ግንቦት ሃያ ለማን?
- 23 ዐመት ከፊት ወይስ ከኋላ
- ተተኪ ወይስ አካኪ
- የምናውቀው መንግስት እና የማናውቀው
ከየካቲት ወደ መስከረም ከመስከረም ወደ ግንቦት የተሻገረው የበዓል ታሪካችን ከግንቦት ጋር የተጣበቀበትን 23ኛ በዐሉን ሽርጉድ ብሎ እያከበረ ነው፡፡
እንዳያልፉት የለም ያዘመን አለፈ
በቀን ሦስቴ ‘መብላት ህልም እየነፈሰ
ድኅነት ተረቶ ነፍስ እየመለሰ¡¡
ከግንቦት 83 በኃላ የተወለዱት 23ኛ ዓመታቸውን ሲያከብሩ ሌሎች ለትምህርት መድረሳቸውን ያበሰራቸው 83 ካለፈ 23 ዓመት ሞላው፡፡ በኢቲቪ ከሚተላላፉ የግንቦት 20 ውዳሴዎች ‹‹ ታሪክ ማውራት አቁመን መስራት ጀምረናል…..›› የሚለው አንዱ ነው፡፡ ለእነዚህ ከ20 እስከ 30 ዓመት ውስጥ ላሉት ወጣት ትውልዶች ደግሞ ታሪካቸው ይህ 23 ዐመት ብቻ ነው፡፡
በታሪካቸው በትምህርት ጥራት ጉድለት የተጎዱትም ሆኑ ከፈረቃ ትምህርት ወደ ሙሉ ቀን የተዛወረላቸው፣ በሥራ እጦት የተንቀዋለሉትም ሆነ እጅ መንሻ ተጠይቀው በምንዱባን ሕይወታቸውን ይማቅቁ ዘንድ የተገለሉት፣ የተሰባሰቡት ለጥቃቅን ሕይወት ማሟያ የሚመስሉት ሆኖም በስማቸው ለተነገደባቸውና የተበላባቸው፣ ሀሳቦቻቸውን መግለጽና ማካፈል የሚያስከፍለውን ዋጋ እንዲረዱት ደማቸው የፈሰሰላቸው፣ የቤት እጦት ችግር ለማቃለል በሚመስል በየማረሚያው (ማጎሪያው) ታፍነው የእድሜያቸው ትኩስና ኃያል ወቅት የከሰመባቸው፣ በታላላቆቻቸው የእናውቅልሃለንና እናስብልሃለን ማማለል ልብና ህሊናቸውን ተሰርቀው የወጣት አዛውንት (ቆዛሚ) የሆኑበት፣ ለውጥ መፍጠሪያና የመለወጫ የወጣትነት እድሜያቸውን በየቀኑ አግኝተው ስለሚበሉት በማሰብ የባከኑበትና ምግብ ፍለጋ እድሜያቸውን የሰዉበት ይህ 23 ዐመት ነው፡፡ ለእነዚህ ደግሞ እማኝ መጥራት አያስፈልገውም ምስክሮቹም እኛ ህያዋን ነንና፡፡
ታዲያ ግንቦት 20 የማነው?
የደርግን መንግስት እኛ ወጣቶቹ አናውቀውም አልኖርንበትምና፡፡ የኖርንባቸውን ዓመታት ለማነጻጸር ደግሞ ያልኖርንበትን ዘመን መፈለግ አያስፈልገንም፡፡ እንኳን እኛ 23 ዐመት የተጣበቀን መንግስት የገዛበትን ዘመን ለማነጻጸር የገረሰሰውን መንግስት ማሰብ አያስፈልገውም፡፡
ምክንያቱም በመጀመሪያ በእድሜ አያክለውም፡፡ የሚወቀሰው ወታደራዊ መንግስት ከቆየበት በላይ ወያኔ/ኢህአዴግ ገዝቷል፡፡ (የጫካውን እድሜ ቀንሰንለት’ኳ መሆኑ ነው)፡፡ ወያኔ የእርሱን ሥራ ከደርግ ጋር ለማነጻጸር አሁን ሞራል የለውም፡፡ ዛሬ ላይ ከ83 በፊት ከነበረው ጋር ለማነጻጸር የሚፈልግ 40ና 60 ዐመታት ለመግዛት የሚሻ ነው እንጂ ለ5 ዐመት ስልጣን ለመቆየት የሚፈልግ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ሁኔታው ነገ ከደቡብ ሱዳን ጋር ኢትዮጵያን ማነጻጸሩ የሚቀር አይመስልም፡፡ በ80ቹ የሥልጣን ዘመኑ የሰራቸውን ከ90ቹ የ90ቹን ከሚሊኒየሙ ቢያነጻጽረው እንኳ የሚፈልገውን ቁጥር ለመናገር አይከብደውም፡፡ የግድ በደርግ ዘመን ለነበሩት ልምጭ ይሆን ዘንድ ያለፈውን መቀስቀስ ያለበት መስሎት ካልሆነ በቀር፡፡
