መልካም አስተዳደር ወዴት ነህ?

መልካም አስተዳደር ወዴት ነህ?

To read in pdf
በተለያዩ የጡመራ ገጾች ላይ አፍሪካውያን የሚመላለሷቸው ሐሳቦቻቸው ይደንቃሉ፡፡
”ባክህ! አፍሪካ ፈጽሞ አትነቃም፤ በጣም ብዙ አፍሪካውያን ተኝተዋል፡፡ በአፍሪካ ያለው የትምህርት ሥርዐት የተቀረጸው የምዕራባውያን አምልኮ ማስረጫ ሁኖ ነው፡፡ እናንተ አፍሪካውያን የራሳችሁን ቋንቋ እንኳ አትናገሩም፡፡ አፍሪካውያንን በየሰዓቱ ይሰልላሉ፣ እርስ በርስ መራኮታችሁና መገዳደላችሁን ለማጠንከር የጦር መሳሪያ በገፍ ይሸጡሏችኋል፡፡”
” ሥራው ረዥም እድሜ የሚጠይቅ ነው፡፡ ጽናት ይፈልጋል፣ ተስፋችን እስካሁን አለ ሕልማችን ፈጽሞ አይሞትም፡፡ አፍሪካ አንድ ቀን ትነቃና በሌላው ተራራ በኩል ያለውን ውጋጋን ትመለከታለች፡፡ የጉዞ ጅማሬ ላይ እንዳለንና ጅማሬውም ከቀላሉ እርምጃ በመኖር ተስፋ (መንፈስ) መጀመር እንዳለብን ማወቅ የሁላችን ነው፡፡”
”ወዳጄ! አፍሪካውያን ያለፉትን 500 ዓመታት ፈጽሞ አልተማሩባቸውም፡፡ በሚቀጥሉት 500 ዐመታትስ የመማር ፍላጎት እንዳደረባቸውና ይማራሉ ብለህ እንድታስብ ያደረገህ ምንድነው?” good governance

እስቲ ለዚህ ምልልስ ማሳያ የሚሆን አንድ ጉዳይ ላንሳላችሁ፡፡ ልክ እንደሳይንሱ፣ የሥነጥበብና ሰላም ኖቤል ሽልማት ያለው ግን በሌላ ደርዝ ሽልማት ስላዘጋጀውና በዚህ ዐመት ተሸላሚ ግለሰብ የጠፋለት በሱዳናዊው ቢሊየነር ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ስለሚዘጋጀው የሽልማት ፕሮግራም፡፡
የሽልማቱ መመዘኛዎች በድህረ ገጹ ላይ ለሁሉም ተገልጸዋል፡፡ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጥክ አፍሪካዊ መሪ መሆን ይገባሃል፣ ባለፉት ሦስት ዐመታት ስልጣንህን ያስረከብክ (የለቀቅክ)፣ በተገለጠና በታወቀ መንገድ አሪፍ ማስተዳደር የቻልክ … ወዘተ ከሆንክና መመዘኛዎቹን ካሟላክ አምስት ሚሊየን ዶላር (ወደ 95 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር) ሽልማት ይሰጥሃል፤ እንዲሁም ለአስር ዐመት ከሚቆይ ዐመታዊ ሁለት መቶ ሺ ዶላር(3.8 ሚሊየን ብር )የጡረታ አበል ጋር፡፡
ሽልማቱ ሙስናን ለመቀነስ የገንዘብ ድጋፍ መስጠትን ዐላማው አድርጓል፡፡ ዳሩ የሽልማት ኮሚቴው ከ50 በላይ ከሆኑ የአፍሪካ ሃገራት በሰባት ዐመት እድሜ ለአራተኛ ጊዜ አሸናፊ የሚሆን መሪ ማግኘት አልቻለም፡፡
ለምን? ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ስልጣናቸውን መልቀቅ ስላልቻሉ! ይልቁን የአፍሪካ መሪዎች ማን የበዛ ይቆያል በሚል የማራቶን ውድድር ገጥመዋል፡፡ የኢኳቴሪያል ጊኒውና የአንጎላው መሪ ከ34 ዐመት በኋላም ኃይላቸው እንደጋመ ወንበራቸው እንደሞቀ ይገኛል፡፡ ሌሎችም ብዙ የአፍሪካ ሃገሮች ራሳቸውን እንደዲሞክራሲ ሃገር የሚቆጥሩ የሚመሯቸው ግን አምባገኖች የሆኑባቸው ናቸው፡፡ ምርጫዎቻቸው (ምናልባት ካካሄዱት) በፍራቻ የተከበበ፣ ግጭትና ግድያ የማይጠፋው፣ ማጭበርበርና ማታለል፣ ስርቆትና ማስመሰል የተሞላ ነው፡፡

