ሃያ ሰባት ዐመታት ያስፈልጉን ይሆን?

ሃያ ሰባት ዐመታት ያስፈልጉን ይሆን?

To read in PDF
”ፍትህና ሰላም ለሁሉም በእኩልነት የሰፈነበት ዐለም በሚለው አስተምሮው ታንጫለሁ”
አቶ ኦባማ የተቃርኖ ፈጣሪውን ኃያሉን ኔልሰን ሮ. ማንዴላ ዜና ረፍት ተከትሎ የተናገሩት ነበር፡፡  ይህቺ የሚመሯት ሃገር ከአሸባሪዎች ዝርዝሯ ውስጥ ገና በ2008 ብትሰርዛቸውም ቅሉ፡፡
በተደረገላቸው የሽኝት መርሐ ግብር ላይ አያሌ የቀደሙትና የአሁን የሃገር መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሽኝት ይመስለኛል፡፡ እንደውም ጥለኞችን ያጨባበጠ ኩርፈኞችን ቃል ያለዋወጠ ሽኝት ሁኖ አልፏል፡፡

ስለምን ግን ከኩባ እስከ አሜሪካ፣ ከኢራን እስከ እንግሊዝ፣ ከቻይና እስከ ኮሪያ፣ ከሩስያ እስከ ኢትዮጵያ አንድ ዓይነት ስሜትን መፍጠር ቻለ? ያሳደዷቸውና ያገዷቸው ሁሉ እንዴት ወደዷቸው?
የማንዴላ ትግል (ሕይወት) ብዙውን ሊያስማማ እንደውም ሁሉን ማስማማት የቻለ እውነት ላይ የቆመ ነበር፡፡ ለዚህም እውነት ተሰጡለት፡፡ ሰላም ፣ነጻነት፣ ፍትህና ይቅርታ ሁሉም ቢሆኑለት የሚሻው ድንቅ ጸባየ ሐልዎት ነው፡፡ ነጻነትና ሰላምን ፍለጋ ከእድሜያቸው ሩቡን በግዞት ቤት በእስር ሰዉት፡፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከገዛበት እድሜ የበለጠ በእስር ቤት ቆዩ፡፡ የሚገርመው መፈታታቸው ግን ይቅርታ ይደረግልኝ ብለው ጠይቀው አሊያም ምህረት ለምነው አልነበረም፡፡ ይልቁን የመኖር ነጻነት ካልታወጀ አልወጣም ብለው እንጂ!
የ97ቱን ምርጫ ብናስታውስ የተቃዋሚዎች አቅም እስር ቤት ሳይገቡ እስከመታገል ይመስል ነበር፡፡ እርግጥ አሁንም ድረስ በግዞት ማጎሪያ የተከረቸሙትን ነጻነት ናፋቂዎች መኖራቸውን ሳንዘነጋ፡፡ አንደ ድርጅት (ተቃዋሚ ፓርቲ) መሪዎችን ለቃቅሞ እስር ቤት ቢያስገባቸው በይቅርታ ወጡ እንድም ከሃገር ሊሰደዱ አንድም የለመደ ጩኸታቸውን ሊከፍቱ፡፡ በቅርቡ ኢንጅነር ኃይሉ በጻፉት መጻፋቸው ይቅርታ ለማኞችም ታሳሪዎቹ እንደነበሩ አሳብቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በነጻነት እጦት እንደያኔዋ የማንዴላ ደ/አፍሪካ ትምሰል እንጂ የእነማዲባ ስቃይ ቢነግሩት የሚከረፋ፣ ቢሰሙት የሚዘገንን፣ ቢያስቡት የሚሰቀጥጥ ነበር ያንንም የዘር መድሎ ለመታገል ነበር 27 ዐመታት እስር ቤት የገቡት፡፡ አሁን ዐለም እንደታነጸባቸው እንደኮራባቸውና እንደከነፈላቸው ያወራላቸው ማዲባ!!
የመናገር፣ የመጻፍ፣ የማሰብና እንደ ዜጋ የመኖር ነጻነቱን ተገፍፎ፤ ከዜጋ ዜጋ በሚመረጥበት፣ ራዕይ ማዘል እንጂ ሕልም ማለም በተነፈገበት፣ የምርጫ ነጻነት ታርዞ ተገደው በሚኖሩባት ኢትዮጵያ፤ እድሜያቸውን የሚሰዉ፣ ከግል ጥቅምና ክብር፣ ዝናና ሞገስ የተሻገረ ለፍትህና ነጻነት የሚታሰርላት ጀግና አጥታ ይሆን??
እኛስ በሃገራችን እንደ ዜጋ ተከብረን ለመኖር፣ የተሰማንን ብንናገር ሰሚ ለመታደል፣ ካልጠገበ ሆዳችን ቆንጥረን፡ ከጠወለገው ገላችን ሰውተን፡ ካዘነበለው ጎጆ ሰብረን፡ ከጎስቋላ ኑራችን ቀንሰን በምናዋጣው የጎደለው የሚሞላልን፣ የተዛነፈው የሚቀናልን፣ የልባችን ሀዘን የሚታበስበት፣ የየኑራችን ስብራት የሚጠገንበት ሀገር እንዲኖረን ስንት ዐመት ያስፈልገን ይሆን????  ሌላ ሃያ ሰባት ዐመታት ያስፈልጉን ይሆን?
ማንዴላ ከግዞታቸው መልስ፤ ሰው መሆናቸው ከመረጋገጡ በኋላ (ከእስራታቸው እንደወጡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ”አሁን ሰው ሑኛለሁ” ሲሉ እንደተናገሩት )፤ የህዝባቸውን እንባ ለመጥረግ የመሀረብ ስልጣናቸውን ከዘረጉ በኋላ የወሰዱት ብሔራዊ እርቅና ይቅርታ ምናልባትም ከነጻነትና ፍትህ ፍላጎታቸው በላይ በዐለም ላይ ያስጠራቸውና ያገነናቸው ነበር፡፡ ብዙዎች ማነዴላ ለነጻነት የከፈሉትን ዋጋ እስከመዘንጋት አድርሷቸዋል- ይሔ የስልጣን ላይ ይቅርታ!
