ትንሣኤ የክርስትና ምኑነው? ሁለት

ትንሣኤ የክርስትና ምኑነው? ሁለት

vክርስቶስ ከሙታን ባይነሣስ?

vትንሣኤ ባይኖርስ?

vየክርስትና ትምህርት መሠረትና አስኳል ምንድነው?

 

በመጀመሪያው ክፍል ስለ ክርስቶስ መነሣትና የእርሱ ትንሣኤ ስለሰው ልጅ ትንሣኤ እማኝና ማረጋገጫ ስለመሆኑ ለማተት ከመነሣቱ በፊት ስለነበረው አስረጅና በነብዩ ኢሳይያስ ዐይነ ትንቢት ከመነሳቱ በፊት ስለተቀበለው መከራና የመከራው ፍጻሜ ስለሆነው ትንሣኤ ጀምረን ማቆየታችን ይታወሳል፡፡ በዚህ ክፍል ከመቃብሩ መውረድ በኋላ ስላለውና የመነሣቱ ድንቅነት ከክርስትና ዕምነት ጋር ስለሚኖረው ቁርኝት እናትታለን፡፡

†       www-St-Takla-org--Ethiopia-2008--St-Stephanos-Beit-Kristian-Addis-09

†          †          †          †          †          †

በሳምንቱ መጀመሪያ ጨለማ ሳለ በማለዳ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ያዩ ዘንድ ሲገሰግሱ መጡ፡፡ ከመቃብሩ ሲገቡ ግን ድንጋዩን መልአክ አንከባሎት በላዩም ላይ ተቀምጦበት ነበር ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው ‹‹እናንተ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለውና››፡፡

በጸጥታና ጭር ባለ ወቅት ሊያውም በሌሊት ወደ መቃብር ስፋራ መምጣት አስፈሪ ነው በተለይ መልአክን በመቃብር ስፍራ ማግኘት ደግሞ በጣም ያስፈራል፡፡ ስለዚህም ነው መልአኩ ቀለል ባለ ቃል እናንተ አትፍሩ ያላቸው፡፡ ስለምን ትፈራላችሁ ልነግራችሁ ያልሁት ምስራች ምንም ሊያስደነግጣችሁ አይገባም መምህራችሁ ቀድሞ ነግሯችሁ ነበርና በማለት ካረጋጋቸው በኋላ ታላቁን እውነት ነገራቸው ‹‹እንደተናገረው ተነስቷ ›› ሲል ሊቀ ካህናቱ ‹ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀውታል› ሲሉ የነዙት ወሬም ሆነ እንደመግደላዊት ማርያም ‹ወደ ሌላ ቦታ ወስደውታል› የሚለውን ሀሳብ ሁሉ ያሸነፈ እውነት ነበር፡፡ አዎ እርሱ ከሙታን ተነስቷል፡፡ የሰው ልጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሞት በሶስተኛው ቀን ሊነሳ ግድ ነው እየለ ገና በገሊላ ሳለ እንደተናገረው፡፡ ስለምን ትደነቃላችሁ? እርሱ እውነት መሆኑን ታውቃላችሁ ስለዚህ ይነሳ ዘንድ ልንጠብቀው ምክንያት አለን፡፡ የተናገራችሁን አስቡ ክርስቶስ በኃይል በስልጣን መነሳቱን እመኑ ፡፡

የመነሳቱን እውነት ለማስረገጥ መልአኩ ‹በዚህ የለም የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ› ሲል እንስቶችን ጋበዛቸው፡- ያዩና አለመኖሩን፤ መቃብራት ኃይላቸው www-St-Takla-org--Jesus--Holy-Shroud-01መክሰሙን፤ የሞት መውጊያ መሰበሩን፤ የሲኦል ድል መንሳት መነጠቁን፤ ትንሣኤ ህይወት መበሰሩንና ተስፋ ህይወት መኖሩን ያረጋግጡ ዘንድ ኑና እዩ! እምኑም ፈጥናችሁም ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ መነሳቱን ንገሩ፤ ለዓለም ሁሉ አብስሩ አላቸው፡፡ [1]

ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን የመነሳቱ[2] እውነት ሲገለጥ፤ ሲታወጅ፤ ሲታተም፤ ተስፋው ሲጸድቅ በከበረች ሰንበት በድህነት ቀን በአምላክ ትነሣኤ ለመላው ዓለም ሁሉ ሰላም፤ የምስራች፤ መጽናናትና ደስታ ተሰበከ፡፡ አዎን መድህንዓለም ክርስቶስ በትንሣኤው በሞት ላይ ድልን አወጀ፤ የሞትን መጎተቻ ቀበቶ ወይም ማፈኛ ልብስ ቀደደው፤ ረጅምና ጠንካራው የማገጃ ግድግዳውን አፈረሰው፤ በባርነት የመገዛት ስምምነት የተጻፈበትን /እዳ ደብዳቤ/ አለት አቀለጠው፤ ሁሉን አፈራረሰው ደመሰሰው፡፡

 

ለሰው ልጅ ከሞት የመነሣት ማረጋገጫ

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋሪያትና ተከታዮች ስለክርስቶስ ትንሣኤ ሙታን ምን አማኝነት /ምስክርነትን/ ሰጥተው ይሆን? በዓለም ዙሪያ የማዳኑንና ከሙታን የመሣቱን ነገር የትምህርታቸው መሰረትና አስኳል አድርገው የምስራቹን ለሁሉም ማብሰራቸው ለምን ነው?

መጽሐፍ እንዲህ ይላል ‹‹ጻድቃንም አመጸኞችም ከሙታን ይነሱ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር አለኝ››[3] እስቲ እንዲህ እንጠይቅ የሰው ልጅ ለነገ ተስፋ ከሌለው ዛሬ ለምን ይኖራል?

www-St-Takla-org--Jesus-Resurrection-17

ማንኛውም ክርስቲያን እንደሚያምነው የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የእምነት ሁሉ መሠረታውያን ናቸው፡፡ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ኃጥያት ሲል ከመሞቱና ለሰው ፍትህና ነጻነት ሲል ከመነሣቱ በላይ ምን ሌላ እርግጠኛ ወይም በጣም ተስማሚና በጣሙን እናምንበት ዘንድ ግድ የሚለን ነገር አለ? ቅ/ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስትያኖች በላከላቸው ክታብ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለን ‹‹ኢየሱስ እንደሞተና እንደተነሣ ካመንን እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋል ››[4] ስለዚህ በመጀመሪያ ስለክርስቶስ መነሣቱ ካመንን ከቅ/ጳውሎስ ምስክርነት ጋር አብረን እንቀጥል፡፡ ማመናችንን ከማረጋገጥ በመቀጠል ያስቀመጠው እጅግ ውብ የሆነ አገላለጽ ‹በኢየሱስ ያንቀላፉት› የሚለው ነው፡፡ በክርስቶስ ያንቀላፉት ሲል ጠዋት መነሳትን ተስፋ አድርጎ ማታ የመተኛት አይነት አይደለም በክርስቶስ ታምኖ በክርስቶስ ውስጥ ማንቀላፋትን ነው እንጂ፡፡ ይህም የእርሱ ሞትና ትንሣኤ ሰላምና ጸጥታ ለሞላው እንቅልፍና ረፍት ምክንያት የሚሆን ነው፡፡ እንደ ሀይማኖት የለሾችና እምነት የለሾች ወይንም እግዚአብሔርን ባለማመን ጨለማ ውስጥ እንደሚዳክሩ የሚያንቀላፉበት አይደለም በተባረከው ተስፋ ክርስቶስ በገለጠው እውነት ማረፍ መተኛት ማንቀላፋት እንጂ፡፡ እርሱ በመቃብር እንደነበረ ያለስቃይ እና ያለመከራ ያርፋሉ በእርግጠኝነትም እንደገና ይነሳሉ አንዳንዶች ለክብር ለህይወት ሌሎች ለመከራ ለአሳር፡፡ በክርስቶስ የሚያንቀላፉት ምንኛ የተባረኩ ናቸው? ምን ዓይነት እንቅልፋሞችስ ናቸው? ከኃጢያት ፍርድና ከመከራ ሁሉ ነጻ የወጡ ከወጥመድ ሁሉ የተፈቱ ናቸው፡፡ የክርስቶስ ከሙታን መነሣት ለሰው ልጆች ሁሉ ከሞት የመነሣት በኩርና ዋስትና ነው፡፡

