ከደርግ ወደ ጎሣዊ ደርግ- “ግንቦት 20” (ክፍል ፫)

ስደት

በመጀመሪያው ከደርግ ወደ ጎሣዊ ደርግ– “ግንቦት 20” (ክፍል ፩) ጽሑፍ ከ“ግንቦት 20” ሃያ መርዛማ ፍሬዎች መሃል ስለከሸፈው የፌዴራል ሥርዓት እና የትምህርት ፖሊሲው ክስረት ማተታችን ይታወሳል። በሁለተኛው ክፍል ሰለ መሬት ነጠቃ አስነብበናል በዚህኛው ክፍል ሁለት ደግሞ የአፓርታይዳዊ አገዛዝ አራማጁ ህወሓት ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ከዘራቸው በርካታ መርዛማ ፍሬዎች መካከል ቀጣዩን ከማሳያዎች ጋር ማስነበባችን እንቀጥላለን።

መርዛማ ፍሬ 4፡ ስደት

የኢትዮጵያዊያን የስደት ታሪክ ረዘም ያሉ ዓመታትን ያስቆጠረ፣ እንደየጊዜ ማዕቀፉ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መነሻ ምክንያቶች ያሉት ቢሆንም ካለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ወዲህ ያለው የስደት ታሪካችን በአመዛኙ ከፖለቲካ ነፃነት እጦቱ ጋር ተያይዞ በሚመጡ ችግሮች መሆኑ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። በዘመነ ህወሓት/ኢህአዴግ ያለው የስደት ጭብጥ መነሻው ዘረኝነት ባጠላበት አፓርታይዳዊ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ የተፈጠሩ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ለስደቱ አባባሽ ምክንያት ሁነዋል።

ምሁር ጠል በሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ሸፍጥ የተነሳ አገር ጥለው በተሰደዱ ምሁራን ቁጥር ኢትዮጵያን ከዓለም አገራት ቀዳሚ ተጠቂ ከሆኑት ውስጥ የሚያሰልፋት የOnlineuniversities.com ዘገባ፤ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያብራራል። እንደ ሪፖርቱ መደምደሚያ ባለፉት አስር አመታት ብቻ ኢትዮጵያ 75 በመቶ የሚሆኑትን የላቁ ምሁራን በስደት ምክንያት አጥታለች። የህክምና ባለሙያዎች የሚበዙበት ይኽው ስደት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ሳይሆን በህዝቡ ጤና መጓደል ላይ ጭምር ከፍ ያለ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።

በቦሌ በኩል ያለው አስፈሪ የስደት መጠን እንደተጠበቀ ሆኖ በሞት ሸለቆ ውስጥ የመጓዝ ያህል በሚከብደው የሰሃራ በረሃ የስደት ጉዞ ውስጥ በአሸዋው ተውጠው ፣ በቀይ ባህር ሰጥመው ፣ በአክራሪ እስላማዊ ቡድኖች ታፍነውና ታርደው፣ … የቀሩት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከግምት በላይ ነው። ብዙ ህልም ይዘው ቢወጡም ገንዘባቸው ባክኖ ህልማቸው ከመብነኑ ባሻገር ህይወታቸውን ያጡት፣ የመንፈስ ስብራት የደረሰባቸው ዜጎች የ“ግንቦት ሃያ” መርዛማ ፍሬ ሰለባ ናቸው።

በህገ-ወጥ መንገድ ከሚሰደዱ ዜጎች ውስጥ 60% የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። እንደ UNHCR (2013፣ 2014፣ 2015፣ 2016) ሪፖርት የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ቁጥር በየአመቱ እየጨመረ ሄዷል። ስደተኞቹ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ የዘለቀ የትምህርት ደረጃ ያላቸው፣ አነስኛ የሙያ ክሂል ባለቤት የሆኑ፣ የሚሰደዱበትን አገር መዳረሻ በቅጡ ያልለዩ፣ ከውጪ አገር ዜጎች ጋር የመግባቢያ ቋንቋ ችግር ያለባቸው መሆኑ የስደተኞቹን መከራ አብዝቶታል።

በሲጋራ ፍም ሰውነታቸው የተለበለበ፣ አሲድ ሰውነታቸው ላይ የተደፋባቸው ፣ ለወራት ተገደው የሚደፈሩ፣ የሰውነት አካላቸውን (ኩላሊት) የተቀሙ (Organ Traffic) ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ታሪክ መስማት የተለመደ ሆኗል። እንደ የመንና ሊቢያ ባሉ መንግስት አልባ አገራት በኩል የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን በሽብርተኛ ቡድኖች በመታገት አስከፊ እንግልት፣ ስቅየትና ግድያ ይደርስባቸዋል። በእገታ የሚያዙ ስደተኞች በአሸባሪ ቡድኖች አስገዳጅነት አገር ቤት ያሉ የቤተሰብ አባላት ገንዘብ እንዲልኩ እንደሚገደዱም በየጊዜው የምንሰማው የመከራ ዜና ነው።

