አንድ ዩኒቨርስቲ ለአንድ ሰው!
እድሜያቸው ለት/ት ሲደርስ ከቀሲስ ወልደ ገሪማ መሠረታዊት/ቤት ተማሩ፡፡ ከዛም በትግራይ ጮኸ በተባለው ገዳም ሰዓታትን፣ ቅዳሴን፣ አምስቱን ዓዕማደ ምስጢራትና ባህረ ሃሳብን ከመ/ር መንግስተ አብ ገ/ማርያም ተምረዋል፡፡ ምዕራፍ ጾመ ድጓን ከመ/ር ገ/ሥላሴ ሲቀጽሉ ከመ/ር ገ/ኢየሱስ ጉባኤ ቤት የ4ቱን ወንጌላት ትርጓሜ፣ ቅዳሴ ማርያምና ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ እንዲሁም ባህረ ሐሳብን ተምረዋል፡፡ ከዚያም በሰሜን ጎንደር ከዶ/ር አለቃ አየለ ዓለሙ 12ቱን የጳውሎስ መልዕክታት የሐዋርያት ሥራ ዮሐንስ ራዕይ… ተምረው የሐዲስ ኪዳን መምህር ሆነው ተመርቀዋል፡፡ ቅኔን ደግሞ ከመ/ር ጌጡ ዕንቁ ባህርይ ተምረው አጠናቀዋል፡፡ (ማኅበረ ቅዱሳን፣ (2005)፣ ሐመር-መጋቢት፣ ገጽ 17)
ይሄ ዓይነት አጻጻፍ የለመድነው ዓይነት የቀደሙት ትውልዶች የእውቀት ሀሰሳን ማሳያ መንገድ ነው፡፡ ከመምህር እገሌና እገሌ ይወጡታል፣ ይቀጽላሉ፤ ያጠናቅቃሉ፤ ያስመሰክራሉ፡፡ ከዚያም ከሊቅ እስከ ሊቀ ሊቃውንትነት፤ ከባለአንድ ዐይና እስከ ባለ አራት ዐይና የሚል ማዕረግ ይደርሳሉ፡፡
የዚህ ዘመን የእውቀት ፍለጋ ዘገባ ግን መልኩ እንዲህ ተቀይሯል፡፡ እድሜያቸው ለት/ት ሲደርስ አዲስ ዓለም የመጀመሪያ ት/ት ቤት ገብቶ እስከ 6ኛ ክፍል ተማረ፡፡ የመለስተኛና ሃይስኩል ትምህርቱን በመድኃኔዓለም 2ኛ ደረጃ ት/ት ቤት ተማረ (አሁን ደግሞ የመሰናዶ ት/ቱን የሚል ይቀጸልበታል) በመቀጠልም የከፍተኛ ት/ቱን ሰመራ ዩኒቨርስቲ በመግባት በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ድግሪ ተመርቋል፡፡ ጀርምን ከሚገኘው ‘ሲልቨር’ ኢንስቲቱት በርቀት በቢሮ አስተዳደር ዲፒሎማ ያገኘ ሲሆን ት/ቱን በመቀጠል ከአ.አ ዩ. በሶሻል ዎርክ የሁለተኛ ድግሪውን (ማስተርስ) አግኝቷል፡፡ ከአሜሪካው ማሳቹሴት ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደር ፍልስፍና ሦስተኛ ድግሪውን (ዶክትሬት) ተቀብሏል፡፡ ከዚያም ሲያስተምር…. ሲሰራ.. ቆይቶ እጩ፣ ተባባሪ፣ አሶሼት ወይም ፕሮፌሰርንት ከእገሌ ቦታ ተሰጥቶቷል ይላል፡፡ እንግዲህ አራት ዐይና ለመሆን ካልሆነም በየደረሰበት ዓይን ይይዝና ይጨርሳል፡፡ (አንድ ዓይና፣ ሁለት ዓይና… ባችለር ማስተርስ ወዘተ ቢሆን)
