እግዚአብሔር ሊሞት ይችላልን?

እግዚአብሔር ሊሞት ይችላልን?

To Read in Pdf

ሰው ልጅ ስለምን ይሞታል? ለእኛ ለሰዎች ለመመለስ የሚቀለን ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ መጽሐፍ “የኃጢአት ደመዎዝ ሞት ነው” ሮሜ 6፥13 ያለውን ጠቅሰን ኃጢአትን የሚሠራት ሁሉ ይሞታል ብንል ሁለት ትርጉም ይሰጠናል፡፡ የመጀመሪያው ሞት ወደዚች ምድር ሀልዎት አግኝቶ የተገለጠው በመጀመሪያው አለመታዘዝ (አለመታዘዝ ኃጢአት ሁኗልና) ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህም ለኃጢአት ዋጋ ሞትን ከፈለ፡፡ ሁለተኛው በምድር ለሚኖር ሰው ሁሉ በኃጢአት ሕይወት ከተገዛ ለተገዛበት ሕይወት ዋጋው ሞት ነው ሲል እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ግና ኃጢአትን ያልተወዳጀችስ ሕይወት ከሞት ትተርፍ ዘንድ ይቻላታልን? ብንል እዚህ ምድር ያለሰው ሁሉ እንዲሞት እናውቃለንና አይቻላትም እንላለን፡፡ ዳሩ ልናነሣው የሚገባን ጥያቄ ስለሥጋ ሞት ነው ወይስ ስለነፍስ የሚለው ይሆናል፡፡ ይሄም ጥያቄያችን ቢሆን ነፍስ ሕያዊት (የማትሞት) ነች ከሚለው ሃይማኖተ ፍልስፍና ጋር ይላተምብናል፡፡ ስለዚህም የሞት ብያኔ (ትርጉም) ላይ ሊያግባባን የሚችለውን ቀላሉን እንመርጣለን፡፡ ሞት ማለት የነፍስና ሥጋ መለያየት የሚለውን ከሌሎች ብያኔዎች መርጠን እንወስዳለን፡፡ ለጊዜው ‘ሞት ነፍሳችን ከሥጋችን መለየቷ የሚፈጥረው ህልውና ነው’የሚለውን በመውስድ የጹሑፋችን መነሻ ጥያቄያችንን እናቅርብሰው ለምን ይሞታል? ሥጋው ከነፍሱ ለምን ትለያለች? ሰውስ ይሄን ማስቆም እንዴት አቃተው?

በአዕምሮአችን ሊመላለስ የሚችለው እውነታ ሰው የመሞት መሻት እንደሌለው በሕይወታችንና በኑሮ ልምዳችን መረዳታችን ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ ሰው ለዘላለም መኖር እንደመፈለጉ ሞትን ማስቀረት አለመቻሉ መሻቱ ብቻውን ሊለውጠው ያለ ነገር እንደሌለና ይልቁን ኃይል/ሥልጣን እንዲያስፈልግ ያስረዳናል፡፡ እናም የሰው ልጅ ይህን የተገለጠ ሞት የማስቀረት ሥልጣንና ኃይል የለውም ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ይታደለዋል እንጂ አይታገለውም! ቀኑ ሲደርስ እየጠበቀ እጁን ለሞት ያቀብላል-ፍንግል፡፡ በሌላ አነጋገር ሰው የሚሞተው (ሥጋው ከነፍሱ የምትለየው) ሞት እርሱ ሊያስቆመው የማይችለው ኃይል ስለሆነበት ነው፡፡ የተፈጥሮ ሂደትን ለማስታጎል ቢጥርም’ኳ ሞትን የመገዳደር አንዳች አቅም የሌለው ምስኪን ነው-የሰው ልጅ! url

