የበረሃዋ ንግስት ከተማ-ክፍል ሁለት

የበረሃዋ ንግስት ከተማ

The Queen City of the Desertክፍል ሁለት

በመጀመሪያው ክፍል የጀመርነውን የምስራቅ ጉዞ እንቀጥላለን፡፡ አሁን ድሬ ዳዋ ደርሰናል

በረሞጫ በረሃ በጋራ ሥር የምታንጸባርቀው ድሬዳዋ እንደዛሬ አልነበረችም፡፡ ንጉስ ሚኒሊክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ መንግስታቸውን ከውጭው አለም ጋር የሚያገናኝ የምድር ባቡር መስመር ግንባታ ለማስጀመር የግል አማካሪያቸው የሆነውን የስዊዝ ተወላጅ መሐንዲስ ሙሴ አልፈርድ ኢልግን መላ እንዲዘይድ አማከሩ፡፡ ሙሴ ኢልግም በንግድ ስራ ተሰማርቶ ከነበረው እና የፈረንሳይ ዜግነት ከነበረው ሙሴ ሉዮን ሸፍኒክስ ጋር በመሆን ከጅቡቲ ወደብ ተነስቶ ሐረር -እንጦጦ የሚዘልቅ የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታ ጥናት አቀረቡ፡፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 9 ቀን 1884ዓ.ም አፄ ምኒሊክ ለስዊሱ መሀንዲስ ኤልግ ከጅቡቲ በሐረርና በእንጦጦ በኩል አቋርጦ ከነጭ አባይ ጋር የሚያገናኝ ሐዲድ እንዲዘረጋ ፈቀዱ፡፡ የፈረንሳይ መንግስትም የጅቡቱን ግዛት እንዲያቋርጥ በመፍቀዱ አቶ ኤልግና ቸርዋ የተባሉ መሐንዲሶች “Companie imperiale des Chiming de fer Ethiopien” የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኩባንያ የተባለ ማኅበር ከሶስት ወር በኃላ ሰኔ/ሐምሌ 7 ቀን 1896 (እ.ኤ.አ) መሠረቱ፡፡

እ.አ.አ ጥቅምት 5 ቀን 1897 ዓ.ም እነሙሴ ኢልግ በአንድ የፈረንሳይ የግንባታ ስራ ተቋራጭ አማካኝነት የምድር ባቡር ግንባታው ከጅቡቲ ተጀመረ፡፡

The-railroad-construction-in-progress

በአካባቢው ተራራማነት እና ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ የምድር ባቡር ሐዲድ በሐረር በኩል ማቋረጡ ቀርቶ በበረሃማው ቀበሌዎች ዘልቆ ጨርጨር ጋራዎች ሥር እንዲያልፍ ሆነ፡፡ መስመሩ እየተዘረጋ ድሬዳዋ የተባለው ባድማ መሬት ሲደርስም ለአንድ ከፍተኛ የባቡር ጣቢያ አገልግሎት የሚስፈልጉት እንደ ውኃ፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ለዎርክሾፕ፣ መጠገኛ ቦታዎች ለጥ ያለ ሜዳ በጅቡቲና አዲስ አበባ ማዕከላዊ የሆነ ሥፍራ ድሬ ዳዋ ሆና ተገኘች፡፡ ጉዳዩም ለዳግማዊ ሚኒሊክ ተገልጾ ሐዲድ ግራና ቀኝ አንድ ሺ ሜትር ስፋት ያለው መሬት ለኩባንያው እንዲሰጥ መፍቀዳቸውን ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ኢኮኖሚክ ሂስትሪ ኦፍ ኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጽፈዋል፡፡

ከጅቡቲ የተነሳው ባቡር በርካታ የምድር ባቡር ኩባንያና የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰራተኞችን አሳፍሮ አመሻስ ላይ ዛሬ ድሬደዋ የምድር ባቡር ኩባንያ እና ጽ/ቤት ያለበት አካባቢ ደረሰ፡፡ በዚያን እለትም በርካታ ዱንካኖች ተተክለው የኩባንያው ሰራተኞችና ኃላፊዎች ከተሙ፡፡ ሐዲድ ድሬ ዳዋ የደረሰባትና ረባዳዋ ድሬ ዳዋ አዲስ ሕይወት ያገኘችበት ታኅሣሥ 13 ቀን 1895 ዓ.ም (እ.ኤ.አ ታህሳስ 22/24 ቀን 1902) ከተማዋ የተቆረቆረችበት ቀን ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለበት ሐዲዱ ድሬዳዋ እንደደረሰ በጣቢያው በልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች የሚያገለግሉ ሰዎች በመቀጠራቸውና መኖሪያ እስኪሰራላቸው ድረስ በየድንኳኑና በየፉርጎ በብዛት ስለከተሙ ነበር፡፡

