የመልካምነትና ክፋት ድልድይ

የመልካምነትና ክፋት ድልድይ

“በጎን ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?” 1ኛ ጴጥ 3፥13

ረጅም ጊዜ የቆየ ጓደኝነት ነው ያለን፡፡ ዛሬ ሳገኛት በሐሴት ውስጥ ነበርኩ፡፡ በጨዋታችንም መሐል በአእምሮዬ ተደጋግሞ የሚመላለስውን ጥያቄ አነሣሁት፡፡

“ሰው ግን ለምንድነው እንዲህ ክፉ የሆነው?” ስል

የጓደኛዬ አተያይ ሁልጊዜም ይማርከኝ ነበርና ነው ከእርሷ ጋ መጫወት መሻቴ፡፡ ግን እውነት ሰው ስለምን ነው እንዲህ ክፋት የተሞላው?

“አንተ ክፉ ነህ?” ጠየቀችኝ

“መልካም እንደሆንኩ አስባለሁ”

“ለምን?”

“ከክፋት ከማተርፈው በመልካምነት የማገኘው ስለሚሻል ይመስለኛል”

“ክፉ የምትላቸው ሰዎች ትርፍ አያገኙበትም?”

“እኔጃ! ይኖራቸው ይሆን?”

“ይኸውልህ የሰው ልጅ የተሰራበት ቅንጣት መልካምነት ነው”

“ማለት?”

“ሰው ከምን ነው የተሠራው? ከአጥንት፣ ከጅማት፣ ከሥጋ፣ ቲሹ፣ ሴል (cell)፣…….. ሴልስ ከምን ተሰራ… ከኒኩለ(nuclei)ና የተለያዩ ኦርጋኔልስ (organells)? እነዚህስ አለባውያን ቅንጣቶች? … ዞሮ ዞሮ መጨረሻው ፍጡር ነው፡፡ ህይወት የሌለውንም ብታይ የተሰሩበት የመጨረሻ ቅንጣት አቶም ነው አተም ደግሞ በራሱ የተገኘ ነው ይልሃል ሳይንስ፡፡ በሁለቱም ክፍል የመጀመሪያ የመፈጠሪያ ቅንጣት የተገኘ ወይም የተፈጠረ ነው፡፡ እናም ሳይንስ ባለው እውቀት የተሠራበትን ከመገመት በላይ ወይም የተገኘ(የተፈጠረ) ከማለት አይዘልም፡፡

ይህ ሰው ግን የተፈጠረውና የተቀረጸበት ባህርይ ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የሥጋ ሌላው የነፍስያው፡፡ ማንም እንደሚረዳውም ሰው ከሥጋና ነፍስት የተዋቀረ ቅዱስ ቤት ነው፡፡ ሥጋነቱ ከአራት ቅንጣተ-ባህርይ ነፍሱ ከሦስት አለባተ-ባህርይ ተመስርተዋል፡፡ በእነዚህም ውህደት ሰው የፈጠረውን መሰለ፡፡ ሥጋዊ ባህርያቱ ነፋሳዊነት፣ አፈርነት፣ እሳትና ውኃነት ናቸው፡፡ ሥጋው ከእነዚህ ቅንጣተ ባህርያት ሲገነባ ነፍስያው የተቀለመመችው ከልባዊነት፣ ሕያዊነትና ነባቢነት የባህርይ ቅንጣት ነው፡፡ የሰውን ባህርይ ብታየው እነዚህን ሰባት ባህርያት ሲመስል ወይም በእነርሱ ሲገለጽ ታገኘዋለህ፡፡ ሌላ አማራጭ የለውም የተሠራበት ነውና፡፡”

የሰንበት ት/ት ቤት ትምህርት አስታወስኩ፡፡ የሥጋ አራት ባህርያት የሰውን ልጅ የህይወት እድሜ ጊዜ መስመር ይወክላሉ፡፡ የልጅነት ጸባዩ በነፋስነት ይመሰላል፡፡ ሩጠው የማይደክሙበት የእንቅዥቅዥነት ወቅት፡፡ ወጣትነቱ እሳታዊ ባህርይው የሚገንበት ወቅት ይሆናል፡፡ ትኩስና ስሜታዊ የሚሆንበት፣ ሁሉን ካላየው ካልቀመስኩ የሚባልበት የነበልባል ወቅት፡፡ ውኃነት በጎልማሳ እድሜው የሚገለጥ ስለሆነ ጎልማሳነቱን ይመስላል፡፡ የእርጋታው፣ የአስተዋይነቱ፣ የዳኝነቱ ባህርይው ይገልጠዋል፡፡ የመጨረሻው መሬትነት የሽምግልና ጊዜ ሲሆን በዚህ ወቅት ሰዋዊ ጸባዩ ቻይነት፣ የዋህነትና ታጋሽነት ይታያሉ፡፡ በእነዚህም የሥጋ የሥሪት ቅንጣት ባህርይው በእድሜው ይገለጣሉ፡፡ እሷ ቀጥላለች፡፡