ይሄን ሰዋዊ ሃሳባችንን ይዘን ነው እንግዲህ ርዕሳችንን የምናነሣው፡ ‘እግዚአብሔር ሊሞት ይቻለዋልን?’ የጥያቄያችን አስኳል ‘ሰውስ ይቻለዋል ምክንያቱም ደካማና ምስኪን ነውና’ የሚለው ሃሳባችን ሲሆን መሠረቱ ደግሞ ‘እግዚአብሔር ልዕለ ኃያል፣ ሁሉን ቻይና አድራጊ ፈጣሪ ነው’ የሚለው ይሆናል፡፡ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው በኃይላት ሁሉ ላይ የሰለጠነ ልዕለ ኃያል እንዴት ለሞት የተገባ ይሆናል? ዘላለማዊ የሆነው ባህርይው እንዴት ለሞት የተገዛ ሆነ? ለሞት በተሰጠ ጊዜ ሌላ ልዕለ ኃይል ሰልጥኖ አሊያም በከሃሊነቱ እጥረት ገብቶበት (ክብር ይግባውና) ካልሆነ እንዴት ሊሞት ይቻለዋል? ብለን ምሉዕነት በጎደለው መረዳታችን አቅም ከሰዋዊ ህሊናችን አቅንተን እንጠይቃለን፡፡ አባ ቴዎድሮስ ማልቲ ዘእስክንድርያ በተመሣሣይ ርዕስ በጻፉት መጣጥፋቸው ላይ ባስቀመጡት ታሪክ እንጀምር፡፡

“ክርስቲያን የሆነውን ቫዚየር (ርዕሰ ብሔር) ንጉሡ ከልብ በመነጨ ስሜት እንዲህ ጠየቀው

“እወድሃለሁ፣ አምንሃለው እንዲሁም በምክርህና በጥበብህ እንደረካሁ ይሰማኛል፡፡ ግን አንድ የሚደንቀኝ ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ሰው እንደሆነና ለሰውዘር ሲል እንደሞተ ማመንህ ነው፡፡ ይሄ ነገር ሞኝነትና ድንቁርና አይደለምን?”

ቫዚየርም ስለእግዚአብሔር ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ ፍቅርና ሰውን እንዴት እንዳከበረው ለንጉሡ ነገረው፡፡ ስለሰው ልጅ ድኅነት እግዚአብሔር ያለውን ናፍቆት፣ለሰው ዘላለማዊ ክብር ለመስጠት ስላለው ፍላጎት አስረዳው፡፡ ዳሩ ግና ንጉሡ እነኚህን አሳቦች ሊቀበላቸው አልተቻለውም፡፡

በቀጣዩም ቀን ንጉሡና ቫዚየር በቤተ መንግስቱ አትክልት ሥፍር እየሄዱ ሳለ ከእነሱ ጎን ራቅ ብላ የንጉሡን ልጅ ህጻኑን ልዑል አቅፋ አሳዳጊዋ እየተጋዘች ነበር፡፡ ቫዚየርም ከአሳዳጊዋ ሕጻኑን ቀምቶ ወደ ሚወርደው ወንዝ ጥልቅ ወረወረው፡፡ ንጉሡም የማሰቢያ ሰኮንድ ሳያባክን እየሮጠ ወደ ወንዙ ሄደ ልጁንም ለማትረፍ ወደ ውኃው ዘሎ ሊገባ ሲል ቫዚየር እንዲህ ብሎ አስቆመው

“እሱ ያንተ ልጅ አይደለም የተጣለው አሻንጉሊት ነው” ንጉሡም ከተረጋጋ በኋላ እንዲህ አለው

“ንጉሥነትዎ! እንደንጉሥ የንግሥና አክሊል መድፋትና የንጉሥን ክብር ልብስ መልበስን በመናቅ ከክቡር ቦታዎ በመውረድ የሚወዱትን ልጅዎን ለማዳን ወደ ማዕበሉ ውኃ ሊዘሉ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር የበለጠ አፍቃሪ መሆን የሚችሉ ይመስልዎታልን? እግዚአብሔርስ ከማዕበሉ ሊጠብቀንና ሊያድነን ወደ ዚህ ዓለም ውቅያኖስ እንዴት አይመጣም?”