ትንሣኤ የክርስትና ትምህርት መሠረትና አስኳል

ክርስትና እምነትን ካቆሙት ምሰሶዎች ዋነኛው ይህ የትንሣኤ ትምህርት ነው፡፡ የጌታ ደቀ መዛሙርትም ለትምህርታቸው አስኳል አድርገው በእርሱ ዙሪያ ዓለሙን የተስፋ ሕይወት ጠባቂና አማኝ አደረጉት፡፡ በጌታ ዘመን ሆነ በሐዋሪያቱ ስለሰዎች ዳግመኛ የመነሣት ሕይወትም ሆነ ስለ በኩሩ ትንሣኤ ጥርጣሬ የተሞላቸው ነበሩ፡፡ የቅ/ጳውሎስ የቆሮንጦስ ደብዳቤም ለዚህ አስረጅ ይሆነናል፡ ‹‹ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ? ትንሣኤ ሙታን ከሌለ ክርስቶስ አልተነሳማ፤ ክርስቶስ ካልተነሣማ እንግዲያስ ትምህርችን ከንቱ ነው ››[5] እኛ በአይናችን ያየነውን የክርስቶስ ከሙታን መነሣቱን ለፍጥረት ሁሉ ተስፋ የሆነ ትንሣኤን እኛ እንዴት እንደሆነ ካላየን አናምንም እንዴት ትላላችሁ?[6]

የክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጅ የመዳኑ፤ በሞት ላይ ድልን የመቀዳጀቱ ዋስትና፤ ከሙታን የመነሳቱ ተስፋ ነው፡፡ በማንኛውም መንገድ ይህ የሰው ልጅ ትንሣኤ ከሌለ፤ ሊሆን የማይችልና ፈጽሞ የማይሆን ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣም ማለት ነው፡፡ በማለት ከጠቅላላው የሰው ልጅ ትንሣኤ ወደ አንዱ የክርስቶስ ትንሣኤ፤ ለአንዱ የክርስቶስ ትንሣኤ እምነት ማጣት ወደ ሰው ልጅ ትንሣኤ አለማመን በመሄድ አጠቃላዩን ካላመኑ አንዱን እንደማያምኑ በመዘርዝር የክርስቶስ ትንሣኤ እውነት ካልሆነ ብዙ አመክንዮ የሌላቸው ተከታይ እውነታዎች እንደሚነሱ በመግለጥ ትምህርታችን ሁሉ ከንቱ፤ ውሸት፤ ባዶ፤ ከንቱ ተስፋ፤ ትርፍ የሌለውና ዋጋቢስ ነው ማለት ነው፤ የክርስቶስ ከሙታን መነሣት የምናምንበት ክፍል ብቻም ሳይሆን ሁሉ /አጠቃላዩ/ እምነታችን ጭምር እንጂ በማለት ያጠቃልላል ፡፡

ወይስ የክርስቶስን ትንሣኤ (ለሰው ልጅ ሁሉ በኩር የሆነው ትንሣኤ) አምናችሁ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ትላላችሁ? በማለት የክርስቶስን ከሙታን መነሳት እውነት መሆኑንና የሰው ልጅም በመጨረሻው ዘመን በዓለም ፍጻሜ ከሙታን እንደሚነሡ በምድር ጽድቅን የሰሩ ለክብር ትንሣኤ በምድር ከእግዚአብሔር መንገድ ተለይተው የኖሩት ወደአሳር /መከራ የሚወስድ ትንሣኤ እንደሚነሱ አረጋግጧል፡፡[7]

ክርስቲያኖችም ይጠብቁት ዘንድ ጉልበታቸው የክርስቶስ መነሣት ይታገሱም ዘንድ ፍጻሜያቸው ዳግመኛ ከምድር እልፈት በኋላ መነሣትና ለሌላ ሕይወት መታጨት ነው፡፡ መልካም የትንሣኤ ሰሙን ይሁንልን፡፡

‹‹አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነስቷል›› ፩ቆሮ ፲፭÷፳

www-St-Takla-org--Jesus-Resurrection-04-2

[1] ማቴ ፳፰፥፩-፲፣ ማር ፲፮፥፩-፰፣ ሉቃ ፳፬፥፩-፲፪፣ ዩሐ ፳፥፩-፲፰

[2] ፩ቆሮ ፲፭፥፳

[3] ሐዋ ፳፥፭

[4] ፩ተስሎ ፬፥፲፬

[5] ፩ቆሮ ፲፭፥፲፪-፲፬

[6] ፩ቆሮ ፲፭፥፴፭ና፴፮ ፤ሐዋ፲፯፥፴፪ ፤ ሐዋ ፳፮፥፰

[7] ፩ጴጥ ፩፥፫ ሐዋ፪፥፴፪

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