የዘመን ኅዳግ

 

Toread in pdf click

የዘመን ኅዳግ    መታሰቢያይሁን ዘመን ለጠፋው

መን ከኮሮጆው ከማደሪያው ገባ እጥፋት አበጀ

ምዕቱን ከምዕት ሺህውን በሺህ አጥፍቶ ጥንተቱን አወጀ

ከዘመኑ ድንበር ከማማው ላይ ቆሞ

                     ልባሙ፡ ሕይወት እየሳለ ምልሰቱን ጀመረ

ዘመኑ ገር ሞልቶት ጥጋብ ትርጉም አ’ቶ ሰልጥኖ ነበረ

ብዙዎች ተኝተው ሲያንኮራፉ ሳለ ከዚ’ች ሃገር ላይ እንቅልፍ ተሰደደ

ሁሉም እየተጋ በእውቀት ሲታነጽ

                    በአስተሳሰብ ልቆ በፈጠራ መጥቆ ከ’ድገት ተዋለደ

ማጀቱ ሞልቶለት እያደለ ሲሰጥ ለጋስ ደግ ተባለ የቅን ሐገር ንጉስ

ዓይኖች አንጋጠው፣ እጆች ተዘርግተው ንጉስ ሲማጸኑ ከበሬታ ሲፈስ

ሰብተናል ብላን፣ አፈራን ቅጠፈን ተማጽኖ ሲበዛ መሪነትን ያዘ ፊት ‘የቀደመ

ጎረቤቶቹ ላይ ኃይሉ ‘የበረታ ክንዱ ‘የረዘመ ድምጹ አስገመገመ፡፡

ክብር በክብር ላይ ሞገስ በሞገስ ላይ ህዝቡ ‘የበዛለት ዝናው ባለም ናኘ

ዓለምን ለመምራት ከቢጤዎቹ ጋር ሥልጣን ተቆራኘ፡፡

አቅሙ እየዳበረ ፋና ወጊ ሆነ

               አግዓዚ ኃይሉ ዓለም እየመራ ድንቅ እየከሰተ

‘ደውቂያኖስ ጠርዝ ድንበሩ እየሰፋ

              ይህ ታላቅ ህዝብ ታላቅ ሀገር ሠራ ለነጻነት ሞተ

እናም…. ዘመን ተሻገረ አዝማናት አለፉ ከዚህ ዘመን ባተ፡፡

እንኳን እሰይ ባተ! እልል ነው’ጂ ምስጋና ነው’ጂ

                ያ ድንቅ ዘመን አልፎ ተራው ዘመን ጠባ

ማድነቅ ትርጉም አጥቶ ጥበብ ተከደነ

                አሻራ አልባ መዳፍ መሪ ‘የሆነ ዝቅጠትን ገነባ

የእድገቱ ሰበዝ እየተመዘዘ እደተራራ ቁንጮ

                ብቃታ እየታየ ጠፈር እንዳበረ

ከትውልዱ መሐል ሰበዙን ሊቀነት

                ጎልማስ ወራዙ ታካች እጁን ቢሰድ ክንዱ አጠረ

ዘመን ተሻጋሪ ግብረ-ጥበባቱን ታሪክ ያደረገ

                 በትውልዱ መሀል ክፍተት ተፈጠረ፡፡

እሰይ ነው’ጂ ታዲያi

ጥንት የተሰደደ የታካች እንቅልፍ በሀገር ከነገሠ

የለጋሽ ክንድ ታጥፎ ለልመና ወደላይ እጁን ከቀሰረ!

ከዚህ በላይ ፍስሃ ከቶ ምን አለi!

