የኛ ሠፈር ፍርድ

እኛ ሠፈር ነው፡፡ አንዲት ሴትዮ በእኩለ ሌሊት እሪታዋን አቀለጠቺው፡፡ እኛም እየተንጋጋን ከቤታችን ወጣን፡፡ ሠፈርተኛው፣ የአካባቢ ጸጥታ አስከባሪዎች፣ መንገደኛው፣ የቀበሌ ሹሙ፣ ውሾቹ እንኳን ሳይቀሩ የተጮኸበት ቤት ጋ ተሰበሰቡ፡፡ ጎረምሶቹ የቤቱን በር ሰብረው ሲገቡ ባሏ ሚስቱን ውኃ ውኃ በሚያሰኝ ዱላ ይደበድባል፡፡ ጎረምሶቹ ዱላውን ነጥቀው እርሷን ከቤት አወጧት፡፡ ልብሷ ተቀዳዷል፤ የተረፈውም በደም አበላ ተጠምቋል፡፡ ከጸጥታ አስከባሪዎች አንዱ ‹‹ለምን ይህንን ያህል በመጮኽ ሠፈሩን ጸጥታ ትነሻለሺ›› አላት ደም በደም የሆቺውን ሴትዮ፡፡ አልመለሰቺም፡፡ እርሷ ደሟን በልብሷ እየጠረገቺ ታለቅሳለቺ፡፡ እንኳን መልስ የምትሰጥበት በሕይወት የምትቆዪበት ዐቅም ያላት አትመስልም፡፡
‹‹ሁልጊዜ ኮ ነው የምትጮኸው፤ እኛ ሠፈሩን ሰላማዊና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ቀን ከሌት እንለፋለን፡፡ የኮብል ስቶን መንገድ አሠራን፣ የጥበቃ ቤት አሠራን፣ ዛፍ ተከልን፤ ትልልቅ ቢል ቦርዶችን ሰቀልን፣ ምን ዋጋ አለው፡፡ ይቺ ሴትዮ ሌሊት ሌሊት
የሠፈሩን ሰላም ትበጠብጠዋለቺ›› አለ የአካባቢው ሹም በምሬት፡፡
‹‹ለምንድን ነው ሠፈሩን እንዲህ የምታሸብሪው?›› አላት ጸጥታ አስከባሪው፡፡ ‹‹ ይልቅ እርሱን ‹ለምን ትደበድባታለህ›? ብላቺሁ አትጠይቁትም›› አለቺ ደሟን እየጠረገቺ፡፡
‹‹የችግሩን ምንጭ ትታችሁ የችግሩ ውጤት ላይ ለምን ታተኩራላችሁ፡፡ የጮኸቺው ስለተደበደበቺ ነው፡፡ መጠየቅ ያለበት ደብዳቢው እንጂ ስትደበደብ የጮኸቺው አይደለቺም› አለ አንድ ወጣት፡፡ ተሰብሳቢዎቹ ‹ዝም በል – ቀዥቀዣ › ብለው ተረባረቡበት፡፡
‹‹እኛን የረበሸን፣ ፀረ ሰላም የሆነብን፣ ሽብር የለቀቀብን እርሱ አንቺን መደብደቡ አይደለም፡፡ ያንቺ በሌሊት መጮኸ ነው፡፡ ‹አንተ ዐውቃለሁ ባዩ› አለው ወጣቱን ‹‹ለኛ ምን? የሚለው እንጂ ለምን? የሚለው ብዙም አያሳስበንም‹‹ አለ የጸጥታ አስከባሪው፡፡
‹‹ታድያ ስደበደብ መሳቅ ነው እንዴ ያለብኝ›› አለቺ ጥያቄው የደሟን መፍሰስ ሊያስረሳት ደርሶ፡፡
‹‹ብትደበደቢስ፤ ሠፈሩ እስኪሸበር መጮህን ምን አመጣው?›› አሉ አንድ ተረኛ ጥበቃ፡፡
‹‹መደብደብ ባንቺ ነው እንዴ የተጀመረው፡፡ በየቤቱ ስንቱ ይደበደባል፡፡ እንዳንቺ የሠፈሩን ሰላምና ጸጥታ የሚነሣ ሰው ግን የለም፡፡ ሁሉም ዕንባውን እያፈሰሰ ውጦ ዝም ይላል እንጂ እንዳንቺ አገር ይያዝልኝ ብሎ እሪ አይልም፡፡ እኛኮ በአንቺ ጩኸት ምክንያት ችግር ውስጥ እየገባን ነው፡፡ ሰማሽ! አሸባሪነት ትልቅና ትንሽ የለውም፡፡ እንዲህ ሠፈር ከማሸበር ተጀምሮ ነው በኋላ ሀገር ማሸበር የሚመጣው፡፡ ሠፈራቺንማ የአሸባሪዎች መናኸሪያ ሲሆን ዝም ብለን አናይም፡፡ ልጆቻችንስ ከዚህ አይደል እንዴ አሸባሪነትን ተምረው የሚያድጉት፡፡›› አሉ ጥበቃው፡፡
