​የምግብ ዝግጅት፡- ዘይት-አልባ፣ ከብሶት ብቻ የሚስሠራ፣ ትኩስ፣ ቀሊል ‹‹ብሔርተኝነት››!

የምግብ ዝግጅት፡- ዘይት-አልባ፣ ከብሶት ብቻ የሚስሠራ፣ ትኩስ፣ ቀሊል ‹‹ብሔርተኝነት››!

(ከበአማን ነጸረ #FB የተወሰደ)

ሀ. በቅድሚያ የሚከተሉት ግብዐቶች ያስፈልጉናል!

1. እንደ ሽንኩርት፡- ብሔረሰብዎ ላይ የደረሱና እየደረሱ ያሉ የሚሏቸው ጥቂት የተላጡ የታሪክ አጋጣሚዎች፣

2. እንደ ድንች፡- ለራስዎ ብሔር ካለዎት ፍቅር የሚወፍር ድፍን የሌላ ብሔር ጥላቻ፣

3. እንደ ጉልቻ፡- ከብሔርዎ የተውጣጡ ጥቂት የጋሉና ስሜታውያን ነዲድ ወጣቶች፣

4. እንደ ምጣድ፡- የተንጣለለና በደንብ የተተከለ የዋሕ ማኅበረሰብ፣

5. እንደ ጨው፡- ጥላቻዎትን ‹‹ምክንያታዊነት›› አላብሶ በዘላቂነት ለማስቀጠል የሚያስችል ደቃቅና ቁንጽል እውቀት፣

6. ለጥንቃቄ፡- እጅዎት በዚያኛው ብሔር በኩል ባለው ሰፊ እውነታና መሬት ላይ ያለ ነባራዊ ሀቅ እንዳይቃጠል በልብዎ ‹‹ጠላት›› በሚሉት ብሔር ጥቂት ውዱቃን የሚራመዱ ውድቅዳቂ አመለካከቶችን እንደ መከላከያ (እንደ ሰበብ – you too fallacy) መጠቀም ፣

7. እንደ እሳት፡- እርስዎ የወጡበት ብሔር የጎረቤት ብሔረሰቦች ምቀኛ ባይሆኑበት ኖሮ እስካሁን ጁፒተር ላይ ሮኬት ያሳርፍ እንደ ነበር፣ በማርስ ሜካናይዝድ እርሻ ይጀምር እንደነበር፣ በሕንድ ውቅያኖስ ማኅፀን ሰርጓጅ የጦር መርከብ ማርመስመሱ እንደማይቀር፣ ለጥፍሩና ለፀጉሩ ኢንሹራንስ ይገባ እንደነበር፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በእርስዎ ብሔር ተጋድሎና ችሮታ ብቻ ዘላለሟን የቆመች በመሆኗ ሸክሙ እንደሚሰማዎት፣ ወዘተ መስበክ፣

8. እንደ ማማስያ፡- ከ‹‹ጠላት›› ብሔረሰቦች ከባድ የጥፋት ድግስ በብሔረሰብዎ ላይ እንደ ተደገሰ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሳይፎርሹ ወዲያ ወዲህ በቀስታ ማማሰል፣

9. እንደ ድስት፡- ጎድጓዳ፣ ስስ እና ቀለል ያሉ ልሂቃንን ለብሶት መቀቀያነት መጠቀም፣

10. እንደ ጭልፋ፣ማንኪያና ሹካ፡- ወፍራምና ከጭንቅላቱ ቀለል ያለ (ቢቻል ራሱን በራሱ ቻርጅ የሚያደርግ ባለ ሦስት ኮከብ ቦርጭ ያለው) ጋዜጠኛ፣ (አሁንም ቢቻል ጭንቅላቱ ከጫንቃውና ከጡንቻው ስር የበቀለ) ባለ 2 ሹካ ብሎገርና ፌዝቡከር ማፈላለግ፣

ለ. አሠራሩ!

