ተ….መጽዋቹ

ተ….መጽዋቹ

በየቤተ ክርስቲያኑ አጥር፣ በየመኪና መንገዱና በየመጓጓዣ ሥፍራ የልመና መስፋፋት ምን የሚያስከትል ይመስልዎታል? ለጋሽ በበዛበት ከተማ ለማኝ ቢበዛስ ምኑን ይገርማል? ለመሆኑ እርስዎ በቀን/በሣምንት ምን ያህል ለኔ ቢጤ (ለነዳይ) ይሰጣሉ? በወር ምን ያህል ወጪ ይሆንልዎታል ማለት ነው?

‘ቀኝህ ስትሰጥ ግራህ እንዳታይህ’ ስለተባለ አላውቀውም ቢሉን ጉዳያችን አልጣመዎትም ማለትን ይመስላል። መስጠቱም መድረሱም መልካም ፤ጥያቄው ግን ምን ያህል መፍትሄ ሰጠናቸው? የእኛ ሳንቲም ወይም ብር (50 ሳ. ወይም 1ብር በትንሹ) ለተቸገረው ምን ያተርፍለታል? እርግጥ ሃሳባችን የእኛ ምጽዋት ከሌሎች ሰጪዎች ጋር ሲደመር ምግም መግዣ ይበቃዋል ብለን ይሆናል። እርግጥ ነው እንደህዝባችን አሰጣጥ ከዛም በላይ ሊተርፈው ይችላል። መቼም ብዙ ተሞክሮዎች ስላሉን።

ግን እንደው ምግቡ ይቅርብኝ ብሎ የእርሱዎን ምጽዋት  ለሱሱ ማስታገሻ፣ ለጥፋት መፋጠኛና ለተንኮል መተረቢያ ቢያደርገውስ? እድሉ ገጥሞዎት ይህን ቢያረጋግጡትስ? ሁለተኛ ብሰጥ ይሉ ይሆን? ወይስ እኔ መስጠቴን እንጂ ከዛ ካለፈ ምን ገዶን ይላሉ? ነው ወይስ እረ! እንደው በሆነልኝና በየዋህነት ለሁሉም በሰጠሁት? ብዙዎች ግን የሚሰጧቸውን ነዳያን (ችግረኞች) መምረጥ ጀምረዋል። ሰው ሊወጋበት እንደሆነ እያወቁ ለብርቱካን መቁረጫ ቢላዋ ቢጠየቁ ይመጸውቱታል ማለት ከባድ ነው። እኔ ‘ብርቱካን ልቁረጥበት’ ነው ያለኝ ማለት ‘የቅዱሳንን ስም ነው የጠራልኝ እንዴት ልከልክለው’ ከማለት ጋር ይመሳሰል ይመስለናል። ልክ ‘ፍሬንድን የማትፈልጊው 5 ብር ይኖርሻል?’ ወይም ‘ባክሽ! ለጡሜ (ሲጃራ) መግዣ ሙይልኝ’ እንደማለትም ይመስላል።

ተመጽዋቹን ከመለየት (አዛውንት፣ ህጻናት፣ ሴቶች፣ አካለ ስንኩላን፣ ህመምተኞች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ ጉልቤዎች..ወዘተ) ባለፈ በየእለቱ/ሣምንቱ የሚሰጡትን ቢያጠራቅሙት በወር በዛ ማለቱ ስለማይቀር ያን ለመረጡት ላንዱ የሚበላውን ወይም የሚለብሰውን ቢዘክሩት የተሻለ ያበረከቱ አይመስልዎትም? እርግጥ ነው ችግረኛ ምግብ ብቻ አይፈልግም፤ መጠለያም ብቻ እንዲሁ።