ተጨማሪ ከኤርምያስ እውነታዎች፡ የእድሜ ልክ መሪዎቻችን

ብዙ ጥናቶችና ማመልከቻዎች አህጉሩ በአስተዳደር ቀውስ ውስጥ እንዳለ ያመላክታል፡፡ የፍሪደም ሃውስ የዐለም ነጻነት ካርታ ዘገባ አፍሪካ ከፍተኛውን ”ነጻነት የጠፋባቸው” ሃገራት ብዛት የያዘች እንደሆነች ገልጿል፡፡ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና ዝርዝር ላይ ደግሞ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገራት በቀይ ተቀልመዋል፡፡ይሄም በሙስና የተዘፈቁ ሃገራትን ማመልከቻ ቀለሙ ነው፡፡
እርግጥ ነው ሌሎች በጎ ዜና ይዘው የሚወጡ ዘገባዎችም አልጠፉም፡፡ ከዐለም በፍጥነት እያደገ የሚገኝ ምጣኔ ሀብት ያላቸው ሃገራት ስድስቱ አፍሪካውያን ናቸው፡፡ እንደ ቬንቸር አፍሪካ አህጉሪቷ 55 ቢሊየነሮች አሏት፡፡
good governance 3ሀብት በመፍጠርና ልማትን በማስፋፋት ረገድ ታላላቅ ለውጦችን እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡ በት/ት፣ በጤና ጥበቃና ድህነትን በመቋቋም መሻሻሎችን አሳይታለች፡፡
ታዲያ እነዚህ ጥሩ ግብአትና መሻሻሎች ካሉ አፍሪካ ስለምን ከመልካም አስተዳደር ራቀች?
ለብዙ አስርት አመታት ያረጁ ፋብሪካዎቿ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለዘመናት ያፈጁ አሰራሮችና ልማዶች የአገልግሎቶቿ መገለጫዎች ናቸው፡፡ የምጣኔ ሀብቷ ግስጋሴዋ ብዙ ባፈሱት መሐልና ባጡት መሀል ያለውን ርቀት ከዐይን የሚሰወር አድርጎታል፡፡ ይሄንን የፈጠረው የመልካም አስተዳደር እጦትና ንፍገት ነው፡፡

ተጨማሪ ከኤርምያስ እውነታዎች፡ 27 ዐመታት ያስፈልገን ይሆን?

