በዓል ከእኛ ጋር
ይህ መግቢያው ነጻ የሆነ ዝግጅት ማስታወቂያ ነው፡፡ የአዲሱን ዓመት በዓል እንዴት ለማሳለፍ እያቀዱ ይሆን? ትንሽ ጊዜ ከሰጡኝ ስለዝግጅቱ ላስተዋውቅዎት፤ ማለፊያ ጊዜ ይሆንዎታል፡፡ በበርኩሜ (milinium) አዳራሽ የሚኖረው ዋዜማ የሚገርም እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡ 2ሺህ አምስት የምርጫ ዘመኑን ጨርሶ ለአዲሱ 2006 ቁልፉን ሲያስረክብ ተጋባዥ የሚሆኑበት ነውና፡፡
ጓደኞቼ ወደ ትውልድ ቀያቸውና ቤተሰቦቻቸው ከዘመቱ ሰነበቱ እኔ ቀዬ አልባ ይመስል ከትዝታ እዘምታለሁ፡፡ ከሁሉም በዓል የዘመን መለወጫ አዲስ ልብስና አዲስ ጫማ የሚያመጣልን በዓል በመሆኑ ለልጅነታችን የተለየ ነው፡፡ በሰፈራችን ሁሉም ህጻናት የተገዛላቸውን አዲስ ልብስ እርስ በእርስ ለማሳየት የሚኖራቸው ጥድፊያ፣ ደስታና ዝላይ የበዛ ነው መስከረም እስኪጠባም አይጠበቅ፡፡ ኳስ ስጫወት ቁርጭምጭሚቴ አካባቢ ቆስሎ ስላልደረቀልኝ የተገዛልኝን ‹ኪቶ› ጫማ ማጥለቅ ባለመታደሌ ጳጉሜን እየተብሰለሰልኩ ሰነበትኩ፡፡ አንድ የተገዛልኝ ደግሞ እርሱ ብቻ ነበር፡፡
ቤተሰቦቻቸውን እያስቸገሩ ይሁን ስለሚወዷቸው በዛን ወቅት ባላውቅም የጎረቤቶቻችን ልጆች በአዳዲስ ልብስና ጫማዎች ይፈራረቁብኛል፡፡ እኔ ግን ተቀምጬ ለአዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ የምልበትን ስዕል በቀለማት አጨማልቄ እስላለሁ፡፡ እስቲ እነሱ ይሞክሯት! ብዙ ከሳልኩኝ የጎረቤቶቻችንን ቤት ካዳረስኩ በኋላ በቀጣዮቹም ቀናት ቢሆን ሩቅ ወዳጆቻችን ቤት ሄጄ የምሰጠው ይኖረኛል፡፡ የሚሰጠኝ ‹ያቀሊጥ› (ለልጅ እንኳን አደረሰህ ሲል የሚሰጥ ፍራንካ ነው) ትንሽ እንዳትመስላችሁ! ቢያንስ ከጓደኞቼ ጋር የገዙትን መግዢያ ትሆነኛለች እናቴን ለጫማ፣ ለልብስ፣ .. ለአቀሊጥ ተጠይቆ እንዴት ይኮናል? አይ የዘንድሮ ልጅ አልሰማኝ!
