የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ምልከታ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ምልከታ

በመድብለ ፓርቲና የሠብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ

መግቢያ To read in PDF

ክርክሩ በአምስት የተመረጡ ፓርቲዎች (ለምን በዚህ ርእስ እነዚህ እንደተመረጡ አስረጂ የለም) በስቱዲዮ ውስጥ በደቂቃ ተገድቦ የተደረገ የመጀመሪያው መርሐ ግብር ነው- ለኢቢሲ፡፡ አዘጋጁ ኢቲቪ እንደመሆኑ ብዙ መብቶች እንዲሰጡት አድርጎታል፡፡ ኢህአዴግ ለ45 ደቂቃ፣ ተቃዋሚዎች 19 ደቂቃ እንዲጠቀሙ በመገደብ፣ ኢህአዴግ በሁለት ተከራካሪ ተቃዋሚያን በአንድ ሰው እንዲመደቡ በማድረግ፣ የሚቀረጸውን ዝግጅት እንደፈለገው ቆራርጦ እንዲያቀርብ ሰፊ መብት በመስጠት.. ወዘተ፡፡

ጠንካራ ጎን

ምንም ካለማድረግ ይሻላል፡፡ ድምጽ አልባዎቹ    ተቃዋሚዎች ጉሮራቸውን የሚጠራርጉበት እድል የሚሰጥ   ስለነበር፡፡

የአወያይ ሚና በሰኣት ቆጣሪነትና ተራ ማስያዝ መገደቡ፡፡ ቢያንስ በመንግስት ሚዲያዎች የሚያወያዩ ጋዜጠኞችና ጥያቄዎቻቸው ምን ያህል በተጽእኖ ውስጥ የወደቀ እንደሆነ እካሁን ስላየን፡፡

ደካማ ጎን

ሰው (ታዳሚ) በሌለበት መደረጉ፡፡ ክርክሩ ሕይወት አልባ አድርጎታል፡፡

ምክንያት አልባ የልዩነት ደቂቃ ምደባ

የፓርቲዎች መረጣ እና እጣ አመክንዮ

ነገረ ጉዳይ

መድብለ ፓርቲ

ማሣያ 1.ሰሞኑን በኢህአዴግ ዘንድ እየተደጋገመ ያለው የመድብለ ፓርቲ ማሣያ በደርግ ዘመን 17 ታጣቂዎች ነበሩ የሚለው ነው፡፡ የመድረኩ ዶ/ር መራራ ይጠይቃሉ “ኦነግ የትነው ያለው? ደቡብ ኅብረት የት ገባ? እነስዬና ተወልደ በልካቸው የተሰፋው ብጥቆ ፖለቲካ ጠቧቸው የት ወጡ?”ይህ ብቻ ሳይሆን በራሱ ሚዲያ እንደምንሰማው ብዙ ነጻ አውጪ ተዋጊዎች በየጫካው ሞልተዋል፡፡ የትግራይ ነጻ አውጪ፣ የኦጋዴን፣ የቤንሻንጉል፣ የደቡብ፣ የአፋር፣ የሱማሌ፣ የኦሮሞ፣ ግንቦት 7፣ አርበኞች… የመሳሰሉት ያሉት በዚህኛው ዘመን አይደለምን? በቅርቡ የአሜሪካ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ ለሚሄዱና በኢትዮጵያ ላሉ ዜጎቹ ያወጣው ማስጠንቀቂያ ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን (ማዕከሉንም ጨምሮ) አሳሳቢ የደህንነት ስጋት እንዳለበት ያመለከተ ነበር፡፡ መንግስትም ለሶቨርኒቲ ቦንድ ሽያጭ ካያያዘው ሰነድ መረዳት የሚቻለው ሊፈነዳ ስላለ ብሶት ያለውን ስጋት ቦንዱን ለሚገዙት ማሳሰቡን ነው፡፡