Ilg_und_die_äthiopische_Eisenbahn_in_Dire_Dawa

dire_dawa_1355384996ለጥቂት ጊዜም ቢሆን አዲሱ የባቡር ጣቢያ የሚቋቋምበት ቦታ አዲስ ሐረር ብሎ መሰየም ተሞክሮ ነበር፡፡ በሐረር የታሰበው መንገድ ቅያሪ/ምትክ ነው ሲሉ፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን ዥን ዱሸስት የተባለ የፈረንሳይ ተጓዥ እ.ኤ.አ በጥር ወር 1902 ሐዲዱ ሺኒሌ መድረሱንና በጥቂት ጊዜ ውስጥም አዲስ ሐረር ይደርሳል ሲል ከትቧል፡፡ ሆኖም ይህ ስያሜ ለአንድ ዐመት አለመቆየቱን ይሄው ተጓዥ ‹‹የመጀመሪያው ባቡር ታህሳስ 24 ቀን 1902 አዲስ ሐረር ገባ፡፡›› ካለበኋላ ጉብኝቱን ጨርሶ በባቡር ከድሬ ዳዋ ወደ ጅቡቲ መጓዙን ፓሪስ ላይ ባሳተመው ‹ሚሽን ኢን ኢትዮጵያ› መጽሐፉ ላይ አስፍሯል፡፡

ድሬ ዳዋ የከተማ መልክ ሳይኖራት በዚህ ሁኔታ ለአንድ ዓመት ቆየች፡፡ የሚሰሩትን ህንጻዎች ለመንደፍና ለመካብ እንዲሁም ሥራውን ለመቆጣጠር ይመቻቸው ዘንድ መሐንዲሶችንና ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ባቡር ጣቢያ አካባቢ ገዚራ ወይም ከዚራ ተብሎ አሁን በሚጠራው ሰፈር አረፉ፡፡ የጉልበት ሠራተኞች ግን ከደቻቱ ወንዝ ባሻገር ሠፈሩ፡፡ ወዲያውም እነዚህ የቀን ሠራተኞች ከተሜ ሥንቅና ሌላም ነገሮች መሸጥ ጀመሩ፡፡ በዚህም ሳቢያ መስፋፋቱን ቀጠለ ያን ጊዜ በእጅ ጥበብና በሌላም የሙያ መስክ ልዩ እውቀት ያላቸው ፈረንጆች ብቻ ከዚራ ይኖሩ ነበር፡፡ አውሮፓዊ ያልሆነ ሌላው ህዝብ ግን ነዋሪነቱ መጋላ ሆነ፡፡ ድሬ ዳዋም ገና ከጅምሩ ለሁለት ተከፈለች፡፡

ከመጀመሪ አንስቶ ከዚራ ሰፋፊ መንገዶችና ለመኖሪያ የሚያመች እንዲሆን በፈረንሳይ መሐንዲሶች ተቀየሰች፡፡ ፈረንሳዮቹም ድሬደዋን የንግድ ማእከል ለማደረግ ህልም ስለነበራቸው የኩባንያውንም ሆነ የመኖሪያ አካባቢዎቹን ግንባታ ያካሂዱ የነበሩት የከተማዋን ቀጣይ እድገት ታሳቢ በማድረግ እና በጥንቃቄ ነበር፡፡ ኩባንያውም በተመሰረተ በጥቂት ወራት ውስጥ ከጣቢያው ህንጻ በተጨማሪ የጉምሩክ ቢሮዎች፤ የመኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ግንባታዎች ተፈጠሩ፡፡ መጋላ ግን አውቆ በቀል የሆነ የከተማው ክፍል ሆነ፡፡ ከተማዪቱ እየተስፋፋች በመሄዷም መጋላ ዋና የመገበያያ ሥፍራ ሆኖ ቀረ፡፡

ከደቻቱ ወንዝ በታች እስከ ባቡር ጣቢያው ድረስ ያለውን ቦታም አፄ ምኒሊክ ለ99 ዓመት ለኩባንያው በኮንሲሲዮን (በኪራይ) ሰጥተው ስለነበረ በዚያን ጊዜ በከዚራ መኖር የሚፈቀደው ለባቡር ኩባንያ ሠራተኞች ብቻ መሆኑ ይነገራል፡፡ ለባቡር ኩባንያው የተሰጠው መሬት ስለበዛበት ለአንዳንድ ሰዎችና ድርጅቶች በምሬት ተሰጠ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ድሬዳዋ መስፋፋት ጀመረች፡፡ ስኪነር የተባለው የኢትዮጵያ የአሜሪካን ዲፕሎማቲክ ሚሲዮን አለቃም እ.ኤ.አ 1990 ዓ.ም እንዲህ ሲል ጻፈ፤

