ቁርቁር ሲኖዶስ

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትላንትና ወይም ዛሬ የተፈጠረች አይደለችም፡፡ ሲኖዶሳዊ ታሪኳ ግን ቁርቁር ነው፡፡  ሲኖዶሳዊ አበቃቀሏ ቁርቁር በመሆኑ ሲኖዶሳዊ ገጽታዋም የተቆረቆሩ ከተሞች ገጽታ ዐይነት ነው፡፡ ለነገሩ ድሮ ድሮ ቁርቁር ከተማ እንጂ ቁርቁር ሲኖዶስ አልነበረም፡፡ ቁርቁር ከተማዎች ለመኖራቸው ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለጊዜው ከጎጃም የበዛብህ መዲና ማንኩሳ፤ ከሲዳማ ተፈሪ ኬላ ምስክሮቼ ናቸው፡፡ እኒህ ከተማዎች እግረ መንገድ በንጉሣዊ ትእዛዝ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ እናም ዛሬ ዛሬ ቁርቁር ከተማዎች አልፈው በዘመናች ነገሥታት ትዕዛዝ የሚፈጠሩ ቁርቁር ሲኖዶሶች እየበዙ ነው፡፡ ቁርቁር ከተሞች በዋናነት ተፈጥሯዊ ሒደትን ተከትለው አይፈጠሩም፡፡ አብዛኛው ጊዜ አፈጣጠራቸው የነገሥታቱን ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ኀይልን ማዕከል በማድረግ ነው፡፡ በቁርቁር ከተሞችም እንዲከትሙ የሚደረጉት በብዛት ከነገሥታቱ ጋር ማኅበረ ፖለቲካዊ ተዛምዶ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ 

ሲኖዶሳችንም አበቃቀሉ እንዲሁ ነው፡፡ ሲኖዶሳዊ የአበቃቀል ሒደትን ተከትሎ ያላደገ እንደመሆኑ የቄብ ስብስብ ነው፡፡ በዚህ የአበቃቀለ ሒደት ውስጥ በሃይማኖት ብሔርተኝነት ራስን ለመቻል የተጋደሉ አበው ቢኖሩበትም፥ የንጉሡ የፖለቲካ ኀይል ሚዛን ፍላጉት ግን ማዕከላዊ ነበር፡፡ የብልጭታ ያህል ጥቡዓን አበውም ቢኖሩበትም፥ ንጉሡም ፖለቲካዊ ፍላጎቶቼን ያስጠብቁልኛል ያሏቸውን አበው እንዲካተቱ ማድረጋቸው አይጠረጠርም፡፡

EOTC-Holy-Synod

በዚሁ የታሪክ አዙሪት የቀጠለው ሲኖዶሳችን  መለካዊነትን በተልዕኳዊ ቅርጽ ያዳበረ ይመስላል፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ ዘመን መንግሥታዊ ፈቃዳትን መፈጽም ሲኖዲሳዊ ተልእኮ ወደ መሆን ያደገ ይመስላል፡፡ መንግሥትም ፈቃዴን ያስፈጽሙልኛል ያላቸውን አባቶችን ለማስረግ የሚጋደለውን ያህል፤ሲኖዶሳችንም ፈጻሜ ፈቃድ የሆኑትን አበው አካቶ ለመሔድ እጅግ የተጋ ነው፡፡ መንግሥት በግልጽ አባ ሠረቀ ወልደ ሳሙኤል፣ አባ ኀይለ ማርያም መለስና አባ ተክለ ሃይማኖትን ሲኖዶሱ በኤጴስ ቆጶስነት አካቶ እንዲሔድ የተለያዩ ግፊቶችን አድርጎ ነበር፡፡ ቅዱስነታቸውም ይህን መንግሥታዊ ፈቃድ ለማስፈጸም ከአቶ ካሣ ተክለ ብርሃን ጋር በመሆን አስመራጭ ኮሜቴውን ማወያየታቸው አብነታዊ ማሳያ ነው፡፡  አባ ሠረቀ ከፓትርያርኩ ጋር በነበራቸው አለመግባባትና ይህን ተከትሎም በአቶ ካሳና በፓትርያርኩ መካከል በተፈጠረው ክፍተት ነጥበው ሲቀሩ፥ አባ ኀይለ ማርያም መለስና አባ ተክለ ሃይማኖትን ተካትተው ሔደዋል፡፡ በርግጠኝነት አባ ሠረቀ ከፓትርያርኩ ጋር ቅራኔ ውስጥ ባይገቡ ኖሮ ተካተው መሔዳቸው አይቀርም ነበር፡፡ ሲኖዶሳችን በመለካዊነት-በፈጻሜ ፈቃድነት አይጠረጠርምና፡፡

