የዜግነት ክብር

የዜግነት  ክብር

all

መንደርደሪያ

ከአራትና አምስት ወራት በፊት ማስጠንቀቂያ ታውጆ እንደ ነበር ተሰማ-አሁን ላይ፡፡ ከህዝቡ ሃያ ከመቶ የሚሆኑት ወጣቶች (ሴቶቹን ሳይቆጥር) ሥራ አጥ መሆናቸውንና የሥራ አቅርቦቱን በአብዛኛው መጤዎቹ (የውጭ ዜጎች) እንደተቀራመቱት ማላከክ ሊፈጠሩበት ከሚችሉ የፖለቲካ ቀውስ የሚገላግለው ቀላል ዘዴ ነበር፡፡

ወደ 40% የሚተጋው ሥራ አጥ ወጣት በሰሜኑና በአረብ የቀሰቀሰውን የተቃውሞ አመጽ እዚህ የማስነሳት አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ስጋት ስለገባው የመንግስት ችግር  ሳይሆን የመጤው ህዝብ ሥራ ተቆራማችነትና የሃገር ባህል አበላሺነት እንደፈጠረው በየሚዲያው ሰበከ፡፡ አስተጋባ፡፡ በተለይ ‘እኚህ ኢትዮጵያውያን’ ተቀጸለበት፣ ህዝቡን አስነሳ፡፡

የሌሎች መጤ ህዝብ የየሃገራቸው መሪዎች መፍትሔ አፈላለጉ-ብዙዎችን ህጋዊ በማድረግ፡፡ ዞር ብሎ ከሚያይ፣ ከሚያሳስባቸውና ከሚያስብላቸው ይልቅ በሩን በርግዶ የሚያበር በየጓሮው በሚኮበልሉት እፎይታ እንጂ ጭንቀት ያልገባው ኢትዮጵያዊ መንግስት ግን በማልጎምጎም የማስጠንቀቂያ ጊዜያቱን ጨረሰ፡

ኢትዮጵያዊ መልክ የታለ?

የሳዑዲ መንግስት በየቤቱ እያንኳኳ ይበረብራል፡፡ ኢትዮጵያዊ መልኮች ተጎለጎሉ ተቀፈደዱ፡፡ በየቤቱ ከመታደን፣ ከመደፈር፣ ከሰቆቃና ከክብር መዋረድ ተሰብስበው ወጡ ይኸው እጃችን ሲሉ፡፡ በታወቀ መረጃ ከ3በላይ ኢትዮጵያውያን ሞቱ፡፡ የቆሰሉ ፣የተገረፉ፣ የታረዙ፣ የተጠሙና የተራቡትን ሳንቆጥር በሺዎች ናቸውና፡፡

ሰርተው የሸመቱትንና ቆጥበው ያዘጋጁትን ሀብት ንብረት ለመያዝ ጊዜው አልነበራቸውም፡፡ ብር ብለው እንደወጡ ብርር ብለው ሊመለሱ ተጋዙ፡፡

ይሄ ዜጋ የማነው?

በአለማት የተሰራጩት ኢትዮጵያውያን ተቆጡ በገኑ፡፡ በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝ… በየኢምባሲው በር ተሰለፉ፤ የሚያወግዝ አካል እስኪጠፋ ሃይ ባይ እስኪነሳ ድረስ፡፡ ለኢትዮጵያው መንግስት ወቀሳና ቁጭት ለሳዑዲው ቁጣና ንዴት ፡፡

የሃገር ውስጡ ግን እዛው ሳዑዲ ያለን ይመስላል፡፡ መንግስት ከዝምታው ከቀናት በኋላ ባንኖ ከዲፒሎማሲው ተጠጋ፡፡ ዐለም የዘገበውን  ሰቆቃ ኢቲቪ ለማሳየት ድፍረት አልነበረውም ይልቁኑ ከተመለሱቱ ’24 ሰዐት በሃገራቸው ሰርተው መለወጥ’ የሚፈልጉ እንዳሉ ፕሮፓጋንዳውን ነዛ እንጂ፡፡ ስለየትኛዋ ሃገር ሊነግረን እንደፈለገ ባይገባንም፡፡ ምን እየደረሰባቸው  እንዳለ ሳይሆን ጉንጩን ሲያለፋበት የከረመውን የስደታቸውን መዋዕል ሲዘግብልን ከረመ፡፡ በቀን እስከ ስድስት በሚሆን ጉዞ ህጋዊ ያልሆኑ የተባሉ ዜጎቹን ከተመድ ጋር በመሆን እያመላለሰ እንደሆነና እስከ 50 ሚሊየን እንደበጀተ ለፈፈ፡፡ እየደረሰባቸው ያለውን ስለማስቆም ወይም የደረሰባቸውን ሰቆቃ ማጥናትና አጥፊዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ስለማድረግም ሆነ ሃገሪቷ ስለፈጸመችው በደል ካሳ ወዘተ የኢትዮጵያ መንግስት የማሰቢያ ጊዜዬ አይደለም ብሎ ደምድሟል፡፡