ሁለተኛው የእድሜውን ሥራ ለማነጻጸር እዚህ ዘመን ላይ ቆሞ ያለፈውን መንግስት መጥቀስ የማያስፈልግበት ምክንያት ለዕኛ እርባናቢስ ሁኖ ውኃ የማያነሳለት መሆኑ ነው፡፡ የእኔ እኩዮች ለኢህአዴግ ሲሰብኩ ለደርግ ዘመን የሚያሳዩት የገሃነምና ኩነኔ ጥላቻ እኔን ይገርመኛል፡፡ ባልኖሩበትንና ባላወቁት ዘመን ላይ ወቀሳ፡፡
እኛ ኢህአዴግ የምንመዝነው በሰለጠነባቸው 23 ዐመታት እንጂ በተዋጋባቸው ዘመናት አይደለም፡፡ ስለዚህ ይቁምና ይሞግተን ከአመት አመት ምን እንደሠራ፣ ከምርጫ ምርጫ ምን እንደለወጠ ያስረዳን የቁም ምስክሮቹ እነሆን፡፡
ፍሬ አንድ የህግ የበላይነት
ሰዎች ለምን በጉልበታቸው ጥቅማቸውን ማስከበር ይቀናቸዋል ቢባል በፍትህ ሥርዐቱ አመኔታ ሲያጡ ነው፡፡ በየቀበሌው፣ በየፍርድ ቤቱ፣ በየእስር ቤቱ፣ በየመስሪያቤቱ፣ ፍትህና ርትዕ ትርጉሙ ለየቅል ሁኗል፡፡ የገንዘብ፣ የሥልጣን፣ የዝምድናና የጉልበት አቅም ያለው ፍትህን በአደባባይ ሲገንባት እውነት ደግሞ ትምክህትነቷ ለውርደት ሁኗል፡፡
የዲሞክራሲ አለባ የሆነው የህግ የበላይነት ህዝብና መንግስት ላወጧቸው ህጎች እንዲገዙ ይበይናል፡፡ ኢህአዴግ (መንግስትም ፓርቲም) የሚያወጣውን ህግ ህዝቡን ለመቀፍደጃ ለእርሱ እድሜ ማራዘሚያ ተጨማሪ በትር ሁኖለት በሕጉ ላይ የበላይ ሁኗል፡፡ ዲሞክራሲ ያልዳበረ ባህል ነው ብለን ብንታገስም አሁን ግን ዲሞክራሲ እንደከሰመ ይረዳን ጀምሯል፡፡
ፍሬ ሁለት የብሔር እኩልነት
በጣሙን አሳፋሪው የታሪክ ፍሬ ይሄ ነው፡፡ በአለም ታሪክ የቀኝ ገዢዎች መላ የነበረው ከፋፍሎ መግዛት በእነዚህ 23 ዐመታት ሽልማታችን ሁኗል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሀገር እስኪጠፋን ድረስ መኖሪያችን ብሔር ሁኗል፡፡ ከተለያ ክልሎች ተባረናል፤ መኖሪያ ጠፍቶንም ተሰደናል፡፡ በሐገራችን የብሔር መጤዎች ተብለናል፡፡ ያለውዳችንም ከአንደኛው ብሔር እንድንጠራ ተገደናል፡፡ አስቂኙና አሳፋሪው እርሱው እሳት ለኳሽ እርሱው ወቃሽ መሆኑ ነው፡፡ የቆዩትንና እስካሁንም የዘለቁትን ግጭቶች ትተን የቅርቡ የተማሪዎች ግድያ የብሔር ግጭት መነሻ እንደሆነ ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡ ለዚህ ግጭት ጥይት ያዋጣው ኢህአዴግ የግጭቱ ቆስቋሽ ብሎ ሌሎች ውጫዊና ውስጣዊ አካሎች ላይ ማላከክና ማሳደድ ይዟል፡፡ ዐመታቱን በሙሉ እኩልነትን ስቴዲየም ወጥቶ በዓል በማክበር ሲገለጥ ከማየት በዘለለ እኩልነት ስለመረጋገጡ የየክልሎቹን እድገትና የሥልጣን ክፍፍል በማየት ማስጠየቅ ቀላሉ ሥራ ነው፡፡
ፍሬ ሦስት የሃይማኖት መቻቻል
