የሕማም ሰው

To read in PDF please click

የሕማም ሰው

“መልክና ውበት የለውም፣ ባየነው ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም። የተናቀ ከሰውም የተጠላ፣ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፤ እኛም አላከበርነውም” ኢሳ 53፡2-3

crisufication

“የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፤ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው። ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው። በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም ሁሉ የታገሠ እርሱ ነው። እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፤ በግ በሚሸልተው ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፤ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም።” የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እንደተናገረው

ዜና ግብሩ ለዕለተ አርብ ጥንተ ስቅለቱ ለእግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ

    በሠማይ እሳታውያን መላእክት ጌታቸውን በፍርድ መንበር ላይ ሲቆም በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ሲመለከቱት በምድር ግን በስላቅና በሳቅ ጌታና መድሐኒታቸውን ይከሱት ነበር። በሰማይ፣ኪሩቤል ጌታቸውን ሲያከብሩ በታች በምድር ግን ወንጀለኞች ይዘባበቱበታል። ከከፍታው ሱራፌል ቅዱስ ቅዱስ ሲሉ ከምድር በታች ግን ክፉዎች ይከሱታል። ለሰማይ ውበትን ያጎናጸፈ ጌታ በምድር የውርደትን ልብሰ ለበሰ። በሰማይ ዙሪያው በሚነዱ የእሳት ሰረገሎች የተከበበው ጌታ በምድር በሁለት ሌቦች መሐል በምስማር ተቸነከረ። ከአባቱ ጋር በሰማይ የሚመሰገንና የሚከብር ጌታ በምድር ከወንበዴዎች ጋር ለፍርድ ቆመ። የነገስታት ንጉስ የሆነ ጌታና የክብርን አክሊል በሰማይ የሚያጎናጽፍ እርሱ በምድር ላይ የእሾህ አክሊልን አጎናጸፉት። በሰማይ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በንግስና ዙፋኑ ተቀምጦ የሚመሰገን ጌታ ከህግ በወጡ ወንጀለኞች በወቀሳና በሐሰት ተመሰከረበት። የህይወትን ዛፍ ይጠብቁ ዘንድ ኪሩቤልን ያዘዛቸው ጌታ በምድር ላይ ጎኑን በጦር ተወጋ። የሞትን መራራ ውኃ ወደ ጣፋጭነት የለወጠ ጌታ በምድር ላይ ሐሞትና ሆምጣጤ ይጠጣ ዘንድ ቀረበለት። ለአዳም የህይወትን እስትንፋስ እፍ ያለበት ጌታ ዛሬ ህይወቱን ይነጥቁትና በከምድር ሆድ ያሳርፉት ዘንድ ከሙታን ዘንድ ተቆጠረ።

***                   ***                   ***

    በመጀመሪያ መልኩ ያማረ፣ የፊቱ ገጽ የሚገዛ፣ ዓይኑ የተዋበ፣ ልብን የሚስብ፣ የሚያዩት ሁሉ ለእርሱ ያላቸው ጥበቃ የሚገንበት የተለየ ሰውነት ሊላበስ ይገባው ነበር፤ የጠበቁት እንዲህ እንዲሆን ነበርና። እኒያ እርሱን ያዩት ግን የተለየ እርሱን እንዲፈልጉት የሚያደርግ ውበትን ማየት አልቻሉም፤ ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ውድ የሚያደርገው ምንም አላዩበትም። መኃ 5፡9 ፣ ሐዋ 7፡20፣ ዕብ 11፡23 ዳዊት በተቀባ ወቅት የተዋበና ያማረ ነበር 1ኛ ሳሙ 16፡12 ጌታ ኢየሱስ ግን ለእርሱ የተጠበቀው አልተገኘበትም ወይም ወደ ዓለም የመጣበትና የተገለጠበት መንገድ የጠበቁትን የማይገልጽ በመሆኑ ትምህርቱ በሰው ጥበብ ሳይሆን መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበር።

ስለዚህም የጠበቁት ንጉሥና ነጻ አውጪ፣ ጦረኛና ተዋጊ ባለማግኘታቸው እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፤ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔር ጥበብ አላወቁትም። ስለዚህም የክብርን ጌታ ይሰቅሉት ዘንድ ወተወቱ።

holdingሐሙስ ምሽት

ከምሽቱ 030303

ወደ ጌተሰማኔ አትክልት የሞላበት ስፍራ  ደቀመዝሙሩ በሆነው በአስቅሮይቱ ይሁዳ የሚመሩ  ሰይፍና ጎመድ፣ ጋሻና ጦር የታጠቁና  በችቦና ፋና የተከበቡ ክርስቶስን ሊይዙ የምኩራብ ጠባቂዎች  ከካህናት አለቆችና ከህዝብ ሽማግሎች ዘንድ መጡ። ከያዙትም በኋላ አስቀድመው ወደ ሐና ቤት አመጡት እርሱም በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ለነበረው ቀያፋ አማቱ ነበርና። በሐና ቤትም ምላሽ ላላገኙበት ጥያቄ ካቆሙት በኋላ በሲንሃድሪን ሸንጎ (72 አባላት የሚገኙበት ከፍተኛ ምክርቤትና የአይሁድ የፍትህ ፍርድ ቤት ነው) በሸንጎው ወደተሰበሰበው ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ላኩት። ዮሐ (18፡1-24) ኢየሱስን የሚከሱ የሐሰት ማስረጃዎች በብዙ ምስክሮች ቀረቡበት እርሱ ግን አንዳች አልመለሰም። በመጨረሻም ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን በእውነት እንዲመልስለት እንደዚህ በማለት መሃላ አስገባው “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደሆነ እንድትነግረን በህያው በእግዚአብሔር ስም አምልሃለሁ” ኢየሱስም ምስክርነቱን አረጋገጠለት፣ “አንተ አልህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” አለው። ሊቀ ካህናቱም ተሳድቦአል ሲል ተናገረ የፍርድ ሸንጎዎቹ (ሲንሃድሪን) የሞት ፍርድ እንዲገባው ተስማሙ። (ማቴ 26፡57-66).

የሐዲስ ኪዳን አብያተ ክርስቲያናት የጌታን ህማማትና መከራ ለማስታወስ የጾማቸውን አንድ ሳምንት ሰሙነ ህማማት ወይም ቅዱስ ሳምንት ብለው ታስቦ እንዲውል ሥርዓት ሰርተውለታል። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የአብይ ጾም የመጨረሻ ሣምንት የሆሳዕና ማግስት ሰሙነ ሕማመት አድርጋ ትውላለች። የሳምንቱ ዕለታት ስያሜ በመስጠትም በየእለቱ የተደረጉትን እያሰበች ትዘክራለች።

አርብ ጠዋት

ከጠዋቱ 010101

በበነጋውም የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎችም ከገዢው ከጴንጤናዊው ጲላጦስ ዘንድ አመጡትና ይህ ህዝባችንን ሲያጣምም፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክልና ራሱን ንጉስ ነኝ ይላል በማለት ከሰሱት (ሉቃ 23፡1-2) ጲላጦስም ለአይሁድ ሽማግሎች እንደ ህጋቸው ይፈርዱበት ዘንድ ፈቀደላቸው እነሱ ግና  የሞት ፍርድ ለመፍረድ ሮማውያን እንዳልፈቀዱላቸው መለሱለት (ዮሐ 18፡31) ጲላጦስም ኢየሱስን ከጠየቀው በኋላ Gugde pilateለተሰበሰቡት ምንም በደል እንዳላገኘበት ነገራቸው። ኢየሱስ ከገሊላ መሆኑን ካወቀ በኋላ ጉዳዩን ወደ ገሊላው መሪ ንጉስ ሔሮድስ ለፋሲካ በዓል ኢየሩሳሌም ነበርና ወደ እርሱ ላከው። ሔሮድስም ኢየሱስን ብዙ ቢጠይቀውም ምላሽ ባለማግኘቱ መልሶ ወደ ጲላጦስ ላከው። ጲላጦስም ለተሰበሰበው ህዝብ እሱም ሆነ ሔሮድስ ምንም ወንጀል እንዳላገኙበት ነገራቸው። ስለዚህም ተገርፎ ይፈታ ዘንድ ወሰነ። (ሉቃ 23፡3-16)