ንጉሡም እግዚአብሔር ሁሉንም ኃይል የሞላው (ልዕለ ኃያል) የሚለው ፍጹማዊ አስተሳሰብ ብቻ ማለት እንዳይደለ ማስተዋል ጀመረ፡፡ እርሱ ራሱ ፍቅር እንደሆነም እንጂ! ታዲያ ለልጆቹ ፍቅር ለማሳየት እንዴት አይቻለውም? ልጆቹ የሚያድናቸውን ፍለጋ ሲቃትቱ ያሉበትን ሁኔታ ካየ በኋላ ወደ እነርሱ ዓለም ወርዶ ለእነርሱ ይሞትላቸውዘንድ እንዴት እምቢ ሊል ይቻለዋል? ምክንያቱም ራሳቸውን ሊያድኑ ደካሞችና ምስኪኖች የሆኑ ልጆቹ ወደ እርሱ ክብርና ጸጋ በድጋሚ ይመለሱ ዘንድ የእርሱ ኃያልነትና ክብር ያስፈልጋቸዋል፡፡ እርሱ ብቻ ከወደቁበት ሊያነሣቸው ይቻለዋልና- እንዴት እምቢኝ ሊል ይቻለዋል?”

ታዲያ ለምን ሞትተመረጠ?

የእርሱ ኃይል ብቻ ከወደቁበት ሊያነሣቸው፣ ከታሰሩበት ሊፈታቸው፣ ከወጡበት ሊመልሳቸው፣ ከተራቆቱት ጸጋ ሊያላብሳቸው እንደሚችል ከተረዳን በኋላ የምንጠይቀው ጥያቄ ቢኖርካሉት የሰው ልጅን የማዳን መንገዶች ‘ሞት’ እንዴት ተመረጠ? የሚለው ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ ለዘመናት (ክርስቶስ እነርሱን እስኪመስል ድረስ) በጎውንም ሥራ በመሥራት መንገዱ ከእግዚአብሔር ጋር የተስተካከለለት ይሁን አሊያም በክፋት ተሞልቶ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው ሁለቱም ሽልማታቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡ በአለመታዘዝ ምክንያት በመጣ ቅጣት ከመኖሪያቸው ተባረው ገነትም ተዘግታ ነበር፡፡ ስለዚህም ይገቡባት ዘንድ የምትጠብቃቸው ሲኦል ብቻ ነበረች፡፡ የተዘጋችውን የገነት በር የሚያስከፍታት ጻድቅ እስኪመጣ ድረስ የሕይወታቸውን ጽድቅ ሳትመለከት መቆያቸው የነበረችው ሲኦል ነበረች፡፡ በዚህች ግዛት ላይ ሰልጥኖ የነበረው ሰይጣን ነበርና ማሰረ ብሔሩ አድርጓት ነበር፡፡ ነፍሳትን ሁሉ በሞት ኃይል እየነጠቀ በሲኦል አስሮ ያስቀምጥ ነበር፡፡  

አባ ቴዎድር የጠቀሱት ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ እንዲህ ይላል “ሰይጣን የሰው ዘር ሕይወት ሁሉ እስኪጠፋ እያንዳንዱን ሰው ይበላና የሆዱ ውስጥ እስረኛ እንዲሆኑ እንደሚሰበስብ ተኩላ ይመስለዋል፡፡ ሰይጣን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰው ሁኖ ባየው ጊዜ እንደ ማንኛውም አይነት ሰው እንደመሰለው አስቦ ነበረ፡፡ ዳሩ ይህ ሆድ [ሲኦል] ትንሣኤና ሕይወት የሚሰጠውን ክርስቶስን ሊይዘው አልተቻለውም፡፡ ክርስቶስም የሞት መግቢያውን አፈራረሰው፤ በእርሱ የሚያምኑትንም ከዘላለም ሞት ይተርፉ ዘንድ አዳናቸው፡፡ በሞት ውስጥ ሞትን አጠፋው፡፡ ቤተክርስቲያንም ‘በሞቱ ሞትን ድል ነሣ፤ በመቃብር ውስጥ ላሉቱ የዘላለም ሕይወትን አደላቸው!’ እያለች የምትዘምረው ለዚህ ምክንያት ነው፡፡”