ስዩማነ ኢህአዴግ ለቤተ እምነቶቻቸው የሚሰጧቸው የሥልጣን ጥቅሞች ትተን በህጉ ያሰፈረው የመንግስትና ሃይማኖት መለያየት አንቀጽ ያልገዛው ኢህአዴግ ጥልቅ ከሚልባቸውና ውሳኔ ሰጪ ከሆነባቸው ተቋማት አንደኛው ቤተ እምነት ነው፡፡ ለፈጣሪያችን አድረናል ብለው ራሳቸውን የለዩት የየሃይማኖቱ አባቶች እምነታቸውን ከምድር ገዢዎች ሥልጣን በላይ ማስቀመት አልተቻላቸውም፡፡ የሚፈልገውን መሪ ማስቀመጥ፣ ውሳኔዎችን በእጅ አዙር ማስወሰንና ማሳጠፍ፣ መወንጀልና ማዋረድ የኢህአዴግ መገለጫዎች ከሆኑ ሰነበቱ፡፡
ለዘመናት ተከባብረው የቆዩ የእምነት ልዩነት ያላጠፋቸው ሕዝቦች አሁን ብሶታቸው ከአፍንጫቸው ስር ተደብቆ መውጫ ምክንያት ይጠባበቃል፡፡ በነገሩና በተገኘው ሁሉ የእምነት ግጭት ሲስተናገድባቸው ይሄንን ግጭት በኃይል ለመፍታትና የማይፈልገውን ወደማጎሪያው ለመስደድ ሲያመቻች እኚያ 23 ዐመታት ያለመቋጫ አልፈዋል፡፡
ፍሬ አራት የሕዝብ ተጠቃሚነት
ግልጽነት ያልፈጠረበት መንግስት ሥራዎቹን ሁሉ (ህዝቡ እንዲሰራ የሾመው እንዳለመሆኑ) እንደ ድራጎት አደረኩላችሁ፣ ፈጠርኩላችሁ እያለ ከመመጻደቅና ምስጋና ከመሻት ውጪ ህዝቡ የሚያሰቃየውን መሰረታዊ ችግሮች (ውኃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ ትራንስፖርት፣፣) ለመቅረፍና እፎይ ለማሰኘት እንዳይችል ሁኖ ተተብትቧ፡፡ ለሚሰጣቸውም ቀርፋፋና ኋላ ቀር አገልግሎት በእርሱ ችሮታ የተገኙ አድርጎ በማስረዳት ተጠምዷል፡፡ እኚያም አገልግሎቶች በፍትሐዊነትና እኩልነት ለሁሉም ነዋሪና ክልል አልደረሱም ህዝቡ የሚሳተፍበት አገልግሎት ባለመፈጠሩ የጥቂቶች መፈንጫ ሆኗል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት የግንቦት 20 ፍሬዎቼ ከሚላቸው ሌላም የሚጠቅሳቸው የጤና፣ የት/ት፣ የመከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊነት ወዘተ በ23 ዐመት ቅርጫቱ የሰበሰባቸው ፍሬዎቹ ቢሆኑም ቅሉ የጤና አቅርቦቱና ስርጭቱ፣ የትምህርት ጥራትና የአካዳሚክ ነጻነት፣ የመከላከያ ሰራዊት መሪዎች የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የፓርቲ አባልነትና ለህዝብ የመወገን አቅም በተለያ ወቅቶች ጥይት ካወረዱብን ወታደሮች አንጻር ብዙ ልንል በተገባን ነበር እኛም ሌላ ዐመታት እንዳይፈጁብን ምስክርነታች እናጠናቅ፡፡
ስለሆነም ግንቦት 20 የእኛ የወጣቱ አይደለም፡፡ 23ቱ ዓመታት የብዙ ብሶትና በደል ዓመታት ነበሩ፡፡ ለእነዚህም ጥያቄዎቻችን መልስ ይሆን ዘንድ ጥይት ምግባችን እስር ቤታችን ሁኗል፡፡ አብረን እንድናከብር ሌላ ግንቦት 20 ያስፈልገናል፡፡ ኢህአዴግ ራሱን ለውጦ የሚመጣበት አሊያም ከተጣበቀን የሚላጥበት ሌላ ግንቦት….
ክብር በየዘመናቸው ለነጻነት ለወደቁት!
: አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ ነው፡፡

Leave a comment