ሲዳሩ ማልቀስ-አግብቶም ማልቀስ
እንኳን ለወርኃ ሚያዝያ- ወርኃ መራዊ አደረሳችሁ አደረሰን። መቼም ጊዜው የሰርግም አይደል ዘንድሮ ሚያዝያ ቢወጣብንም ቅሉ። የፈጣሪያቸው ሙሽራ ይሆኑ ዘንድ ራሳቸውን ለጃንደረባነት የለዩ ብዙዎችን አይተናል። እንደኔ አይነቱ ደግሞ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ..” የሚለውን እያሰበ ብቻነቱን ሊረሳ ይሞሸራል፤ያገባል። ሁለቱም የተገባ ሕይወት ነውና እግዚአብሔር የልባቸውን መሻት ይሙላላቸው። ደስታን ይዛቁ-እርካታን ይሞሉ።
ጋብቻ ሲነሳ አብሮ ከመነሳት የማይቀረው ሰርግ ነው። የብዙዎች ጋብቻና ሰርግ ምንን ይመስላል? እስቲ ያገባችሁ የራሳችሁን ያላገባችሁ የተካፈላችኋቸውን ሠርጎች ውሎ ተመልከቱ
“ኦው! እንዴት አስደሳች ነበር”
“ባክህ አሰልቺና አድካሚ ነበር”
“ሠርግስ እንዲህ ከሆነ ማንም መቅረት አይኖርበትም… አግቡ!”
“ምነው? ‘አንዱ ሊያገባ ሌላው ገገባ’ አሉ”
“አቤት ልብሳቸው ማ.. ማሩ! የሙሽራዋ ብትይ የሙዜዎቹ!”
“እንዴ! በከተማው መኪና የሚባል ቀርቷል እንዴ!”
“ምን መኪና ብቻ ሰውስ ብትይ ማን ቀረ? የጠፋ ሰው’ኳ ሳታገኘ አትቀሪም!”
“ወዳጄ እኔ ማግባቴን ልተወው ነው”
“ለምን?”
“እንዴ ምንሆንህ ነው! ይሄን ሁሉ ወጪ ከየት አባቴ አመጣዋለሁ?”
“የገንዘብ ወጪ ያስጨንቅሻል? ምን ሆነሽ ነው? ዓለምሽ’ኮ ዛሬ ነው ፈጽሞ የማይደገም”
“ወይኔ እን እንቶኔን ብታዪ… እውነት ከአሁን በኋላ ጾም ቢያድሩ’ኳ አይሰማቸውም”
ይበቃችኋል…. ይሄን ዓይነትና የመሳሰሉት ምላሽ እንደሚኖራችሁ አምናለሁ። አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝን ልንገራችሁ “አንድ ጓደኛዬ ሠርጎ አገባ… በማግስቱም እንዲህ አለኝ ‘ስማኝ’ጂ ለሠርጌ የጠራኋቸው ሰዎች 56 ሜትር ቆፍረው ቀበሩኝ’
ማለት?
እንግዲህ 56 ሳምንታት ጉድጓድ ውስጥ ነኝ ወዳጄ ምን ቀረኝና እቤቴ ልቀመጥ?!” በጓደኛዬ ጨዋታ ላይ ጥያቄ አነሳው። ጉድጓዱን የቆፈረው ማነው? ሙሽራው ወይስ እድምተኛው? ምናልባትም ራሱ የቆፈረው ጉድጓድ ላይ ሰዎች ደስታውን ሊጋሩት በደስታ ሲያቅፉት ገፋ (ጎሸም) አድርገውት ሊሆን ይችላል።
መቼም የቀደመን ሰርግ ማየት ለሙሽሮች የተለመደ ነገር ነው። ከሚያዩት ሰርግም ላይ ኮረጅ ማድረግም እንዲሁ፣ አለ አይደል እንዳያንስባቸው። ሰርጉ ሳይሆን እነሱ ከሰው እንዳያንሱ። እንዴ ዓለማቸውም አይደል’ዴ ከሰው በላይ ከፍ ብለው ነግሠው መታየት አለባቸዋ! የደስታቸው ቀን ለምን ከሌላው የጎደለ ይሁን ቢቻል ይብዛ’ጂ።
ተጋቢዎች የሠርጋቸውን እለት ደስታ ቀድመው ካዩዋቸው ሠርጎችና ከቤተሰቦቻቸው ፍላጎት እነሱም ካደጉበት ከባቢ አንጻር ይቀርጹታል። ደግሞስ ዓለሙ ሁሉ ስለነሱ ሰርግ ቢያወራ ማን ቅር ይለዋል? በጋዜጣ በቲቪ ቢተላለፍ ማን ይከፋዋል? ወዳጅ ዘመዱ በዝቶ ደስታቸውን ቢጋራ፣ በየመናፈሻው፣ በየሆቴሉ፣ በየመዝናኛው፣ በየአውራ መንገድ አሻራቸውን ጥለው ቢያልፉ ማ’ነው የማይደሰት?! አሊያማ እንግዳ በመጣ ቁጥር ምን ሊያሳዩ ነው?