በአዲስ ዓመት ሴቶች በሃገር ባህል ልብሳቸው ደምቀው በየቤቱ ‹አበባየሆሽ.. አበባ አያችሁ ወይ?› ሲሉ እኔን በሚያውቁኝ ልብስና ጫማ ሲያዩኝ ተሰማኝና እናቴ ወደ ጓዳ ገባ ስትል ‹ኪቶ› ጫማዬን አውጥቼ ጭምት- እሰይ የት አባቱ! እንዲህ ነው’ጂ ከሰው አለማነስ ምንም’ኳ ማታ ላይ ቁስሌ ቢነፈርቅም ቅሉ፡፡
በልጅነት አዕምሮ ልጅ ከልጅ ጋር እንዲህ ከተያየና የሚሰማው ከሆነ ባለ አዕምሮው ትልቁ ሰውማ እንዴት! በተለይ የልጆች እናት/አባት ከሆናችሁ በኣል በመጣ ቁጥር መሳቀቃችሁ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ከሚያሳቅቀው የሚያንስ አይምሰላችሁ፡፡ በተለይ በዚህች መንግስቷ ህዝቡን አጥግቦ አይደለም አቅምሶ ማሳደር ባልቻለባት ሃገር የበዓል ቀን ሌሎች በአዘቦቱ የሚያገኙትን ማግኘት እድል የሚሆንላቸውን ነፍሰኞች ለማግኘት የፖለቲካ አመራር መሆንን አይጠይቅም፡፡ አመራሮቹ ቢሮአቸው ከተማ ነዋሪው የሌለባት ጋር ሲሆን ነፍሰኞቹ ግን እኛው ጎረቤት ይገኛሉ፡፡ በየምንገዳችን በየህንጻውና ጉራንጉሩ በነተበውና በወደቀው ወጋግራ ስር አርፈው ይገኛሉ፡፡
ይሄን ለመጻፍ ምክንያት የሆነኝ ‹እንዳልክና ማህደር› የራድዮ መርሐ ግብር የእንኳን አደረሳችሁ እጅ መንሻ ይዞ በመንደራችን ጉብኝት የወጣበትን ዝግጅት የሰማሁበት ጊዜ ነው፡፡ እነሱ ስፖንሰር አድራጊ ቢያገኙም’ኳ ተነሳሽነቱ የነሱ ዋጋ በመሆኑ ብዙዎቻችን ማድረግ የምንችለው ይመስለኛል፡፡ የእኛ ሀገር ነዋሪ አንዱ በሌላው እገዛና ድጋፍ የቆመና የበረታ ነው፡፡ ምናልባት የተረፋቸው ባሳረፉንና ባጽናኑን አንዳንዶች ደግሞ ካለቸው ላይ ቆንጥበው ባበሉንና ባለበሱን ልክ ነው በርትተን የቆምን፡፡ እንደ’ኔ ደግሞ ይሄን ማድረግ ውለታ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ መሪዎቿ ኑሮዋን ሊያሻሽሉላት ቀርቶ እንዴት እንደምትኖር በቅጡ ላልተረዷትና የት እንደወደቀች ባላወቋት ሃገር ውስጥ ያለ ነዋሪ ለሌላው መድረሱ ግዴታው እንጂ ውለታው አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ይህ የሰውነት ክብር ነው፡፡ በዚህች በበዛለትና ባጣ በነጣው መሐል ያለው የወሰን ክልል በሰፋበት፣ የሚያተርፈው በሚነጥቀው በተዋጠበት፣ አጭበርባሪው በአማኙ ላይ በነገሰበት፣ ሰዉ በጎጥ ጎሳና ዘር በተቧደነበት፣ በሃይማኖትና ርዕዮት በሚቧረቀስበት አኗኗር ውስጥ የሚገኝ ዜጋ በምንም ምክንያት ለወገኑ መድረሱን ከውላታ ሳይሆን ከግዴታው የሚጻፍ ነው፡፡ ይህ እርግጥ ሰው የመሆን ክብር ነው፡፡
