ትንሣኤ የክርስትና ምኑነው?

ትንሣኤ የክርስትና ምኑነው?

vክርስቶስ ከሙታን ባይነሣስ?cross

vትንሣኤ ባይኖርስ?

vየክርስትና ትምህርት መሠረትና አስኳል ምንድነው?

ትንሣኤ ሙታን ማለት ተለያይተው ይኖሩ የነበሩት ነፍስና ሥጋ እንደገና ተዋህደው መነሣትና ከሞት በኋላ በሥጋና በነፍስ ህይወት ማግኘት ማለት ነው፡፡ ለዚህም ለሰው ልጅ ከሞት የመነሣት አስተምህሮ መሠረት የሆነው የጌታችን የመድኋኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ ሰው ልጅከሞት የመነሳት አስተምሮ መሠረት የሆነው የጌታችን የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶሰድ ትንሣኤ ቀድሞ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በነብያቱ አንደበት ሁሉ የተመሰከረለት ነው ፡፡

ከክርስቶስ መነሣት በፊት (ቅድመ ትንሣኤ)

ለሰው ልጅ ከሞት መነሣት ሕያው መሠረት ስለሆነው ስለጌታ ትንሣኤ ፡ ዘመንን አቅርቦና አጉልቶ በሚያሳይ፤ የዘመን መነጽር በሆነው ትንቢት ቃል በነብያቱ ተነግሮለት በብዙ ተስፋ ሲጠበቅ የኖረ ነበር፡፡ ኢሳይያስ ሞት ለዘላለም እንደሚለወጥ ተስፋና እምነት ነበረው (ኢሳ 25፣8) እንዴት እንደሚለወጥና የዘመናት እንባ እንዴት እነደሚታበስ ሲያስረዳም ባርነት ቀረለት፣ ሞትንም በሞቱ ድል በማድረግ ያኔ ይታወቅበት የነበረው አበስብሶ በሲኦል በትር የመቅጣት የማሰቃየት ግብሩ ቀረ ተለወጠ በማለት በትንቢት መነጽር አርቆ ተመለከተው፡፡ ቅ/ጳውሎስም ይህ እውነት በእርግጠኝነት ስለመፈጸሙ ‹‹ ሞት ሆይ መውጊያህ የታለ? ሲዖል ሆይ ድል መንሣትህ የታለ?››[1] በማለት ሞት ድል በመነሣት ተውጦ ለዘላለም ስለመለወጡ አትቷል፡፡ ይህ ማለት በሰው ልጅ ላይ ሰልጥኖ ገኖ የነበረው ሞት ጸባዩ ተቀየረ፣ አቅሙን አጣ፣ የኃይሉ በትር ተሰበረ በነፍሳት ላይ የነበረው ድል መንሣት አበቃ ሲል ነው፡፡ ይህን የመገለጥ እምነት እንዲህ በሚል ምስጢር ጠቀለለው ‹‹ሙታን ህያዋን ይሆናሉ ሬሳዎችም ይነሳሉ ››[2] ሲል፡፡

ከዘመናት በኋላ የተቀባው ነብዩ ዳዊት ‹‹ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም››[3] በማለት ከዚህ ዓለም በኋላ ስላለው ሕይወት ያለውን መጓጓት ባሳየበት ቃል ተሰፈ፡፡ እርግጥ ነው ቅዱስ ዳዊት በአካል ሞቷል እውነት ነው ስለዚህ ነፍሱ በሲኦል ገብታለች ፡፡ ያኔ የገነት በር በመላዕክቱ ሰይፍ ተዘግታ ትጠበቅ ነበርና[4] ሥጋው መበስበስን አይቷል መሞት ብቻ ሳይሆን አፈር ሆኖ ነፍሱም በሞት ኃይል ተገዳ ትኖር ነበር እናም ከዚህ መከራ የሚያሳርፈውና ከሞት ኃይል የሚያወጣውን ታላቁን ትንሳኤ ይናፍቅ ነበር ፡፡

ML ስለዚህም ነፍሴ በሲኦል አትቀርም ሲል ተነበየ ፡፡ ቅድሱን ሲል አንዱና ብቸኛ ቅዱስ አምላክ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ መበስበስን (ሙስና መቃብር) ያይ ዘንድ አትተወውም ፡፡ ያለሐጥያት ያለበደል በመስቀል ላይ የሚሰዋው ክርስቶስ ፈጽሞ ተቀብሮ አይቀርም ይነሳል በማለት የእርሱም መነሳት ለዳዊት ነፍስ ከሲኦል መውጣት ዋስትና/መድህን/እንደሆነ ተናገረ ፡፡ሐዋርያው ጴጥሮስም ይህን በማረጋገጥ በምስክርነቱ እንዲህ ብሎ አፀናው ‹‹ስለክርስቶስ ትንሳኤ አስቀድሞ አይቶ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተነገረ››[5]

