የእድገት ጣጣው

የእድገት ጣጣው

  • አብዮታዊ እድገት Vs አብዮታዊ ልማት

የየትኛው ዘመን አዝማሪ እንደነበረ ባይታወቅም እንዲህ ብሎ ገጥሞ ነበረ

እኛስ መስሎን ነበር

        እድገት ቀውላሎ

በየቤቱ ‘ሚያስር

      ከሜዳ አውሎ

ለካንስ ካሮት ነበረ

        ሲያድግ ወደኋላ

‘ሚ’በላ አሳ’ቶም

          የሚጥል አውላላ፡፡

ሃገራችን ከሩጫዋና ከትግያዋ ጎን የቀራት አንድ መፈክር ያለ ይመስለኛል፡፡ ደሞ መፈክር የዘራችን አይደለምን፡፡ የቀደመውን ትተን’ኳ ከ 21 ዓመት በላይ የተዘራንበት ነው፡፡ እንደው ወደ ሃገሯ በእግሩ ለሚገባ በየመሽሎኪያ ጫካና ጢሻ ውስጥ በመኪና ገስግሶ ለሚጎበኛት መኪናው ደህና መጥቻለሁ ብሎ የሚያሰማበት አካባቢ፤ በአየር ተንሳፎ ለሚዘንብላት ደግሞ ቢቻል ከህንጻዎቿ በላይ ህዋው ላይ ካልተቻለ ደግሞ የሃገሪቷ እግር ረግጠው አየሯን የሚስቡበት ቦታ ላይ

“እንኳን ወደ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሃገሮች ተርታ ከምትጓዘው ሃገር በደህና መጡ!”

“በየመንገዱ መካከለኛ ገቢ ያለው ነዋሪ እየበዛ የሚያዩባት ሃገር ይህቺው!” ተብሎ ቢሰቀል

እንዴ ወደውንና ናፍቀውንም አይደል ከሌሎች ሃገራት አስበልጠው እኛን ሊጎበኙ መምጣታቸው (መቼም ሌላን ሃገር ሊጎበኝ ወጥቶ ቶሎ የሚመለስ የነዋሪዋ ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለምና)፡፡ ለዚህ ውለታቸው ደግሞ

“እርስዎም የመካከለኛ ገቢነት ትግሉን ይቀላቀሉ!”

“በአቋራጭ እየተለወጠች ባለች ሃገር ላይ በቶሎ እንለውጥዎታለን”

ተብሎ ቢፎከርላቸው ይገባቸዋል፡፡ ደግሞ አያቅተንማ፡፡

IMG_3430

የቀድሞ መጓጓዣ/ አውቶቡስ

መንግስት በገንዘብና ምጣኔ ሀብት ልማት ሚኒስቴር በ2003 ባወጣው የ5ዓመት የእድገትና ልውጥ እቅድ እስከ 2007 ሊፈጽማቸው የዘረዘራቸው 16 ማዕቀፎች /Sectors/ ነበሩት፡፡ በኢኮኖሚና ድኅነት ቅነሳ ማዕቀፉ የሚሊንየሙን የዕድገት ግብ (በግማሽ የሃገሪቷን ነዋሪ ከድኅነት ወለል በላይ ማድረግ የሚለውን) ለማሳካት በሚል በ 2002 ከድኅነት ጠለል በታች የነበረ ህዝብ ለአጠቃላይ ነዋሪው ሲካፈል 0.292% የነበረውን (ወይም የነዋሪው 29 ከመቶ ደኃ የነበረውን) አማካይ መነሻ በየዓመቱ በሚደረግ ቅነሣ በያዝነው ዓመት ወደ 0.234% (የነዋሪውን 23 እጅ ከመቶ ብቻ ያጣ የነጣ ድሃ በማድረስ) ለመቀነስና አንድ ሰው በየቀኑ ሊመገብ ከሚገባው በታች የሆኑትን 28% ምግብ የማይቀምሱ ደሃዎችን እስከ እዚህ ዓመት የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ ወደ 24% ለመቀነስ አቅዶ ነበር፡፡

 