“ሰው በሥጋው በእግዚአብሔርባህርይ ውስጥ በሚገለጹ ምሳሌያዊ ባህርያት ሲሠራ፡፡ በነፍሱ ፈጣሪውን የሚመስልበት ምናልባትም የነፍስ ባህርይዋ ምክንያት ፈጣሪን የሚሆንበት መገለጫ ነው፡፡ ነፍስ ያለው- ሰው የሚባል ፍጡር አሳቢ(ልባዊ)፣ ለዘላለም ኗሪ (ሕያው) እና ተናጋሪ (ነባቢ) ሁኖ እንዲኖር ስለሚያደርገው ከሌላው ፍጥረት ሁሉ ተለይቶ ይታወቃል፡፡ ፈጣሪውን ለዘላለም በመኖር ሲመስለው፣ ፍጥረቱን በተመራማሪ አእምሮውና ሐሳቡን በመግለጽ ጸጋው ይበልጠዋል፡፡

መጀመሪያ ላይ ያነሳውልህ መልካምነት እነዚህ የነፍስ ባህርይያት ውስጥ የሚገኝ ቅንጣት ነው፡፡ ማሰቡን የምትገልጽልን ልባዊት ባህርይው የተሰራችበት አንደኛው ቅንጣት ይህ መልካምነት ነው፡፡ ስለዚህ መልካም የመሆን ጸባይ የሰው ልጅ የተሰጠው ሽልማትና የታደለው ችሮታ ሳይሆን የተሠራበት ባህርይው ነው፡፡ ይህ የሚያስረዳው ሰው መልካም ከማሰብና ከመሥራት በቀር ሌላ አማራጭ ያልተሰጠው ፍጥረት መሆኑን ነው፡፡ ይሄን ባህርይ የቀዳው ነፍስያው ከተቀዳችበት ከፈጣሪው ባህርይ ነው፡፡ እና አምላኩን ይመስለዋል፡፡ አምላክ መልካም አሳቢና መልካሙን ብቻ አድራጊ በመሆኑ በሰው ባህርይ ውስጥ ይህን ወርሶ ይመስለዋል፡፡ ይገለጥበትማል፡፡

በአንድ ወቅት ታስታውስ እንደሆነ ኤች አይቪ መዛመትን ተከትሎ የነበረው መፈክር ‘የባህርይ ለውጥ እናምጣ’ የሚል ነበር፡፡ በዚህም በምሁራንና የሃይማኖት መምህራን ዘንድ የተነሣው ተቃውሞ ሰው ባህርይውን አይለውጥም ይልቁን ጸባዩን እንጂ! በሚል ‘የጸባይ ለውጥ እናምጣ’ በሚል ይስተካከል የሚል ሙግት ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ለዚህ እንደምክንያት የሚቀርበው ሰው የተፈጠረበት ባህርይ እርሱ የፈጠረው ወይም የጨመረው ሳይሆን ሲፈጠር የተሠራበትና የተሰጠው ሥሪተ ባህርይ መሆኑን በማመላከት ማስተካከል አይቻለውም ይልቅ በህይወቱ ቆይታ በመላመድ የመሰሉትን ጸባያት ማስተካከል ይቻለዋል የሚል ነው፡፡

