ቀና ቀውስ

ቀና ቀውስ

ያለጦርነት እንዴት የሃገር ፍቅርን እንገልጻለን? ልጅ አባቱን ይጠይቃል፡፡ አባት በተደጋጋሚ በዋለባቸው የጦር አውድማዎች የፈጸማቸውን ጀብዱዎች፣ በሰማቸው ውጊያዎች የተፈጸሙትን ታሪኮች ተርኮለታል፡፡ ወዳጆቹ ለሃገራቸው ያላቸውን ፍቅር የገለጹበትን ጀግንነት አውርቶለታል፡፡ ማታ ለእንቅልፉ ማስተኛ ተረት ቀን ለውሎው ማገጃ ምክር እንደሆነ ገብቶታል፡፡ ያልተመለሰው በአእምሮው የሚመላለስ ጥያቄ ግን ልጅ ከጦር ጋር ሳይዘምት ፍቅሩን በምን ሊያሳይ እንደሚቻለው ነው፡፡

የልጁ ጥያቄ በማኅበረሰብ ውስጥ ከሚነሱ ጥያቄዎች አንዱ ነው፡፡ አርበኞቹን ሲያዩ ጅላጅል የሚሆኑባቸው የፋኖ ፋኖ ዜማ ሲሰሙ ጉሮሯቸው የሚታነቅባቸው ብዙዎች ሁነዋል፡፡ ሁሉም ለእነርሱ ታሪካዊ እንጉርጉሮ እንጂ ነባራዊ ፈንት የሌለው ይሆንባቸዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ቆይታችን ወቅት አዘውትረን የምንወያይባቸው ጉዳዮች ነበሩን፡፡ ብዙዎቻችን ከህቅታችን እየሞሉ የሚመለሱ ብሶቶቻችን እያንገበገቡን ነበርና ለሃገር ያለንን አፍአዊ ጥላቻና ንቀት እንገልጻለን፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ሱማሌያዊ ከመሆን ወይም ማዳጋስካራዊ ከመሆን ልዩነቱ አልታይ ብሎን ታግለናል፡፡ ኑ በቃችሁ ሃገራችሁ ግቡ ብለው እያዜሙ ወደ ሃገራቸው የመጡት ዜማቸውን ሰጥተውን ይመለሳሉ፡፡ ሰለሃገሪቷ እድገት የደሰኮሩት በማግስቱ መገኛቸው በባዕድ ሃገር ውስጥ ይሆናል፡፡ የሕዝቡን የለውጥ ብሶት የቆሰቆሱት መዳረሻ መሸሸጊያቸው ባህር ዳር ሳይሆን ባህር ማዶ ይሆናል፡፡

“ኢትዮጵያዊ መሆን ምን አተረፈልን?” አንዱ ይጠይቃል ሌላው “ድህነት፣ ግዞት፣ ሙስና፣ እስራት፣ ተመልካችነት..” ይመልሳል እያቋረጡት፡፡ “የዛሬውን አትዩ እነዚህ ወጪ ወረጅ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ግን ደም ነው! ተቀብቶህ ታትሞ የሚኖር ልፋቀው ብትል የማይፋቅ ማኅተም” የበረታው ያስረዳል፡፡

የምን አገባኝ ፍቅር

የአንዱ ጎረቤት ወይም መደዳ (ረድፍ) መብራት ከጠፋባቸውና ቀናት እየቆጠሩ ሳለ ቢበዛባቸው ምሬታቸውን ለማስታወቅ፣ለመቃወምና ከኃላፊነታቸው ይነሱ ዘንድ ለመጠየቅ ተሰብስበው ቢወጡ ያኛው ረድፍ ያሉት ነዋሪዎች መብራት እየበራላቸው ነውና ተቀላቀሉን ሲባሉ እምቢ ምን አገባን? ማለታቸውን ከሰማን፤ የተሰማውን በመጻፉና በመናገሩ የትአባክ እጅህን ለካቴና አፍህን ለልመና ሲባል ሌላው ይሄኔ ነው መሸሽ ብሎ እግር አውጭኝ በዝምታ ከሸመጠጠ የሚያምንበት ቢሆንም’ኳ ምን አግብቶኝ ካለ፤ ወይም የቀበሌው ካድሬ ለሚኖርበት መንደር መንገዱን ሲያስነጥፍ ተወካይ ያጣው ነዋሪ በዝናቡ ጭቃ በሰፈሩ ሲርመሰመስ እረ! ‘እኩል የመጠቀም ያለህ’ ብሎ በጣት ከሚቆጠሩት ካድሬዎች የበለጠ ኃይሉን ማሳየት ካልቻለ ይልቁን የጌቶች ፍርፋሪ ይበቃኛል ሲል ከተገኘ፤