ስለዚህም የሰውን ልጅ ለማዳን የመጀመሪያው ብቸኛ መንገድ በሞት ኃይል ተነጥቆ ወደሲኦል መግባት አስፈላጊ ነበር፡፡ ነፍሳት ሁሉ የእስራት መገኛቸውና የሰይጣን የግዛት ብሔር (ሃገር) በሆነችው ሲኦል አርፈዋልና፡፡ በሞትም ወደዚህች መንደር መምጣት አንድም የሲኦል ድል መንሣትን ለመንጠቅ አንድም የነፍሳትን አርነት ለማወጅ ብቸኛው ምርጫ ነበር፡፡መሲሁ የሰውልጅ (ክርስቶስ) ከሞት በኋላ ወደ ሲኦል በመሄዱ የሲኦል የጽድቅ ሕይወታቸው እንኳ ሳይበግራት አፍሶ የማስገባት ስልጣኗ ተገፈፈ፡፡ ታስረው በግዞት የነበሩት ነፍሳትም ሁሉ ነጻነት ወጡ፡፡ መጽሐፍ እንዲህ እንደሚል “ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ። ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ….ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” 1ኛ ቆሮ 15፥54፣55“ስለዚህምክንያትኃጢአትበአንድሰውወደዓለምገባበኃጢአትምሞት፥እንደዚሁምሁሉኃጢአትንስላደረጉሞትለሰውሁሉደረሰ፤ነገርግንበአዳምመተላለፍምሳሌኃጢአትንባልሠሩትላይእንኳ፥በአንዱምበደልሞትበአንዱበኩልከነገሠ፥ይልቁንየጸጋንብዛትናየጽድቅንስጦታብዛትየሚቀበሉበአንዱበኢየሱስክርስቶስበኩልበሕይወትይነግሣሉ።” ሮሜ 5፥12-17

የእርሱ ሞት አስፈላጊ የሆነበት ምን ምክንያት ነው?

ሞትስ ይሁን ካልን መስዋዕት መሆን የሚችል ብዙ ምርጫ እያለ የእርሱ (የልጁ)ሞት ለምን ግድ አለ? የሚለው ቀጣይ ጥያቄያችን ይሆናል፡፡ ሞትን ድል መንሣት፣ ሲኦልን ማፈራረስና ትንሣኤን ለማብሰር በሞት መስዋዕት መሆን አስፈላጊ ነው ስንል ይህን ሊያደርግ የሚችለው ማነው የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከሊቀ ነብያቱ ክርስቶስ በፊት የነበሩ ብዙ ነብያት እስከሞት በተገባ ሕይወት ተመላልሰዋል ዳሩ የእነርሱም ነፍስ ከሲኦል ምንደኝነት አልተረፈችም፡፡ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንገድ በመምራት ብዙ ሕይወትን ቢያተርፉም እንኳ ካተረፏቸው ነፍሳት ጋር በሲኦል አድረዋል፡፡ ማንም ከሰው የተፈጠረ ይሄን ኃይል መጋፋት አልተቻለውም የመለኮት ጸጋ ቢበዛላቸውም እንኳ! አስቀድመን እንዳልነው የጥያቄያችን አስኳል ሰው ደካማና ምስኪን ፍጡር ነው የሚለው ነውና፡፡ ስለዚህም ልዕለ ኃያል የሆነ ሞትን ለማሸነፍ የሚሞት፣ ነፍሳትን ከታሰሩበት ለማውጣት ወደሲኦል ገብቶ በድል አድራጊነት የሚወጣ፣ የመውጊያ ጦርን የሚሰብር፣ የእስራት ሰንሰለትን የሚበጣጥስ ያስፈልጋል ይኽም ከመለኮታዊ ሥልጣን ና ኃይል በቀር ለማንም አይቻለውም፡፡ ስለዚህ ነው በሞት የማዳን ብቸኛ መንገድ የነበረውን የማዳን ሥራ በራሱ በልጁ እንዲሆን ያደረገው፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ከልደቱና ከሞቱ ጋር የተሳሰረው እንደ እኛ የሰዎች ሕይወት የመጀመሪያና የፍጻሜ ሁለት እውነታዎች ነው፡፡ ይሄም አስፈላጊ የሆነበት የእርሱ የሕይወቱ ሁሉም አኗኗር በእኛ የአኗኗር ሕይወት ውስጥ የተተገበረ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ቅዱስ ኢራንየስ እንዲህ እንዳለ “ተፈጥሯችንን ለሚቀይረው ኃይል ሁለቱንም ጥጎች እንዲደርስባቸው አስፈላጊው ነበር፡፡ መነሻውን ይነካና እስከ ፍጻሜው ይደርስ ዘንድ አስፈላጊው ነበር፡፡ በዚህም በሁለቱ መሐል ያለው ሁሉም ነገር ይሸፈንበታል፡፡”

