ጀግና ያጡ ጀግኖች

      Click to read in pdf

ጀግና ያጡ ጀግኖች

በአንድ ወቅት የድሬዳዋ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት ብጹእ አቡነ ቀውስጦስ ይሄን ተናግረው ነበር “ሰው ሌላውን ሲያሸንፍ ጀግና ይላል፤ ራሱን ሲያሸንፍ ደግሞ የጀግኖች ጀግና ይባላል” የዚህ ዘመን ትግል ራስን ማሸነፍ እንደሆነ አጽንኦት ለመስጠት፡፡

አንዱ ሌላውን በእውቀትም ሆነ በትግል፣ በጥበብም ሆነ ሞኝነት፣ በእብደትም ሆነ የዋህነት፣ በሕይወትም ሆነ በሞት ሲያሸንፈው አሸናፊ ይባላል፡፡ አሸናፊ ሁሉ ደግሞ ላሸነፈበት ጀግና ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ራሱን ታግሎ በጥበብ አንጾ፣ በእውቀት ቀርጾ፣ በልምዶቹ ታግዞና ፈጣሪውን በመፍራት ተሞልቶ በሰብአዊ ሕይወቱ ላይ አንዳች ለውጥ፣ ጽናት፣ ብርታትና አርያነት ሲያሳይ ጀግና መባል ያንስበታል፡፡ የጀግኖች ጀግና ይባላል፡፡ ስለዚህ ሰው ሁሉ ለጀግንነት ነው በሕይወት የሚቆየው ማለት ነው፡፡ በዚህ የህይወት ቆይታው ለሚገጥሙት ማናቸውም ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች መሰላል፣ጽናትና ጥንካሬ የሚሆነው አርአያ ሰብእ ያስፈልገዋል፡፡ ይሄ አርአያው እርሱ ሊያልፍበት ያለውን ያለፈ እንቅፋቱን ነቅሎ የተሻገረ ተግዳሮቶች ያላንበረከኩት ምሳሌያዊ ጀግና ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይሄኔም የበለጠ ብርታት ይሞላዋል፡፡ የበለጠ ጽናት ይሰማዋል፡፡

ጀግና ከሌላው ሰብእ ከፍ ያለና የተለየ መገለጫ ያለው ጽናቱ የተመሰከረና የተገለጠ፤ ጥንካሬው የተፈተሸና የተረጋገጠ ልዩ ሰው ማለት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በበዙ ቁጥር ሌሎች እነሱን ተከታይ ውብና ውድ ትውልዶች ይበዛሉ፡፡ እኚህ ጀግኖች ባነሱ ቁጥር ወይም ባልታወቁ ቁጥር ደግሞ የመከነ ትውልድ ይበዛል፡፡ ባለበት የሚድህ ተስፋ የጠፋው ራዕይ የራቀው ቅዠት እንጂ ህልም የነጠበው ባጠቃላይ በሕይወቱ አነዋወርና ልማዱ መሐል የተሻለ ወይም የተለየ ነገር የማይፈጥር “ቢረግጡት እንቦጭ…” ዓይነት ይሆናል፡፡

ለጀግና መብቀል የቀደመ ጀግና አርአያነት ያስፈልጋል—የህልም ዓርማ ይሆናልና፡፡ እስቲ የእኛ ትውልድ ማንን ይከተላል ብለን እንጠይቅ? ጀግና ቤተሰብ የሚለው ማንን ነው? ጀግና የሚለው መሪስ? ጀግና ሊባሉ የሚገባቸው የሃይማኖት አባቶችስ? ጀግና ጥበበኛ ጀግና ተመራማሪ? ጀግና ተዋጊ..? ወዘተ ሁሉም የሙያ መስክ የየራሱ ጀግና ያስፈልገዋል፤ይኖረዋልም፡፡ መሪ አንድ ሲሆን ተመሪ ብዙ ነው፡፡ ሀሳብ አፍላቂ አንድ ሲሆን ሰሪው ግን ብዙ ነው፡፡ አለቃ ጥቂት ሲሆን ምንዝር ግን የትየለሌ ነው፡፡ ጀግኖች ጥቂት ናቸው— ሲንከባከቧቸውና ሲያከብሯቸው የሚበዙ፡፡