የሁለቱ ዘመናት ትውፊት ባሰብኩ ቁጥር ሁሌ የሚደንቀኝ ነገር አለ፡፡ የቀድሞዎቹ የተማሩትን ት/ት (ሙያቸውን) ሲናገሩ ያስተማራቸው መምህር ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ ኩራትም ነውና ከመ/ር እገሌ፣ ይሄን ከየኔታ እገሌ፣ ዳግም ያንን ከቀሲስ… በማለት፡፡ በእርግጥ ለእኛ ዘመን መምህር እገሌ ሆኑ የኔታ ምናችን ናቸው? እናውቃቸዋለንስ? የለም፡፡ ለእኛ ለመረዳት የሚቀለን ከእገሌ ዩኒቨርስቲ፤ ከእገሌ ኮሌጅ ወይም ከምንትስዬ ሃይስኩል ማለት ነው፡፡ ይሄ የሚያመለክተው የያኔዎቹ መምህራን ወንበር ዘርግተው (ት/ት ቤት ከፍተው ማለት ነው በዛሬ ቋንቋ) ሲያስተምሩ አንድ የት/ት ተቋምን ወክለው ነበር ማለት ነው፡፡ አንድ የኔታ አንድ ዩኒቨርስቲ ነበሩ፡፡ ሙዚቃን ያሬድ ለመማር ወይም ለህክምና ት/ት ጥቁር አንበሳ (አአዩ) እንደምንመርጠው (ለሃገር ውስጥ ምርጫ ማለቴ ነው) ወይም ደግሞ ሙያ ስንመርጥ በዝናቸው እገሌ ተቋምን እንደምንመኘው የያኔዎቹም ድጓን ለማስመስከር ቤተልሔም መግባትን፣ የትርጓሜ እውቀት ለመዋዠት ጎንደር፣ ጎጃም መውረድን ይፈልጉ ነበር፡፡ ወይም ከመ/ር እገሌ ጋር ለመማር የሚከለክላቸው ተሻግረው የማይሄዱት ድንበር የለም፡፡ እገሌ የኔታን ፍለጋም የማያልፉት እንቅፋት አይኖራቸውም፡፡ የቀለም ቤቶቻቸው ዩኒቨርስቲዎች ነበሩና፡፡
አንድ ደቀ መዝሙር (ተማሪ) ከቆየበት ቦታ ከመምህሩ ማንኛውንም ነገር ከተቀበለ ለበለጠ ትምህርት በዚያው በያዘው ወይም በቆየበት የትምህርት መስክ የታወቁ መምህራን ወዳሉበት ቦታ ይሄዳል፡፡ እንደዚህ እያለ ለብዙ ዓመታት ሲዘዋወር ይቆያል፡፡
እነኚህ ለሕዝብ መምህርነት የተመረጡትም ሆነ እነሱን ፍለጋ የሚጓዙቱ አራት አይነት ለምርጫ የቀረቡ የት/ት ቤቶች ነበሯቸው፡፡ መጀመሪያ ቃል ወደሚጠናበት ት/ቤት ይገባሉ፡፡ እንደ ሙያ ፍላጎታቸውም በማስከተል ዜማ ቤትን ይቀላቀላሉ፡፡ በዜማ ቤትም በድጓ (ቤተልሔም)፣ በዝማሬ መዋስዕት (ዙር አምባ)፣በአቋቋም (ደብረ ታቦር፣ኤልሻማ፣ ጎንደር) በቅዳሴና ሰዓታት (ደብረ ዐባይ፣ ሰለልኩላ በዋድላ) በአንዳቸው ወይም በየቅደምተከተላቸው በየሁሉም ማስመስከር (መመረቅ) ይችላሉ፡፡ ሦስተኛ ት/ቤት ቅኔ ቤት ይሆናል ይሄንንም ት/ት በዋሸራ፣ ዋድላ ደላንታ (ወሎ) ወይም ጽላሎ (ጎጃም) ተጉዘው ጥሩ ዘራፊ መሆናቸውን ማስመስከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የበረቱና የጎበዙ ከዚህ በኋላ የትርጓሜ ትምህርት እንዲማሩ ይፈቀድላቸዋል፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ከ20 ዓመት በላይ እንዲቆዩ ይገደዱባቸዋል፡፡ በዚህም ቆይታቸው የብሉያትን ትርጓሜ (በጎንደር፣ አክሱም፣ ጎጃም)፣ የሐዲሳትን ትርጓሜ (በጎንደር)፣ የሊቃውንትን ትርጓሜ (በደብረ ሊባኖስ፣ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም) እንዲሁም የመጽሐፈ መነኮሳትን ትርጓሜ (በአታ ለማርያም ገዳም) ያጠናሉ፤ ያስመሰክራሉ፡፡ በዚህም አራት ዐይና ይባላሉ፡፡ (ክርስቲያን ሻዮ ትርጉም መላከ ሰላም ዳኛቸው ካሣሁን፣ (1999) ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እና መንፈሳዊ ሕይወት፣ ገጽ 90-102)
በዘመናዊት ኢትዮጵያ ዘመናዊ ት/ት ተጀምሮ የምዕራቡ ፍልስፍና እስኪገባ ድረስ የሃገሪቱ ልሂቃን፣ መሪዎችና መምህራንን ሲያፈሩ የቆዩት እነኚህ ት/ቤቶች ናቸው፡፡ በተለይም ከ1930ዎቹ በፊት ዘመናዊ ት/ት በሀገራችን ሳይጀመር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ገዳማትንና አድባራትን እንደ ዩኒቨርስቲ በመጠቀም ኢትዮጵያውያን ከድንቁርና እንዲላቀቁ በማድረግ የነገሥታት አማካሪ፣ የሕግ ባለሙያ፣ የሥነጥበብና የዜማ ባለሙያ፣ ፍርድ ሰጪ ዳኞች እና የሕዝብ መምህር እንዲሆኑ አድርጋለች፡፡ (ማኅበረ ቅዱሳን፣ (2002)፣ ዝክረ ዘመን፣ ገጽ 31-32)
አንድ መምህር በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች (ደቀመዛሙርት) ሊኖሩት ይችላል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ሲመረቁ ግን ብዙዎቹ ሥራ ነበራቸው፡፡ ሐገሪቷንም ለዚህ ዘመን እያሻገሯት ያሉት እኚህ ሊቃውንት ናቸው፡፡ በመባህትነት (ሚኒስተርነት) ደረጃ ሃገር አስተዳድረዋል፡፡ የፍትህ፣ እርሻና ግብርና፣ የገንዘብና የምጣኔ ሐብት፣ የትምህርት፣ የጤና ወዘተ በመሆን ያገለገሉ ሌሎችንም ያፈሩ ምሁራን ነበሩ፡፡ ት/ታቸው እንደሚገመተው የሃይማኖት ብቻ አልነበረም፡፡
ይሄ ትውፊት ነው ኢትዮጵያን ከዝና ወደ ዝና ያሻገራት፤ ዛሬ የምናወራውን ታሪክ የፈጠረልን፡፡ አሁን ተቋማቶቻችን በዝተውልን መምህራኖቹም ተቆጥረው በሺዎች እየተመረቁ ሃገር ከመወቀስ አላተረፉም፤ ታሪክ ከመናገር በላይ ታሪክ ለመሥራት (የለውጥ ታሪክ ማለቴ ነው) የታደሉ አይደሉም፡፡ ያለውን ሃገር በቀል ልማድና ትውፊት አሽቀንጥሮ የሕብረተሰቡ የሕይወት ልምድ ሳይቀየር ‘የተማረ’ በማምረት ብቻ የተሻለች ሃገር ለመገንባት ከብዶናል፡፡ ጥቂት የቀሩት እኚያ መምህራን ካልቆዩና ካልቀጠሉ፤ ደቀመዝሙሩ ካልበዛ ”የሃገሩን ሰርዶ… በልውጥ በሬ” ዓይነት የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲ የሚያህሉ መምህራን እጅግ ሊደነቁና ሊከበሩ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ምን ትላላችሁ?
Leave a comment