አርብ ጠዋት

ከጠዋቱ  022222

የተሰበሰበው ህዝብ በሙሉ በካህናት አለቆች ታውከው ነበርና ስለአመጽና ሰው መግደል ታስሮ የነበረው በርባንን ለፋሲካቸው ልማድ ይፈታላቸው ዘንድ ጠየቁት። ጲላጦስም ኢየሱስን ምን እንዲያደርገው እንዲወዱ ጠየቃቸው። እነሱም “እርሱን ስቀለው” ሲሉ እየጮኹ ግድ አሉት። (ማር 15፡6-14). የጲላጦስ ሚስት ከዚያ ቀን በፊት በህልሟ ኢየሱስን አይታው ነበርና ጲላጦስን “በዚህ ጻድቅ ሰው ላይ ምንም አታድርግ” ስትል አስጠነቀቀችው (ማቴ 27፡19). ጲላጦስም የተገረፈውን ኢየሱስን ሊፈታው ወደ ህዝቡ አወጣው። የካህናት አለቆችም ለሞት ተላልፎ እንዲሰጥ በመጠየቅ አዲስ ክስ ለጲላጦስ ነገሩት “ምክንያቱም ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጓልና”። ስለዚህ ጲላጦስ ይሄን ነገር በሰማ ጊዜ ፈራ ኢየሱስንም ወደ ገዢው ግቢ መልሶ ካስገባው በኋላ ከወዴት እንደሆነ ይነግረው ዘንድ ጠየቀው።

 

የ ፴ ብር.. የደም ስፍርbetrayle

የደም ጤዛ.. የደም ቤዛ

የደም ዋጋ.. የሰው ሰንጋ

የደም መሬት.. የሰው ህይወት

የሰው ሽያጭ.. የብር ልዋጭ

የደሃ ማረፊያ.. ጊዜያዊ ማቆያ

የደም ማማ

አኪልዳማ!

 ማቴ 27፡9-10፣ ሐዋ 1፡19፣ ዘካ 11፡12-13

አርብ ረፋድ

ከረፋዱ  030303

ጲላጦስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደተሰበሰቡት ህዝብ መጥቶ ኢየሱስ ንጹህ መሆኑን በማወጅ ከእርሱ ደም እንደሌለበት ለማሳየት እጁን ታጠበ። ዳሩግን ኢየሱስን ይሰቅሉት ዘንድ ለፍቃዳቸው አሳልፎ ሰጠው። (ማቴ 27፡24-26)። “የአይሁድ ንጉስ የናዝሪቱ ኢየሱስ” የሚል ጽፈትም ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረ። መስቀሉን ተሸክሞም (በቀሬናዊ ስምኦን ታግዞ) የራስ ቅል ወይም በዕብራይስጥ “ጎልጎታ” በላቲን “ካልቫሪ” ወደ ተባለ የሚሰቅሉበት ስፍራ ሄደ።(ዮሐ 19፡17-22)

cross journyይህ የመስቀል ጉዞ ነው። ከፍርዳቸውም ሲወጣ የራሱን መስቀል በትከሻው ተሸከመ። የዕብራውያን ሴቶች አንድነት ስለደረሰበት ፍትህ ያጣ ፍርድ ዋይ ዋይ እያሉና ሙሾ እያወረዱ ብዙዎች ተከተሉት ። እናቱም ርቃ ከወዳጆቿ ጋር ቆማ ነበር። እንደ እርግብ እየበረረችና እየጮኸች ሀዘንና ብሶቷን በመራር ሁኔታ ትገልጽ ነበር። ወዴት እየሄድህ ነው ልጄ፣ ውዴ ሆይ? ወዴት እየወሰዱህ ነው? ፍትህ በእጃቸው ለሌለ ሰዎች ራስህን ስለምን አሳልፈህ ሰጠህ? ህመምህ ለእኔ ይሁን ልጄ፤ ስቃይህ ለእኔ ይሁን ውዴ እያለች።

    በአርብ እለት አዳምን ፈጠረ እናም በአርብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ቦታ ተሰቃየ እኛንም ተቤዠን። በአርብ እለት አዳምን ውብ አደረገው እናም በአርብ የኃጢአተኛውን የአዳምን ልጆች ምራቅ ተቀበለ። በእለተ አርብ የፈጠርካቸው እንሰሶች ወደ አዳም መጥተው አንገታቸውን ሰብረውና ተንበርክከው ስም ያወጣላቸው ዘንድ ይጠይቁት ነበር እናም በአርብ የሽማግሌዎች ስብስብ በክርስቶስ ላይ እየተሳለቁ  “የአይሁድ ንጉስ ሰላም ላንተ ይሁን” በማለት ዘበቱበት። የዳዊት ትንቢትም ፍጻሜውን አገኘ “ ብዙ ውሾች ከብበውኛል፣ የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ” (መዝ 21፡16) የተባለው።