‹‹ድሬዳዋ ከመድረሳችን ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያን ወሰን ተሻገርን፡፡ በተባለችውም ከተማ ጉልህ የሆነ የዘመናዊ አስተዳደር ምልክት አየን፡፡ ነገር ግን የከተማዋን እርምጃ ጊዜው ጨልሞ ስለነበር ለማየት አልተቻለም፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይህቺ የምድረ በዳው ንግስት የሆነች ከተማ እንቅስቃሴ በጣም የተፋጠነ ይሆናል ብለን እንገምታለን›› ብላል፡፡

ሊሰሙ በኢትዮጵያ በተባለው መጽሔትም የመጀመሪያው ትምህርት ቤት እ.ኤ.አ በ1908 ዓ.ም መከፈቱን ጽፏል፡፡ በዚሁ ዓመትም የቅዱስ አልዓዛር ማተሚያ ቤት ከሐረር ወደ ድሬ ዳዋ ተዛወረ፡፡ እ.ኤ.አ በ1915 ዓ.ም ካስትሮ የተባለ ኢጣሊያዊ ኔላቲራ ዲል ንጉሥ በተባለው ጽሑፍ ድሬዳዋ በፕላን የተሠራች ልትጎበኝ የሚገባ ከተማ ነች ብሏል፡፡

የባቡር ሐዲዱ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለጊዜው ድሬዳዋ ላይ በመቆሙ ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ የሚላከው ዕቃ ወደዚች ከተማ መጓጓዝ ነበረበት፡፡ እ.ኤ.አ በ1917 ዓ.ም የባቡር መስመር አዲስ አበባ በመድረሱ የከተማዋ ንግድ እንቅስቃሴና ታዋቂነቷን በመጠኑም ቢሆን ቀንሶታል፡፡

3959124609_8cb8e79872_o

እ.ኤ.አ ከ1922 ዓ፣ም እስከ 1930 ዓ.ም ለከተማ ኑሮ የሚስፈልጉ እንደ ኤሌክትሪክ፣ የቀለምና የእጅ ጥበብ ትምህርት ቤቶች የተቋቋመበት 1928 (እ.ኤ.አ) ፣ ከተማዋን ከሐረር ጋር የሚያገናኛት መንገድ መሠራቱንና የመጀመሪያው ተሽከርካሪ እ.ኤ.አ 1929 ወደ ከተማ መምጣቱን መዛግብት ዘግበውታል፡፡

እስከ 1926 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ‹ገዚራ› የተሰኘውን የከተማ ክፍል ያስተዳድር የነበረው የምድር ባቡር ንብረትና ሥራውም ከሚያስፈልጉት ቦታዎች በስተቀር የተቀረው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ለከተማዋ ማዘጋጃ ቤት አስረከቡ፡፡ እንዲሁም ዘልቃ ፋሺሽት ኢጣሊያ በ 1927 ኢትዮጵያን በግፍ በወረረችበት በግንቦት ወር ድሬዳዋ ለመግባ ቻለች፡፡

ጣሊያኖችም እዚህ በነበሩበት ጊዜም ለከተማዋ ማስተር ፕላን ከማዘጋጀታቸውም በላይ በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድረገዋል፡፡ እንደ ግሪክ ካምፕ፣ አዲስ ከተማ፣ና ለገሀሬ ያሉ የመኖሪያ ቀበሌዎች ጥጥና ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተሠሩበት ዘመን ሆነ፡፡ ወደ ሐረር፣ አይሻና አዲስ አበባ የሚወስዱትንም መንገድ ሞቃዲሾን ከአዲስ አበባና አሥመራ ጋር ለማገናኘት ሲባል ጣሊያኖቹ አሻሽለውት ነበር፡፡ ከወረራው በፊት ተጀምሮ የነበረውም አውሮፕላን ማረፊያ ሥራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

The-railway-station-during-the-Italian-occupation

የፋሺሽት ጦር ሠራዊት ድል ከተመታ በኋላ በመጋቢት ወር 1933 ዓ.ም እንግሊዞች ድሬ ዳዋ ገብተው ከተማዋ ውስጥ ‹ነበርዋን› ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ሠፈሩ፡፡ ከድሬ ዳዋ ያጭር ዘመን ታሪኳ ውስጥ ጥቁር ነቁጥ ያነቆጠባት የእንግሊዝ ወታደሮች ድርጊት ነበር፡፡ ድሬዳዋን ሁለት የከፈላት ደቻቱ ወንዝ እግረ መንገዱን የጥቁርና የነጭ ጠረፍ ሆነ፤ ጥቁር ለከባድ የጉልበት ሥራ እንጂ እንደ አገሩ አገሬ ብሎ ለመዝናናት ከዚራ እርም ሆነችበት፡፡ ያለ ማለፊያ ደቻቱን አልፎ ከዚራ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ወሮበላ ተሰኝቶ በፀሀይ የጋለ በርሜል ላይ ተንጋሎ በጉማሬ መጠብጠብ ደሙን እያዘራ እዘሩ መደባለቅ እጣው ነበር፡፡   ይቀጥላል….

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