የሰው ልጅ ምልክትን አጥብቆ ፈላጊ ነው ፡፡ የክርስቶስን አምላክነት ለመረዳትና ለመቀበል አጥብቀው ምልክት ያሳያቸው ዘንድ ይወተውቱት እንደነበረ የተጻፈው ይህን ያስረዳል ፡፡ ምልክትን ለሚሻ ግን ቀድሞ ምልክት ተስጥቶት እንደነበር ሰዉ ግን ሁል ጊዜ አዲስ ፈላጊ እንደሆነ እንዲህ ብሎ ገስፆአቸዋል፤ እናንተ ምልክት ናፋቂዎች ታውቁት ዘንድ በመጻሕፍቱ ሁሉ የዮናስ ምልክት ተሰጥቷችሁ አልነበረምን ? እንግዲስ ስለምን ምልክትን ትሻላችሁ?[6]

ታሪኩ እንዲህ ነው ነብዩ ዮናስ የነነዌን ሰዎች ያስተምርና ይመልሳቸው ዘንድ ታዞ ነበረ፡፡ እርሱ ግን መሄድን እንቢ ብሎ ወደ ተርሴስ ሊኮበልል ከመርከብ ገባ፡፡ ዳሩ የተሳፈረባት መርከብ ልትሰበር እስክትደርስ ክፉኛ ክፉኛ ተናወጸች፡፡ በባሕሩም ላይ የመጣው ማዕበል አላቆም ቢል የተሳፈሩባትም ሰዎች ስለሃጢያታችን ብዛት ይሆናልና በማን ምክንያት እንደመጣ እናውቅ ዘንድ እጣ እንጣጣል ተባባሉ፡፡ እጣውም በዮናስ ላይ ወጣ እርሱም በእኔ ምክንያት ይህ ታላቅ ማዕበል እንዳገኛችሁ አውቃለሁና አንስታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ አላቸው እነርሱም እንዳላቸው አደረጉ፡፡[7] ክርስቶስም ከዚህ በኋላ ስለሆነው ምልክት ነበር ይነግራቸው የነበረው፡፡ ከባሕር ቢጣልም ጌታ ባዘጋጀለት ታላቅ ዓሣ ሆድ ለ፫ ቀናት /ሌሊትና ቀን/ ማደሩን ከ፫ ቀናት በኋላም ተርፎ የነነዌን ሰዎችን ያስተምር ዘንድ መሄዱን ታውቃላችሁ፡፡ የሰው ልጅ በመቃብር ሶስት ቀን ሶስት ሌለት ያድራል፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ፡፡ በኃይሉም ሞትን ድል አድርጎ ከሲኦል ላይ ድል መንሣቱንም ነጥቆ ይነሣል ብታምኑስ ይህን ህይወት በናፈቃችሁና ሌላ ምልክት ፍለጋ ባልቃተታችሁ (ባልደከማችሁ )ነበር፡፡ የነነዌ ሰዎች መጥተው ይፈርዱባችሁ ዘንድ አላች አታምኑ ዘንድ ትጠራጠራላችሁና አላቸው፡፡

ብዙው የመጸሐፍ ቃል የዘመናት ትንቢትና ምሣሌያቸውን በአንድ በክርስቶስ ትንሣኤና ስለሰው ልጅ ትንሣኤ መናገራቸው ያስረዳል፡፡ ሐዋሪያው ቅ/ጴጥሮስ እንዲህ እንዳለ ‹‹ነብያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ (በክርስቶስ ትንሳኤ ስለሚገኝው ድህነት ወይም የመነሣት ተስፋ እየፈለጉ ማለቱ ነው) በእርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ ስለክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ ፤በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር››[8]

እንግዲህ የዚህ በብዙ ትንቢት ምስክርነትና በብዙ ምሳሌዎች ማስረጃነት የተገለጸው የክርስቶስ የመነሣት ዜና የምስራች እንዲህ ነበር…   ያየው መስክሯል ይህም ምስክርነት እውነት ነው፡፡ ዮሐ ፲፱፥፴፭                       

