የባከነ እውቀት

የባከነ እውቀት

To read in pdf

ከልጅነት እድሜዬ በአንዱ ወቅት ነው፤ እናቴ ኃይለኛና ተቆጪ በመሆኗ ያለችውን ከመፈጸም ያዘዘችውን ከመተግበር ዝንፍ ላለማለት እጥራለሁ፡፡ ሳልፈጽም ብገኝ ቁጣዋን ተከትሎ ልምጭ ይልመጠመጣል፡፡ በአንዱ ቀን ቤቱን ሳላስተካክል- ሳልጠርግና ሳላነጣጥፍ ይመስለኛል- ስራገጥ ውዬ እርሷ ትመጣለች፡፡ እርግጫው ያው ኳስ ጨዋታ ነው፤ እርሷ እንዲህ ስለምትጠራው ነው፡፡ የማይቀሩት ተግሳጽና ቁጣ ተከታተሉ፡፡ ከጎረቤታችን የነበረች እኩያዬ  ደግሞ የወጣላት ባለሙያ ነች፡፡ እናቴም በቁጣዋ መሀል

 “እርሷን አታያትም! ቤቷን ጠርጋና አጽድታ ቡናዋን ቆልታ …. እናቷን ትጠብቃታለች” ያቺን ልጅ አለመጥላቴ የሚገርም ነው፡፡

“ከእርሷ ታንሳለህ? እኩያህ አይደለችም?” በዛን ወቅት የተሰማኝ ስሜት ለአሁኑ ስብዕና አንዲት የመሰረት ጥርብ ድንጋይ ጥሎልኛል፡፡ ለምንድነው ከ’ሷ ጋር የምታነጻጽረኝ? ለራሴ ጥሩ የምላቸው ችሎታዎችና ተሰጥኦዎች ነበሩኝና እኚያን ከማየትና ከማበረታታት ይልቅ ሌላ ሰው ላይ ባለ መልካም ሙያ ስትወቅሰኝ እልህ ተጋባሁኝ፡፡ “እኔ መነጻጸር ያለብኝ ከራሴ ጋር’ጂ ከሌላ ሰው ጋር አይደለም” የሚል እልህ፡፡

ሳስበው በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ የእውቀት ብክነት የሚጀምረው ከልጅነታችን ጊዜ ይመስለኛል፡፡ ሊበረታና ሊሻሻል የሚችለው እውቀት እውቅና ያጣና ይባክናል፡፡ ከዛም ይከስማል፡፡ ካለው እውቀት ብርታት ይልቅ የሌለው ጥበብ ድካም ይሆናል፡፡ ብዙዎቻችን ስንት የከሰሙ ተሰጥኦዎች እንደነበሩን ወደ ኋላ መለስ ብንል አናጣቸውም፡፡ በለሱ የቀናቸው ልዩ ሰው ሁነውበታል፡፡ እድላቸው ያልቀና አንዱን ሲይዙ ሌላውን ሲጥሉ፤ ይሄን ተማሩ ይኼኛውን ተጠበቡ ሲባሉ በጅምር ሲቀር አሊያም ክህሎቱን ይዘውት በሌላ ዓለም ውስጥ ራሳቸውን ያገኙታል፡፡

ት/ትቤቶቻችንም የተሰጥኦ ማትነኛ እንጂ መሰብሰቢያ ቤተ ሙከራ የላቸውም፡፡ ያለን እውቀት በሚያዳብርና ጎዳናውን በሚያበራ ሙከራ ላይ ከማቆየት ይልቅ በደረቅና ወዝ አልባ ንድፈ ሐሳብና መላምቶች ጊዜ ይባክናል፡፡ የሆንነውን ጥለን ሌላ ተሸክመን እንወጣባቸዋለን፡፡ ለሸክሞቻችን እውቅና በሰጡበት ልክ የ’ኛን እውቀት እውቅና ነፍገው ያባክኑብናል፡፡

ብዙ መስሪያ ቤቶችን እያንኳኳን ብንፈትሽ የሙያ ወረቀት የተሸለሙ ሥራው ግን እንቆቅልሽ የሆነባቸውን ማግኘት ቀላል ነው፡፡ ቀጣሪዎችም ባለወረቀት እውቀተኞችን እንጂ የሙያ ባለማዕረጎችን አይፈልጓቸውም፡፡ ምንም ዓይነት አማራጭም አላስቀመጡላቸውም፡፡

የሂሳብ አያያዝ በቂ እውቀት አላት ግን በወረቀት አልሸፈነችውም ስለዚህም ማንም አያምናትምና እንዳትሰራ እድሉን ይነፍጓታል፡፡ የኤሌትሪሲቲ/ኤሌክትሮኒክስ ክህሎቱ ኖሮት ሳይንሱን በወረቀት ስላልተሸለመው ግን ማንም አያስጠጋውም፤ ለመወዳደር የመጀመሪያ መስፈርት ወረቀት ነውና፡፡ ደንበኛ የመያዝ ጥበብና የማሻሻጥ ክህሎቷ የነጠረ እንደሆነ ቢያውቁትም ቅሉ እርሷ የመስሪያ ቤቱ ጽዳት ሁና ትቀራታለች እንጂ ያለወረቀት ሽልማቷ ማንም አያስጠጋትም፡፡ግና  በቦታው ተመድባ የምትሰራዋ ምናልባት የነበሩትንም ደንበኞች እያባረረቻቸው ይሆናል፡፡