ጣራው ተቀዶበት በሚጨነቀው፣ መሬቱን ተነጥቆ ሜዳ በተጣለው፣ ‘ሚያርፍበት ያይደል የሚጠለልበት ጠፍቶት የክረምቱ ዝናም በሚያደማው፣ ደሳሳው ጎጆ ከጎኑ በሰገገው የህንጻ ተራራ በተረሳበት አነዋወር ውስጥ የሚረሱና የሚዘነጉ ብዙአን በዓል አክባሪዎች ይኖራሉ፡፡ የበአል ዳቦዎትን ማን በልቶ ይጨርሰው ይሆን? የተጠመቀው ጠላስ ማን ያንጫልጠዋል? የተሰዋው እንስሳስ ለነማን ይተርፋል? የበአል ቀን ነውና በባህርይው ደስታና ፈንጠዝያ ወዘተ በዓልን ይከተለዋል፡፡ ለዋዜማው ሆነ ለበአሉ በየጭፈራና ዘፈን ዝግጅቶች ላይ ብንታደምም የሚከፋ አይደለም፡፡ እኔም የጠራዋችሁ ዝግጅት ይሄ የሚጎድለው አይደለም፡፡ በአንድ ጦማሬ ላይ የአዲስ አመት ውሎዬን ማጫወቴን አስታውሳለሁ (ለማንበብ ይሄን ይጫኑ)
በዋዜማው ‘P-square’ ይመጣሉ አሏችሁ? እኔ ደግሞ ‘ህሊና’ ለረፍት ሸክፎ ገብቷል እላችኋለሁ፡፡ እነ ‘P-square’ የዛሬ ናቸው ነገ ደግሞ ‘T-square’ ከነገ ወዲያ ሌላ እንዲሁ ዛሬ አብሯችሁ ሊያከብር የተዘጋጀው ‘ህሊና’ ግን ሁልጊዜ አብሯችሁ ይኖራል፡፡ እንደ ጉድ ይቀወጣል ትደሰታላችሁ ነው ያሏችሁ? እኔም እላችኋለሁ ደስታና እርካታ ትዝቃላችሁ እነኚህ ደስታና እርካታ ግን የማይጠፉና የማይሰክኑ ናቸው፡፡ ይልቁን በልባችሁ ውስጥ የሚበዙና የሚፈኩ ለሌላው የሚረጩ እንጂ፡፡
ከብዙ ቅወጣዎች (ጨዋታና ጭፈራዎች) በኋላ ድካም ይከተላል ከድካም መልስ ደግሞ ነገ ሌላ ጨዋታ ሌላ ጭፈራ ያስፈልጋል፡፡ ለነገ የሚሆን ዝራዥ አያስቀርልንም፡፡ ይህ ዝግጅት ግን ባለስንቅ ነው በአንዱ መስተንግዶ ለሌላ ጊዜ እየቆነጠሩ የሚቀምሱት ማዕድ ነው፡፡ በዓልን ከእኛ ጋር አሳልፉ የሚሉ ብዙ ድምጾች በዙሪያችን ከበውናል፡፡ እስቲ ጧሪ የሌላቸው አዛውንት ከሆኑ፣ አቅም አጥተው ልጆቻቸውን ማብላት ተስኗቸው ባዶቤት ተቆልፈው ከተኙት፣ የሚለብሱት አጥተው ተራቁተው ባዶ ግድጊዳ ከተከለሉት ከአንዳቸው፡ ብቻ ከእርስዎ ኑሮ ያነሰ መስሎ ከተሰማዎት ከአንዱ ደሳሳ ጎጆ ይግቡና በዓልን አብረው ያሳልፉ፡፡ ወይም አንዱን/አንዷን የእኔ ቢጤ መስለው ከወደቁት፣ ችግረኛ ሆነው ከተራቆቱት እቤትዎ ወስደው በዓልን አብረው ቢያከብሩስ? አቤት የሰዎቹ ደስታ የአዛውንቱ ምርቃት፣ ሰው የራበው ሰው ፍቅርና ስስት ልትገምቱት ከምትችሉት በላይ ይሆናል፡፡ የእናንተ ጉብኝት የሚፈጥርላችሁን ደስታ መዝገን ብቻ ነው፡፡ ለማያውቁት ሰው ደስታ መፈጠር ምክንያት ከመሆን በላይ ደስታ ይኖር ይሆን?
የብዙዎችን ችግር በአንድ ቀን አይቀርፉ ይሆናል ግን የአንድ እለት ሕይወታቸው የደስታ ምንጭ ይሁኑላቸው፡፡ ያለዎትን ያካፍሉ ይካፈሉ በዓልዎን ፈጽሞ አይዘነጉትም፡፡ በአሉም አዲስ ይሆናል ዘመኑስ አዲስም አይደል!! ደስ የሚሉበትና ደስ የሚሰኙበት ዘመን ለእርስዎ ይሁን!


የብዙዎችን ችግር በአንድ ቀን አይቀርፉ ይሆናል ግን የአንድ እለት ሕይወታቸው የደስታ ምንጭ ይሁኑላቸው፡፡