የእድሜ ልክ መሪዎቻችን!
በሥልጣን ላይ ለብዙ ዓመታት የቀዩ ፕሬዝዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮችን በአፍሪካ ማግኘት ብርቅ አይደልም፡፡ ምንም እንኳ በቅርቡ ተገደው ከተጣበቋት ወንበር የተፈነገሉት ሦስት መሪዎች የሥልጣኑ ንጉስ ሙሐመድ ጋዳፊ (1969-2011) ለ42 ዐመታት ሊቢያን፣ ሁስኒ ሙባረክ (1981-2011) ለ30 ዐመታት ግብጽን ፣ ቤን አሊ (1987-2010) ለ23 ዐመታት ቱኒዚያን ከመሩ በኋላ ከወንበር እድሜ መሪነታቸው ቢቀየሩም፤ ተፈጥሮ የለያቸውን እንደ መለስ ዜናዊ (1991-2012) ለ21 ዐመታት ኢትዮጵያን የመሩትንም ሳንዘነጋ ብንፈልግ አሁንም አያሌ የወንበር ፍቅር ያቆማደራቸው ጥቡቅ መሪዎች በብዙ እናገኛለን፡፡
አፍሪካ ከቅኝ ገዢዎቿ እንድትላቀቅ በየሃገራቱ ጠመንጃ አንስተው ከወንበር ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ እንኳ ሌላ ቀኝ ገዢ ሆነውባት ለሦስትና አራት አስር ዐመታት እንደነገሱባት ታሪኳን የዳሰሰ የሚረዳው ይሆናል፡፡
- የቶጎው መሪ ጊናሲንግቤ ኢያዴማ (1967-2005) ለ38 ዐመታት
- የአይቬሪኮሰቱ ፌሊክስ ሆፌት ብሪግኒ (1960-1993) ለ33 ዐመታት
- የማላዊው ሃሰቲንግ ካሙቱ ባንዳ (1964-1994) ለ30 ዐመታት
- የጋምቢያው ሰር ዳውዳ ጃዋሬ (1964-1994) ለ32 ዐመታት
- የዛየሩ ሞቦቱ ሴሴኮ (1965-1997) ለ32 ዐመታት
- የኮሞሮሱ አልበርት ኬን (1977-2004) ለ27 ዐመታት
- የዛምቢያው ኬኒት ኩዋንዳ (1964-1991) ለ27 ዐመታት
- የቱኒዚያው ጁሊየስ ኒሬሬ (1962-1985) ለ23 ዐመታት
- የጂቡቲው ሃሰን ጉሌድ አብቲደን (1977-199) ለ22 ዐመታት
- የኢትዮጵያው መለስ ዜናዊ (1991-2012) ለ21 ዐመታት
- የሴንጋሉ ሊኦፒልድ ሴንጎር (1960-1980) ለ20 ዐመታት
- የካሜሮኑ አህማዱ አሂጆ (1960-1982) ለ22 ዐመታት
- የቤኒኑ ማቲው ኬረኩ (1972-1991) ለ19 ዐመታት
- የኬኒያው ዳንኤል ቲ. አራፕ ሞይ (1978-2002) ለ24 ዐመታት
የመሳሰሉት መሪዎች አንድም ሀገራቸውን ነጻ አውጥተው ሕዝቡን አስረኛ ያደረጉ አንድም ከነጻነት መልስ የነበሩ የሃገሩ ተወላጅ መሪዎችን በመሳሪያ ፈንቅለው ራሳቸውን የሾሙ የእድሜ ልክ መሪዎች ነበሩ፡፡ በየሥልጣን ዘመናቸውም ራሳቸውን የዲሞክራሲ አባትና የነጻ ሃገር ጠባቂ አድርገው የሚቆጥሩ ሲሆን ለዚህም ማደላደያ ”ምርጫ” በመሰየም ከህዝብ የተመረጡ መሆናቸውን በመናዘዝ ራሳቸውን ሹመው ኖረዋል፡፡ በንጉስ የሚተዳደሩ አፍሪካዊ ሃገራትን ሳናነሳ
- የቻዱ መሪ ኢድሪስ ዴቢይ (1990-አሁን) ለ23 ዐመታት
- የቡርኪናፋሶው ብሌይ ካምፓሬ (1981-አሁን) ለ32 ዐመታት
- የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ (1991-አሁን) ለ22 ዐመታት በአሁን ሰዓት ከወንበራቸው ተሹመዋል፡፡

50ኛ ዐመቱን እያከበረ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት (የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት) የኢዩቤልዩ ክብረ በዓል ወቅት የኡጋንዳው መሪ ዮዌሪ ሙሴቬኒ ‹‹ ወጣቶች ወጣቶች ትላላችሁ›› (ከስብሰባው ጎን አፍሪካውያን ወጣቶች ተሰብስበው ተወያይተው ነበር፡፡ የአፍሪካም አንደኛው ችግር ለወጣቶቿ ቦታ የማትሰጥ መሆኑ ተወስቶ ነበር) ያንን በማስመልከትም ነው ሙሴቪኒ አፍሪካ ወጣት አይደለም የምትፈልገው የጠነከረ ፖለቲካ እንጂ በማለት እንደሳቸው ያሉ መሪዎች የጠጠረ ፖለቲካ ስለገነቡ እድሜያቸው በወጣት ተተኪዎች ሊነጠቅ እንደማይገባ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ 