‹‹ጋሽ እርገጤ ልክ ናቸው፡፡›› አለ አቶ ለጥ ይበሉ፡፡ ‹‹አንደኛ የርሷ ጩኸት ሠፈሩን ሰላም አሳጥቶታል፡፡ ሰላም ደግሞ ለሠፈራችን ዕድገት ወሳኝ ነው፡፡ በሠፈራችን ይኼንን ሁሉ ዕድገት ያስመዘገብነው በአንጻራዊ መልክ ሠፈራችን ሰላም ስለነበረው ነው፡፡ አሁን ግን እንደ እርሷ ዓይነት ፀረ ሰላም ኃይሎች እየበጠበጡን ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ዕድገታችንን እያደናቀፈቺ ነው፡፡ ተመልከቱ ይኼ ሁሉ የመንደሩ ነዋሪ በእኩለ ሌሊት ዕንቅልፉን አጥቶ እዚህ ተሰብስቧል፡፡ የጸጥታ ሠራተኞች እዚህ ናቸው፡፤ ጥበቃዎች እዚህ ናቸው፤ የሀገር ሽማግሌዎች እዚህ ናቸው፡፡ እንደምታውቁት ነገ የውኃ መፍሰሻ ቦይ ለመሥራት ሠፈሩ ተቀጥሯል፡፡ እንደዚህ ዕንቅልፍ አጥተን እያደርን ነገ በጠዋት መነሣት አንቺልም፤ ብንነሣም ድካም ስለማይለቀን ቦዩን መሥራት አንችልም፡፡ ታድያ ዕድገታችን ተደናቀፈ ማለት አይደለም?›› እዚያ የተሰበሰቡት ሁሉ ‹ልክ ነው› ‹ልክ ነው› አሉ፡፡
‹‹ሦስተኛው›› አለና ቀጠለ ለጥ ይበሉ፡፡ ‹‹የዚህች ሴትዮ ጩኸት የሠፈራችንን የገጽታ ግንባታ እያበላሸው ነው›› ሲል ወሮ እንዳሉሽ ወገባቸውን ያዙና
‹‹ልክ ነው የገጥታ ግንባታው ነገር ሊታሰበብበት ይገባል፡፡ እኛ ወሸቅ ወሸቅ አድርገን ሰርቪስ ቤት የሠራነውኮ ተርፎን አይደለም፤ ከሌላ ሠፈር ተከራይ ለመሳብ ነው፡፡ አሁን የሠፈሩ የገጥታ ግንባታ ከተበላሸ ተከራይ አናገኝም፡፡ ብናገኝም በርካሽ ነው የሚከራዩን፡፡ ይኼው የገጥታ ግንባታቸው ያማረ ሠፈሮች አንድ ክፍል በሁለት ሺ ብር ያከራያሉ፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻ ይቺ ሴትዮ ናት፡፡ ገጥታችን ተበላሽቷል፡፡››
‹‹ልክ ነው›› አለ ወጣት ዘለሌ ‹‹ባለፈው ጊዜ ስንት ዘፈን አዘጋጅተን፤ መፈክር ሰቅለን፣ ቢል ቦርድ አሠርተን፣ ቀለም ቀብተን የገነባነውን የሰፈራችንን ገጽታ ይቺ መናጢ ሴትዮ አበላሸቺው››
‹‹እዚህ ላይ ልጨምርበት›› አሉ አንድ የትምህርት ባለሞያ፡፡ ‹‹ባለፈው ዓመት በያዝነው ዕቅድ ዘንድሮ የትምህርቱን ውጤታማነት ለማሻሻል ብዙ ጥረት ማድረጋችንን ታውቃላችሁ፡፡ ምንም እንኳን የወንበርና የጠረጲዛ፣ የላቦራቶሪ ዕቃዎችና የመብራት ችግር በትምህርት ቤቶች ላይ ቢገጥመንም ትምህርት ቤቶችን ግን ገንብተናል፡፡ ምንም መስተዳድሩ ይህንን ሁሉ ጥረት ቢያደርግ ልጆቻችን ግን የትምህርት ውጤታቸው ሊሻሻል አልቻለም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ልጆቹ ማታ ማታ ማጥናት አልቻሉም፡፡ ይቺ ሴትዮ በጮኸች ቁጥር ይረበሻሉ፡፡ የሠፈሩ መምህራን የትምህርት ዕቅድ ለማዘጋጀት አልቻሉም፡፡ ሥራቸው የእርሷን ጩኸት ማዳመጥና እየመጡ መገላገል ሆኗል፡፡›› የከበቡት ሁሉ ራሳቸውን በስምምነት ነቀነቁ፡፡