ጀግንነትን ቤተሰብና ግለሰብ ድረስ አውርጄ ለማየት የፈለኩት የጀግንነት ዋጋውን ለመረዳት ካስቻለን በማለት ነው፡፡ በአቅራቢያችንና  በአጠገባችን ያሉ አርአያና ምሳሌ ሊሆኑን የሚችሉ ኮኮቦቻችንን መንከባከብና መጠበቅ ማክበርና ማፍቀር ከቻልን ለትውልድና ለሀገር የሚተርፉ ጀግኖችን ማፍራት አይከብደንም፡፡ ከህጻናት አፍ የጀግኖችን ውዳሴ መስማት ከቻልን፤ ከጎረምሶቹም የአክብሮትና የተምሳሌትነት ናፍቆት ዝማሬ መስማት አይዳግተንም፡፡ ጎልማሳዎችም ተተኪ/አዳዲስ ጀግኖችን ስለማወጅ አይጨነቁም፡፡ በፍቅርና በጥባቆት ሌላኛውን ውድና ውብ ጀግና ለሐገር ያስተዋውቃሉ፣ ያስረዳሉ ይንከባከባሉ፡፡ አዛውንቱም በክብር ያርፋሉ፡፡ “ይህቺን ሃገር ጀግና አታሳጣት” የሚል ጸሎታቸውም የእረፍተ ዘመናቸው መገታት አያቆመውም፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለዓለም የተረፉ ጀግኖች ነበሯት፤ አሏት፤ ይኖራሉም፡፡ የኑሮ ልምዳችን ግን የመቃብር ላይ ዜና ገድል አንብቦ ከመርሳት በቀር አክብሮ የማስከበር ባህሉን አላዳበርንም፡፡ ለትውልድ ሊተላለፍ ቀርቶ ያለበትም ትውልድ በቅጡና በተገቢው አያውቃቸውም፡፡ ስለማያውቃቸው አያከብራቸውም፡፡ አይጠራቸውም አያገናቸውም ይሄ የማይጠግ ስብራት ነው፡፡ እንዴት ጀግናውን የማያውቅ ጀግና ነኝ ጀግና አለኝ ማለት ይቻለዋል? መገለጫዎቹን ያላወቀ እንዴት ስለጀግንነት ሊያወራ ይችላል? ለዓለም ጠቃሚ ግኝት ያበረከቱ ተማራማሪዎች ኢትዮጵያ አፍርታለች ግን የት ነው ያሉት ማነው የሚያውቃቸው? የለውጥ ሐዋሪያ የሆኑ በዓለም ዙሪያ የተሰማሩ ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን መሪዎች አሉ ማነው ጠንቅቀን እንድንረዳቸው የረዳን? የጥበብ ቃላቸውና ሥራዎቻቸው አንቱ ሊቅ/ሎሬት ያሰኛቸው ኢትዮጵያዊያን አሉን ግን እነሱ ለእኛ ምናችን ናቸው? ለእነርሱ ያለን ክብር ወዴት ነው? በእውነት ጀግናዎቹን ያጠፉትና እንዳናውቃቸው ያዳፈኑትን በስብራት ያቆሙንን ልንጠይቃቸው ይገባናል፡፡ እናንተ ለምን ስብራታችንን መጠገን አልተቻላችሁም? ብለን፡፡ እናንተ የሁሉ ነገር አዋቂያችን ናችሁን? ብለን ቢያንስ የጎደላችሁን እንዲሞሉ ልታስተዋውቁንና ልታወዳጁን ይገባ ነበር ብለን ልንጠይቃቸው ይገባናል፡፡

የተረቶቻችን ጀግኖች እንኳ ወዴት ደረሱ? በህጻናት ት/ት ቤቶቻችን ውስጥ በተረት (በቃለ ትውፊት) የተማርናቸው ጀግኖቻችን አሁን በሌሎች ጀግኖች ተቀይረዋል፡፡ ባዕድ ቋንቋ አንግበው መጤ ባህል ለብሰዋል፡፡ የህጻናት ተሰብስቦ ተረት የማውራት ባህሉ ሳይቀር ተቀይሯል፡፡ ኢትዮጵያዊ ተረት የሚያወራው ህጻን ማነው? ለህጻናት ስለጀግንነትና ጀግኖቻችን ማስተዋወቂያ አንዱ መንገዳችን ነው—ተረት፡፡ በለጋ እድሜ እንዲስሏቸውና ሲያድጉ ይበልጡን ስለእነሱ እንዲያውቁ የሚያበረታታ አንዱ መንገድ ነው፡፡

ኪነጥበቦቻችን ሌላው ጀግኖችን ማስተዋወቂያና ማክበሪያ መንገዶች ናቸው፡፡ በፊልሞቻችን የቀደሙትንም ሆነ አሁን ያሉትን ጀግኖች ፈልፍሎ በማውጣት ማስተዋወቅ ይገባል፡፡ ይሄ ማለት ግን ስለ ግለሰብ ብቻ(ግለ ታሪክ) ፊልም ይሰራ ማለቴ አይደለም፡፡ በፊልሞቻችን ውስጥ በምንቀርጻቸው ገጸ-ባህሪያት፣ ቃለ-ተውኔቶች፣ አልባሳትን ምሳሌዎቻችን ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን የሚያከብር የሚያበረታታና የሚያስተዋውቅ መሆን ይችላል፡፡ በተቀበረው ባህልና ታሪክ ውስጥ ብዙ የተቀበሩ ጀግኖች ሞልተዋል፡፡

