ከደርግ ወደ ጎሣዊ ደርግ- “ግንቦት 20” (ክፍል ፭)

ኢትዮጵያዊነትና ሰላማዊው ትግል

መርዛማ ፍሬ 7፡  የኢትዮጵያዊነት ፈተና!

ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን ከአካባቢያዊ ማንነትና ከጎሣ በተሻገረ ለኢትዮጵያዊነት መታመን ህይወትን እስከማጣት የሚደርስ ዋጋ የሚያስከፍል አደጋ ሆኗል። እስር፣ እንግልት፣ ስቅየት፣ ስደት፣ እልፍ ሲል ደግሞ ሞት በኢትዮጵያዊነት የመታመን አደጋዎች ናቸው። በዜግነት ማዕቀፍ የሚተረጎም የጋራ ማንነት በቀጨጨባት ኢትዮጵያ ዘውጋዊ ማንነት የፖለቲካ ሜዳው መገለጫ ሆኗል። ዘመናዊት ኢትዮጵያ እንደ አገር እውን ከሆነች ወዲህ ኢትዮጵያዊ መሆን (ዜጋ) እና ኢትዮጵያዊነት እንዲህ እንደ ህወሓት የአገዛዝ ዘመን የፖለቲካ ልዩነት ምንጭ እና አከራካሪ የሆነበት ዘመን አልነበረም ማለት ይቻላል። ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን ውስጥ የዘውግ ፖለቲካ የሁሉም ነገር መስፈርት በመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ፈተና ላይ ወድቋል። በዚህም የአንድነት ሳይሆን የመለያየትና የቅራኔ ምንጭ መሆን በህዝቡ ዘንድ ስጋትና ውጥረት ሲፈጥር ይታያል። ዘውጋዊ ግጭቶችም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እስከ ስፖርት ሜዳዎች ድረስ እየታዩ ነው።

በአካባቢያዊ ማንነት የታጠረ የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኙ ህወሓት የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለመቅበር ረዥም ርቀት ተጉዟል። በአደባባይ “የጋራ ማንነት የለንም” የሚለውን የታሪክ ኑፋቄ ከማስማት እስከ ታሪክ ክለሳ ድረስ፣ የቀደሙ የታሪክ ቁርሾዎችን በማንሳት ትውልድ ከፋፋይ ሃውልቶችን ከማቆም እስከ የወል የማህበራዊ እሴቶችን የማጥፋት እኩይ ድርጊት፣… የደረሱ አውዳሚ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል።

ቂምን ለትውልድ በማውረስ ኢትዮጵያዊነትን እያከሰመ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ለመሹለኪያ ይሆነዉ ዘንድ ትግራይን እንደ አገር የመገንባት ሂደቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። የቅኝ ገዥ ባህሪ የሚንፀባረቅበት ይሄው ድርጅት ኢትዮጵያን እንደ አገር ያቆሟትን አገራዊ አዕማዶች በማፍረስ ተጠምዷል። በርግጥ በዚህ እኩይ ተግባር የተጠመደው ህወኃት ብቻ ሳይሆን በተቃውሞ ጎራው ያሉት የዲያስፖራ አክራሪ ዘውጌ ብሄርተኞችም የድርጊቱ ተሳታፊ ናቸው። የሳይበር ልፈፋው መዋቅራዊ ድጋፋ ካለው የህወሓት አፍራሽ ድርጊት ጋር የሚነፃፀር እንዳልሆነ ግን እንረዳለን። የግራ ቀኙ አዉዳሚ ተግባር አገሪቱን ወደብተና እየገፋት ይገኛል።

የትላንቷ ኢትዮጵያ ፍጹም ልክ ነበረች ማለት ተገቢ ባይሆንም የጊዜውን አስገዳጅነት የተከለች ነፃ አገር ኢትዮጵያ መመስረቷ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይመስለንም። በዚህ አግባብ ኢትዮጵያዊነት በጭፍን የሚቀበሉት ውርስ ቀኖና አይደለም። ይልቁንም እንደዘመኑ ማህበረ-ፖለቲካ የለውጥ ሂደት እየተገለጸ የሚሄድና የሚሻሻል አካታች አገራዊ ምልከታ ውጤት ነው።