ዮዌሪ ሙሴቬኒ አራት ምርጫዎችን በማሸነፍ ከ1986 ጀምሮ ከወንበራቸው ተጣብቀው ለ 27 ዐመታት ኡጋንዳን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ መንግስታቸው በሙስና የሚመሯት ሃገር ለኑሮ ከፍተኛ ወጪ የምታስወጣ በመሆን ይታወቃሉ፡፡
ካሜሮን
ካሜሮን ነጻ እንደወጣች የመሯት የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት በሕመም ሲነሱ ጠ/ሚኒስተር የነበሩት ፖል ቢያ ከ1982 ዐ.ም ጀምሮ በመረከብ ለ31 ዐመታት በአደራ እያስተዳደሯት ይገኛሉ፡፡ የአደራ ሃገራቸውን ሲያስተዳድሩም
የመንግስታቸውን ፋይናንስ የሚያንቀሳቅሱት ልክ ለራሳቸው እንዳስቀመጡት petty cash fund ነው ይባላል፡፡ ለዚህም ማሳያ ከካሜሮን የአሜሪካ ኢምባሲ የወጣ መረጃ በ2008 የተመድ ስብሰባ ለመካፈል አሜሪካ በሄዱበት ወቅት የቅርብ ሰዎቻቸው ከሆኑት መሐል አንዱ በቦርሳው 3.4 ሚ. ሰዊስ ፍራንክ (ወደ 6.8 ሚ. ዶላር) ይዞ ከቢያ ጄኔቫ ሆቴል ሊያመልጥ ሲል መያዙ ተዘግቧል፡፡
ሙስና፣ የተቃዋሚዎች ውክቢያ፣ የምጣኔ ሀብት አስተዳደር ችግር፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወዘተ ዝምቧቤ ስትነሳና ከ1980 ጀምሮ ላለፉት 33 ዐመታት በላይ እየመሯት የሚገኙት የሮበርት ሙጋቤ መንግስት መገለጫዎች ናቸው፡፡ በ87 ዓመታቸው እንኳ ሥልጣንን ላለመልቀቅ ቃል የገቡት ሙጋቤ 60% የሚሰራው ያጣ ህዝብ መሪ ናቸው፡፡
የመሪዎቹ መሪዎች
በአፍሪካ የእድሜ ልክ መሪ በመሆን ከጋዳፊ ሥልጣንና አንደኝነቱን የተረከቡት የአንጎላው ጆሴ ኤድዋርዶ ዶ ሳንቶስ በቅጽል ስማቸው ‘ፍጹሙ አባገነን’ እና በወራት እድሜ የሚቀድሟቸው ከ1979 ጀምሮ ለ 34 ዓመታት ኢኳትሪል ጊኒን የሙጥኝ እየመሩ የሚገኙት ቴዎድሮ ኦቢያንግ ንጉማ ናቸው፡፡
ቴዎድሮ ኦቢያንግ ንጉማ በ2002 ምርጫ 97 ከመቶ ማሸነፋቸው የእኛኑ ሃገር የ99 በመቶ አሸናፊው ትዝታ አመጣብኝ፡፡ አወይ መመሳሰል አለ አስተዋዋቂ! 80%
ህጻናቶቿ ጥራት ላለው ትምህርትና ጤና ያልታደሉ ሲሆን 20% የሆኑት ህጻናት 5 ዐመት ሳይሞላቸው ይሞታሉ፡፡ ግና የሃገሪቷ ከሀብት የምታገኘው ገቢ ምጣኔ በዐለም ከፍትኛ የሚባለው ነው ይኸውም በከፍተኛ ደረጃ ከምታመርተው ነዳጅ ነው፡፡
የጆሴ ኤድዋርዶ ዶ ሳንቶስ አንጎላ እንደ የአሜሪካ አለማቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) መሰረት በዓለም 4ኛዋ ያልተጣራ አልማዝ አምራች አገር ስትሆን በነዳጅ ምርቷም ከሰሃራ በታች ካሉ ሃገራት ሁለተኛዋ ነች፡፡ ይህም ሆኖ ለ34 ዐመት የተጣበቋት ሀገር ከሕዝቧ 68 ከመቶው ከድኅነት ወለል በታች ሲኖር የቀን ገቢው 1.7 ዶላር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ባለሰ ደግሞ 28% ከ30 ሳንቲም (የአሜሪካ) በታች ገቢ የሚያገኙ ናቸው፡፡ እንደ ተባበሩት መንግስታት የሕጻናት ፈንድ መረጃ 30% የሃገሪቱ ህጻናት በተመጣጠነ ምግብ እጦት የሚሰቃዩ ናቸው፡፡ ዳሩ የፕሬዝዳንቱ ቤተሰብ ከአንጎላ ኢኮኖሚ ግዙፉን ድርሻ የያዙ ናቸው፡፡ ሴት ልጃቸው የሃገሪቱ የናጠጠች ሀብታም እንደሆነችው፡፡
ወርኃ ኅዳር 2006ዐ.ም
አዲስ አባባ
ዋቢ፡- የድረ ገጽ መረጃዎች በኅዳር 2013 እንደተጎበኘው