ብዙዎች አሜሪካን የረገጡ የሚናገሩት ነው፡፡ በሆሊውድ ያለችው አሜሪካ ከሆሊውድ ውጭ ካለችው ጋር ብዙ ልዩነት እንዳላት፡፡ አሜሪካኖች በሚሰሩት ፊልሞቻቸው ሁሉ አሜሪካዊ ጀግንነት ሲያንጸባርቁ አነዋወሩንና ሕይወቱን እስኪያዛባ ድረስ ነው፡፡ አሜሪካዊ ጀግንነት በእያንዳንዱ ዜጋ የሚገለጽ ነው፡፡ ለሃገሩ ያለው ፍቅር አሜሪካዊ በመሆኑ ብቻ የሚፈጽማቸው ጀብዱዎች፣ አይበገሬነት፣ ርህራሄና ፍቅር አሜሪካዊ ባልሆነው ሰው ሁሉ ውስጥ ተጽፎና ተስሎ እንዲቀመጥ ያደርጋል፡፡

ሙዚቃችንና መጽሐፋችን ሁሉ ጀግኖቻችንን በማስተዋወቅ በማስተላለፍና በመጠበቅ በኩል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ ሙዚቃዎቻችን እስካሁን የሚያነሱት በአብዛኛው የጦር ሜዳ ጀግኖቻችንን ቢሆንም እነኃይሌና ደራርቱም በጊዜያቸው ተዘፍኖላቸዋል፡፡ ዳሩ ግን በሌላውም መስክ እንዲሁ ጀግኖች ይኖራሉ ያልተቀነቀላቸው፡፡ የሞያው ባለቤቶች በማስተዋወቅ ሊያግዙን ይገባቸዋል፡፡ ያወቅናቸውንም ሊያከብሩልን እንዲሁ፡፡ የህትመትና የድምጽ ሚዲያዎቻችንም ሌሎች ኃላፊነት ያለባቸው ክፍሎች ናቸው፡፡ በጋዜጣና መጽሔት ላይ አዲስ ዓመት ሊጠባ ሲል የዓመቱ ሰዎች (ታዋቂ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ..) እያሉ ከማውጣት በዘለለ በየእትሞቻቸው ላይ ኢትዮጵያን ያስጠሩ ያኮሩና ያስከበሩ ጀግኖች የሚተዋወቁበትና የሚከብሩበት ዓምድ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡

ሌላውና ዋናው በተለይ እየተራመደ የሚያራምድ እየሰራ የሚያሰራ መንግስት ያለበት ኃላፊነት ነው፡፡ ህብረተሰቡ ውስጥ ጀግኖችን የማክበር ንቃተ ህሊናን የማንቃትና ማዳበርም የእርሱ ኃላፊነት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ችግሩ ይህቺን ሃገር እናስተዳድራለን የሚሉ አባወራዎች እራሳቸውን እንደሁሉ ነገር ምንጭ አዳይና ነሺ አድርገው ስለሚቆጥሩና ስለሚስሉ ነው፡፡ ለሌላው ክብርና ቦታ ይነፍጋሉ፡፡ የአፍሪካ አባት እያለ ዓለም የሚያከብራቸው አጼ ኃ/ሥላሴ በወጣቱ ትውልድ ውስጥ በጎነታቸውና ጀግንነታቸውን ከማስረጽና ከማስጠበቅ ይልቅ እዚህ ዘመን ድረስ ጉድለትና ክፋታቸውን ለማስተማር ይተጋሉ፡፡ ጀግና ማለት ግን ሰብአዊ ሕይወቱ ሁሉ ስሙር ሁሉ ፍጹም ማለት አይደለም፡፡ በየትኛውም ዓለም ያሉ ጀግኖች ሕይወታቸው በሙሉ በጀግንነት የተሞላ እንከን የማይወጣለት እንዳልሆነ ታሪካቸው ያስረዳናል፡፡ ግን ለሐገርና ለህዝብ ስላደረጉት ጀግንነታቸው ብቻ ሲባል ይከብራሉ ይገናሉ፡፡ በደርግ ዘመን ለለውጥ፣ ለሐገር ጥቅም ሲሉ ራሳቸውን መስዋት ያደረጉ ብዙ ናቸው፡፡ እንዲሁም ለህዝብና ለዓለም የሚጠቅም ሥራ የሰሩም ነበሩ፡፡ ግን ማን ያስታውሳቸው ማን ያንሳቸው? መንግስት ራሱን እንደጀግንነት ምንጭ እየቆጠረ ያዜምልን እንጂ፡፡