የትላንት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለዛሬው የኢትዮጵያዊነት እርሾው የሚዘነጋ አይደለም።ይህም ሆኖ ኢትዮጵያዊነት ባለበት መርገጥ ግድ የሚለው አጀንዳ ሳይሆን ተራማጅነቱን የማያቋርጥ የጋራ ቤት ምስረታ (አገረ-መንግስት) ሂደት ባካተተ መልኩ የዛሬዋን ኢትዮጵያ የሚመጥን የኢትዮጰያዊነት ስሜት ለመፍጠር የተሻለ መንገድ እንደሆነ ይስማናል። ኢትዮጵያዊነት ከአካባቢያዊ ማንነት በተሻገረ ዜግነትን የተንተራሰ የአገራዊ ምልከታ ውጤት ነው። በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ያሉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ቅርሶች መገለጫቸውና ሃብትነታቸው አገር አቀፍ እንዲሆን የሚያስችል መዳረሻውን (ግቡን) የጋራ ማንነት በማጠናከር ላይ የሚያተኩር አገራዊ ስሜት ነው።

እውነታው ከዚህ በተቃራኒው እየሆነ መሆኑ ግን ኢትዮጵያዊነትን ፈተና ላይ ጥሎታል። የኢትዮጵያዊነት ፈተና በማወሳሰቡ ረገድ ደግሞ ህወሓት መዋቅራዊ ኃይሉን ተጠቅሞ ሌት ተቀን ተግቶ እየሰራበት ይገኛል። በርግጥ ኢትዮጵያዊነት ከተጋረጠበት ፈተናም ሆነ ከቀደመ ውርስ ቀኖናዊ ባህሪው ተሻግሮ አካቶነት ያለው የጋራ ማንነት ማሳደግ የሚችል የአገራዊ ስሜት መገለጫ እንዲሆን ከተፈለገ የ“ግንቦት 20” መርዛማ ፍሬ ባለቤት የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ላይ መቅበር ግድ ይላል።

መርዛማ ፍሬ 8. የሰላማዊ ትግል መጨፍለቅ!

በ1987 ዓ.ም በብዙ ንትርኮች ግን ደግሞ በህወሓት/ኢህአዴግ ርዕዮት ዓለም የተቀነበበው “ሕገ-መንግስት” ሲፀድቅ፤ ምንም እንኳን እስካሁን ድረስ ለቀጠሉ የህዝባዊ ተቃውሞ ጥያቄዎች መስረታዊ መነሻ የሆኑ ጭብጦችን ቢያካትትም የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲመጣ ሊጠቀም ይችላል የሚያስብሉ አንቀፆችን አካትቶ ነበር። ለዚህ መሰሉ ተስፈኝነት አስተዋፆኦ ያደረጉት ደግሞ፣ በሰነዱ ላይ የተካተቱት በነፃ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት፣ እንዲሁም በምርጫ ፖለቲካ  ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ የሚያስችሉ አንቀፆች መኖራቸው ነበር።

ይሁንና ከነእንከኑ “ሕገ-መንግስቱ” ከፀደቀ ማግስት ጀምሮ በተደረጉት ተከታታይ ፌዴራላዊና የአካባቢ “ምርጫዎች” የመድብለ ፖርቲ ሥርዓት ህልው የሚሆንበትን ዕድል በመጥበብ ጀምሮ ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ ተዘርግቷል። በአገሪቱ የፖለቲካ ተቋማት መቃብር ላይ የቆመው አገዛዝ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት”ን ወደ  “ህወሓት/ኢህአዴግ ምክር ቤት” ቀይሮታል። የፖለቲካ ምህዳሩን በመዘጋጋት የተጠመደው አገዛዝ መንግስታዊና ህዝባዊ ሃብትን በመጠቀም እስከ እያንዳንዱ ቤተሰብ በወረደ የ1፡5 ጥርነፋ አወቃቀር ጠቅላይ አምባ ገነንነቱን አደንድኖታል። አገዛዙ የተቃወሞ ፖለቲካ አመራሮችን በማስር፤ በማሳደድ እና በማዳከም የብቻ የረዥም ጊዜ ገዠነቱን ለማፅናት ብዙ ርቀት ሄዷል። ይህም የአፈና መንገድ፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን ከጅምሩ ከመቀልበሱ ባሻገር በ“ሕገ-መንግስቱ” የተቀመጠውን የመድብለ-ፓርቲ ፖለቲካን የመመስረት  ህዝባዊ ዕድልን አጨልሞታል።