ሰው ሲጋራ ማጨስ እንዴት ለመደ? የሆነ ቀን ጀምሮት በመለማመድ አይደለምን! የሻይ ወይም የቡና ሱስ እንዴት ሌላ ሰው ሊይዘው ቻለ? እንዲሁ ደጋግሞ በመጠጣት አይደለምን! ሌሎችን ጸባያትን (የልማድ መግለጫ ባህርያትን) እንዲሁ የሰው ልጅ መልመድ ይቻለዋል እናም እኚያ የለመዳቸው ባህርያት መገለጫዎቹ- ጸባዮቹ ሆኑለት ስለዚህም ለምዷቸው በእነርሱ እንደተገለጸ መተውን በመልመድ ሊገለጽባቸው ይችላል፡፡ ልማዶች ሁሉ ጎጂ ሳይሆኑ በጎም ልማዶች አሉና! ሰው ጎጂ የሆኑ ልማዶችን በመደጋገም እንደተለማማዳቸው ጠቃሚ የሆኑ በጎ ልማዶችንም እንዲሁ መለማመድ ይቻለዋል፡፡ ምሳሌ መጽሐፍ ማንበብ በጎ ልማድ ነው- በመደጋገም የሚፈጠር ልማድ፡፡ አንባቢ ሰው የተፈጠረበት ባህርይ አንባቢነት ሁኖ ሳይሆን በሕይወት ጉዞው በአንዳች አጋጣሚ ወይም በጎ ተጽእኖ የተገለጸበት ጸባዩ ነው፡፡ ስለሆነም የሰው ባህርይ ሳይሆን ጸባይ ነው ሊስተካከል የሚችል፡፡

የሰው ልጅን ሥሪተ ባህርይ ስለሆነው መልካምነት ለማስረዳት እስቲ ይህን ልጠይቅህ” አለችኝ በምልክት መስማማቴን ገለጽኩላት፡፡

“የመልካም ተቃራኒ ምንድነው?”

“ክፉ/መጥፎ!”

“አየህ ይህ የብዙሃኑ አሳብና መልስ ይመስላል፡፡ ግን የመልካምነት ተቃራኒ መጥፎነት ወይም ክፋት ሳይሆን ‘መልካም አለመሆን’ ነው፡፡ ክፋት የመልካም አለመሆን አንድ መገለጫ ነው እንጂ ሙሉነት አይደለም፡፡ እስቲ ይህን መልስ

በአንድ ወቅት ሦስት ሰዎች በተለያየ መንገድ ይሄዱ ነበር፡፡ ከፊታቸውም የሚሄደው ሰው ብዙ ብሮችን ከኪሱ አውጥቶ በምንገዱ ላይ እየቆጠረ ይሄዳል፡፡ የያዛቸው ብሮች እጅግየሚያስጎመጁና የኔ በሆኑ የሚያሰኙ ነበሩ፡፡ በአንደኛው መንገድ የሚሄደው ሰው ከፊቱ ብር እየቆጠረ የሚሄደውን ሰው ብሩን እያየ ሲሄድ ሳለ ሌላ አንድ ሰው ከየት መጣህ ሳይባል የብር ቆጣሪውን ሰው ብሩን ቀምቶት ይሮጣል፡፡ ይሄኛው ከኋላ የነበረው ሰው ደንግጦ በመስፈንጠር ይከታተለውና ይይዘዋል፡፡ አንቆም ብሩን ከተቀበለው በኋላ ለባለቤቱ ይመልስለታል፡፡ በሁለተኛው መንገድ ያለው ሰው እንዲሁም በፊቱ ብር እየቆጠረ የሚሄደውን ሰው ሌላ ሰው ብሩን ቀምቶት ሲሮጥ ቢያየውም ከማዘንና ከመቆጨት ውጪ ምንም ለማድረግ ሳይሞክር በዝምታ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ በሦስተኛው መንገድ ያለው ሰው ከፊቱ ብር እየቆጠረ የሚሄደውን ሰው ሲያየው ገና ልቡ በምኞት ተሞላና የእርሱን ብር ፈለገ፡፡ ማንም ሳያየው እንዴት እንደሚወስደው ካሰበ በኋላ ከኋላው በመንደርደር በፍጥነት ቀምቶት ሮጠ፡፡ ከላይ ካየናቸው ሶስቱ መንገደኞች የትኛው ሰው መልካምን ሠራት?”

“ብሩን ከቀማኛ ያስመለሰለት ይመስለኛል”

“ክፋትን የሠራው መንገደኛስ?”