የጀግንነት መለኪያው ርዕዮተ ዓለም (የፖለቲካ አስተሳሰብ)፣ ወገንተኝነት፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት አይደለም፡፡ የሀገርና የህዝብ ጥቅም እንጂ፡፡ ህዝብ የሚያከብራቸውና የሚወዳቸው ጀግኖች መኖር’ኮ ለራሱ ለመንግስትም ትልቅ ጥቅም ነው፡፡ ቢያንስ ህዝቡ የሚሰማው ሰው አለው፡፡ ችግሩ ግን እርሱ የሚያወድሳቸውና የሚያከብራቸው ጀግኖች እንዲነቅፉት አይሻም፡፡ ሐገሪቷም የህልም ጀግኖች አፍቃሪ ሆና ትዘልቃለች፡፡ እኚያ ጀግኖች ደግሞ ገጽና ግበረ አካል የሌላቸው በመሆኑ ብዙው የሚተኛ እንጂ የሚነቃ አይሆንም፡፡ ይኸው እስካሁን ተኝተን የሕይወት ጸሐይ ብቅ አልል ብላናለች፡፡ ስለዚህ በብሔራዊ ደረጃ ጀግኖች እንዲወደሱ፣ እንዲተዋወቁና እንዲከበሩ ሊደረግ ይገባል፡፡ እውቅና ከሽልማት በላይ ነው፡፡ ዜጋ እስከሆኑ ድርስ መንግስት ሊያፍርባቸው አይገባም፡፡ በተቋም ደረጃ ጀግኖችን አስተዋዋቂና አክባሪ ክፍል ተዘጋጅቶ በሰፊውና በተጠና መልኩ ሊሰራበት ይገባል፡፡ መንግስት እንዲመጣለት የሚፈልገው የገጽታ መቀየርም አንዱ ማገዣው ገጽታ መገንቢያ መንገድ ነው፡፡ የራሱን ተቋማትንም ጀግኖችን የሚያበረታቱበት ሥርዓት ቢበጅላቸው ይጠቅማል፡፡ ህዝቡም በሥርዓቱ ውስጥ ሲሳተፉ ጀግኖች ያብባሉ፡፡

እኚህ የምናከብራቸው ጀግኖች ኢትዮጵያዊነትን ያስለከበሩ በመሆኑ እነሱን ማክበር ኢትዮጵያዊነትን ማክበር ነው፡፡ ይሄም ጀግኖች ያጡ ጀግኖች አድርገን ራሳችንን ከመቅረጽ ያድነናል፡፡

አርአያ ፍለጋ ዘመን ለኳተረ

ከእንቅቡ በላይ ፋኖሱን ላኖረ

ምስጋና ይብዛለት ትውልድ ላሰለፈ

እርሱም ሻማ ሆኗል ፋኖስ የታቀፈ፡፡

ነሐሴ ፲፬/፳፻፬ ዓ.ም

አዲስ አበባ

2 thoughts on “ጀግና ያጡ ጀግኖች

Add yours

  1. አርአያ ፍለጋ ዘመን ለኳተረ
    ከእንቅቡ በላይ ፋኖሱን ላኖረ
    ምስጋና ይብዛለት ትውልድ ላሰለፈ
    እርሱም ሻማ ሆኗል ፋኖስ የታቀፈ፡፡

  2. ለጀግና መብቀል የቀደመ ጀግና አርአያነት ያስፈልጋል—የህልም ዓርማ ይሆናልና፡፡ እስቲ የእኛ ትውልድ ማንን ይከተላል ብለን እንጠይቅ? ጀግና ቤተሰብ የሚለው ማንን ነው? ጀግና የሚለው መሪስ? ጀግና ሊባሉ የሚገባቸው የሃይማኖት አባቶችስ? ጀግና ጥበበኛ ጀግና ተመራማሪ? ጀግና ተዋጊ..? ወዘተ ሁሉም የሙያ መስክ የየራሱ ጀግና ያስፈልገዋል፤ይኖረዋልም፡፡ መሪ አንድ ሲሆን ተመሪ ብዙ ነው፡፡ ሀሳብ አፍላቂ አንድ ሲሆን ሰሪው ግን ብዙ ነው፡፡ አለቃ ጥቂት ሲሆን ምንዝር ግን የትየለሌ ነው፡፡ ጀግኖች ጥቂት ናቸው— ሲንከባከቧቸውና ሲያከብሯቸው የሚበዙ፡፡

Leave a reply to Anonymous Cancel reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