ቁርቁር ሲኖዶስ የቁርቁር ተሿሚዎች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን ፥ የኤጴስ ቆጶሳት የምርጫ ሥርዐቱም ስሪታዊ ነው፡፡ በስሪታዊ የምርጫ ሥርዐት ደግሞ በአንድ በኩል የምርጫ ሕጉ ጉቦ ለተቀበሉባቸውንና ለመንግሥታዊ ተልዕኮ ለተመለመሉት እጩ ኤጴስ ቆጶሳት ማለፍ ጋሬጣ መሆኑ ከታወቀ፤ ጋሬጣ የሆነው የሕግ አንቀጽ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ የኤጴስ ቆጶሳት የምርጫ ሕግ ለጥቆማ እና ለምርጫ ቋንቋ እና ዘውግ መስፈርት ነበሩ፡፡ነገር ግን ጉቦ ለተቀበሉባቸውንና ለመንግሥታዊ ተልዕኮ ለተመለመሉት እጩ ኤጴስ ቆጶሳት ማለፍ ጋሬጣ እንደሆነባቸው የተረዱት ቀንደኛ አማሳኝ እና መለካዊ ሊቃነ ጳጳሳት ተረባርበው ከምርጫ ሕጉ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ ለአንቀጹ መውጣት ግን ምክንያት ያደረጉት አሰቀድመው የተቀዎሙትንና በኋላ ደግሞ ለሽፋን የተጠቀሙበትን ፥ ‹‹ አካባቢና ቋንቋ በመስፈርት መካተቱ ከመንፈሳዊ አሠራርና አንድነትን ከማጽናት አንጻር ችግር ያስከትላል፡፡ ›› የሚለውን ነው፡፡ እውነታው ግን እርሱ አነበረም፡፡ ሕጉ በአንድ ገጽታው  በአቡነ እስጢፋኖስ የተደራጀው (በጎልህ መገለጫው) የመለካዉያን ጳጳሳት ስብስብ እንዲመረጡ ለሚፈልጓቸው ለአባ ተክለ ሃይማኖት ዘጋቤላ እና በሌላው ገጽታ ደግሞ በአቡነ ኤልያስ የተደራጀው (በጎልህ መገለጫው) የአማሳኝ ጳጳሳት ስብስብ እንዲመረጡ ለሚፈልጓቸው ለአባ ሔኖክ ሁኔታውን ማመቻቸት ነበር፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት አባ ተክለ ሃይማኖትም ሆኑ አባ ሔኖክ የተወዳደሩበት ሀገረ ስብከት ቋንቋቸውም ሆነ ዘውጋቸው አይደለም፡፡ ሰለዚህ ቋንቋና ዘውግን የተመለከተው አንቀጽ መደምሰስ ነበረበት፡፡ እነርሱም እንዲካተቱ ተደረገ፡፡

Coptic-Holy-Synod

በሌላ በኩል ድግሞ  ስሪታዊ የምርጫ ሥርዐት ለገዳማዊ ሕይወት እና ለትምህርት ደረጃ ተገቢውን ዋጋና ክብር ሰለማይሰጥ፥ በገዳማዊ ሕይወታቸውም ሆነ በትምህርት ደረጃቸው የተመሰከረላቸውን እየገፈተረ፤ በገዳማዊ ሕይወታቸውም ሆነ በትምህርት ደረጃቸው ነቀፋ ያለባቸውን አካቶ ይጓዛል፡፡ መንግሥታዊ ድጋፍ አላቸው ያላቸውን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ ሲያካትት፤ መንግሥታዊ ድጋፍ ሳይኖራቸው በሊቃውንት እና በምዕመናን ዘንድ ቅቡል የሆኑትን የሚገፈትር ነው፡፡ ይህ ማለት በገዳማዊ ሕይወታቸው የተመሰከረላቸውን እና በትምህርት ደረጃቸው እጅግ የላቁትን  ሊቀ ሊቃውንት እዝራን በአጣማጅ አወዳድሮ፤ በገዳማዊ ሕይወታቸውም ሆነ በትምህርት ደረጃቸው ነቀፋ ያለባቸውን አባ ተክለ ሃይማኖትን ያላጣማጅ በብቸኝነት አወዳድሮ ኤጴስ ቆጶስ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ መንግሥታዊ ድጋፍ ያላቸውን አባ ተክለ ሃይማኖትን ወይም አባ ኀይለ ማርያምን ሹሞ፤ መንግሥታዊ ድጋፍ የሌላቸውንና ቅቡል የሆኑትን ሊቀ ሊቃውንት እዝራን  አለመሾም ነው፡፡

ስሪታዊ ምርጫ  ቁርቁር ተሿሚዎችን መቀፍቀፍ ባሕርይው ነው፡፡ አሁን ያለው ሲኖዶሳችን የዚህ መንስኤ እና ተግብሮት ነው፡፡ ከስሞኑ የተካሔደው ምርጫ ደግሞ የተግብሮቱ ክትያ ነው፡፡ ሲኖዶሳችን ከዚህ ባሕርያዊ መገለጫው አኳያ፥ በአምስተኛው ዘመነ ፕትርክና የተሾሞ መለካውያን ኤጴስ ቆጶሳትንም ሆነ አሁን በእነዚሁ መለካውያን የተቀፈቀፉትን አዲሶቹን መለካውያን እጩ ኤጴስ ቆጶሳት አካቶ መሔዱ ግድ ነበር፡፡ ነገሩ ከእንክርዳድ ስንዴ አይለቀምምና ነው፡፡