ደስታ ሁሉ ንጽጽር ነው። አንዱ ካ’ንዱ ይለያል- እንደሰማናቸው ዓይነት የሰርግ ዜናዎች በሰረገላ ተጋቡ፣ ኳስሜዳ ውስጥ ተጋቡ፣ ኧረ በአየር ላይም የተጋቡ አሉ። 20 ሰላሳ ሰው ብቻ ጠርተውም ፀበል ቅመሱ ያስመሰሉትም አሉ፤ ሌሎች ሰርጋቸውን የተራቡትንና የተቸገሩትን ሰብስበው አብረው በመመገብ በእንግዶቻቸው ምርቃት የተጋቡም አሉ፤ ሌሎችስ ቢሆኑ የሠርግ ወጪያቸውን ለአንድ ህጻናት ወይም ሴቶችን አሊያም እናቶችን ወዘተ ለሚረዳ ድርጅት እጅ መንሻ አበርክተው በነ’ሱ ቡራኬ የተጋቡትስ፤ ጋብቻቸውን እንደ እምነታቸው ሥርዓት ፈጽመው በወረቀት እወቁልን ተጋብተናል ግን እኛ እቤት የለንም ሥራ ላይ ነን ያሉትስ የሉም ብላችሁ ነው? አንዳንዶች ሰርጋቸውን ከከተማ ወጥተው ሁለቱ ጀምረው ከፈጣጠሙ በኋላ የተመለሱትና በቅልቅል የተዋወቁትስ… ብዙ እጅግ ብዙ ዓይነት የጋብቻ ዜናዎችን ሰምተናል ልንሰማም ተዘጋጅተናል።
ጋብቻ መባረክ ነው አንዳንዴ ሰርግ ግን መለከፍ ነው። ሁሉ በልክና በአቅም ቢሆን ይመረጣል ምክንያቱም የፍላጎታችን ጣራ ሰማይ ነውና የማይደረስበት። ትንሹም ሆነ ትልቁ ፍላጎታችን ሲፈጸም ደስታ ይሰጠናል። ታዲያ ሠረግ ብሎ ደግሶ ካላበሉና ካላጠጡ (ያውም እዛው ተቀምጦ ሐሜቱን ለሚጀምር) አላገቡም’ዴ? በየመናፈሻ መዝናኛ፣ በየሆቴል በየመንገዱ ካልዞሩና ካልተቀረጹ ወይም ፎቶ ካልተነሱ መጋባታቸውን ማስታወስ አይችሉም እንዴ? የቀደሙትን ካልመሰሉና ካልኮረጁ የራሳቸውን ዓይነት ትዝታ ጥሎ የሚሄድ አማራጭ መንገድ የለም ወይ? ተቀዶ የሚጣል ፎታቸውን በወረቀትና በካርድ … እያደረጉ ካልበተኑት የተጋቡት ሁለቱ ስለመሆናቸው ማስረዳት አይቻልም እንዴ? መቼም ‘ከእግረኛም ኩሺኔትም ያለው ይበልጣል’ ያለውን የጓደኛዬን ሀሳብ ሳልረሳ ባለአንድ በር ፣ባለሁለት በር… ፣ሚዜ የሚከት… ፣ቤተሰብ የሚያጉር ፣ተንቀሳቃሽ ቤት፣ ወይም በራሪ መኪኖችንና ሌሎች በመጠቀም ካልተጋቡ አፉን የሚያጣምም ወይም የሚያሽሟጥጥ ማነው? እግረኛው ወይስ መኪናውን ያዋሳቸው ?ይቅርታ ያከራያቸው? ሙሽሮቹም ከዚያ በኋላ እዛ መኪና ውስጥ ስለመግባታቸው እርግጠኞች አይደሉም። ለነገሩ ዓለማቸው ዛሬም አይደል ባይገቡበትም የያኔውን ምቾት አሊያም ጭንቀት ካወሩ ይበቃቸዋል።
እስቲ ገንዘቡ ብቻ እናንሳ። መቼም ስለገንዘብ ማውራት መስቆንቆን አይደለም። እርግጥ ነው ወጪን አቅዶ የሚቆጣጠርን ሰው ‘ቋጣሪ’ ማለት የተለመደ ነው። ግን ሰርግ ለመደገስ ምን ያህል ይበቃል? 10 ብር? ሩብ ኪሎ ቡና’ኳ በዚህ አይገኝም እሺ 100 ብር? ይሄ የአንድ ሰው ልብስ ኪራይ’ኳ አይችልም የለም 10 ሺህ ምን አላት ለሰርግ 110 ብር እንደማለት ናት ኧረ 100 ሺህስ? 400 ሺህ? 900 ሺህ?…. አይ ከዚህ በላይ’ኳ አልጥራ።
ሠርግ ላይ ወጪዎች ቁጥሮች ላይ 0 እንደመጨመርና ምክንያት እንደመፍጠር (እንደመስጠት) በቀላሉ የሚበዙ ናቸው። ትንሽ ወጨ የለምን። እዚህ ላይ ሰርጋቸውን በጣም እጅጉን በጣም በአነስተኛ ወጪ የሸፈኑ ሰዎችን ማግኘት አዳጋች ቢሆንም ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች አቅም ስላልነበራቸው ነው ወይስ አቅሙ ኖሯቸው በአነስተኛ ወጪ (እንደ አቅም) ማድረግን ስለመረጡ? ልውጣ ልውጣ እያለ የሚታገለውን ገንዘብ ማፍሰሻ አማራጭ አቅደውስ እንደው? ማን ያውቃል -እራሳቸው።
ለሚያገቡቱ ና ለሚታደሙቱ ሁሉ ሠናይ ጋብቻ ይሁንላቸው!
Leave a comment