በአርብ የንግስናን አክሊል በአዳም ራስ ላይ ደፋለት እናም በአርብ በአዳም ጌታ ራስ ላይ የእሾህን አክሊል ደፉበት። በአርብ እለት ሄዋን የተከለከለውን ፍሬ ለአዳም ሰጠችው እርሱም በላው እናም በአርብ ክርስቶስን የሰቀሉት የአሁድ ሸንጎ ሐሞት የሞላውን መጠጥ በሰፍነግ ሞልተው ሰጡት እርሱም ጠጣው። በአርብ እለት ለሦስት ሰዓታት አዳም እራቁቱን በገነት ውስጥ ተቀመጠ እናም በአርብ የአዳም ጌታ ለሶስት ሰዓታት ራቁቶን በመስቀል ላይ ቆየ። የመስቀል ሕማማት ሁሉ ታገሠ።

አርብ ቀትር

ከቀኑ  060606

የካህናት አለቆችና ጸሐፎች በእነሱም የተቃናው ሕዝብ የቅናታቸውና ቁጣቸው መጨረሻ ደረሰ። በተሸከመው መስቀል አስተኝተው በችንካር ቸነከሩት። ‘የናዝሪቱ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉስ’ ከሚል ጽሑፍ ጋር ሰቀሉት። የወንጀለኞች አለቃ ይሉት ዘንድ ቀኝአዝማችና ግራዝማች ወንበዴዎች ከእርሱ ጋር ሰቀሉ። ለጥማቱ ሐሞትና ሆምጣጤ  በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕ አድርገው አዘጋጁ። ልብሱን ተከፋፈሉ እጀ ጠባቡንም ዕጣ አወጡበት- አንድ ወጥ ነበርና። ጠባቂዎቹና አላፊ አግዳሚውም ይዘብቱበት ዘንድ ተቻኮሉ። እራሳቸውን ይነቀንቁበትና ይሰድቡት ዘንድ ተሞሉ። የካህናት አለቆች ከጻፎችና ሽማግሌዎች ጋር ተዘባበቱበት። (ማቴ 27፡33-44) እርሱ ግን ስለሁሉ መልካምን ተመኘ። እኚህ የመስቀል ላይ ቃላት ተስፋ የሞላቸውና ፍቅር የገዛቸው ሠላምን የሚያድሉ ሆኑ።

 

በዚህ ዓለም ጭካኔን በሞላው ሰዓት ሁሉ ባደመና በወገነ ወቅት ለእኛ ሁሉ በጎ ትምህርት ይነግረን ዘንድ የቀኙ ሽፍታ መሰቀሉ ለበጎ ሆነለት፤ ሆነልን። “ነብያተ ኢሐተተ ወሐዋርያተ ኢተሎከ አላ ፀሐይ ቀጸበተ ሶበ ርኢከ አመነ… የነብያትን መጽሐፍ አላነበበም፣ ሐዋርያትንም አልተከተለም እሱ ጸሐይ ጠቀሰው እንጂ፤ባየውም ጊዜ አመነው” ።  በመንግስቱ በመጣ ጊዜ እንዲያስበን፤ እንደሥራችን ሳይሆን እንደቸርነቱ ብዛት ይምረንም ዘንድ ልመናን አስተማረን።

አርብ ከሰዓት

ከቀኑ  090909

ኢየሱስ ለስድስት ሰዓታት በመስቀል ላይ ተሰቃየ። ከቀትር እስከ 9ሰዓትም ጨለማ ምድርን በሙሉ ሞላት። ኢየሱስም  በታላቅ ጩኸት ነፍሱን ሰጠ። ተአምራት ተፈጸሙ። ተአምራቱም በተፈጸመ ጊዜ በመስቀሉ ስፍራ ጠባቂ የነበረውም የመቶ አለቃ (ሴንትሪየን) “ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ!” ብሎ መሰከረ። (ማቴ 27፡45-54)