ማሣያ 2.በሃገሪቷ 75 የሚሆኑ የተመዘገቡ ፓርቲዎች ስለመኖራቸው፣ 58ቱ በዚህ ምርጫ እንደሚወዳደሩና ከ1805 በላይ እጩዎች ውስጥ በ1218 እጩዎች ተቃዋሚዎቹ እንደተወከሉ፣ ለዚህም መንግስት 30 ሚሊየን እንደመደበ እነ ሬድዋንና አስመላሽ የመድብለ ፓርቲ ማሳያ ያቀርባሉ፡፡እኛም እንጠይቃለን፡- እነማን ናቸው 75ቱ ፓርቲዎች? ለዚህ ክርክር እንኳ ከሚወዳደሩት 58 ፓርቲዎች ባላቸው እጩ ብዛት 12ቱ ብቻ ናቸው የተመረጡት፡፡ ስለዚህ የቀሩት ስምና አንድ መሪ ብቻነው ያላቸው ማለት ይሆን? ማን መሠረታቸው? ለምን ተመሠረቱ የሚለውን ትተን ማለት ነው፡፡ ለመሆኑ መድብለ ፓርቲ በተወዳዳሪ ፓርቲዎች ቁጥር ብዛት ብቻ ነው የሚገለጸው? ነው ወይስ ኢህአዴግ እንደ አንድ ፓርቲ እንደ ሶህዴፓ ያሉ አጋር ድርጅቶች ተደምረው ይሆን መድብልነቱን የሚያሳዩን? ወይስ ‘ሕዝቡ’ ስለመረጠኝ 100 % ፓርላማውን ወረርኩት በማለት ይሆን? ለቁጥር ጣት የማይሞሉ፣ ብዙ ተከታይ ያላቸውና የመሰማት እድል ያገኙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዴት ተከፋፈሉ? ማንስ ዳኛቸው? መቼም ኢህአዴግ 100% የፓርላማ ጥቅሙን ለማስቀረት ፓርቲዎች እንዲፋፉ፣ እንዲሰፉና እግራቸው እንዲቆም፣ ድምጻቸው እንዲሰማና እንዲቀናቀኑት መንግስት ሁኖ አገዛቸው እንበል? ነው ወይስ ሥምና መሪ እያደለ ፓርቲዎችን ደልድሎ ይሆን?

አመለካከት

እነሬድዋን አሁንም’ኳ ተቃዋሚዎች የጥፋት ኃይል ፣ ተላላኪዎች እንደሆኑ አጠገባቸው ተቀምጠው ይሰብካሉ፡፡ አንድ መንግስት ተቃዋሚው የጥፋት ኃይል እንደሆነ እንጂ ከእርሱ ጋር የሚፎካከር ግን ሕዝቡ በድምጽ የመጨረሻውሳኔ የሚሰጥበት እንደ ሆነ ካላመነ እንደዚህ ያደርጋል፡፡ ለክርክር ሲቀመጡ እጣ ሲያወጣ ኢህአዴግ ለብቻ ተቃዋሚ በአንድነት በሌላ ወገን፡፡ የክርክር ሰዓት ሲመድብ ለገዢው ከ250% በላይ በተቃዋሚ ላይ ጨምሮ ይሰጣል፡፡ በተገኘው ጥቃቅን መንገድ ሁሉ ለመጠቀም የገዢ ተከራካሪዎች በቁጥር እንዲበልጡ፣ የሚከራከሩባቸው መድረኮች እንዳይመጣጠኑ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ እኩል ልዕልና ኖሯቸው ሕዝቡ ነጻ ፍርዱን እንዲሰጥ የተቀመጡ ተከራካሪዎች እንደሆኑ አያምንም፡፡ ግና መድብለ ፓርቲ እንዳለ ይሰብካል፡፡ ፍትሐዊና ሉዓላዊ ሥልጣን ለሚቃወሙት ሳይሰጥ! ይህ ማለት ከሕዝቡ ቀድሞ እርሱ ውሳኔ አሳልፏል እንደ ማለት ነው፡፡ እንዲህ እንደተባለ፡- አሜሪካዊ፣ ሩሲያዊና ኢትዮጵያዊ አንድ ላይ እየተጫወቱ ነው፡፡ አሜሪካዊው “እኛ ምርጫ ስናደርግ ሕዝቡ እየመረጠ ውጤቱ የደረሰበት ይታወቃል” ሲል ራሺያዊው “እኛም ተሻሽለናል ሕዝቡ ከመረጠ በኋላ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ውጤት ይታወቃል” አለ፡፡ ኢትዮጵያዊውም ቀበል አድርጎ “እኛ ከሁላችሁም ፈጣኖች ነን፡፡ ውጤቱ ሳንመርጥ በፊት ይታወቃል”

