅግ ከማሰብ የሚመነጭ ጥያቄ ነው፡፡ ከስሜት ህዋሱ መረዳት በላይ የሆነበት፡፡ ታዲያ ግን ይህን አሳቢ ምንም ሳይቆይ እንዲህ ሲል የሰማነው ለምንድነው? “የዚህ ሰው ስህተቱ ምንድን ነው? ምትኑ ጌጋየ ለዝ ብእሲ” ማቴ ፳፯፥፳፫ ፣ሉቃ ፳፫፥፳፪፣ማር ፲፭፥፲፬፡፡

እውነትን ጠያቂ እንዴት ከእውነት ውስጥ ስህተትን ይፈልጋል? ስህተት ቢያጣስ እንዴት ይደነቃል? እውነትን በምን ዓይነት ሚዛን መዝኖ ነው ጉድለት ያገኝለት ዘንድ የፈለገው? አይ አሳቢ ጲላጦስ ! በጥረቱ ሁሉ እውነትን ስህተት አጣለት…. ዮሐ ፲፰፥፴፱፣፲፱፥፬፣፲፱፥፮ እኔ ግን የዚህን ሰው ስህተት አገኘሁት…… ተረዳሁት፤እነግራችሁማለሁ፡፡

የዚህ ሰው ስህተቱማ ፍቅር! ፍጹም መውደድ ፍጹም ማፍቀር፡፡ ይህ ለፍጥረቱ ያለው ፍቅር ለባህርይው መገለጫ በሆነበት በዛ ቅጽበት እርሱ ከመንበሩ ተዋረደ፤ከዙፋኑ ወረደ፡፡ ነገር ሁሉ በዚህ ፍቅር ተመስርቷልና!

ታዲያ ለሞት ያበቃው ይህ ስህተት፤ይህ ፍቅር ማንን ወደደ? ማንን ገዛ? ማንን ሀብት አደረገ? ጥበብና እውቀት የማይፈተንበት፣ ሀብትና ንብረት የማይከፈልበት፣ ዋጋ የማይጠየቅበት ፍጹምና ነጻ ፍቅር ነውና ያጣሮች፣አመንዝሮች፣ ህመምተኞች፣ሞኞች፣ ኃጢአተኞችና ድውዮች በዓለም ዘንድ ዋጋና ክብር ያጡቱ ሁሉ በዚህ ፍቅር ተገዙ፤ ለዚህ ፍቅር ተንበረከኩ፡፡ ተወደደዱ፤ በክብር ላይ ክብር በዛላቸው፡፡ ፩ቆሮ ፩፥፳፮-፳፰፣ዮሐ ፯፥፵፰፣ያዕ ፪፥፭፣ሮሜ ፬፥፲፯

የአንዱን ፊያት ሕይወት ባሰብኩት ጊዜ ይደንቀኛል መጽሐፍ እንዲህ እንዳለው “አንተ ፊያታዊ ዘየማን ታምንበት ዘንድ ማን ጠቀሰህ ማን አስተማረህ?… መኑ መሀረከ ወመኑ ቀጸበከ ከመ ታእምር ዘንተ”፡፡ በዚያች በእድሜው መጨረሻ በፍጻሜው ሰዓት ወደ ሕይወት መንገድ ስለመራው ጥበብ ሲያወሳ እንዲህ ይላል “ነብያተ ኢሐተትኩ ወሐዋርያተ ኢተሎኩ አላ ፀሐይ ቀጸበተኒ ሶበ ርኢኩ አመንኩ… የነብያትን መጽሐፍ አላነበብኩም፣ ሐዋርያትንም አልተከተልኩም እሱ ጸሐይ ጠቀሰኝ እንጂ፤ባየሁትም ጊዜ አመንኩት”

እውነት ምን ዓይነት ጥቅሻ ነው የጠራው?! እርሱስ ምን ዓይነት ማየት ነው ያየበት! የሚደንቀኝ በዚህ ጥቅሻ(ጥሪ) ውስጥ…. በዚ’ች እይታ ውስጥ ያገኘው፣ የገዛው ያ ፍቅር ነው! ወዮ ምን ዓይነት መውደድ ነው! ወዮ ምን ዓይነት ፍቅር ነው እንዲህ ‘ሚገዛ! ያ የስህተቱ ምክንያት የሆነ የክርስቶስ ፍቅር በማን ሰው ልብ ውስጥ ይኖራልን? በማን ሰው ህሊና ውስጥ ታትሟልን? በአንድ በእሱ በእግዚአብሔር ባህርይ ውስጥ ይኖራል እንጂ፡፡ እሱም አንድያ ልጁን ለሞት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ለሰው ልጅ ያለውን ይህን ፍቅር ገለጠ፡፡ ጲላጦስም ከእውነት ውስጥ ይህን ስህተት ፈለገ፡፡ ባልተረዳው መጠን ይህ ፍቅሩ ይገለጥ ዘንድ ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጠው፡፡ ሕይወቱንም ሰጠ፡፡ ይህን ጊዜም ነበር ለሞት ያበቃውን ጲላጦስ ፈልጎ ያጣለትን ስህተቱን ያገኘውና የተረዳው፡፡ ጲላጦስም ለዚህ ፍቅር መረታቱን የሕይወት ዘመኑን ፍጻሜ ሰማነው፡፡

አዎ የእግዚአብሔር ፍቅር ጽኑና ዘላለማዊ ነው፡፡ በሰው ልጅ አእምሮ የማይመዘን፣ በሰውልጅ ህሊና የማይመረመር፣ በዓለም ሚዛን የማይመዘን፣በሥጋ መስፈሪያ የማይሰፈር ከነገር ሁሉ በላይ ነው—–የባህሪው የእርሱ ብቻ ነውና፡፡ ይህ ባህሪው ይበልጡን እንድንወደው እንድንናፍቀውና እንድንጠማው ያደርገናል፡፡ ይበልጡን በቀረብነው ልክ እንናፍቀዋለን፤ ይበልጡን በረካን ቁጥር እጅጉን እንጠማዋለን፤ በክርስቶስ ፍቅር መታሰር ምን መሆኑ በገባን መጠን እጅግ ጠብቀን እንታሰር ዘንድ እኛነታችንን እንሰጣለን፡፡

አሜን አምላካችን ሆይ በፍቅርህ ፈሳሽ እንረሰርስና እንሟሟ ዘንድ ይኸው……

፲፬/፮/፳፻፪ ዓ.ም

አዲስ አበባ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