ቅ/ኤፍሬም ሶሪያዊ “ሞት ጌታችንን (ሰው የሆነውን ጌታ) ናቀው፡፡ ጌታም በተራው መንገዱን ድል በማድረግ ሞትን ናቀው፡፡ የሞትን ኃይል ያጠፋው ዘንድ ራሱን በፈቃዱ ለሞት አሳልፎ ሰጠው፡፡ መስቀልን ተሸክሞ በመሄድ በመስቀሉ ላይ ራሱን አሳልፎ ለሞት ሰጠበት፡፡ ከመሞቱ በፊት ሞትን ጠርቶ ከመቆያው (Hades) አወጣው! በዚህ ወቅትም ሞት ተሸነፈ፡፡ ሞትንም ይዋጋው ዘንድ መለኮት በሥጋ ውስጥ ተሰወረ፡፡ ስለዚህምሞት ተገደለ…. ግና ከዛም እርሱም ተገደለ! ሞት ተፈጥሮአዊ ሕይወትን ሲያጠፋ ነበረ ግና ልዕለ ኃያሉ ሕይወት እርሱን አጠፋው፡፡”ዮሐንስ አፈወርቅ የክርስቶስን የሞትን ኃይል እንዴት እንዳፈረሰው ሲያስረዳን “ትጉህ እረኛ መንጋውን የሚያሸብረውንና በጎቹን የሚያጠፋውን አንበሳ ማርኮ ይይዘዋል፡፡ ጥርሱን ሰባብሮ፣ ጥፍሮቹን ነቃቅሎ፣ ፀጉሩን ነጭቶ ለህጻናት እንዲጫወቱበት አሻንጉሊት እንዲሆን ይተወዋል፡፡ ክርስቶስ የሰዎች ፍርሃት ምንጭ በነበረው ሞት ላይ ድል የነሣው በዚህ መልኩ ነው፡፡ እርሱ ሞት የሚያሸብርበትን ንብረቱን ቀማው፡፡” ብሏል፡፡

የክርስቶስ በሲኦል ላይ የነበረው ኃይል “እንደ ተርታ ሰው ወደ መቃብር ወረደ እናም የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ ሁኖ በክብር ወጣ፡፡እንዲህ እንደተጻፈ “ከመራራ ውስጥ አንዳች ጣፋጭ መጣ” ሞት መራራ ሲሆን ኢየሱስ ግን እርሱን ለቀመሱት ጣፋጭ ነው፡፡ ስለዚህም ለሕዝብ ሁሉ ምግብ ሆነ” ሲል ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ገልጾታል፡፡

 

crucified_jesus__the_face_by_devcager-1024x675በክርስቶስ የማዳን ሕይወት ላይ አንዳንዶች ጥያቄዎች ይፈጠርባቸዋል፣ ለማመንም ይቸገራሉ፡፡ ለምን? አባ ቴዎድሮስ ጥያቄዎቻቸውን ለመዳሰስ ይሞክራሉ፡፡

አንዳንዶች ክርስቲያኖች በመለኮታዊ ሞት ያምናሉ ብለው ያስባሉ፡፡

እርግጡ ግን ይህ አይደለም! ሰው የሆነው እግዚአብሔር በመለኮቱ አልሞተም ከሰው በነሣው (በወሰደው) ሥጋ ሞተ እንጂ፡፡ ሞት ህልው የሚሆነው ነፍስ ከሥጋ በምትለይበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ሥጋ ሲሞት ነፍስ ግን መኖር ትቀጥላለች፡፡