”ጥላቻን ብወድ ኑሮ ነጻነቴን አላውቅም ነበር” የሚለው ንግግራቸውም የነጻነትን ዋጋና ጥጋት ያሳዩበት ሁኗል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ወቅት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲጓዙ
”አብራሪው ጥቁር መሆኑን ተመልክቼ ጥቁሮች መንዳት ይችላሉ እንዴ ብዬ አሰብኩ፡፡ ለካ ሳላውቀው ነጮቹ ለጥቁሮች የነበራቸው አስተሳሰብ በእኔ ውስጥም ተቀርጾ ነበር፡፡ በጣም ተናደድኩኝ” በማለት እንዴት ላደረጉላቸው በሰፈሩት ቁና መስፈር ያው ዞሮ እነሱን መምሰል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይህቺ ሃገር ይሄን ሙሴ ለማግኘት ስንት ዘመናት መጠበቅ ያስፈልጋት ይሆን? የሰው ቀለሙ ጎጥና ብሔር በሆነበት ስለአንድነትና ብሐራዊ ጥቅም ለማሰብ የሚያበረታ ቴዎድሮሳዊ-ሙሴ-ማንዴላ በየትኛው ዘመን ይነሳላት ይሆን? በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ኤርትራውያኑ የደቡብ አፍሪካውያንን የጦር መሳሪያ ለመግዛት መጠየቃቸው የደረሳቸው ማንዴላ ”እንዴት የእኔ ሃገር መሳሪያ ወንድምና ወንድምን ለማጋደል ይውላል” በማለት መከልከላቸውን ታሪካቸውን የተከተሉ ይናገሩታል፡፡ ያቺ የነጻነትን መንፈስ በልባቸው ያነገሰች ምድር፣ ያቺ ነጭ ለጥቁር ሲሰግድ ያሳየቻቸውና ክብርና ሙላት የሆነቻቸው ሃገር፣ ያቺ የድልና ነጻነት ዜማዋን እያቀነቀኑ ተስፋና ብርታት የሆነችላቸው ኢትዮጵያ እርስ በእርሷ ስታልቅ ማየት ሕመማቸው ነበር፡፡
አንደኛና ብቸኛ የስልጣን ዘመናቸውን በህዝባቸው ውስጥ የይቅርታ መንፈስ በማጽናት፣ ቁስሉን በማበስና ብሶቱን በማድመጥ ካሳለፉ በኋላ ለአፍሪካ መሪዎችና ለሌሎች የከበዳቸውን (በአፍሪካ የማይታሰበውን) ሌሎች ወጣቶች ይመሩ እኔ በቃኝ ብለው ሥልጣናቸውን አስረከቡ፡፡ ሌሎቹ የኢትዮጵያን ጨምሮ ቀድመዋቸውና አብረዋቸው ስልጣን ላይ የወጡ ለመውረድ ሩ..ቅ ሆኖባቸው መሰላል እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እርግጥ ነው በደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ ባይቀየር እንኳ መሪ ለእድሜ ልኩ የሚገዛበት ሃገር ትተው አልሄዱም፡፡
ተጨማሪ ከኤርምያስ እውነታዎች፡ የእድሜ ልክ መሪዎቻችን
የማንዴላ የሕይወት ርዕዮት መላ ዐለሙ የሚያነግሠው የገነነ እውነት ነበር፡፡ ነጻነት፣ ፍትህ፣ ሰላምና እርቅ፡፡ አንድ ጓደኛዬ ”የዐለም መሪዎች ሁሉ ተሰብስበው ስለማንዴላ ፍቅርና ክብር የሰበኩት ለምን መሰለህ?” አለችኝ
”ያው የግል እውነታቸው የዐለም እውነት ስለሆነ” አልኳት
”ያ ብቻ አይደለም መሪዎች ሁሉ እንደማንዴላ መሆን ይመኛሉ ይፈልጋሉም ግን አይችሉም፡ አልቻሉምም ስለዚህ ምኞታቸውንና ህልማቸውን በማንዴላ ውስጥ ሰለሚያዩት ያን ህልማቸው ነው የሚያከብሩት የሚያገኑት”
የማዲባ ሕይወት ሁሌም ይዘከራል፡፡ ሁሌም በውስጣችን ይሞላል፡፡ የእኛው ሙሴ ማዲባ እስኪመጣና አብረን እስክንዘክርለት ድረስ………

 : አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ጽሑፍ ነው፡፡

One thought on “ሃያ ሰባት ዐመታት ያስፈልጉን ይሆን?

Add yours

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