በደቡብ አፍሪካ፣ በሊባኖስ፣ በኩዌት፣ በቤሩት፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ … ወዘተ በመሳሰሉ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አረብ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በግፍ ተገድለው በአደባባይ መጣላቸውን፣ በመኪና አደጋ ህይወታቸው ማለፉን፣ ከፎቅ ላይ ራሳቸውን በመፈጥፈጥ ህይወትቸውን ማጥፋታቸውን … መሰል አሰቃቂ የዜና ዘገባዎች እንደ ሜትሮሎጂ ዘገባ በየዕለቱ መስማት ከጀመርን ውለን አድረናል። የዜጎቹ የመከራ ዜና ግድ የማይሰጠው ህወሓት/ኢህአዴግ በብዙ ጭንቀትና መከራ ስደተኞቹ የሚያገኙትን ገንዘብ ለቤተሰብ መደጎሚያ ወደ አገር ውስጥ መላካቸው የምንዛሬ እጥረቱን የሚሸፍንለት በመሆኑ ህገ ወጥ ስደቱንም ቢሆን በበጎ ጎኑ ይመለከተዋል። የአገዛዙ ጭንቀት የምንዛሬ እጥረት እንጅ የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች  የመከራ ህይወት ግድ አይሰጠውም።

ምዕራባዊያኑም ቢሆን ለራሷ ዜጎች መሆን አቅቷት በወደቀ አገዛዝ ስር የምትከላወስ አገር መሆኗን እያወቁ “ኢትዮጵያ የስደተኞች ቤት” ሲሉ ከደቡብ ሱዳን የምንሻል መሆናችንን በምፀት ይነግሩናል። ራሱን ከሱማሌያ እና ከኤርትራ ፈራሽ “መንግሥታት” ጋር የሚያወዳድረው ህወሓት/ኢህአዴግ የራሱን ዜጎች አሰቃቂ የስደት ገመና ደብቆ ስለጎረቤቶቹ ያወራል።

የኢትዮጵያን ድንበሮች ተሻግሮ የሚደረግ ስደት እጅግ የከፋ አደጋ ያለው ተግባር መሆኑ እየታወቀ ኢትዮጵያዊያኑ ወጣቶች ወደ ኋላ አላሉም። በየጊዜው ከሚመጡ መረጃዎች አኳያ የስደቱ ቀዳሚ ተሳታፊ ክልሎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላ (አዲስ አበባን በውስጠ ታዋቂነት ይዘን) ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ክልሎች ህወሓት/ኢህአዴግ ምን ያህል የበረታ በደል እንደሚፈጽም አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነው። ከዚህ እውነታ አኳያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ስደትን ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ብቻ በመነሳት በፍቃዳቸው የሚያደርጉት አለመሆኑን መረዳት እንችላለን። ይልቁንስ ከፖለቲካ መዋቅሩ ዘረኛ አካሄድ የተነሳ የኢኮኖሚ የኃይል ምንጮች (የገቢ ሁኔታ) ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመንፀባረቁ ውጤት ነው። በጥቅሉ ስደት ከ”ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬዎች ውስጥ አንዱ ነው ስንል የኢኮኖሚ ውድቀቱ ከፈጠረው ጥልቅ ድህነት ባሻገር በፖለቲካ ጉዳይ በገፍ የተሰደዱ/ የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር የበዛ በመሆኑ ጭምር ነው።

“ጠላት” ካላበዛ ህልውናውን የሚያስረግጥ የማይመስለው ህወሓት/ኢህአዴግ በግፍ ጭቆና አስመርሮ ከአገር የሚያስወጣቸው ኢትዮጵያዊያን የአገዛዙ ራስ ምታት ሲሆኑ እየታየ ነው። የዲያስፖራው ፖለቲካዊ መከፋፈልና የውስጥ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የአገዛዙን ውድቀት በማፋጠኑ ረገድ ዲያስፖራው ደጋፊ ኃይል ነው። ላወቀበትም የመርዛማ ፍሬው ማርከሻ (ማምከኛ) ከምንጩ ዳር ይገኛል።

ኢትዮጵያን ላለፉት 26 ዓመታት በግፍ ሲገዙ የቆዩት የህወሓት/ኢህአዴግ ፖሊሲዎች ያፈሩት እነዚህን መርዛማ ፍሬዎች ብቻ አይደሉም። የእነዚህ ፖሊሲዎች ባለቤቶች ግን ማን እንደሆኑ ከላይ በመግቢያው ላይ ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ በሚገባ ተናግረውታል። እንዲህ ነበር ያሉት፤

“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …”።

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