ሌሎች ደግሞ የክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ደካማነት ነው ብለው ያስባሉ፡፡

እነርሱ ግን ያልተረዱት ነገር ቢኖር ክርስቶስ ከራሱ በጎ ፈቃድ ከወጣ ፈቃደኝነት እንደሞተ ነው፡፡ እርሱ እንዲህ እንዳለ “ነፍሴንም ስለበጎቼ አኖራለሁ፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ” ዮሐ 10፥15፣18

እኛ ከሞት ጋር ያለን ልምድ ሀዘንና ብዙውን ጊዜ ከኃጢአተኛነት እና ከሥጋ ድካም ጋር እናያይዘዋለን፡፡

ግና ክርስቶስ ሞትን የኃጢአት ፍሬ ከመሆን ወደ የተለየ የፍቅር ሥራ ለወጠው፡፡ በዚህም ፍቅር ውስጥ የሰይጣንን ሰንሰለት ሊሰብርና ወደ ገነት እንድንገባ ነጻ ሊያወጣን ሲል ሞተ፡፡ የእርሱ ሞት የእኛ የመደሰታችን ምንጭ ነው፡፡ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ክርስቶስን እንመልከተው፥ እርሱ ነውርን ንቆ የውርደት ምልክት የነበረው መስቀል ላይ በመዋል የደስታችን ምንጭ ሠራልን (ዕብ 12፥2) “እንደሰውተገኝቶራሱንአዋረደ፥ለሞትምይኸውምየመስቀልሞትእንኳየታዘዘሆነ”ፊልጵስዩስ 2፥8

የመለኮታዊ ፍቅር ሊጋሩት የሚገባ ነው፡፡ ቁስላችንን ለመፈወስ፣ ሞትን ለማጥፋትና ለሰው ልጅ ይቅርታ ለማድረግ እግዚአብሔር በትዕዛዝ አላደረገውም እርሱ ግን የሚደንቅ ፍቅሩን ተጠቀመ፡፡ ሕይወታችንን ሊካፈል መጣ፤ ሞታችንንም ጭምር እንዲሁ፡፡ ወደዘላለም ሕይወት ይወስደን ዘንድ ከመቃብር አደረ፡፡ የሚሞተውን ሥጋ ከእኛ ጋራ ተጋራህ ከነፍስ ሞት ታርቅልን እና የዘላለም ህይወት ታድለን ዘንድ፡፡ ከፍቅርህ ጋር ወደ እኛ ዓለም መጣህ፡፡ ከእኛ ጋራ መቃብር ወረድህ ስለዚህም እኛም ያንተን ሞት በሥጋችን እንሸከም ዘንድ እንፈልጋለን፡፡ (2ቆሮ 4፥10)

ይሄን ጽኑና ታላቅ ፍቅር ባሰብሁ ጊዜ ሞትን ፈራሁ እርሱ እርግማን ነው፡፡ አሁን ግን እርሱን እፈልገዋለሁ መባረክ ነውና፡፡ ምክንያቱም ወዳንተ መሄጃ መንገዴ ነውና ልቤ ትፈልገዋለች፡፡

2 thoughts on “እግዚአብሔር ሊሞት ይችላልን?

