የበረሃዋ ንግስት ከተማ -ክፍልአንድ

  የበረሃዋ ንግስት ከተማ

The Queen City of the Desert

dd

ከ500 ኪ.ሜትሮች በላይ ስለምንጓዝ በጠዋት መነሳት ይኖርብናል፡፡ በአዲስ አበባ ስሙ እንጂ አገልግሎቱና አቅርቦቱ ባልሰፋው አውቶቢስ መናኸሪያ ሳንቀሳቀስ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ሊል ነው፡፡ ከበር ለመውጣት ያደረግነው ሙከራ ታክስ አልከፈልክ፣ ጠፍተህ የመጣህ መኪና ነህ በሚል ከበሩ ተገተረ፡፡ ወትሮ ማልዶ 12 ሰዓት የሚነሳ መኪና ፪ ሰዓት ጉዞ ጀመረ፡፡

የመጓጓዢያ ሥርዓቱ (Transportation service) መሠረታዊ የአሰራር ለውጥ እንደሚያስፈልገው መናኸሪያ እንደረገጡ መረዳት ይቻላል፡፡ ዘመናት ጥለውት የሄዱት መናኸሪ ነውና፡፡ የከብት ትከሻ በመኪና ተቀይሮ የተሳፋሪው ጋቢና ኩታ በጃኬትና ሹራብ ተለውጦ እርሱ እዛው ሲቆረቆር ካለበት ነው፡፡ የተሳፋሪዎች መንገላታት ብርቅ አይደለም፡፡ ለሚጭኑት እቃ ሥርዓት ባለመበጀቱ ሁሉ ያሻውን ይጠይቃቸዋል፤ አንዱ የጫነበትን፣ ሌላው የክብደቱን፣ የቀረው ደግሞ ያወረደበትን! አማን አስጉዘኝ ብለው የተሳፈሩ መንገደኞች አማን መግባታቸው እንደ ኦማን ከተማ የራቀና ህልም ይሆንባቸዋል፡፡ በየመንገዱ እያቃሰተ ሲለው እየቆመ (እየተበላሸ) ለተጨማሪ ወጪ የሚዳረጉበት ግና ለዚህ ጥፋታቸው ሃይ ባይ የጠፋበት ሥርዓት ነው የነገሠው፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሳላጭ የሆነ (ቀልጣፋ) ሥርዓት መዘርጋት ፍቱን መፍትሔ ቢያመጣም ቅሉ አገልግሎቱ የሚሰጠው በልምድ፣ ሥርኣቱ የተወጠረው ባረጀ ገመድ በመሆኑ እርስ በእርስ ሲታከኩ መኖር ነው- እንዳይበጠስ አንድም የተበጠሰውን በመቀጠል፡፡ የሚያስተዳድረው አካል በዘመቻ ለመኪኖቹ ደረጃ ከመስጠት ባለፈ የደረጃ መለኪያና የየደረጃዎቹ ልዩነት እንኳ ያልገባው ይመስላል፡፡ ማኅበራቱ የሚያሰማሩትን መኪና አይቆጣጠሩትም የባለመኪና ባለቤት ኃላፊነት ነው በማለት፡፡ መንገደኞች ለሚገጥማቸው ችግር ሜዳ ከመቅረት በቀር አለሁላችሁ የሚል የተጓዦች ጥበቃ ማኅበር (ማዕከል) የላቸውም፡፡
እኛም የዚህ ሥርዓት እማኞች ሁነን ከ አ.አ 4 ሰዓት ላይ ወጣን በጊዜ እንደማንገባ ከወዲሁ ተረድተንዋል፡፡ ዘፋኞች በዘፈኖቻቸው፣ ገጣሚያን በብዕሮቻቸው ቀለም፣ ደራሲያኑ በጽሑፎቻቸው ቃላትና ሐረጋት፣ በፊልምና ድራማው በመቼትና ታሪክ መወቀሪያ በመሆን የምትነግሠው ፣ በታሪክና በህዝብ ልቡና ውስጥ በእንግዳ አላማጅነትና ፍቅር አጉራሽነት የምትወሳ፣ የግልጽነት ህዋ ቅርቅብ፣ በነጻነት ኮኮብ ከሚላት ከበረሃዋ ንግስት- ውቧ ከተማ- ድሬዳዋ ለመድረስ ሽምጥ ጉዞአችንን ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ተያይዘንዋል፡፡

                                                           Old railroad cars on railroad tracks, Dire Dawa, Harar, Ethiopia
ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ሰፍቶ፣ ረዝሞና ተባዝቶ አገሪቷን ማስተሳሰር ያልቻለው ይልቁን ለአካባቢው ተወላጆች ካልሆነ በቀር ታሪክና ዝና ሁኖ የቀረው የባቡር መስመር ትቶት የቀረውን የተቋረጠ ፣ መሬቱ የተቦደሰና የተቦረቦረ ሐዲዱን እያየነው በአውቶቢስ ውስጥ ሙዚቃ ደንቁረን እንጓዛለን፡፡

 

በዘመቻ የሰለጠነው መንግስታችን- አሁን ህዳሴ ባለው ዘመቻው የቀድሞውን ባቡር ለመመለስ ‘ህዳሴ-ባቡር’ ላይ በመሆኑ ከአሮጌው ጥቁር ብረት ማዶና ጎን የተደለደለ መሬት፣ የተካበ ድንጋይና የሚቀደደድ ተራራ ይታያል፡፡ የህዳሴውን እውንነት በጉጉት ናፍቀናል- የባቡሩን ጠረን ለሚያውቁት ይሸታልና!