ተቃዋሚዎች እስካሁን ከፈር የለቀቀ ስድብም ሆነ ወቀሳ በኢህአዴግ ሲያቀርቡ አላየሁም- አትንኩኝ ካላለ በቀር፡፡ ይልቅ እስር ቤቱን የሞሉት እነሱ፣ አሸባሪዎች እነሱ፣ የጥፋት ኃይል ተብሎ የሚታወጅላቸው ለእነርሱ ነው፡፡ ኢህአዴግን ግን በዚህ አናማውም በ1997 አብረውት የተፎካከሩትና በሕዝብ ዘንድ የነበረውን ሌጣ ድጋፍ ያሳዩት ተቃዋሚ መሪዎችን በሃገር ክህደት እስር ቤት የወረወረው እርሱ ነው፡፡ እንግዲህ ከ’ከሃገር ከሃዲዎች’ ጋር ነበር ሲፎካከር የነበረ- ሊያውም መንግስት ለመሆን…. ወይ ግሩም!

ቀጣዩ የኢህአዴግ አዝግ ለቅሶውና የጋዜጠኞች የገደል ማሚቶ ጥያቄ “አማራጭ የላችሁም!” የሚለው ነው- እንደ ሬድዋንና አስመላሽ ልቅሶ፡፡ አማራጭ ምንድነው? እስካሁን ኢህአዴግ በሚያቀርባቸው ምረጡኝ ዘመቻ፣ ክርክር ሆነ መግለጫ ስለ እያንዳንዱ ፖሊሲ ዝርዝር ሲያቀርቡልን ሰምቼ አላውቅም፡፡ ፖሊሲው ስላመጣቸው ለውጦች እንጂ! በለውጡ ስለተገኙ እድገቶች፣ ልማቶች…. ብላ ብላ ይህ ስህተት ነው አላልኩም፡፡ ተቃዋሚዎች ይህኛው የኢህአዴግ ፖሊሲ ትክክል አይደለም፣ የርዕዮት አስተሳሰቡ ስህተት አለበት፣ ወይም አስተዳደሩን አላወቀበትም ሲሉ ሌላ መንገድ አለ ማለታቸው ነው፡፡ ምን እንደሆነ መንገዳቸው ለማወቅ ፕሮግራማቸውን ማንበብ ነው፡፡ በዓመታት በሚገኝ የደቂቃ መከራከሪያ ላይ ለአካዳሚ ነጻነት እንሰጣለን ይኸውም የአካዳሚ መሪውን በብቃትና በውጤት በመሾም….. እየተባለ መዘርዘር አይቻልም፡፡ መንግስት (ኢህአዴግ) ራሱ ሊብራል (እነሱ አወቁትም አላወቁትም) ናቸው እያለ እንዴት አማራጭ የርዕዮት የላቸውም ይባላል፡፡ዶ/ር መራራ እንዳለው ሌላ ሙዚቃ ይቀየርልን፡፡ የኢህአዴግ መሠረታዊ ችግር እነርሱ (ተቃዋሚዎች) እንዲህ ናቸው ብሎ ለሕዝብ መንገር የፈለገውን ብቻ ይናገራታል እንጂ እነሱ የሚያወሩትን አይሰማም፡፡ ‘እኔ እንዲህ ነኝ’ ሲሉት አጠገቡ የሰማውን ሳይሆን እርሱ ሕዝብ እንዲያውቃቸው የሚፈልገውን ‘እንዲህ ናቸው’ ይላል- እንደ ልብ አውልቅ!

ሌላው አሰልቺ ዜማ ተቃዋሚዎች መሠረታቸው አክራሪ ዲያስፖራ ነው ይላል የሁሴን ልጅ! በእርግጥ የተቃዋሚዎች አሳብ የምሁርነት ስለሆነ የጥቂት ምሁራን (elite)እንጂ ሕዝቡን እንደማይወክል በአስመላሽ በኩል ነግሮናል፡፡ የሠማያዊው ኢንጂነር ይልቃል “ዲያስፖራው በት/ት፣ በፖለቲካ ምክንያት ከሃገር የተለየ ቢሆንም በት/ት በልምድ ማገዝ የሚችሉ የሃገር ልጆች ስለሆኑ እነርሱን የሚያቅፍ ፖሊሲ ቀርጸናል” ብለዋል፡፡ ጨምረውም “በኢትዮጵያ ታሪክ እንደኢህአዴግ የፈረንጅ ጥገና የሆነ መንግስት የለም፡፡ ብድር አገኛለሁ ብሎ በፓርላማ የሚያጸድቅ መንግስት!”