ምእመኑ ለሚቀጥለው ትውልድና ስለነገይቱ ቤተ ክርስቲያን ህልውና ሲጨነቅ፤ አንዳንዶቹ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ዛሬ ሊያገኙ ስለሚጓጉት ተጨማሪ ሹመት፣ ቤት፣ መኪና እንቅልፍ አጥተው ይጨነቃሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰብዓዊ ገጻቸው ወደ ማኅበራዊ ትምክህተኝነት እንዲዘቅጡ አድርጓቸዋል፡፡ ምጣኔ ሀብታዊ ቅርምት ውስጥም ከቷቸዋል፡፡ ውጤቱ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መተረማመስ አስተዋጽኦ ያደረጉ የጥፋት ኃይሎች ዛሬ ደግሞ በእነሱ ትከሻ ላይ ታዝለው እንዲመጡ ረድቷቸዋል፡፡ የሚያስጨንቀውም የእነርሱ መምጣት ሳይሆን የአባቶቻችን መለካዊነታቸው አይሎ የተውኔቱ አባላት መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ መልኩ በሩ የተከፈተላቸው አተራማሽ ኃይለ ግብር ቁስላችንን ዘወትር እንዳሰፉት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከኦርቶዶክሳውያን መዳፍ ውስጥ ፈልቅቀው በማውጣት እና ዘላለም በሰማዕትነት ከአከበሯት አባቶቿ ብብት ውስጥ በመስረቅ አይሆኑ ሆና እንድትኖር ግዴታ ይጥሉባት ዘንድ ሢመታዊ መደላደልን ተቀዳጁ፡፡

ይህ ሲሆን ግን የእነ አቡነ ቄርሎስ፣አቡነ ቀውስጦስና አቡነ ገብርኤል ከለላ ሰጪነት፤ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን ጨርሶ ወደ ጥፋት፣ ወደ ውድመት፣ ወደ ሞት የመሔዷ ማስረጃ አይደለምን? በርግጥ እንዲህ ዓይነቱን የኋላ ሩጫ ከጀመርነው ይኼውና ሃያ ስድሰተኛውን ዓመት ጀምረነዋል፡፡ ሆኖም ግን የሰማዕታቱ ቤት፣ የነጻዎቹ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን እስካሁን ፈርሳ አላበቃችም፡፡ በእርግጥ ግን ተዋርዳለች፡፡ ውርደቷም በእርሷ ስም ያሉት መሪዎቿ መዋረድ ነው፡፡ እነሱ ምንም ይሁኑ ምን ፍርዱን ከእግዚአብሔር የሚያገኙት ሲሆን፥ የሚያሳዝነኝ ግን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር መጣኝ ባልሆኑ ድርጊቶቻቸው በሌላው ዓለም ፊት ተዋርደው የኛኑ ቤተ ክርስቲያን ማዋረዳቸው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከእነሱ መኖሪያ ቤት ክብር በታች ስትታይ ምን ይሰማችኋል? የቆራጦቹ ሰማዕታት ቤት፣ የነጻዎቹ ሊቃውንት ቤት ተዋረደች አያሰኝም?በርግጥ ነገሩ ሁሉ የተበላሸው አሁን አይደለም፡፡ ሢመተ ጵጵስናው ክብር ሲያጣ፣ የምልመላው መስፈርት ቦታ ሲያጣና ከሕግ ውጪ ያለ ምእመናን ይሁንታ ሲታደል ነው፡፡

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ሁሉ የበላይ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በእንዲህ ዓይነቱ መለካዊ ግብር መታጀሉ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ለእኔ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቁርቁር ሲኖዶስ አባላት ገጽ ይኼ ነው፡፡ የእናንተን ገጻዊ ትንታኔ ደግሞ በእናንተው መንገድ አሳዩኝ፡፡ ለእኔ ግን አሁንም ቁርቁራዊ ገጹ አይሏል፡፡ መንፈሳዊ ገጹ ኮስምኗል፡፡ የዘወትር ምኞቴም ሆነ መሻቴ እንደ ዘውድ የተቆጠረው ቆብ ተገቢውን ቦታና ሰው እንዲያገኝ ነው፡፡ የዘወትር ሕልሜ እውነት ሸባቢው “ዘውድ” ወልቆ እውነት አናጋሪው ቆብ እንዲጫን ነው፡፡ ይህም እውን የሚሆነው  ሲኖዶሳችን  ከመለካዊነት ወይም ከቁርቁርነት ወደ ኦርቶዶክሳዊ ኵላዊነት  ሲለወጥ ብቻ ነው፡፡ ይህንንም እናፍቃለሁ፡፡

(ከታደሰ ወርቁ)

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