በአንድ ወቅት ለምን ዘላቂ የሆነ እርዳታ ለምን አናደርግላቸውም በሚል ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ተሰበሰቡ። የነዳያኑ መሠረታዊ ችግር ምንድነው? የሚለውን አጠገባቸው ከነበሩት ካጠኑ በኋላ መጠለያ እንደሆነ ተስማሙበት። ከዚያም መንደር ውስጥ በቆርቆሮ የተሰራ አንገት ማስገቢያና ማረፊያ የሚሆን ዳስ አበጁላቸው። የቀን ዋዕይ የሌሊት ብርድ ያቆማየዳቸውን፣ ፀሐይና ዝናብ በፈረቃ የተፈራረቁባቸውን ሰብስበው ያርፉበት ዘንድ ሰጧቸው። ግን ዳስ ብቻ እንደማይበቃቸው ባደረጉት አሰሳ ተረድተዋልና ወደሁለተኛው እርዳታ ተሻገሩ። ከሣምንቱ በተወሰኑ ቀናት ምግብ ያበስሉላቸውና ያገለግሏቸው ጀመሩ። ተረጂዎቹ ግና ሌሎች ደባል አመሎች ነበሯቸውና ያስቸግሩ ያዙ። አካል ማረፊያ ማግኘቱ ወይም ሆድ የሚበላውን ማትረፉ ሌላ ፍላጎታቸውን እንደከለከላቸው ያህል ምቾት አንገላታቸው። ሊያገለግሏቸው የሚመጡትን መተናኮል፣ ለክፉ ማሰብ፣ መጣላትና መበጣበጥ የየዕለት ውርሳቸው ሆነ መፍትሄው እየራቀ ረብሻውና አምባጓሮው እየበረታ ሲመጣ ማረፊያቸውን በደሉ። አጎንብሰው የሚገቡባትን ታዛ በቁመታቸው ትሆን ዘንድ ገነጠሏት፣ አፈረሷት። ያው ሜዳው የድሮው ቀያቸውን ሊመርጡ ወጡ። ላለመሳካቱ ብዙ ምክንያት መደርደር ቢቻልም የተረጅዎችን ፍላጎት ያሳየን ይመስለናል። ይህን ልምዷን ያካፈለችን እህት ተመጽዋች የበላበትን እንደሚረግጥ አሊያም የተኛበትን እንደሚያፈርስ አስተምሮናል።

ማጠራቀማችን ሊደርሳቸው የሚችሉ በአፍአ ተገኝተው አፍ አውጥተው ልምና ላይ ለተሰማሩት ይሆናል። በየቤታቸው ጣራ ስር በርሃብ አንጀታቸው ታጥፎ፣ በአልባሳት እጦት ሰውነታቸው ተዘንትሎ፣ ከሰው ተራ ወጥተው መልካቸው መለያው እስኪጠፋ የሚሰቃዩ በየመንደራችን ማግኘት ያን ያህል የሚያስቸግር አይደለም። ልጆቻቸውን ማብላት ቢያቅታቸው ነገ ተምሮ ለራሱ ይትረፍ በማለት ምግብ ካገኘ በሰነበተ ሆዱ ተማሪ ቤት የሚልኩ ወላጆች ሆነ አዛኝ ደራሽ አይዞህ ባይ አጥተው ያለእድሜያቸው ጉስቁልና አስረጅቷቸው አንገታቸውን ከተኙበት ቀና ሳያደርጉ ቀንና ሌሊቱ የሚፈራረቅባቸው፤ የሰው ድምጽ ተርበው በብቸኝነት የሚማቅቁቱን በየመንደራችን ብንፈልጋቸው አናጣቸውም። የቤተሰቡ ወጋግራ/ምሰሶ የነበረው አባታቸው ከዓለም ተለይቷቸው በእናታቸው ለወር ዳቦ መግዣ በማትበቃ ጡረታ አይን ለዓይን እየተያዩ በፍቅር ለመጥገብ፣ ቤተሰቡን ላለመበተን፣ የእናታቸው ሆድ ታጥፎ ያላትን ሥራ ላጡ ልጆቿ ሆነ ለአዳጊዎቹ እያከፋፈለች በቀን አንዴም በልተው ቢሆን ሕይወታቸው ትቆይ ዘንድ የእርሷን ሕይወት ሳትሳሳ የምታካፍል በእንባና በልብ በሃዘን ተወግታ የምትሰቃየውን ቤተሰብ በመንደራችን አንኳኩተን ከገባን ማግኘት አይከብደንም።  ግና ማጠራቀማችን እንዴት ለእነዚህ ወገኖች እንዲደርስ እናድርገው?  ሐሳብዎትን እንካፈል፤ ይጻፉልን። ይወያዩበት ይቆየን!

 

ግንቦት ፳፻፭

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