Add yours

  1. የሰው ልጅ ለዘመናት (ክርስቶስ እነርሱን እስኪመስል ድረስ) በጎውንም ሥራ በመሥራት መንገዱ ከእግዚአብሔር ጋር የተስተካከለ ይሁን አሊያም በክፋት ተሞልቶ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያላደረገው ሁለቱም ሽልማታቸው ተመሳሳይ ነበር፡፡ በአለመታዘዝ ምክንያት በመጣ ቅጣት ከመኖሪያቸው ተባረው ገነትም ተዘግታ ነበር፡፡ ስለዚህም ይገቡባት ዘንድ የምትጠብቃቸው ሲኦል ብቻ ነበረች፡፡ የተዘጋችውን የገነት በር የሚያስከፍታት ጻድቅ እስኪመጣ ድረስ የሕይወታቸውን ጽድቅ ሳትመለከት መቆያቸው የነበረችው ሲኦል ነበረች፡፡ በዚህች ግዛት ላይ ሰልጥኖ የነበረው ሰይጣን ነበርና ማሰረ ብሔሩ አድርጓት ነበር፡፡ ነፍሳትን ሁሉ በሞት ኃይል እየነጠቀ በሲኦል አስሮ ያስቀምጥ ነበር፡፡
    ስለዚህም የሰውን ልጅ ለማዳን የመጀመሪያው ብቸኛ መንገድ በሞት ኃይል ተነጥቆ ወደሲኦል መግባት አስፈላጊ ነበር፡፡ ነፍሳት ሁሉ የእስራት መገኛቸውና የሰይጣን የግዛት ብሔር (ሃገር) በሆነችው ሲኦል አርፈዋልና፡፡ በሞትም ወደዚህች መንደር መምጣት አንድም የሲኦል ድል መንሣትን ለመንጠቅ አንድም የነፍሳትን አርነት ለማወጅ ብቸኛው ምርጫ ነበር፡፡ ከመሲሁ የሰውልጅ (ክርስቶስ) ሞት በኋላ ወደ ሲኦል በመሄዱ የሲኦል የጽድቅ ሕይወታቸው እንኳ ሳይበግራት አፍሶ የማስገባት ስልጣኗ ተገፈፈ፡፡ ታስረው በግዞት የነበሩት ነፍሳትም ሁሉ ነጻነት ወጡ፡፡ መጽሐፍ እንዲህ እንደሚል “ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ። ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ….ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” 1ኛ ቆሮ
    ሞትስ ይሁን ካልን መስዋዕት መሆን የሚችል ብዙ ምርጫ እያለ የእርሱ (የልጁ)ሞት ለምን ግድ አለ? የሚለው ቀጣይ ጥያቄያችን ይሆናል፡፡ ሞትን ድል መንሣት፣ ሲኦልን ማፈራረስና ትንሣኤን ለማብሰር በሞት መስዋዕት መሆን አስፈላጊ ነው ስንል ይህን ሊያደርግ የሚችለው ማነው የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከሊቀ ነብያቱ ክርስቶስ በፊት የነበሩ ብዙ ነብያት እስከሞት በተገባ ሕይወት ተመላልሰዋል ዳሩ የእነርሱም ነፍስ ከሲኦል ምንደኝነት አልተረፈችም፡፡ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንገድ በመምራት ብዙ ሕይወትን ቢያተርፉም እንኳ ካተረፏቸው ነፍሳት ጋር በሲኦል አድረዋል፡፡ ማንም ከሰው የተፈጠረ ይሄን ኃይል መጋፋት አልተቻለውም የመለኮት ጸጋ ቢበዛላቸውም እንኳ! አስቀድመን እንዳልነው የጥያቄያችን አስኳል ሰው ደካማና ምስኪን ፍጡር ነው የሚለው ነውና፡፡ ስለዚህም ልዕለ ኃያል የሆነ ሞትን ለማሸነፍ የሚሞት፣ ነፍሳትን ከታሰሩበት ለማውጣት ወደሲኦል ገብቶ በድል አድራጊነት የሚወጣ፣ የመውጊያ ጦርን የሚሰብር፣ የእስራት ሰንሰለትን የሚበጣጥስ ያስፈልጋል ይኽም ከመለኮታዊ ሥልጣን ና ኃይል በቀር ለማንም አይቻለውም፡፡ ስለዚህ ነው በሞት የማዳን ብቸኛ መንገድ የነበረውን የማዳን ሥራ በራሱ በልጁ እንዲሆን ያደረገው፡፡

  2. በእውነት ጌታ ዘመንህን ይባርከው!

    ይሄን ጽኑና ታላቅ ፍቅር ባሰብሁ ጊዜ ሞትን ፈራሁ እርሱ እርግማን ነው፡፡ አሁን ግን እርሱን እፈልገዋለሁ መባረክ ነውና፡፡ ምክንያቱም ወዳንተ መሄጃ መንገዴ ነውና ልቤ ትፈልገዋለች፡፡

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