አንድ የቀበሌ ሹም ጠጋ አለና ‹‹ስትደበደቢ ሠፈር እስኪበጠበጥ ከምትጮኺ ለምንድን ነው ወደ ቀበሌው ፍርድ ሸንጎ በጠዋት የማትሄጂው›› አላት በቁጣ። ደሟን ከጉንጯ ላይ ጠረገቺና የንዴት ፈገግታ ፈገግ ብላ፣
‹‹የቀበሌው ፍርድ ሸንጎ ሰብሳቢ ባሌ አይደለም እንዴ፡፡ እንዴት ነው ለደብዳቢየ አቤት የምለው›› አለቺው፡፡ ይህንን ሁሉ ሲያዳምጥ የነበረው ባሏ በደስታ ቀና አለ፡፡ መግረፊያውን ቀምተውት የነበሩት ጎረምሶችም ይቅርታ ጠይቀው ሌላ አንድ መግረፊያ ጨምረው መለሱለት፡፡ ያ ሁሉ ሕዝብ ሲሰበሰብና በሩን ሰብሮ ሲገባ ‹ሚስትህን ለምን ደበደብክ? የሚስትህን ሰብአዊ መብት ነክተሃል፤ በአካል ላይ ጉዳት አድርሰሃል፤ ወደ ሕግ መውሰድ ሲገባህ ራስህ ከሳሽ ራስህ ዳኛ ሆነህ ወንጀል ሠርተሃል› ብለው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይወስዱኛል ብሎ ገምቶ ነበር፡፡ የሆነው ግን ተገላበጠለት፡፡ እርሱም ፍርሃቱን ገለበጠው፡፡ መግረፊያውን እያወዛወዘ፣
‹‹ተቸገርንኮ ጎበዝ፡፡ አሁን በዚህ ተመታሁ ብላ ይህንን ያህል መጮህ ነበረባት፡፡ ሠፈሩንስ ሰላም መንሣት ነበረባት፡፡ አሁን እኔ ስማታ ሠፈሩን እረብሻለሁ?››
‹‹ኧረ ፈጽሞ፤ እርስዎ ሲደባደቡ በጭራሽ ድምጽ አልተሰማም፤ በሰላማዊ መንገድ ነው የሚደባደቡት›› አሉት የከበቡት ሰዎች ‹‹እኔ ስጋረፍ ገጽታችንን አበላሽቻለሁ? ሥራ አስፈትቻለሁ?›› ሁሉም አለማድረጉን መሰከሩለት፡፡
‹‹እርሷም’ኮ ጸጥታ ሳትነሣ፣ ሽብር ሳትፈጥር፣ ዕድገት ሳታደናቅፍ፣ ገጽታ ሳታበላሽ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ልቅሶዋን ማልቀስ ትችል ነበር፡፡ ለማልቀስ ይህንን ያህል መጮህ ምንድን ነው?›› ሁለት ጎረቤቶች ቀረብ ብለው ትከሻውን እየነኩ አጽናኑት፡፡ በዚህ መካከል የከበበውን ሰው ገፋ ገፋ እያደረጉ አንዲት እናት ወደ መሐል ገቡ፡፡
‹‹የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ፤ የሟች ልጅ እያለ የገዳይን ልጅ ልቅሶ ደረሱት› አለ ያገሬ ሰው፡፡ የተጎዳቺዉ እያለቺ ምን እርሱን አይዞህ ትሉታላችሁ፡፡ ይልቅ እርሱን ወደ ሕግ፣ እርሷንም ወደ ሐኪም ቤት እንውሰዳት›› አሉ፡፡ የተሰበሰቡት ሰዎች ገላመጧቸው፡፡
‹‹ካልሆነ እኔ ወደ ሐኪም ቤት እወስዳታለሁ›› ብለው ሊወጡ ሲሉ ቀበሌው ሹም ያዝ አደረጋቸው፡፡
‹‹እማማ አሁን አይወስዷትም›› አላቸው፡፡
‹‹ለምን?›› አሉ እኒያ እናት
‹‹የቀበሌው ጋዜጠኞች እየመጡ ነው››
‹‹ለምን?›› አሉ ሴትዮዋ
‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ በቀበሌያችን ቴሌቭዥን የሚቀርብ ዶክመንተሪ እንሠራለን›› የኛ ሠፈር ፍርድ
source: satenaw
Posted from WordPress for Android
Leave a comment