በእኩለ ቀንም ምድርን ጨለዋ በዋጣት ጊዜ እርሱ አሰምቶ ጮኸ “አቤቱ አቤቱ ስለምን ተውኸኝ?” በማለት በዚህ ወቅት የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ ወደ ታች ከሁለት ተቀደደ። ምድር ተገለበጠች አለቶች ተሰነጠቁ መቃብራትም ተከፈቱ። አርፈው ከነበሩ የቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ። ጌታቸው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በማየታቸው ኪሩቤል በፍርሃት ደነገጡ፤ ሱራፌል  ተንቀጠቀጡ፤ መላዕክትና ሊቃነ መላእክት ግራ ተጋቡ። ሐዋርያት ሮጡ ተከታዮቹም ተበታተኑ። ጌታ ሆይ! ትንቢት ስላንተ “ ኦ! የባራኪው ልጅ ተነሣ የበጎች እረኛ ተመታ በጎቹም ተበታተኑ” የተባለው ተፈጸመ። እናንተ መላእክትና ሊቃነ መላእክት ወዴት ናችሁ? ኦ! ሚካኤል ኃያሉ መላእክ ያንተ ቁጣ ወዴት አለ? የአስሪያን ሺዎች ያጠፋው ሰይፍ ወዴት አለ? ኦ! ገብርኤል የመላእክት አለቃ ንዴትህ ወዴት አለ?

 

አርብ ሰርክshouded

ከምሽቱ  105959

የአርማትያሱ ዮሴፍ የአይሁድ ሸንጎ አባል የነበረ ግና በምክራቸውና በሥራቸው ያልተባበረ ጲላጦስን የክርስቶስን ሥጋ ይሰጠው ዘንድ ለመነው  (ሉቃ 23፡50-52)ሌላኛው ድብቅ የክርስቶስ ተከታይ የነበረው የአይሁድ ሸንጎ አባል ኒቆዲሞስ የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ (ዮሐ 19፡39-40). ጲላጦስም ኢየሱስ ሞቶ እንደሆነ የመቶ አለቃውን ጠየቀው (ማር 15፡44) ከጭፍሮቹ አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ (ዮሐ 19፡34) የመቶ አለቃውም ለጲላጦስ ኢየሱስ መሞቱን ነገረው (ማር 15፡45) ዮሴፍ ዘአርማትያም የኢየሱስን ሥጋ በንጹህ በፍታ ከፈነው፣ኒቆዲሞስም እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈነው (ዮሐ 19፡40) ከተሰቀለበት የአትክልት ሥፍራ ቅርብ በነበረ ማንም ባልተቀበረበት ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፤ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ።(ማቴ 27፡59-60)

አሜን!

ብዙ ዘመን በርሃብ በችጋር ተውጠን ምንበላው ብናጣ

ከመሐከላችን ያ’ንዱን ሕይወት ሰዋን ሥጋውን ልንበላ ደሙንም ል’ጠጣ

ዛሬ..

እሰየው አበጀን! ያን ዘመን ተሻገርን

በሰዋነው ሕይወት ባገኘነው መብል

ይኸው አምሮብን ሕይወት እየበላን

ዛሬን ብቻ ሳይሆን ለነገም ተርፈናል።

ሚያዝያ 1 ቀን 2005 ዓ.ም አዲስ አበባ

 

ዋቢ መጻሕፍት

  1. መጽሐፍ ቅዱስ የብሉይና ሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት፤ 1954፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት
  2. “HOLY LITURGY OF PASSION WEEK FROM HOSANNA TO KYMTHO (EASTER)”, 2011, THE MALANKARA ORTHODOX SYRIAN CHRISTIAN’S, compiled by St. Gregorios Indian Orthodox Church Mississauga, Ontario, Canada.
  3. Isaiah 53:1-3 commentary, Matthew Henry’s commentary on the whole bible, e-sword bible software V.10.1
  4. “ስምዐ ጽድቅ ልዩ ዕትም መጋቢት 20-24” ፤ 2002 ፤  ማኅበረ ቅዱሳን ፤ ሜጋ ማተሚያ ቤት (ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ቀራንዮ ጉዞውን የሚያሳይ ሥዕል)
  5. www. St-takla.org (especially for the holy pictures)

3 thoughts on “የሕማም ሰው

Add yours

  1. አሜን!

    ብዙ ዘመን በርሃብ በችጋር ተውጠን ምንበላው ብናጣ

    ከመሐከላችን ያ’ንዱን ሕይወት ሰዋን ሥጋውን ልንበላ ደሙንም ል’ጠጣ

    ዛሬ..

    እሰየው አበጀን! ያን ዘመን ተሻገርን

    በሰዋነው ሕይወት ባገኘነው መብል

    ይኸው አምሮብን ሕይወት እየበላን

    ዛሬን ብቻ ሳይሆን ለነገም ተርፈናል።

  2. ይኸው አምሮብን ሕይወት እየበላን

    ዛሬን ብቻ ሳይሆን ለነገም ተርፈናል።

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