የሐዘን ዘመን-እምባችንን ለማን?

የሐዘን ዘመን-እምባችንን ለማን?

ወቅቱ ለኢትዮጵያውያን እጅግ አሳፋሪና አሰቃቂ ዘመን ሁኗል፡፡ እምባችን እንደጎርፍ ቢወርድም ብሶታችንና ሐዘናችንን ጠርጎ መውሰድ አልተቻለውም፡፡ ይልቁን ብዙ ባነባን ቁጥር ብዙ ምናነባበት ይፈጠራል፡፡ እኛ ከሌሎች ሃገራት ዜጎች የተለየን የሰው ፍጡሮች አይደለንም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሰውነት ነው፡፡ የዓለም ዜጋዎች ነን፡፡ የአፍሪካ መንደርተኞች ነን፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የትውልዳችን ወይም የመኖሪያችን ሥፍራ ነው፡፡ ለዚህ ስያሜ ከቀሩት የዓለም ፍጡራን በተለየ ለእኛ ትርጉምና ዋጋ አለው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት አንድም ይህ የተሰፈረና የታጠረው ቦታ እንዲሁም በእዚህ ሥፍራ የተወለደን ወይም የምንኖር ሰዎች ማለት ነው፡፡ ይሄን መሆን ግን ከሌሎች የዓለም ዜጎች የተለየን ፍጡራን አያደርገንም፡፡ የተለየ ፍላጎትና ምኞት አይኖረንም፡፡ የሰዋዊና ሰብአዊ ፍላጎት የቦታና የሥም ልዩነትን መሠረት አያደርግም፡፡ መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት የዓለም ዜጋ ሁሉ ፍላጎት ነው፡፡ በምጣኔ ሐብትና በፖለቲካ ኃያል ከሆኑት የአሜሪካ ዜጎች ፍላጎት ደቃቃ የሆነ ምጣኔ ሐብትና ዐይን አልባ የሆነ ፖለቲካ ያለን እኛ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የተለየ ፍላጎት የለንም፡፡ የምጣኔ ሐብትና የፖለቲካው ልዩነት የሚፈጥረው ሰው ሰራሽ ፍላጎትን እና የመሠረታዊ ፍላጎት የማሟላት ፍጥነትና ዝግምተኝነት ላይ አስተዋጽኦ ከማድረግ በላይ ድርሻ የለውም፡፡

እኛም ኢትዮጵያውያን ክብር ይገባናል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን መዋረድን አንሻም፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን መገፋትን አንፈልግም፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን እንደ ዜጋ የመቆጠር መሠረታዊ ህልም አለን፡፡ ህልም አልኩኝ- ኑረንበት አናውቅምና ነው፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን በነጻነት መኖር ይገባናል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ብልጽግና ይገባናል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን በዜግነታችን ደኅንነት እንዲሰማን ይገባናል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ ልዕልና ይገባናል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ሰው የመሆን መብት ይገባናል፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ስንጪህ የሚሰማን መንግስት፣ ስንቸገር ፣ ስንሰቃይ፣ ስንገፋ፣ ሲያጠፉን የሚደርስልን መሪ ይገባናል፡፡ እነዚህ የሚገቡን እንጂ የሚያስፈልጉን አይደሉም፡፡

isis-beheads-ethiopians-in-libya

ዳሩ ግና

በየመን የሚደርሰው ሰቆቃ “በየሜዳው ወድቆ ፈላጊ ያጣው ውሻና የሐበሻ ዜጋ ነው” እስኪባል ቢደርስም፤ አሁንም መከራው ባያባራም ከሐዘናችን ሳንጽናና የደቡብ አፍሪካው ሰቆቃ ቀጠለ፡፡ የሀዘናችን ጽናት ሲበረታ መረጋጋት ሲሳነን ይባስ ብሎ በሊቢያ የክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሕይወት ለጥይትና አንገታቸው ለሰይፍ የመዳረጉን ዜና ሰማን፡፡ እናነባው ዘንድ ምን አለን? እናዝን ዘንድ ምን መጽናኛ ተረፈን? ከስቃያችን እምንደበቅበት ምን ጥግ አለ? እምንሄድበት ምን ሃገር ፤ እምንወጣበት ምን ተራራ ይኖር?

በየመን ያሉ ዜጎቿቸውን ሃገራት የማውጣትና ከእልቂት ሰቆቃው የማትረፍ ጥረታቸው ዛሬም ድረስ የቀጠለ ነው፡፡ የ’ኢትዮጵያው’ መንግስት የዲፕሎማሲ ማኅበረሰቡን ለማውጣት ካደረገው ጥረት በኋላ መዝናናት ላይ ይገኛል፡፡ ከሃገሩ ተሰዶ ለጉልበቱና ለእድሜው ሳይሳሳ ኑሮውን ለማሸነፍ ሲባክን ያለው ዜጋ አይዞህ ባይ አጥቷል፡፡ የት እንደወደቀ የሚፈልገው መሪ የለውም፡፡

በደቡብ አፍሪካ ስለተፈጸመው አሳፋሪ ድርጊት የ’ኢትዮጵያው’ መንግስት ጊዜያዊ ችግር ነው ከማለት በቀር የመረበሽ ስሜትም እንዳልፈጠረበት ነግሮናል፡፡ እንደሱ አፍሪካዊ የሆኑት ሃገራት ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ዚምባቤ፣ ሱማሊያ ወዘተ ወታደራቸውን እዛው ድረስ በመላክ፣ ዜጎቻቸውን በማውጣትና ድንበሮቻቸውን በመዝጋት ቁጣቸውን ገልጸዋል፡፡ የእኛ ዜጋ ምን እንደደረሰበት’ኳ ሊያውቅለት የተገባው መሪ የለውም፡፡