የኢኮኖሚ ፕሮፌሰሩ ዶ/ር ጌታቸው እንዲህ ይላሉ “ኢህአዴግ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ መንግስታት በተለየ ሶስት ነገሮች ተጠቃሚ ነው፡፡ የመጀመሪው የውጭ ብድር የተሰረዘለት ሲሆን በአዲስ ጀምሮ ከዓመታዊ ምርት (GDP)ጋር የተቀራረበ ከ32 ቢሊየን በላይ ብድር ለትውልዱ እዳ አስተላልፏል” እኛ መጨመር እንችላለን በሶቨርኒቲ ቦንድ ሽያጭ አንድ ቢሊየን ዶላር እንዳገኘ በገሃድ መንግስት አስታውቋል፡፡ ይሄ ሁሉ የትውልድ እዳ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ይላሉ ዶ/ር ጌታቸው “ከብሔራዊ በጀት እኩል የሆነ ግን የቀደሙት ሁለት መንግስታት ያልነበረ የሀዋላ (remittance) ገቢ ውጪ ካለ ኢትዮጵያዊ አግኝቷል፡፡ በተጨማሪ ኢህአዴግ ከኤርትራ ጦርነት ውጪ እንደ ደርግ በጦርነት ውስጥ ያልነበረ መንግስት ነው፡፡” በእነዚህ ሁሉ መደላደል ውስጥ ሁኖ ነው እንግዲህ ዓመታዊ እድገት እንዳመጣ እየነገረን ልብሳችን በላያችን የሚያልቀው፡፡ ዶ/ር ጌታቸው “ኢህአዴግ እንደሚለው ዓመታዊ እድገት መጥቶ ቢሆን ኑሮ እካሁን መካከለኛ ገቢ ያላቸው እንሆን ነበር” ብለዋል፡፡

የሠብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቶች

እነሬድዋን ነጥብ ያገኙበት ነገረ ጉዳይ ይሄ ይመስለኛል፡፡ ተቃዋሚዎች እናመጣለን የሚሉት የሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቶች በህገ መንግስቱ ላይ እንደሰፈሩ በመጥቀስ፡፡ እርግጥ ነው የ20 ዓመት እድሜ ያለው ሕገ መንግስት አስተያየት እንዲሰጥበትና ውይይት እንዲደረግበት የማይሹት የእነርሱ ፍጹማዊ ሕግ ነው፡፡ ዶ/ር መራራ “ህገ መንግስት ማርቀቁን እኛ የተሻለ እንደምንችል አትጠራጠሩንም፡፡ ታምናላችሁ” ብለዋል- የመማርና ጫካ የመቆየት ልዩነት ሲያስረግጡ፡፡ እርግጥ ነው የዲሞክራሲ መብቶች መገለጫ ተቋማቱ ተዘርግተዋል እካሁን ‘ወፌ ቆመች’ ለማለት ባይታደሉም፡፡ ምሳሌ ምርጫ ቦርድ አስካሁን ስምምነት የፈጠረና መግባባት ያመጣ ተቋም አይደለም፡፡ አሁንማ ፓርቲ መከፋፈልና መጣመርን ማደናቀፍ ይፍአዊ ሥራው አድርጎት የተቋሙ የገለልተኛነት ጥያቄን ገሃድ አውጥቶቷል፡፡ ዶ/ር መራራ “የእንባ ተቋም የሚያለቅሰውን ነው ወይስ የሚያስለቅሰውን የሚያብሰው?” ሲሉ በመጠየቅ የተቋማትን ገለልተኛነት በመቃወም ያሉት ተቋማት የአንድ ፓርቲ መጠቀሚያ ሁነዋል ይላሉ፡፡

እውነታው ግን ዜጋው የፈለገውን አመለካካት ማራመድ፣ ሀሳቡን በነጻነት መግለጽ፣ በነጻነት መደራጀት፣ ያለተጽእኖ እምነቱን ማራመድ ተፈቅዷል፡፡ እኚህን ሁሉ ያደረገ ግን ማደሪው እስርቤት ሁኗል፡፡ የፈለገውን አመለካከት የሚያራምድ ዜጋ፣ በነጻነት የሚጽፍ ጋዜጠኛ፣ የተደራጀ የፓርቲ አባል፣ ስለእምነቱ ጣልቃ ገብነት ለመቃወም የጮኸ ሁሉ ማጎሪያው ወህኒ ቤት ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ – ሁሉም በአሸባሪነት!! የሃይማኖት ነጻነት ስላለ ይኸው አስካሁን የታሰሩ ይፈቱ እያለ የሚሰማው ያጣ ድምጽ ይጮኻል፡፡ ለማያውቅሽ .. አለ!