Stop violence

ተቋውሞው ጠንክሮ በሳዑዲም ሆነ በመንግስት ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በየሃገሩ በዝቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ለተቃውሞ ቢወጡ ሌላ ሳዑዲ ወታደር ተላከባቸው፡፡ ተደበደቡ፣ ከእስር ቤት ታጎሩ፡፡ እንደ መንግስት ተመላሾቹን መቀበል እንጂ ሌላ ተቃውሞ ማስነሳት አልነበረባቸውምና ነው ነገሩ፡፡

ወደ ሃገራቸው የሚመለሱት ሁሉ ፈቅደውና ወደው ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ በሳዑዲም ጥገኝነት መጠየቅ ስለማይችሉ የማይመለሱትም ይመጣሉ፣ የሚመለሱትም ባዶዋቸውን መረጃዎቻቸው ሁሉ ተሰውሮባቸዋል፡፡ እንደ አንድ የተከበሩ ዜጋ ሳይሆን…. መድረሻ እንዳልነበራቸው ዘላኖች፡፡

ሥርወ መዘዝ

መንግስት በተደጋጋሚ በተወካዮቹ በኩል ሊነግረን የሚፈልገው የዚህ ሁሉ መዘዝ ድኅነታችን መሆኑንና እርሱ ላይ ለመረባረብ መነሳቱን ነው፡፡ ባለስልጣናቱም ከወትሮ በተለየ ርብርብ ላይ እንዳሉ ያዜሙልናል-ሲያሻቸው በስብሰባ ሲፈልጉ በመግለጫ፡፡ በቅርቡም ስለስደት ባቀረበው ምክረ ውሳኔ የስደቱ መነሻ አታላዮቹ ደላሎች መሆናቸውን ተናግሮ ሳይጨርስ ሰብስቦ ከርችሟቸዋል፡፡

ግን ይቺ ኢትዮጵያ ምን ያህል የሥራ እድል በየዐመቱ እየፈጠረች ይሆን? መንግስት ፈጠርኳቸው የሚላቸው የሥራ እድሎች (ጥቃቅንና አነስተኛ፣ ኮብልስቶን….) ምን ያህሉ ከወር ወር ቀጠሉ? ከዐመት ዐመት ዘለቁና አፈሩ፡፡ ሚሊየነር ገበሬዎችን መዳሊያ የሰጡት አቶ መለስ ነበሩ፡፡ ሌላው ገበሬ እስከ አሁን እጅጉን ደኸየ ወይስ ሀበተ??

በየዐመቱ እንደ መፈልፈያ ማሽን ያለ ብቃትና ጥራት በገፍ ለሚመርቃቸው ተማሪዎቹ ምን ያዘጋጀውን ሰጣቸው? (ድንጋይ መቀጥቀጡን ሳላነሳ ማለቴ ነው) ወደግል ንግዱ የተሰማሩት ባለሀብቶችና ኢንተርፕሪኒየሮች በመሠረታዊ ልማት እጥረት የተነሳ (የመብራቱ ጣጣ፣ የስልኩ መከራ፣ የውኃው እጦት፣ የመንገዱ ድንቃር….) ተሰቃይተው ከሥራ ወጡ ወይስ በረቱበትና የበለጠ አትራፊ ሆኑ? እርግጥ አጎብዳጅ፣ አድርባዮችና ሌቦቹን ሳናነሳ፡፡ ወጣቱ እውቀቱ ተመረጠ ወይስ ታማኝነቱ? ችሎታው በለጠ ወይስ ጎጠኝነቱ? ህልሙን አበረከተ ወይስ ራዕይ ተረከበ?

እረ! የገጠሩን ብዙሃን ትተን ጥቂቱን የከተማ ሰው’ኮ ብናየው ያልታሰረበት ገመድ የለም፡፡ ምርጫዎቹ ገመድ በጥሶ ከሃገር መውጣት አሊያም ያለ እስራት ባክኖ መቅረት የሆኑለት፡፡ መንግስት በሚያስተዳድራቸው መስሪያ ቤቶች ሁሉ ለውጥ በወረቀትና በመፈክር ብቻ የቀረው ሃገሪቷ የፈጠረችው ሕዝብ ሳይሆን ፓርቲ የወለደው ሰው ተመራጭ መሆኑ ነው፡፡ ለሃገሪቷ ሕዝብ መልካም አስተዳደር እጦቱ አሰቃየውና ሃገር ጥሎ ሸሸ እንጂ ድርጅት የወለደው ህዝቧማ ያማረ አስተዳደር ከዚህ ሌላ ምኑ?!

የተሰደዱቱ እኚህ የሃገሪቷ ህዝብ ናቸው፡፡ ሃገራቸውን መንግስት የወረሳቸውና ዘላን የሆኑቱ፡፡ የመሰደዳቸው ምንጭ የሃገር አስተሳሰብን በጠባብ (በደረቀ ራዕይ..) የፓርቲ አስተሳሰብ የቀየረ መንግስት መኖሩ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ የፈጠራቸው ደግሞ ከላይ ያየናቸው መዘዞችና ቁስለቶችን ነው፡፡ የዜግነት ክብር ያጡት በእነዚህ የተሰቃዩት ናቸው፡፡

እርግጥ ከመንግስት ጋር እዚህ ጋር መስማማት ይኖርብናል እነኚህ መዘዞች ድህነትን ተረት ሊያደርጉልን ቀርቶ ከድህነት መውጣትን ተረት እንዳደረጉብን!!!!

ኅዳር 12 ቀን 2006

አዲስ አበባ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