Crusificatioon

ጊዜው ሌለት ተሰናብቶ ቀን የሚረከብበት በሰንበት ፍጻሜ በስራ ቀን መጀመሪያ ነው ፡፡ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛይቱ ማርያም በሞት የተለያቸው መምህር እንዴት እንደሆነ ያዩ ዘንድ ሽቱውን አዘጋጅተው ማለዳ ሳይደረስባቸው በሌሊቱ ውጋጋን ሲሮጡ ወደ አርማትየስ ሰው ወደ ዮሴፍ መቃብር መጡ -በዚህ ሰው መቃብር ውስጥ ወደ ተቀበረው ወደ መምህራቸው ክርስቶስ ዘንድ ፡፡

መምህራቸው በሥጋ ሳይለያቸው በፊት የቃሉን ትምህርት እየሰሙ የእጁን ተአምራት እየዩ ለፍቅሩ ተገዝተው በፍቅሩ ሲኖሩ ነበር ፡፡ ምንም እንኳ ስለክብርና ዝናቸው ሊገሉት በብርቱ ይፈልጉት የነበሩት ሊቀ ካህናቱ፤ በመጨረሻ ስለቃሉ ትምህርትና ስለ እጁ ተአምራት ወንጅለውት አሰሩት ፡፡ ከፍርድ ወንበርም አቁመውት በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ፈራጅ የሆነውን ፈረዱበት ፡፡ ስለፍርዳቸው በዚህ መምህር ላይ ያደረሱትን መከራና ግፍ ከነብዩ ኢሳይያስ ምስክርነት እንውሰድ እንጂ እኛስ እንገልጸው ዘንድ እንዴት ይቻለናል ?

የሰማነውን ነገር ማን አምኗልን? ምንም እንኳ ያለጥርጥር የነብዩ ኢሳይያስ ምኞት የማዳኑን ታላቅ ክብር መግለጽ ቢሆንም ቅሉ የበለጠ የክብሩን ልዕልና ለመግለጽ በተላከላቸው ሰዎች እንቢተኝነት የደረሰበትን የመዋረዱን ጥልቀነትና የሕማሙን መጠን መግለጽን መረጠ፡፡ በታላቅም የለቅሶ ድምጽ እየጮኸ የሰማነውን ማን አምናል ሲል በመጠየቅ ይጀምራል፡፡ የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጧ? ልእለ ኃያል የሆነው የሃይሉ መገለጫ ክንዱ ለነማን ተገልጣል ማንስ በማዳኑ ሥራ የተገለጠውን ኃይሉን ተረድቶታል? መልክና ውበቱን ማን አጠፋው? ባየነው ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባቱን ማን ሰወረው ? የተናቀ ከሰውም የተጠላ፤ ይህ ትርጉም የሞላው ሐረግ ነው፡፡ ሁለቱ ቃላት ከማዳኑ ጋር የሰውልጅ ስላለው ታሪክ የሚያስረዱን ናቸው፡፡ ከሰው የተጠላ የሚለው ስያሜ ጥልቅና ማለቂያ ስለሌለው ሐዘን ይገልጣል፤ በአይሁድ ስለመገፋቱ፤ በሀብታሞች፣ በተማሩት ታላላቅ አዋቂዎች፣ በሚሰበሰበው ሕዝብ፤ በየደረጃው፣ በየጾታው፣ በየማዕረጉ ስለመገፋቱ ያስረዳል፡፡ ከሰው መጠላቱ ተስፋ የሌለውና ክብሩን ያጣ መጨረሻው ሰው፣ መገለጡ ከብዙዎች ይልቅ ሞገስ ያጣና ከሰውልጆች የጎደለ እንደሆነ የሚገልጽ መጠላት ነው፤

በመቀጠልም የሕማም ሰው ሆነ አለ፡፡ ምን የሚደንቅ አገላለጽ ነው! በጣሙን ሐዘንና ሕማም የሞላው ሰው፣ ሕይወቱ ሁሉ ለስቃይ የተሰጠ፣ ሰውም ፉቱን እንደሚሰውርበት ተናቀ እኛም አላከበርነውም ፡፡ ከጠበቁት ሌላ ሁኖባቸዋልና ፊታቸውን አዞሩበት የመጠላት ራስ ሁኖ እንደማይረባ ቆጥረው ፊታቸውን ነሱት፡፡ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት ፤በሸላቶቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ ፡፡ ተጨነቀ ተሰቃየም፡፡ የሰው ልጅን ደዌ ሁሉ ተቀብሎ ሕማማትን ተሸከመ ፡፡ የሰዎችን የአዕምሮ ሕመም ለራሱ አደረገ፤ ሕመማቸውን ከሰው ማራቅና መውሰድ ብቻ ሳይሆን የእእምሮአቸውን ስቃይ አጥፍቶ ለእርሱ አደረገ፡፡