በውጤቱም አገሪቱን ወደብተና የሚገፉ ህዝባዊ አመፆች እዚህም እዚያም ገንፍለው ወጥተዋል። ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የኃይል አማራጭን የሙጥን ያለው አገዛዝ መንግስታዊ ፍጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። አገዛዙ የመጣበትን መንገድ ምርጫቸው ያደረጉ የነፃነት ኃይሎች በሚያደርሱት ጥቃት አገሪቱን “መንግስት” አልባ አስመስሏታል። በጎንደርና ባህርዳር አካባቢ በየጊዜው እየፈነዱ ያሉ ቦምቦች የጋዛ ሰርጥን ውጥረት የሚያስታዉስ ሆኗል። የፖለቲካ ነፃነት እጦት እና የሰላማዊ ትግል መጨፍለቅ ወደ ህዝባዊ አመጽ እና የህብዑ ጥቃት እንደሚገፋ የህወሓቷ ኢትዮጵያ ከበቂ በላይ ምሳሌ ነች።

ህወሓት/ኢህአዴግ “እታመንለታለሁ” የሚለውን “ሕገ መንግስት” በመጨፍለቅ የሚስተካከለው የፖለቲካ ኃይል የለም። “ሕገ-መንግስት” መኖሩ ትዝ የሚለውም ሆነ የሚያስታውሰው በአገዛዙ ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎችንና የፓርቲ-ፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦችን ከነፓርቲያቸው ለመምታት “ህገ – መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ …” የሚል ሃሳዊ የውንጀላ “ክስ” ለመመስረት ሲፈልግ ብቻ ለመሆኑ በተደጋጋሚ የታየ እውነታ ነው።

የኢትዮጵያን ማህበራዊ ስሪት በቅጡ መረዳት ባልቻሉት የትግራይ ሽፍቶች የሚመራው ህወሓት በበረሃ በኩል በምዕራባውን አንጋሾቹ ተረድቶ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የሰላማዊ ትግል ጀምበር ለአፍታ ፈንጥቃ ተመልሳ በማዘቅዘቋ ብረት ማንሳት ብቸኛ የነፃነት መንገድ ሆኖ ቀርቧል። አሁን ባለው ዘውጋዊ መካረር ኢትዮጵያን ለርስ በርስ ጦርነት የቀረበች አገር አድርጓታል። የችግሩ መውጫ ጫፍ ከነፖለቲካዊ ልዩነቶቻችንም ቢሆን የጋራ ጠላት የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ ላይ ሙሉ ኃይልን ማሳረፍ ያልተፈተሸው የትግል መንገድ ነው በማለት በርካታዎች ይከራከራሉ። ነውጥ አልባ ትግልን በፍጹም ልባቸው የሚደግፉና የሚያምኑበት ደግሞ በትክክለኛው አልተሞከረም እንጂ ነውጥ አልባው መንገድ ለኢትዮጵያ ችግር ፍቱን ነው ይላሉ፡፡ እስካሁን በኢትዮጵ የተካሄደውን ትግል ሰላማዊ የፓርቲ ምርጫ ትግል እንጂ እውነተኛ ነውጥ አልባ ትግል አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

የግንቦት ሃያን መርዛማ ፍሬዎች በተከታታይ ዕትም መዳሰሳችን ይቀጥላል።

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