ሚዲያ

የዲሞክራሲና የነጻነት መገለጫ አድርገው እነሬድዋን የገለጿቸው፡- ከ1300 በላይ የኅትመት ፍቃድ፣ ከ20 በላይ ራዲዮ፣ ከ10ሺህ በላይ መጻሕፍት መታተም ብለዋል፡፡ ከኢ/ር ይልቃል “አንድ ቲቪ!”ለሚለው ግን ምላሽ የላቸውም፡፡ ከ1300 በላይ ፍቃድ ከተሰጣቸው ኅትመት ሚዲያዎቹ የት ገቡ? አሁን ምን አማራጭ ኅትመት ሚዲያ አለ? ከዚህ ይልቅ እየፈቀዱ የሚዘጓቸው ሚዲያዎች መቁጠር ይቀላቸዋል!

ኢህአዴግ ጎረቤቶቹን ሱዳንና ኬንያን ለማየት እፍረት ስለሚይዘው አጎንብሶ ደርግና ንጉሡን እያወሳ ይኸው ለዚህኛውም ምርጫ ደርሷል፡፡ የሠማያዊው ዮናታን እንዳለው “ኢህአዴግ ዘመኑን የማይዋጅ- ያረጀ ፓርቲ ስለሆነ ንጽጽሩ ከደርግና ከንጉሡ ጋር ነው” ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ስላለ እርሱ የፈረጃቸውን ማንም እንዲያጽድቅ አይፈልግም፡፡ በፍርድቤት አሸባሪ የተባሉትን ሠማያዊ ጀግና ነጻ አውጪ ይላቸዋል ሲሉ እነሬድዋን ይከሳሉ፡፡ መቼም ይሄን ሲሉ ‘ነገ.. ይሄ ምርጫ ይለቅ እንጂ… እዛው ትገቢያታለሽ’ በማለት ማኖ እያስነኩ ይመስላል፡፡ ተቃዋሚዎችና ሕዝቡ’ኮ በፍትህ ሥርዓቱ እምነት የለውም ስለዚህም የፍትህ- ርትዕ ለውጥ ለማምጣት ይታገላል፡፡ ታዲያ ይህ ሃሳብ ‘አሸባሪነት’ ይሆን?? በግፍና ያለፍርድ (ያለአግባብ) ተበይኖብኛል ሲል ለሚታገል ይሄን ማላዘንህን ካልተውህ አስገባኻለው ማለት ያው እንግዲህ የዲሞክራሲ መብት መገለጫ ሳይሆን አይቀርም!

ተቃዋሚዎቹ በአንድነት እንደሚያምኑት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ አስመሣይ (pseudo-) ዲሞክራሲ ነው፡፡ የቅብ ዲሞክራሲ- ስሙ እንጂ ተግባሩ የሌለ፡፡ በስተመጨረሻ የተነሣው ጥያቄ እርግጥ ተገቢ ይመስላል፡፡ የአንድነቱ አቶ ትግስቱ “ኢህአዴግ በምርጫው ቢሸነፍ ስልጣን ያስረክባል ወይ?” ሲሉ የአትፓው “ለዚህ የ1997ቱን ተመልከቱ” ይላል፡፡ መድረክና አንድነት መልሱ በሕዝቡ ጫንቃ ላይ እንዳረፈ ሲገልጹ ሠማያዊ አማራጩ ሁለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የመጀመሪያው ኢህአዴግ ሕዝብ ባልመረጠው ጊዜ ለመውረድ ማመንና መቀበል ይኖርበታል፡፡ ይሄን ለውጥ እንዲያመጣ መታገል፡፡ ሁለተኛው ሕዝብ ነጻነቱን ለማስከበር መደራጀትና መብቱን መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ሁለቱም አማራጮች ላይ ዋና ተጽእኖ አድራጊውም ሆነ ሆ ባይ ተንቀሳቃሹ ሕዝብ ነው!! ሁሉም ጥላ ያደረጉት የሕዝብ ስም ነውና!ኢህአዴግ እንዲህ ይላል “መጠርጠር ብቻ ለሞት የሚያበቃበት ጊዜ አልፏል” ስለዚህም ሕዝብ አርፎ እንዲቀመጥ ሠማያዊን እንዲህ ይለዋል “ጭር ሲል አይወድም!”