Holy Crossእንደተመታ ፤እንደተቀሰፈና እንደተቸገረ ብንቆጥረውም እርሱ ግን ስለ ሰው ልጅ መተላለፍ ቆሰለ፡፡ ስለበደል ሁሉ ደቀቀ፤ የሰው ልጅ የደህንነት ተግሳጽ በእርሱ ላይ አረፈ፡፡ እኛ ከፈጣሪ ጋር እንታረቅበትና ከጌታ ጋር ያለንን ሰላም እናገኝ ዘንድ የደኅንነታችን ተግሳጽ ለእርሱ አጸና፡፡ ያኔ ዓለም ሁሉ በእርሱ ቁስል ተፈወሰ ፡፡ የመንፈስ መታደስ፣ የኃጢአት ይቅርታ፣ የጌታ ልጅነት መመለስ መፈወስ ሆነልን፡፡ የመድኃኒታችን ስለሰውልጅ የተቀበለው የማዳኑ መከራ ዐለምን አዳነው፤ አሳረፈው፡፡ ገነትን ዘግቶበት ከነበረው ኃጢአቱ የመንጻቱ ማኅተም ሆነለት፡፡ ኃጢአት ሲባል እስከሞት የሚያስቀጣው ወንጀል ብቻ አይደለም ክርስቶስ የገዛልን ይቅርታ ይልቁንም ነፍሳችንን ለሞት ከሚሰጥ በሽታና በመመታቱና በመገረፉ ቁስል የእግዚአብሔርን ጸጋና መንፈስ ገዛልን እንጂ፡፡ ለውርደት የተገዛች ነፍሳችንን ሊያጸዳትና በደኅንነት ሊሞላት፣ በክብር ዳግመኛ ፈጣሪዋን ታገለግል ዘንድ ሊያድሳትና የእርሱ ልጆች እንሆን ዘንድ ፈውስን ገዛልን፡፡ ሁላችን እንደበጎች ተቅበዝብዘን በጠፋንና ወደገዛ መንገዳችን ባዘነበልን ጊዜ መምህራችን ፈጣሪ ዓለማት አልፋ ኦሜጋ ክርሰቶስ የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ ፡፡

ሊቀ ካህናቱ ግን ከክፉዎች ጋር መቃብሩን አደረጉ ተንኮልንም በአፉ አላገኙበትም እነርሱ ግን ከአመፀኞች ጋር ቆጠሩት እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጥያት ተሸከመ፤ ነፍሱንም ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ የማይሞተው ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፤ በሞቱ ህይወት ይሰጥ ዘንድ ሞተ፤ ሶኦልን ይበረብር ገነትን ይከፍት ዘንድ ሞተ፡፡ በዛች እለት በማእከለ ቀራንዮ አምላክ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ቀረበ፡፡ የሰው ልጅ የተራቆተውን ጸጋ መልሶ ለበሰ የተገፈፈውም ክብር ተመለሰ፡፡ ጥልን በመስቀሉ ገደለ ለሰው ልጅና ለፍጥረቱ ሁሉ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፡፡ ለሰው ልጅም ሰላምንም አደለ፡፡[9]

ለማየት ተከማችተው የነበሩ ህዝብ ሁሉ የሆነውን ባዩ ጊዜ ደረታቸውን እየደቁ ተመለሱ፡፡ የዩትም ሁሉ መሰከሩ በእውነት ጻድቅ ነው ሲሉ ምስክራቸውም እውነት ነው፡፡[10] ከዚህ በኋላ ከመስቀል ወርዶ በመቃብር አደረ፡፡ ……. ይቆየን

 

[1] ቆሮ ፲፭÷፶፬ና፶፭

[2] ኢሳ ፳፮÷፲፱

[3] መዝ ፲፭/፲፮÷፲

[4] ዘፍ፫÷፳፬

[5] ሐዋ ፪÷፴፩÷ሐዋ፪÷፳፰÷ሉቃ፲፫÷፴፮

[6] ማቴ፲፪÷፴፱ና፵

[7] ዮና ም.፩፥፬-፲፭

[8] ፩ጴጥ፩÷፲፩(አስረጅ፡- መዝ፳፩/፳፪፣ አሳ፶፫፣ መዝ፸፰/፸፱÷፰፭፣ መዝ፻)

[9] ቆላ ፩፥፲፱ ፣ ኤፌ ፪፥፲፮

[10] ኢሳ ፶፫ ፣ሉቃ ፳፫፥፵፯ ፣ዩሐ ፲፱፥፴፭

2 thoughts on “ትንሣኤ የክርስትና ምኑነው?

Add yours

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