ምንም’ኳ ለዘመናት መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ምዕራባውያን የሚሰጡትን የእርዳታ ገንዘብና የንግድ ውሎችን ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ሲዋዋሉ የሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች ቢኖሯቸውም ቻይና ይሄን አሰራር አዙራዋለች፡፡ ቤጂንግ እርዳታና ለንግድ ፊርማዋን ያለምንም ማያያዣ በመስጠት ተገልጣለች፡፡ የቅድሚያ ፍላጎቷም ሸቀጦቿን በተመረጠ አሪፍ ዋጋ ማቅረብ ነው፡፡ ይሄም ተሳክቶላት አፍሪካ ለእድገቷ በእነዚህ ሸቀጦች ተሞልታ ትገኛለች፡፡
እንደ ኒውዮርክ ጥናት በአፍሪካና ቻይና መሐል ያለው የንግድ ልውውጥ በ2000 ከነበረው 10 ቢሊየን በ2011 ወደ 166 ቢሊየን በመጎን አስራ ስድስት እጥፍ አድጓል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቻይና የአፍሪካ ታላቋ የንግድ ሸሪክ ነች፡፡ በቅርቡ እንደተሰማውም የቻይና አጠቃላይ የብድር እቅድ በ2001 ከነበረበት 1.7 ቢሊየን በ2011 ወደ 189 ቢሊየን አድጓል፡፡ ከዚህም ብዙው ድርሻ ወደ አፍሪካ የተጓዘ እርዳታ ነው፡፡
ምናልባትም የአፍሪካ መሪዎች በእንደዚህ አይነቱ ውል እየተደሰቱና እየተዝናኑ ይገኙ ይሆናል፡፡ የምዕራቡን ዐለም ወቀሳና ክስ ለመስማት ጆሮዋቸውን ሳይደፍኑም አልቀሩም ምክንያቱም እንደ ቻይናና ሌሎች ብራዚልና ህንድ ያሉት ያለምንም የሚጠበቅ ማያያዣ ለመነገድ ፍላጎት አላቸውና፡፡ (CNN: GPS, Fareed zakaria)
አፍሪካውያን አምባገነኖች ግን ሊረዱት የሚገባ ነገር ሰሜኖቹንና የአረቡን ዐለም መመልከት ብቻ ነው፡፡ ያኔም መሪዎቹ የተፈጥሮን ህግ(ሞት) በመጠበቅ ነጻነትን ባፈኑ ወቅትና ለብዙ ዘመናት ወንበራቸው ላይ በተሰፉ ወቅት ምን እንደሚፈጠር ይረዱታል፡፡ ያዩታል፡፡ እጅግ ብዙ የሆኑት አፍሪካውያን አዲሶቹ ወጣት ትውልዶች ከእነሱ የበለጠ ብልህ እየሆኑና እርስ በእርስ እየተገናኙ ሃሳቦቻቸውን እየተካፈሉ ይገኛሉ፡፡ ምናልባትም (በቅርቡ ሊሆን የሚችል) የታፈነውን ድምጽ፣ ተቀባይ ያጣ ሀሳብና የታመቀ ጩኸት ለማፈንዳት ተዋጊና ተቋዋሚ ሆነው ይነሳሉ፡፡ ሕዝባዊ ተቃውሞ በጣም ጠቃሚና የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ ያደርጉ ዘንድ መሪዎችን የሚያስገድድ ነው፡፡good governance 2
የረጅም ዘመን የስልጣን እድሜ ጠባቂዎች የመልካም አስተዳደር እጦት ምንጭ የሆነውን አስተዳደራቸውን ሁሉን ያማከለ፣ ኃይላቸው በሕግ የተገደበና ቦታውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባልሆኑበት መጠን የሰሜን አፍሪካዎቹ እጣ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ አይሆንም፡፡

ይህ ጽሑፍ ከዚህ በፊት በ /2014/01/20 የተለጠፈ ቢሆንም ቅሉ ሰርጎ ገቦች ከሰረዟቸው ጹሑፎች አንዱ በመሆኑ እንዲመለስ አድርጌዋለሁ፡፡

 : አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ ነው፡፡

3 thoughts on “መልካም አስተዳደር ወዴት ነህ?

Add yours

  1. የረጅም ዘመን የስልጣን እድሜ ጠባቂዎች የመልካም አስተዳደር እጦት ምንጭ የሆነውን አስተዳደራቸውን ሁሉን ያማከለ፣ ኃይላቸው በሕግ የተገደበና ቦታውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባልሆኑበት መጠን የሰሜን አፍሪካዎቹ እጣ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ አይሆንም፡፡

  2. ሕዝባዊ ተቃውሞ በጣም ጠቃሚና የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ ያደርጉ ዘንድ መሪዎችን የሚያስገድድ ነው፡፡

  3. እጅግ ብዙ የሆኑት አፍሪካውያን አዲሶቹ ወጣት ትውልዶች ከእነሱ የበለጠ ብልህ እየሆኑና እርስ በእርስ እየተገናኙ ሃሳቦቻቸውን እየተካፈሉ ይገኛሉ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