ስንት ዐመት ከኖረበት መንደርና ቀዬ ለባለሃብት የህንጻ ቅርጫነት አሊያም የእርሻ ጎተራነት ይፈለጋልና መሰደጃህን ፈለግ ሲባል አልቅሶ የሚያስጠጋውን ፍለጋ ከባከነ፣ እምቢየው እድገቱን እፈልገዋለሁ ግን በእኔ ኑሮ ጉስቅልናና ሕይወት መባከን አይደለም ይልቁን የትም የመኖር ነጻነቴን አትንኩብኝ ማለት ከከበደው፤ በጉራጉር ሰፈሩ ካልገባው ያለው እንደልቡ ባለመኪና በገጨው የስልክ እንጨት ስልኩ ሲቋረጥበት ባለመኪናውን ቀፍድዶ ስለጉልበትህ አምላክ (ስለ ህግ….) ቴሌንም ለችግሩ ፈጥኖ ይደርስለት ዘንድ ከመወትወትና ከማስገደድ ይልቅ እንደድራጎት እስኪሰራለት በዝምታ ከጠበቀ፤

በሌላ ወገን ደግሞ በስሙ የተከፈተ ሚዲያ ሊሰጠው ከሚገባው አማራጭ መረጃ ወጥቶ ስብከቱንና የልማት ውዳሴውን የሚያሰማ ጸሎተኛ ከሆነበትና በተዛባ መረጃ ከበረዘው፣ ይልቁን እርሱን እንዳላዋቂ ቆጥሮት ከናቀውን አሳቢ እርሱ ብቻ መሆኑን ሲገልጽለት ‘በል ስሜን ንሣ እኔ ህዝብ ነኝ’ ብሎ ሊቃወመው ሊዘጋው ላያዳምጠውና ላያነበው እንዲሁ በህግ ሊያስገድደው ሲያቅተው ካየን፤ የውኃን መልክ እንደክረምት ዝናብ በየሶስት ወሩ እንዲያይ ለተገደደ ግና አለቅየው ሦስት እጁ ህዝብ ውኃ ተትረፍርፎት የሚያስቀምጥበት እቃ የሚያጥበው ልብስና ገላ አጥቷል ሲል ከዘበተበት እረ እኔ አንድ እጅ አይደለሁም እነማንን ቆጥረህ ነው ሲል ካልሞገተው ብቻ ምን አለፋችሁ ሊያገኘው የሚገባው የዜግነት መብቱ (አንዳንዱም ሰው የመሆኑ መብት) ሁኖ ሳላ ስለተለያዩ ምክንያቶች ሲነጠቅ በኃ/ሥላሴ ዘመን ደመዎዝ ስጦታ ነው እንጂ የሚጠየቅ መብት አይደለም እንደተባለው እንደ ጉርሻ እንዲሰጠው የሚለምን ከሆነ ይህ ህዝብ ህመምተኛ ሁኗል ማለት ነው፡፡ መሪ የህዝቡን መብት ሊያስከብር የቆመ ወዛደር እንጂ ህዝብ የሚያጎበድድለት ንጉስ እንዳልሆነ ማሳወቅ ከተሳነው የበፊቱን የልጁን ጥያቄ እንጠይቃለን፡፡ የሃገር ፍቅር ያለጦርነት እንዴት ይገለጻል? ስንል፡፡

ሕዝብ ሃገር ሲሆን ሃገር ማለት ግለሰብ ነው ግለሰብ ደግሞ ህዝብ እንደሆነ ስለተረሳ እንጠይቃለን፡፡ የሃገር ፍቅር መገለጫው የህዝብ ፍቅር ነው፤ ህዝብ ደግሞ ግለሰብ ነው፡፡ ማርቲን ሉ. ኪንግ እንዲህ ብሎ ነበር ‘’any where injustices every where’’ በአንድ አካባቢ ያለ የፍትህ እጦት ሁሉም ቦታ ላይ አለ እንደማለት ነው፡፡ ለዛም ነው የአንድ ግለሰብ መብት መና’ቅና መዋረድ የህዝብ፣ የህዝብ ደግሞ የሃገር የሚሆነው፡፡ ይህ የሃገር ፍቅር መግለጫ ሰላማዊ መለኪያ ነው፡፡ አባትየው ልጄ እንዲህ ይገለጻል ሊለው ይገባል፡፡