ህዝብ መሪ አ’ቶ ቀንድ እየነቀለ ጅራትን ከሰካ’

               ከፊት መቅደም ቀርቶ ዳና ካሸተተ

በ’ራብ ጠኔ ታስሮ ወኔው ተኮላሽቶ’ ከደም ስሩ ተኖ’

               መንፈሱ ተራቁጦ’ ልቡን ካሸገተ፡፡

የነገን ተስፋ ታርዞ ህልሞቹ ሁሉ ቅዠት ከሞሉበት

                ባለመኖር ስሌት እድሜ ከሰረቀ

የቅን ሀገር ንጉስ ልጅ በ’ውቀት በላ ሥልጣን

                 ግለ-ከርሱ ላይሞላ ነጠላ መሻቱ ታሪክን ካነቀ

ሠርቶ ማሰራት ተጣፍቶት ያገር..የሰው መቅንዒ ከበላ

                 ህልም ተስፋ ምኞትን ከ’ዝቡ ልቡና ከፋቀ፡፡

በታሪክ ስላቅ ተውጦ’ ማጀቱ ለዘመናት ተርቦ’

                  ክብሩˉሞገሱ ተነፍጎ’ በ’ምባ የ’ድሜ ወንበሩ ከራሰ

የታላቂቱን ሃገር የታላቅ ህዝብን ስም እምነት አጉድፎ

                  በረከሰ ምኞት ካ’ናት ከነገሠ፡፡

እሰይ ነው’ጂ ታዲያi

መሳቅ ነው’ጂ መደሰት

የለም! የለም!ልባሙን ልትሞግት

የመጻኢ ዘመን ፍካሬ የተቃርኖ ቃልዋን ነፍስያው ቃተተች፡፡

የለም የለም! ስላቅ ዘመኑ አብቅቷል….

አሁን የምን ሳቅ እልልታ?

እንዴት ሊሸመት ነው ደስታና ፍስሃ ከጽማዌ ህይወት በአርምሞ ዋጋ

‹እሰይ› ይፈራርስ! ብናኙም ይረጭ ካ’ዝማናት ትናጋ!

ዘመን ከዘመን አይበልጥም……

ጽድቅና ኩነኔ ልባምና ሰነፍ

              ብርቱና ታካች የሁሉም ዘመን ጸጋ ነው

ይህ ዘመን ድንግል ነው ይህኛው ‘ርኩስ ነው

              በ’ጅህ የ’ይወት አሻራ ስያሜ ‘ምትሰጠው

ኃይሉ’ ስልጣኑ ያንተ ነው በመዳፍህ ደብቀህ

              ልታሳይ ልትገልጠው ያስፈራህ

ያ’ገር ፍቅር ረግቦ’ ስሜትህ ከስሞ’

              መንፈስህ ቆዝሞ’ ከራስ የተጣላህ

የማደግ ጉጉትን የመለወጥ ተስፋን የመሻሻል ህልምህ

              ከታሪክ ድረሳናት ተቀብረው ‘ሻገቱ

ተነስ! አዕምሮ ህሊና ሰውነትህ ይንቁ

    በመዳፍህ ስር-ኃይል ህይወት እየዘሩ ለትንሣኤ ይበርቱ!

በትውልድ መሀል የተፈጠረው ግንብ

        በጽኑዕ ወኔና በቁርጠኝነት’ጂ በጩኸት አይፈርስም

የ’ንባ ዝናም ያራሰው ወንበሩ ሊሰበር

        መዳፍህን ካዋጣህ ለተስፋ ከተሰጠህ ጊዜ ብዙ አይርቅም፡፡

የዚ’ች ሃገር ታሪክ የዝናዋ ረመጥ ዳግም ‘ዲያያዝ

                         ያንተን ቆስቋሽነት እጅግ ይናፍቃል

ላገር ያለህ ፍቅር ውስጥህ ሲለመልም

        ክንድ እየተዋዋስክ ኅብረት እያጸናህ ትንሣኤን ብትሸልል

ከግል ፍላጎትህ ላ’ንድነት ብ’ተጋ

          ምሽትና ንጋት ሌሊት ጠፍቶላቸው ጉርብትና ይሆናል

ያኔ.. ፈጣሪ እጆቿን በበረከት ሞልቶ

          መንፈሷን ያድሳል ነገር ይቀየራል ሀበሻም ይከብራል!!

 

አሜን ለመጪው ቀን

አሜን ለትንሣኤው

አሜን!!

 

One thought on “የዘመን ኅዳግ

Add yours

  1. የዚ’ች ሃገር ታሪክ የዝናዋ ረመጥ ዳግም ‘ዲያያዝ

    ያንተን ቆስቋሽነት እጅግ ይናፍቃል

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