  በጭርታ ውስጥ ግን የሕዝብ ድምጽ የለም

                                           ብሶትና መብሰክሰክ እንጂ!!

 

 

3 thoughts on “የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ምልከታ

Add yours

  1. እውነታው ግን ዜጋው የፈለገውን አመለካካት ማራመድ፣ ሀሳቡን በነጻነት መግለጽ፣ በነጻነት መደራጀት፣ ያለተጽእኖ እምነቱን ማራመድ ተፈቅዷል፡፡ እኚህን ሁሉ ያደረገ ግን ማደሪው እስርቤት ሁኗል፡፡ የፈለገውን አመለካከት የሚያራምድ ዜጋ፣ በነጻነት የሚጽፍ ጋዜጠኛ፣ የተደራጀ የፓርቲ አባል፣ ስለእምነቱ ጣልቃ ገብነት ለመቃወም የጮኸ ሁሉ ማጎሪያው ወህኒ ቤት ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ – ሁሉም በአሸባሪነት!! የሃይማኖት ነጻነት ስላለ ይኸው አስካሁን የታሰሩ ይፈቱ እያለ የሚሰማው ያጣ ድምጽ ይጮኻል፡፡ ለማያውቅሽ .. አለ!እውነታው ግን ዜጋው የፈለገውን አመለካካት ማራመድ፣ ሀሳቡን በነጻነት መግለጽ፣ በነጻነት መደራጀት፣ ያለተጽእኖ እምነቱን ማራመድ ተፈቅዷል፡፡ እኚህን ሁሉ ያደረገ ግን ማደሪው እስርቤት ሁኗል፡፡ የፈለገውን አመለካከት የሚያራምድ ዜጋ፣ በነጻነት የሚጽፍ ጋዜጠኛ፣ የተደራጀ የፓርቲ አባል፣ ስለእምነቱ ጣልቃ ገብነት ለመቃወም የጮኸ ሁሉ ማጎሪያው ወህኒ ቤት ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ – ሁሉም በአሸባሪነት!! የሃይማኖት ነጻነት ስላለ ይኸው አስካሁን የታሰሩ ይፈቱ እያለ የሚሰማው ያጣ ድምጽ ይጮኻል፡፡ ለማያውቅሽ .. አለ!

  2. ሠማያዊ አማራጩ ሁለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የመጀመሪያው ኢህአዴግ ሕዝብ ባልመረጠው ጊዜ ለመውረድ ማመንና መቀበል ይኖርበታል፡፡ ይሄን ለውጥ እንዲያመጣ መታገል፡፡ ሁለተኛው ሕዝብ ነጻነቱን ለማስከበር መደራጀትና መብቱን መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ሁለቱም አማራጮች ላይ ዋና ተጽእኖ አድራጊውም ሆነ ሆ ባይ ተንቀሳቃሹ ሕዝብ ነው!! ሁሉም ጥላ ያደረጉት የሕዝብ ስም ነውና!ኢህአዴግ እንዲህ ይላል “መጠርጠር ብቻ ለሞት የሚያበቃበት ጊዜ አልፏል” ስለዚህም ሕዝብ አርፎ እንዲቀመጥ ሠማያዊን እንዲህ ይለዋል “ጭር ሲል አይወድም!”ሠማያዊ አማራጩ ሁለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የመጀመሪያው ኢህአዴግ ሕዝብ ባልመረጠው ጊዜ ለመውረድ ማመንና መቀበል ይኖርበታል፡፡ ይሄን ለውጥ እንዲያመጣ መታገል፡፡ ሁለተኛው ሕዝብ ነጻነቱን ለማስከበር መደራጀትና መብቱን መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ሁለቱም አማራጮች ላይ ዋና ተጽእኖ አድራጊውም ሆነ ሆ ባይ ተንቀሳቃሹ ሕዝብ ነው!! ሁሉም ጥላ ያደረጉት የሕዝብ ስም ነውና!ኢህአዴግ እንዲህ ይላል “መጠርጠር ብቻ ለሞት የሚያበቃበት ጊዜ አልፏል” ስለዚህም ሕዝብ አርፎ እንዲቀመጥ ሠማያዊን እንዲህ ይለዋል “ጭር ሲል አይወድም!”

    1. በጭርታ ውስጥ ግን የሕዝብ ድምጽ የለም

      ብሶትና መብሰክሰክ እንጂ!

      ብሶትና መብሰክሰክ እንጂ!!

Leave a reply to Ethiopian Person Cancel reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