ትልቅ መጥበሻ
ቆም ብለን ሰዎችን ብንመለከት እያንዳንዱ ሰው የሆነ አንድ ቦታ ተጣብቆ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ በሕይወታቸውም ውስጥ አንዳንዴ እንዲሁ ነው፡፡ አንዳንዶች በየቤቶቻቸው ሥራዎች ተጠምደው የተጣበቁ ሲሆን፤ ከከበባቸው ሁናቴ ጋር የተጣበቁ ወይም ይቀየራል፣ ይሻሻላል፣ ወይም ይለወጣል ብለው ተስፋ ባላደረጉት ሥራ ላይ ሙጥኝ ብለው ተጣብቀው ይኖራሉ። ሌሎችም ከልምዶቻቸው ጋር ደንዝዘው በሕይወታቸው ብርሃን አልባ ድንግዝግዝ ውስጥ ተጣብቀው ይገኛሉ።
ይህ መጣበቅ፡ እንቅፋቶችን (ችግሮችን) ከመጋፈጥ ጋር የሚመሳሰል አይደለም። ምክንያቱም እንቅፋት ወይም ችግር ቢያጋጥምህ ቢያንስ ምንላይ ማተኮር እንዳለብህ ታውቃለህ- ከችግሩ ለመላቀቅ። ደንዝዞና ተጣብቆ መኖር ግን አለማወቅ ነው። በየት መታጠፍ እንዳለብህ አለማወቅ፣ እገዛ የት ማግኘት እንደሚቻል አለማወቅ ነው፣ ወደፊት የመሄጃ መንገዱን አለማወቅ፣ እንዴት ከታሰርክበት ሰንሰለት ሰብረህ ማምለጥ እንደምትችል አለማወቅ።
እርግጥ በህይወቱ አንድ ዋጋ ያለው ነገር ለማሳካት ለሚሞክር ማንም ሰው ከአንድ ነገር ላይ መጣበቅ የጉዞው አንድ ክፍል መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ግን ለዚህ እውነት እውቅና መስጠት ሳይንቲስቱ አንስታይን እንዳለው “ችግርን በፈጠርክበት በዛው አስተሳሰብ ላይ ሆነህ ለዛው ችግር መፍትሔ ማበጀት አትችልም” የተለያየ መመልከቻ መነጽር እንደሚያስፈልግ እንድታውቅ ያሳይሃል- ነገሮችን መመልከቻ አዲስ መንገድ፡፡ ችግሩ ግን እንዴት ማድረግ እንደምትችል አለማወቅህ ነው።
ምናልባት በትክክል ነገሮችን የማሳካት አቅማችንን የመረዳት ውስንነት ሊኖርብን ይችላል። በጥልቀት ካየነው ግን አጥብቀን የምንፈልገውን ስኬት ለእኛ ይሆናል፤ እንፈጽመዋለን ብለን አናምንም። ስለዚህ እራሳችንን እናላምደዋለን ። እኛ ስለራሳችን ዋጋ/አቅም ማሰብ የምንችለው ይሳካልናል ብለን በምንፈቅደው (በምንፈልገው) መጠን ሳይሆን ይሳካል ብለን በምናምነው ልክ ይሆናል። በተደጋጋሚ ራስን ስለማሳደግ ከሚሰብኩ ሥልጠናዎችና መጻሕፍት ‘ተግባራዊ /ሐሳባዊ ያልሆነ- realistic’ እና ‘ሊተገበር የሚችል- achievable’ ግብ ሊኖረን ይገባል የሚሉ ትምህርቶች አግኝተናል።
አዎን ግቦቻችን ተግባራዊና ሊሰሩ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል። ነገር ግን በአቅማችንና ችሎታችን ላይ ጠልቆ ያቀፈን ራስን የመወሰን እምነት ከሆነ ልናሳካቸው ያቀድናቸው ግቦች በጣሙን የደበዘዙ (ብርሃን የማያሳዩ) እና እኛን የሚያስፈልገውን አቅም እንድናወጣ ሊያነሳሱን ያለመቻላቸው እድል የሰፋ ነው። በዚህም ወቅት ቢሆን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ግብ አልነደፍንም ማለት ነው። ምክንያቱም ራሳችንን በትንሹ እየሸጥን ነውና። ልንሰራው እንችላለን ብለን በምናውቀው ልክ ራሳችንን አዘጋጀን እንጂ ራሳችንን ለማስፋትና በውስጣችን ያሉ ግና ያልተጠቀምናቸውንና ያላወቅናቸውን ሀብቶቻችንን ለማውጣት አልደፈርንም ወይም አልታገልንም።