አንድ ሰው አውቃለሁ- የንድፍ ሥራ (drawing) የጠለቀ እውቀት እንዳለው ከሚያነባቸው ንድፍ ሥራዎችና ከሚስላቸው ስዕሎች መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት የንድፍ ሥራ አስተማሪ ሆኜ ስለማውቅ ት/ቱን ሲማሩ በተማሪዎች ውስጥ ያለውን ጭንቀት አውቃለው፡፡ የሚ’ያዝና የሚጨበጥ ጠፍቷቸው ኳትነው የሚመረቁ ተማሪዎች ‘draft man’ ወይም ‘office engineer’ ሆነው ሲቀጠሩና ሥራ ግን ገና ሲለማመዱ ሳይ ይሄን ሰው አስበዋለው፡፡ የአጋጣሚ ነገር የእርሱ ሥራ የሕንጻ  ግንባታና ዲዛይን የሚሰራ ድርጅት ውስጥ ጥበቃ ነው፡፡ አስቡት ‘ምን ያህል’ እውቀት የያዘ ሰው ማሰልጠን ቢያስፈልግ’ኳ ሸክሙ የቀለለ ሰው ያለቦታው ይኳትናል፡፡ ሊከስም ይበራል፡፡ ማንም ቦታ ሊሰጠው የደፈረ የለም ሽልማት ‘ሚሉት ወረቀት እውቅና አልሰጠውምና፡፡ ከጥበቃው ጎን ወረቀት ፍለጋ ተማረ እዛው ተቀጠረ፡፡ ወረቀቱን ያመጣ እለት ለእውቀቱ እውቅና ሰጡለት፡፡ በእርግጥ ወረቀት በማምጣቱ እንጂ ባክኖ ይቀር ነበር፡፡ ድሮ በ’ኛ ዘመን በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ በተርም ማለፍ የሚባል ነገር ነበር፡፡ ለምሳሌ የሦስተኛ ክፍል ተማሪ የላቀ ብልጫ በመጀመሪያው ወሰነ ት/ት (semister) ካመጣ ወደ አራተኛ ክፍል ይዛወርና ሁለተኛውን ወሰን ይማራል በቀጣዩ ዓመትም አምስተኛ ይገባ ነበር፡፡ ይህ ሰው ግን በጉልምስናው የተቀነሰለት ዓመት የለም፡፡

ከዚህ ቀደም አንድ ዶክተር (ፒኤችዲ) ውጪ የት/ት እድል አግኝቶ በመሄድ ለሁለተኛ ድግሪው (ለማስተረስ) መግቢያ ሲፈተን ያመጣውን ውጤት አይተው ለሦስተኛ ድግሪ (ዶክትሬት)ቀጥታ እንደፈቀዱለትና ዶክተር ሁኖ እንደመጣ አጫውቶኝ ነበር፡፡ አሁን ለቴክኒክና ሙያ ሰዎች እውቀቱ አለን ካሉ መጥተው የሙያ ምዘና (COC) መውሰድ እንደሚችሉ (ያለትምህርት ማስረጃ መሆኑ ነው) ማዕከሉ ይናገራል፡፡ ተግባራዊነቱን ባላረጋግጥም ቅሉ በ COC ወረቀት ብቻ ያለ ት/ት ማስረጃ የት ቦታ መወዳደር እንደሚችሉ መገመት ከባድ ነው፡፡

ይሄ የሚባክን ወይም እውቅና የሚነፈግ እውቀት ከመደበኛ ት/ት ውጪ በንባብ፣ በጥናት፣ በልምምድ፣ በተፈጥሮ ሥጦታ፣ በሙከራዎች፣ በተጽእኖ፣ በሕይወት ልምድ፣ በእድሜ፣ በመፈለግ ጉጉት (Curiosity)  ወዘተ በተለያዩ መንገዶች ይዳብራል፡፡ እነዚህን ‘መደበኛ ያልሆኑ ት/ት ቤቶች’ እውቅና የሚሰጥ ደፋር በማጣት ብቻ ብክነት ይበረታል፡፡ ለእነዚህ ‘ት/ቤቶች’ ምሩቅ የሚኖረው አማራጭ የግላቸውን ሥራ ለመሥራት መጣር፣ በሰውና ዘመድ ትከሻ ሥራ መፈለግ ግፋ ሲልና ሲከፋ የወረቀት ሽልማት እንዳላቸው ማስመሰል (forgery) ይሆናል፡፡

አንዳንድ የሥራ ዓይነቶች የተፈጥሮ እውቀትና አጭር የሥራ ላይ ሥልጠና ብቻ የሚበቃቸው ሆነው ሳለ ድርጅቶች ግን የተቋማትን ምርቃት ይፈልጋሉ፡፡ ሁለት፣ ሦስትና አራት ዓመታት ተምሮ ወረቀቱ ብቻ ሥራ ይሆነዋል፡፡ ሥራው እዳው ገብስ ነውና- የተለየ እውቀትን ስለማይጠይቅ፡፡

እውቅና የተነፈጋችሁት ወይም የባከነ እውቀት ሰለባ የሆናችሁ ካላችሁ እስቲ ምን ትላላችሁ?

ነሐሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም       አዲስ አበባ

2 thoughts on “የባከነ እውቀት

Add yours

  1. እነዚህን ‘መደበኛ ያልሆኑ ት/ት ቤቶች’ እውቅና የሚሰጥ ደፋር በማጣት ብቻ ብክነት ይበረታል፡፡ ለእነዚህ ‘ት/ቤቶች’ ምሩቅ የሚኖረው አማራጭ የግላቸውን ሥራ ለመሥራት መጣር፣ በሰውና ዘመድ ትከሻ ሥራ መፈለግ ግፋ ሲልና ሲከፋ የወረቀት ሽልማት እንዳላቸው ማስመሰል ይሆናል፡፡

Leave a reply to Leul Ethiopia Cancel reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