“ብሩን ቀምቶት የሮጠው ይመስለኛል”

“አየህ ስለመልካምነትና ክፋት ብቻ የምናወራ ከሆነ በሁለተኛው መንገድ ስለተጓዘው ሰው የምንለው አይኖረንም፡፡ እርግጥ በመጀመሪያው መንገድ የሄደው ሰው መልካምን አድርጓል፡፡ ለጉዳቱ ካሳ ሁኖለታል ማለትም የተቀማውን ብር አስመልሶለታል፡፡ ክፍትን ያደረጉት ግን የተቀሩት ሁለቱም ናቸው፡፡ ማለትም መልካምን ያላደረጋት ሁሉ ክፋትን እንዲሁ አድርገዋታል፡፡ ሁለተኛው መንገደኛ በእጁ አልቀማም፡፡ እንደምናስበው ክፋትን አላደረገም፡፡ ዳሩ ሲቀማ (ክፋት ሲደረግበት) ላየው ወዳጁ በጎውን ለማድረግ አልጣረም፡፡ እንኳንስ በጎ ሊያደርጓት የተዘጋጀችለት ቀርቶ በጎን ሊያደርግ ከውስጡ ያላቀናት እርሱ እንዲሁ ክፋትን አድርጓል፡፡ ለሰው መጥፎ ነገር ማድረግ ብቻ አይደለም ክፋት፡፡ በጎን አለማድረግ ጭምር ክፋት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ለሰው በጎም አለማድረግ ክፋትም አለማድረግ የሚባል መሀል ሰፋሪነት የለም፡፡ መጽሐፍ በጎን ሊያደርጋት አይቶ [ወይም ሲገባው] ያላደረጋት እንዲሁ ክፉ እንዳደረገ ይሆንበታል እንዲል፡፡

ስለዚህ ክፋት የመልካምነት ተቃራኒ ሳይሆን መልካም ያለመሆን መገለጫ ነው፡፡ ስለዚህም ክፉ ሰው መልካምን ሁሉ የማያደርጋት ነው፡፡ ለምን ያልኸኝ እንደሆነ መልካም ሁኖ ተሠርቶ ሳለ፣ መልካምን ማድረግ ለእርሱ ድካም፣ ሸክም የማይሆንበት ሁኖ ሳለ፤ በጎነት ለእርሱ ጥበብና ብልጠት የማይጠይቅ ሁኖ ሳለ ባህርይውን የሚገልጽበትን ዋና መገለጫ ደብቆታልና፤ ይልቁን አዲስ ጸባይ ተጸናውቶት እርሱን ልማድ አድርጎ መገለጫው ይሆን ዘንድ መርጧልና መልካምን ማድረግ ያቃተው ሁሉ ክፉ ሰው ሁኗል፡፡

በጎነት የሰው ባህርይ ውስጥ እንዳለ እና የተሠራበት ቅንጣት እንደሆነ በሰው አኗኗርና ተፈጥሮ ተነስተን እንዲሁም መረዳት ይቻለናል፡፡ መልካምን ማድረግ ዋጋ የማያስከፍል፣ ድካም የሌለው (ጥረት አልባ)፣ ራስንም የማይጎዳ፣ ይልቁን ለሌላው ሕይወት የሚያረዝም፣ ተስፋን የሚዘራ፣ ለራስ ፍስሃና ደስታ የሚሞላ እግዚአብሔርን የመምሰል ባህርይ መገለጫ ነው፡፡”

“ታዲያ ክፍት ከየት መጣ?”

ይህ የእኔም ጥያቄ የእርሷም እኔ ውስጥ የሚነሣ ጥያቄ መሆኑን የምትገምተው የእርሷ ጥያቄ ነበር፡፡ እርግጥ መልካምነት የሰውልጅ ተፈጥሮአዊ ባሕርይ መሆኑን የተረዳ መልሱን የሚያውቀው ጥያቄ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የገባው የዚህ ጥያቄ ምንጭ የሚረዳው ይሆናል፡፡ ስለዚህም ቀጣዩን እርሱ መጻፍ ይቻለዋል፡፡

ሌላው በመልካምነት ተፈጥሮአዊ ባህርይ ላይ ጥርጣሬ የገባው፤ በሰው እግዚአብሔርን መምሰል ምሥጢር ያልተረዳው- ያልተመለሰለት የእርሱም ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህም ቀጣዩን ክፍል ይጠብቃል፡፡ ይቆየን!

 

 

 

One thought on “የመልካምነትና ክፋት ድልድይ

Add yours

  1. “በጎን ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?” 1ኛ ጴጥ 3፥13

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