ያለና የነበረውን የታሪክ ሽንኩርት ዐይን እንባ እስኪያወጣ ሞልጮ መላጥ፡፡ ከዚያ በላዩ ላይ ድፍን የጥላቻ ድንች አድርጎ በወጣት ጉልቻዎች ተጠቅሞ ምጣዱ ላይ ማመስ፡፡ የታመሰውን ጥላቻ በጎድጓዳ ልሂቃን ድስት አድርጎ ኅሊና እውነትን ሲጋፈጥ አልጫ እንዳይሆን ምክንያታዊነት የተባለችውን ጨው ነስነሶ ማጣፈጥ፡፡ አስከትሎ የብሔረሰብዎን ከዓለም የተለየ ጠቢብነትና ገናናነት በማቀጣጠል በአጸፋው የጎረቤት ብሔረሰቦችን ክፋትና ምቀኝነት ከነስፍናቸው ‹‹እፍ›› ማለት፣ ማንደድ – ማናደድ፡፡ እነዚሁ ምቀኛ ብሔረሰቦች በእርስዎ ‹‹ጠቢብ›› ብሔር ላይ ያሰቡትን ጥፋት ሴራ በማጋለጥ የትውልድ ቀዬዎን (ዋ!ቂጡ እንዳይዝ!) እስኪጦዝ ማማሰል፡፡ በዚህ መልኩ እንደ ብሔርዎ ሁኔታ ከ25-150 ዓመታት ካበሳሰሉ በኋላ እጅዎ እንዳይቆሽሽ የሌላውን ብሔር ጥቂት ውዱቃን ልሂቃን ውዱቅ አመለካከት ለአበሳዎ ማበሻ በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ ወፍራም ጭልፋ ጋዜጠኛ፣ ወይም ወፈፍ ያለ ብሎገርና ፌዝቡከር ሹካና ማንኪያ አድርገው ለአፉኪ፣ ለከርሥኪ፣ ለአስናንኪ…ማለት ነው…ዋው!!! ብሔርተኝነት ብሎ ዝም! …በየብሔርዎ ጓዳ ይሞክሩት!

ሐ. በቀጣይ…!

ይሕን ቀመር ተጠቅመን ‹‹አቡሎ›› እና ‹‹ድንቡሎ›› የተባሉ ባሕል-ዘመናዊ፣ ቅባት አልባ የብሶት ብሔረሰቦች ብሔርተኝነትን በየሳሎናችን እንሠራለን፡፡ ጠብቁን! ከጥቂት የመናቆር ማስታወቂያዎች በኋላ እንመለሳለን፤ የትም እንዳትሄዱ (ለነገሩ መሄጃ ሲኖራችሁ አይደል!) በነገራችን ላይ፡- ተመልካቾቻችን! ዘይት ማለት ፍቅር ነው፤ የዛሬው የምግብ አሠራር ከዘይት የፀዳ፣ ደረቅና ነጣ ያለ ብሔርተኝነትን የሚመለከት ሲሆን ፕሮግራሙን ስፖንሰር ያደረገው ‹‹ከኔ ወዲያ ላሳር!›› የተባለው ራስ-ተኮር ኃላፊነቱ ያልተወሰነ የጥቃቅንና አነስተኛ ጥላቻዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ማስታወቂያው ይቀጥላል…

መ. የስፖንሰር መልእክት!

ከኔ ወዲያ ላሳር!…አድራሻችን በሁሉም ያገራችን ጥቃቅን ስርጓጉጦች! ካገር ውጭ፡- በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አውስትራሊያ፣…በየስርቻው! ምን አለፋዎት! እርስዎ ብቻ ይጥሉ! እኛ በልክዎ የጥላቻ ምርቶችን ቢፈልጉ በአካል፣ ካስፈለገም በWWW.ጥላቻ ኦን ላይን እናቀርባለን! ያስታውሱ! ጥላቻዎች ሁሉ እኩል አይደሉም! ተመሳስለው በተሠሩ የፍረጃ፣ የጦርነት፣ የረሀብ፣ የኢፍትሐዊነት ጥላቻዎች እንዳይታለሉ! ትክከለኛዎቹ የ‹‹ከኔ ወዲያ ላሳር›› ምርቶች ባለ አንድ ዐይና መነጽር ደቃቅ ፍጡራን በሌባ ጣታቸው ወደራሳቸው ሲጠቁሙ የሚያሳይ ደብዛዛ ምስል አላቸው! ምንጊዜም ‹‹ከኔ ወዲያ ላሳር!›› ቺርስ… ለጠበስነው ፍቅር!

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