የ’ኢትዮጵያው’ መንግስት ለሐገሪቷና ለዜጎቹ ያለውን ንቀትና ምን አለብኝነት ያሳየበት የሊቢያው ጭፍጨፋ ነው፡፡ ይህ የውርደት ቀናችን ነው፡፡ ቢያንስ መሪር ሐዘን እንደተሰማው ሊነግረን፣ እኛንም ከሐዘኑ ተካፋይ በማድረግ ችግሩ እንዲሰማን ሊያደርገን፣ በሃገሪቷ ሃዘንን ሊያውጅ ይገባው ነበር፡፡ እርሱ ግን የነገረን የስደተኞቹ መሞት እንደማይቀበለው በመግለጽ ኢትዮጵያውን መሆናቸውን አለማረጋገጡን ነው፡፡ በቃ አለቀ!! ለነገሩ በየመን ባህር የተተፉ ሰባ ኢጥዮጵያውያን አላውቃቸውም ብሎ ሸምጥጦ ክዶን የለ፡፡

እንዴትና መቼ ነው የአንድ ዜጋ ዋጋና ክብር ከልቡ የሚሞላው? መቼና እንዴት ይሆን የኢትዮጵያዊነት ክብር ከመንፈሱ የሚሰርጸው? የኢትዮጵያዊነት መዋረድ፣ መገፋትና መጠላት ሌሎች ከፈጠሩት በላይ የመንግስታችን ድርጊት አድምቆታል፡፡ የኢትዮጵያውያን መሞትን ከገደላቸው በላይ እንዴት ነው ልናረጋግጥ የሚቻለን? በዲ ኤን ኤ ይሆን? አቅም የሌለው ቢሆንም’ኳ ይሁን የሚያረጋግጣቸው ጉዳዮች ይኖራሉ ብንል ሐዘኑንና ቁጣውንስ መቼ ይሆን የሚያረጋግጥልን! ሌሎች የቀሩት ዜጎች እጣ ፈንታቸው ምን ይሆን? ለአንዲት ሃገር ከዚህ በላይ ውርደት ያላት አይመስለኝም! የቡድን መብት አቀንቃኝ ስሆነ ስለመደብ ጥማቱ የተገደሉት ክርስቲያኖች በሚል መደብ ነውና ምነው የመደብ ቋንቋስ አጣ?

ድሮም ቢሆን ምንም ሊያደርግ ፈቃደኝነትም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ይልቁን ለፖለቲካ እርካሽ ጥቅም ሊጠቀምበት እንዲችል እምነቱ ነበረን፡፡ ዳሩ የእኛ ችግር የሚመነጨው ከምኞታችን ነው፡፡ እንደሌሎች ሃገር ዜጎች የመሆን ምኞት! ስለዚህ ምኞታችን ስንልም ‘መንግስት’ አካሄዱን እንዲቀይርልን እንመኛለን፡፡ ሁሌም እንደዜጋ እንድንቆጠር እንመኛለን ስለምኞታችን “መንግስታችን” የሚስተካከል ይመስለናል እንጂ መልክና ጸባዩን ከተረዳን ሁለት አስርት ዓመታት አለፉ፡፡

ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ሕዝቦቻችን ዋና የመሰደዳቸው ምንጭ የምጣኔ ሐብት ጥገኝነት ነው ከፖለቲካው ጎን፡፡ የዚህ ጥገኝነት ምንጭ ደግሞ የህወሃት ፖለቲካ ነው፡፡ የኢህአዴግ ነገን አርቆ የማያይ የግል ጥቅምና ስልጣን ጥማት መሠረት ያደረገው ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ፖለቲካ! ሰዎች ለመሞት የሚፈሩት መኖርን ሲጓጉ ነው፡፡ ሞት ወዳለበት መንደር በበረሃ፣ በባህር የዜጎቻችን መጓዝ የሚያሳየን በሃገራቸው የመኖር ጉጉት እንደሌላቸው ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ቢሞቱ እንኳ ወደሚመርጡበት ይጓዛሉ፡፡ እንዲህ እንደተባለ ‘በግዞት/እስራት ከመኖር ነጻነትን ፍለጋ መንገድ ላይ መሞት ይበልጣል’፡፡

መሪር ከሆነው ሐዘናችን ላይ ሆነንም ቢሆን ማሰብ የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ በሃገር የመኖር ጉጉት ጠፍቶ መሞትን የምንመርጥ ከሆነ ምትስ የማይቀር ነውና ሃገርን በማቆየትና ሃገርን በመቀየር መሞት ይበልጣል፡፡ ለዚህ ሁሉ ምንጭ የሆነውን የህወሃት አገዛዝን በመቀየር የሚገቡንን የዜግነት ፍላጎቶች ለማሳካት የሚሆን ሥርዓት ለመፍጠር መሞት ይገባናል፡፡ ያኔ ሞታችን ዋጋ ያለው ይሆናል፡፡ የሃገሪቷም ባለውለተኞች እንሆናለንና ሁሌም በለውጡ እንነሣለን!

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