አሁን የሚታየው ሁኔታ ይሄን ይመስላል፡፡ ግማሹ ህዝብ በዝምታው የሃገሩን ፍቅር ለመግለጽ ታሟል፡፡ ሌላው እንደ ሃገር ትልቅ እንደሆነ ያምናል በአኗኗሩ ግን ድኃና በድን በመሆኑ ታሟል፡፡ እንዳደገ ይነገረዋል የኑሮ ሁናቴው ግን እየባሰ በመሄዱ በእንቆቅልሹ ታሟል፡፡ እኚህ ነገሮች የአመጽ ግፊት ይፈጥራሉ፡፡ ያ አመጽ ከመነሣቱ በፊት ግን ልዩነቶችን (discrepancy) ማጥበብ ያሻዋል፡፡ ዶ/ር ምህረት ደበበ በአንድ ቃለመጠይቁ ላይ እንዲህ እንዳለ፡-

በሚባለው ና በምትኖረው መሐል ልዩነት ስታይ ግጭት ይፈጥርብሃል፡፡ ይህን ግጭት ለመከላከል ልዩነቱን ማጥበብ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ መከላከያ ዘዴ (defense mechanism) የለውጥ ስሜት መፍጠር ነው፡፡ ይሄ የለውጥ ስሜት ካልተፈጠረ ወደ ኋላ መንሸራተት ይጀመራል፡፡ ቀና ቀውስ የሚባለው የለውጥ ስሜት አስፈላጊ ነው፡፡

የመለወጥ ስሜት ለመሪዎች (በተለይ ለአምባገነኖች) ሁልጊዜም የሚፈራና የማይወደድ ነው፡፡ እነርሱ የሚገሩት ስለማይሆን ይሄ ስሜት ቀውስን መፍጠሩ አይቀርም በሚል ስጋት ይወጋሉ፡፡ ዳሩ ይሄ ቀውስ ግን እነርሱን ከስህተታቸው የሚያርማቸው ከድካማቸው የሚያነቃቸው በሆነ ነበር፡፡ ይሄ ቀውስ ለበጎ (ለለውጥ) የሚፈጠር ስለሆነም ነው ቀና ቀውስ መባሉ፡፡

በ60ቹ ውስጥ የነበረው የተማሪዎችና የነዋሪው የለውጥ ስሜት ይሄን ይመስል ይመስለኛል፡፡ ለውጡ እስኪመጣ ጠፋ ሲሉት የሚግም-እሳት በረደ ሲሉት የሚሞቅ ጽኑ ለውጥ ፍላጎት ነበር፡፡ ከለውጡ በኋላ የሆኑት ድርጊቶች በዚህ ዘመን ሊሆኑ የማይችሉበት መቶ ምክንያቶች መደርድር ይቻላል፡፡ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚደረደሩ መቶ ምክንያቶች ካሉ፡፡

ከህመማችን ለመፈወስና ጤነኛ ዜጎች እንድንሆን ይሄ የለውጥ መንፈስ በጽኑ ያስፈልገናል፡፡ አሊያ ግን እዚህም እዛም ቡጭቅ ቡጭቅ ያለ የለውጥ ስሜት ወንዝ ቢሞላ አያሻግርም….. ሌላ ዘመን እንቆጥራታለን እንጂ! ከነህመማችን እያቃሰትን…

 : አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ ነው፡፡

2 thoughts on “ቀና ቀውስ

Add yours

  1. ከህመማችን ለመፈወስና ጤነኛ ዜጎች እንድንሆን ይሄ የለውጥ መንፈስ በጽኑ ያስፈልገናል፡፡ አሊያ ግን እዚህም እዛም ቡጭቅ ቡጭቅ ያለ የለውጥ ስሜት ወንዝ ቢሞላ አያሻግርም….. ሌላ ዘመን እንቆጥራታለን እንጂ! ከነህመማችን እያቃሰትን…

Leave a reply to Leul Ethiopia Cancel reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