አንድ ሰው ነበር አንዲት ቆንጆ ብቻ ሳትሆን ምርጥ ምግብ አብሳይ የሆነች ሚስት ያገባ። ከተጋቡ በኋላ ባለው የመጀመሪያ ሰንበት የእርሷን ልዩ የሰንበት ጥብስ አዘጋጀችለት። አዘገጃጀቷ በጥብስ ቅጠልና ቅመሞች የተዋሃደ በልዩ የሥጋ አቆራረጥ የተገለጠ ነበር። የሥጋዎቹን ሁለት ጫፎች እየቆረጠች ትጥላቸው ነበር።
ምግቡ ፍጹም ጣፋጭ ነበር። ባልየው ቀምሶት የማያውቀው ጣፋች ምግቡ ሆኖለታል። ሆኖም ስትሰራ ቆርጣ የምትጥላቸው የሥጋ ቁራጮች (ለእርሱ ጥሩ ሥጋዎች ነበሩና) በማየት ግራ ተጋብቶ ነበር። እናም ለምን እንደዛ እንዳደረገችው ጠየቃት። እርሷም እንደዛ ያደረገችው እናቷ ያስተማረቻት አሠራር መሆኑንና የቤተሰቡም የሰንበት ጥብስ የሚጣፍጥበት ምስጢር መሆኑን ነገረችው።
ከሳምንት በኋላ ወደ አማቹ (የሚስቱ እናት) ቤት የሰንበት እራት ተጋብዘው ሄዱ። እናትየዋ ምግቡን ስታሰናዳ በአንክሮት ያስተውላት ነበር። የአዘገጃጀቷ መንገድ ተመሳሳይ ነው፣ የተጠቀመቻቸው ቅጠሎችና ቅመሞች አንድ ዓይነት ሲሆኑ የምትወስዳቸው የሥራ ጥንቃቄዎች ሳይቀሩ ተመሳስለዋል ከአንድ ነገር በቀር። ሚስቱ እንዳደረገችው አማቱ የሥጋዎቹን
ሁለት ጫፎች ቆርጣ አትጥላቸውም ነበር። በመገረም ለሚስቱ እናቷ እንደሷ አለመስራቷን አሳያት። ሁለቱም ተገረሙ። ባለቤቱም ወደ እናቷ ዞራ
“እማዬ ሕይወትሽን ሙሉ ስትከተይው የነበረውን የጥብስ አሰራር ምነው መከተል አቆምሽ?” በማለት ጠየቀቻት። እናትየዋም ስትመልስ
“ትልቅ መጥበሻ ካገኘው በኋላ የሥጋዎቹን ጫፍ መቁረጥ ትቻለው” አለቻት።
አንዳንድ ጊዜ በጭፍን የሆነ ልማድ (መንገድ) እንከተላለን። ምክንያቱ ቀላል ነው፡ ሁልጊዜ በዚያ ዓይነት መንገድ ስለምንሰራ ነው። ነገር ግን እንደ ወጣቷ ሴት እኛም በሕይወታችን ውስጥ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ቆርጠን ጥለን ይሆናል።
አንድ ነገር ላይ ተጣብቀሃል? ምናልባት ይሄ ረጅም ጊዜ መውሰጃህ ይሆናል። ባሉህ ጊዜያት ምን ነገሮች እያደረክ እንዳለህ በጥልቀት ለመመልከት፣ የትኞቹ ድርጊቶችህ ልማዶች እንደሆኑብህ ለመረዳት፣ ሳታስብባቸው ዝምብለህ ስታደርጋቸው የነበሩትን ነገሮች ለመለየት ጥሩ ጊዜህ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደነዚህ ዓይነት ቅዠቶች (ብዙ የምናምንባቸው ግን ውሸቶች) ወደግባችን እየደረስን እንዳለን ያሳምኑናል ሐቁ ግን ውጤት እንዳልሰጡን ለመረዳት ታውረንባቸዋል።
ምናልባት ሕይወት በምታቀርብልህ ብዙ በረከቶቿ ለመደሰት የመነሻህ ይሄ ጊዜ ያንተ ነው። ምናልባት ትልቅ መጥበሻ ማግኘት የሚኖርብህ ጊዜ ይሄ ሳይሆን አይቀርም። አጣብቆ የማያስቀር መጥበሻ።
ሠናይ ጊዜ
የካቲት ፳፻፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ
ምናልባት ሕይወት በምታቀርብልህ ብዙ በረከቶቿ ለመደሰት የመነሻህ ይሄ ጊዜ ያንተ ነው። ምናልባት ትልቅ መጥበሻ ማግኘት የሚኖርብህ ጊዜ ይሄ ሳይሆን አይቀርም። አጣብቆ የማያስቀር መጥበሻ።