የአዲስ አበባ ነዋሪ ታክሲ በመጠበቅ የሚያጠፋውን 45 ደቂቃ (እንደ መንግስት ጥናት) በዚህ ዓመት 23 ደቂቃ ብቻ ጠብቆ መጓጓዣ እንዲያገኝ ለማድረግና ቆመው ከሚጠብቁት መኪና አግኝተው መጓዝ የሚችሉ ተሳፋሪዎችን ቁጥር በ513 ሺህ ለመጨመር ማቀዱንም ሰነዱ ያስረዳል፡፡ እንዲሁም በቤት እጦትና በኪራይ ውድነት የሚማቅቀውን የአዲስ አበባ ነዋሪ እስከ 2002 ዓ.ም 53 ሺህ ገደማ ቤት የሰጠሁት ሲሆን በየዓመቱ 30 ሺህ የቅናሽ ቤቶችን ሰርቼ አስረክበዋለሁ ብሎ አቅዶ ነበር፡፡

 

ሌሎችን ትተን በየመስሪያ ቤቱ (የመንግስት) ስንሄድ የሚያስተናግዱንን የላዕላይ (Top managements) ና ማዕከላዊ (Middle mgt) አስተዳዳሪዎችን ከነበሩበት የ50% የአገልግሎት አቅም ሙሉ በሚሉ ተቀናጅተው እንዲያገለግሉንና እንዲያስተዳድሩን በዚህ ዓመት በ100% ውጤታማና የተቀላጠፉ እንዲሆኑ አደርጋለሁም ብሎ ነበር፡፡

 

ከላይ ያሉትን የመንግስት እቅዶች በግርድፉ ያነሣዋቸው ምን ያህል ተሰሩ በሚለው ጉዳይ ላይ ለማውጋት አይደለም፡፡ እድገታችን እንደአዝማሪው ወደላይ እንደታቀደ ለማሳየትና  የእድገታችን ጣጣ ምን አመጣብን ለማለት እንጂ፡፡ ሃገሪቷ አሁን በሚያስፈልጓት አፋጣኝ ጉዳዮች ላይ የተሻለና ቀጣይ የሚሆን መፍትሄ እያመጣ ባይሆንም’ኳ የ5 ዓመቱ እቅድ በሙሉ ተፈጻሚ ቢሆን የእድገት ጉዞ ለመጀመራችን ጥሩ ማሳያ አድርጎ ለማቅረብ የተመቸ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ዘግይተናልና፡፡

 

የህዝቡ የቤት እጦት ብዛትና ሊሰራ የታቀደው በየዓመቱ የሚጨምረውን ፍላጎት ሳይጨምር ከ10 ዓመት በላይ ይፈጅበታል፡፡ እየተሰሩ የሚረከቡ ቤቶች ቢሆኑ እንኳ ለታሰበላቸው ችግረኛ ነዋሪዎች አይደርሱም ወይም አያማክላቸውም፡፡ በአሁን ሰዓት መካከለኛ ገቢ አለው የሚባል ሰው እየጠፋ በድህነትና በሐብት አጽናፍ ብቻ እየተከፈለ ይገኛል፡፡ መካከለኛ ናቸው ተብሎ የሚሰራላቸው መኖሪያ ለዚያውም በቅናሽ ሊገዙት የማይቻላቸው ነው (በህጋዊ መንገድ ለሚጓዙት ማለቴ ነው) 40/60 ተብሎ የመጣ የቁጠባ እቅድን ብናይ በትንሹ አንድ ሰው ከ800 ብር ያላነሰ በየወሩ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ መካከለኛ የሚባሉት ደመዎዝተኞች የኪራይ የትራንስፖርትና ሎሎች የፍጆታ ወጪዎችን ለመሸፈን’ኳ ከማይበቃ ገቢያቸው ተርፎ ለመቆጠብ ይችላሉ ብሎ ማሰብ እጅግ ይከብዳል፡፡ ስለዚህ እንደቀደመው ላላቸው መጠቀሚያ ይሆናሉ፡፡ ይህ እንግዲህ የእድገታችን ሸክም መሆኑ ነው፡፡

 

የእድገት ጡዘቱና ሩጫው የፈጠረው የዋጋዎች መናር በተለይ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች ጭማሬም ሆነ የመገበያያ ብር ዋጋ መውረድ በማደግ ህልማችን ውስጥ የተሸከምነው እዳ ነው፡፡ በተለይ ወርተኛ ሸማች የሆነ ሰራተኛ በየጊዜው ለሚጨምሩ ዋጋዎች ዋነኛ ተጠቂ በመሆኑ በምግብ ራስን መቻሉም ሆነ ከድህነት ወለል ከፍ ማለት አቅቶት እንደመሬት ስበት ወደታች ይጎትተዋል፡፡ መንግስት ቆንጥሮ ከሚያወጣቸው/ከሚያሻሽላቸው የዘቀጠ ድህነት የሞላቸው ነዋሪዎች የበዙ በየጊዜው ከወለሉ በታች ይቀላቀላሉ፡፡ ከሚወጣው ቁጥር በላይ ይበዛሉ፡፡

 

IMG_3428

 

 

 

የዘንድሮ ታክሲ

­

ያኔ ለእድገት ከመጣደፋችን በፊት ምንም ያህል ሰዓት ብንቆይ ተሰልፈን አውቶብስ እንጠብቅ ነበር-እነ ሃይገሮች መጥተው እስኪያግዟቸው ድረስ፡፡ ሃይገሮች እየተሻሙ ሲያመላልሱን እንዳልከረሙ እነሆ አሁን ደግሞ ልፍጠንና ላውጣ ያለ ባለታክሲ ተጠቃሚ በሰልፍ ከአውቶብሱ ተቀላቅሏል፡፡ እህ የማደጋችን ምልክትም አይደል! እንግዲህ ሃገራት ሁሉ ሲያድጉ በእንደዚህ ዓይነት የእድገት ጣጣዎች ተገርፈው ይሆናሉ ብሎ ማሰቡ ደግ ነገር ሳይሆን አይቀርም- የተሻለ መፍትሔና አማራጭ ፖሊሲ እስኪመጣ ድረስ፡፡

 

እድገታችን አብዮታዊ ጠበል እየተረጨ ስለሚንቀሳቀስ በፉከራና ሽለላ ቢታጀብ አይከፋም፡፡ የአብዮታዊ እድገት ጸባይ መሆኑ ተነግሮን የለ! ልማታዊ ድህነትን ግን ሳይነግሩን የረሱት ታሪክ ይመስለኛል፡፡ እያደጉ መራብ፣ እየሀበቱ መደህየት፡፡ ምናልባት እያየነው እንድንረዳው ሳይሆን አይቀርም አብዮታዊ ልማት የፈጠሩልንና ጆሮአችን የደነቆረው፡፡ ዳሩ ምን አስደነቃችሁ የእድገት ጣጣው እንዲህ ነው አትሉም! ሲዳሩ እንደማልቀስ……

ጥቅምት ፳፰/፳፻፭ ዓ.ም

                                                                   አዲስ አበባ

እቤት

2 thoughts on “የእድገት ጣጣው

Add yours

  1. እያደጉ መራብ፣ እየሀበቱ መደህየት፡፡ ምናልባት እያየነው እንድንረዳው ሳይሆን አይቀርም አብዮታዊ ልማት የፈጠሩልንና ጆሮአችን የደነቆረው

  2. እድገታችን አብዮታዊ ጠበል እየተረጨ ስለሚንቀሳቀስ በፉከራና ሽለላ ቢታጀብ አይከፋም፡፡ የአብዮታዊ እድገት ጸባይ መሆኑ ተነግሮን የለ! ልማታዊ ድህነትን ግን ሳይነግሩን የረሱት ታሪክ ይመስለኛል፡፡ እያደጉ መራብ፣ እየሀበቱ መደህየት፡፡ ምናልባት እያየነው እንድንረዳው ሳይሆን አይቀርም አብዮታዊ ልማት የፈጠሩልንና ጆሮአችን የደነቆረው፡፡

Leave a reply to unknown Cancel reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