rail way
የድሬዳዋ ጉዞ ሦስት ክልሎችን ማቋረጥ ይጠይቃል፡፡ ምንም’ኳ በረሃውን ሲያቋርጡ የትኛው በረሃ የየትኛው ክልል እንደሚወክል ከመረዳት ይልቅ አንድ የጤና ኬላ ወይም የውኃ ጉድጓድ ማን እንደሰራው ማወቅ ይቀላል፡፡ UN ወይም USAID ያሰራው ለመሆኑ ከአውራው መንገድ ማስታወቂው ቆሞ ይናገራል፡፡ ክልሎቹ ግን የምናቋርጣቸውን ዞንና ወረዳዎች (ከተሞች) የሚያውቃቸው ለመሆኑ ያጠራጥራል፡፡ እነ ሚኤሶ፣ አዋሽ፣ ወለጪቲ፣ መተሃራ፣ ሐረር ወዘተ (እንዲሁም ከስም ጥላቻ ገብተው ከታሪክ ሽሚያ ዘምተው ለእድገቱና ለለውጣቸው ግብዓት ያልሆኑላቸውን) እነ ቢሾፍቱ የተባለችው ደ/ዘይት፣ አዳማ የተባለችውን ናዝሬትና ጭሮ ያሉአት አሰበ ተፈሪ በዚሁ መንገድ ይገኛሉ (በኦሮሚያ ክልል)፡፡ የማዕከላዊውም መንግስት ያስቸገረን በዚሁ ነው- ከሥርዓቱ ይልቅ እንጎቻ መቀያየር፣ ከአሰራር ባህሉ ይልቅ ስም መሰረዝ መደለዝ መገልበጥ መውደድ!

way to DD Adama-Nazareth
በዚህ በምስራቅ ጉዞ ምናልባት በሰፊው የሚታይ ነገር ቢኖር የክልሎች እድገት አለመመጣጠንን ነው፡፡ ክልሎችን ታናናሽ አድርጎ የቀረጻቸው ሥርዓቱ እንዲያድጉ ሳይሆን እድል የሰጣቸው ምንዳን እንዲጠብቁና ባሉበት አቧራቸውን እንዲያቦኑ፣ የውኃ ጥማቸው እንዲግም፣ የት/ት እጦትና የጤና አገልግሎት ህልማቸው እንዳይነቃ ማድረግን መሆኑ ግልጽ ብሎ ይታያል፡፡ ለዘመናት ብትጓዝባቸው ያው ናቸው፡፡ ትላንት በረሃ ነበሩ ዛሬም በረሃ ናቸው፡፡ የተፈጥሮውን በረሃ ብቻ ሳይሆን የኃላቀርነትና አለመለወጥ በረሃነቱን ጭምር፡፡
ቁልቢ ስንደርስ አይን መያዝ ጀምሯል፡፡ ቆቦና ቀርሳ የተባሉ አውራ ወረዳዎችን አልፈን ደንገጎ ስንደርስ የሐረርን ቀጥያለ ሜዳማ መንገድ ተሰናብተን ወደግራ በሸለቆ በታጀበው የደንገጎ ጠመዝማዛ ቁልቁለት(ሲመለሱ ዳገት) ልብ የሚሰልብ ጉዞአችንን ቀጠልን፡፡ ድሬዳዋ የለውጥ ህዳሴ ላይ መሆኗን ለማሳየት በከዋክብት የተከበበ በመሰለው በብርሃን ትንታግ በተሞላው አዲሱ ሲሚንቶ ፋብሪካዋ ተቀበለችን፡፡

እንኳን ደህና መጡ
ከበረሃዋ ንግስት ከተማ
ድሬዳዋ

welcome to DD

በልጅነቴ የዘመርኩት ዜማ ትዝ ብሎኝ አንጎራጉር ጀመር፡፡
”አንቺ ድሬዳዋ ውብ ከተማችን
ነዋሪውን ሆነ የውጭ እንግዳን
በማስደሰት ረገድ ማን ይደርስብሻል
አንድ ሁለት አይደሉም ሁሉም ያደንቁሻል
መጋላ ከዚራ አሃ ሸጋው ገንደ ቆሬ አሃ
ብርቱኳን መንደሪን አሃ አፍሪው ለገሃሬ አሃ
አየሯ አ’ሀ ነፋሻነት አ’ሀ
ተስማሚ ነው አ’ሀ ለጤንነት!” ግጥሞቹን ብረሳቸውም’ኳ በዜማው እየታገዝኩ ሰባብሬ እየገጣጠምኩ ከትዝታዬ ስንቅ እየቆነጠርኩ ዘው ብዬ ገባሁ፡፡ እስከ 1994 ድረስ (እስከ መቶ አመቷ መሆኑ ነው) ብቸኛ የመንግስት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ት ቤት የነበረውን ሃይ ስኩልና ታዋቂ ተጫዋቾችን ያፈራውና በሃገሪቷ የራሱን ሊግ አቋቁሞ ይጫወቱበት የነበረው ስቴዲየም በመኪና የሚመጡትን ይቀበላሉ፡፡

ይቀጥላል……..

One thought on “የበረሃዋ ንግስት ከተማ -ክፍልአንድ

Add yours

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