Christmas Vs ገና Vs Nativity-የመጀመሪያ ክፍል

Christmas Vs ገና Vs Nativity

የመጀመሪያ ክፍል

  • ለመሆኑ ሁለት የገና (ክሪስመስ) በዐል ለምነው የምናከብረው?            
  • በምድር ዘመን አቆጣጠር ክርስቶስ መቼ ተወለደ?
  • የክሪስማስ (ገና) በዐል ማክበሪያ ልምዶች ከየት የተገኙ ይሆን?     
  • ታህሳስ 25 እንዴት መከበር ጀመረ?
  • የመጀመሪያው የተዘገበ የኔቲቪቲ (ክሪስማስ) በአል የትና መቼ ነበር?   
  • የልደት በዐልስ ስለምን ማክበር ይገባናል?

እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ!!

ከክ/ዘመናት በፊት ክፉ መልአክ ወደ አንዲት ሴት (ሔዋን) የሞት መልእክት ይዞ መጥቶ ነበር፡፡ ሴቲቱም የጌታን ትዕዛዝ ተላለፈች፡፡ ይህም የዐለም ኋጢአት መጀመሪያ መሆኑ ነው፡፡ ሊቀ መልአኩ ቅ/ገብርኤልም የዘላለም ሕይወት ብስራት ይዞ ወደ ማርያም መጣ፤ የሁለተኛይቱ ሴት የፍቃድ ታዛዥነት የጸጋ ሁሉ ምንጭ የሆነ እርሱን አሰጠን፡፡

ሰው የሆነው አንድ ልጁ ክርስቶስ ወደ እኛ በጠለቀ ውርደትና በታላቅ ትህትና መጣ፡፡ ንጉስ ህዝቡን ከጠላት ይጠብቅ ያድናቸውም ዘንድ፤ ንጉሱ መድኅን ሊሆን መጣ፡፡ አዎ ክርስቶስ ንጉስ ነው እንደጌታ ብቻ ያይደለ እንደሰውም እንጂ፡፡ አዎ ንጉስ ነው- ስለ ትህትናው ፍጽምና ምክንያት ብቻ ሳይሆን፣ የራሱ ህዝብ ሊያደርገን በደሙ ቤዛነት ስለገዛንም ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ የአለማት ሁሉ ፈጣሪ በመሆኑ ንጉስ ነው፡፡ የእስክንድሪያው ቅ/ቄርሎስ ፟ክርስቶስ በፍጥረት ሁሉ ላይ የገዢነት ኋይል አለው ፟እንዳለውና መዝሙረኛውም እንደዘመረው መዝ 23፥7

ለምስራቃውያኑ ቀኑ የፍስሃ ቀን ነው ምክንያቱም የዘላለም ደኅነትን በሰማይ ከጌታ ዘንድ ተቀብለውበታልና፡፡ ለምዕራባውያንስ?

ለመሆኑ ሁለት የገና (ክሪስመስ) በዐል ለምነው የምናከብረው?

በምድር ዘመን አቆጣጠር ክርስቶስ መቼ ተወለደ?

ታህሳስ 25 እንዴት መከበር ጀመረ?

የክሪስማስ (ገና) በዐል ማክበሪያ ልምዶች ከየት የተገኙ ይሆን?

የመጀመሪያው የተዘገበ የኔቲቪቲ (ክሪስማስ) በአል የትና መቼ ነበር?

የልደት በዐልስ ስለምን ማክበር ይገባናል? የሚሉና ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች በዚህ ጽሑፍ ይዳሰሳሉ መልስም ይበጅላቸዋል፡፡

በምድር ዘመን አቆጣጠር ክርስቶስ መቼ ተወለደ?

በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዘመን አቆጣጠር መሠረት ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ከፍጥረተ ዐለም ጀምሮ የነበሩት 5500 ዘመናት ዘመነ ፍዳ ተብለው ወደ ታች እየጎደሉ (countdown) እስከ ዜሮ ድርስ ተቆጠሩ፡፡ የ5500 ዘመን ተቆጥሮ አልቦ (ዜሮ) ሲደርስ የክርስቶስ የተወለደበት አመት ሁኖ ዘመኑን ከኩነኔ (ፍዳ) ወደ ምኅረት ቀየረው ዘመናት እንደ አዲስ መቆጠር ጀመሩ፤ እየቀነሱ ሳይሆን እየጨመሩ፡፡ ከዚያም የምኅረት አመቶች ተቆጥረው አነሆ ዛሬ 2007 ዐ.ም ሆነ፡፡ የምድር ዘመንም 7507 ዐመተ ዐለም ሆነ፡፡

NativityIcon20th

ከላይ የተገለጸው አይነት ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላ የሚለው አቆጣጠር በአለም የዘመናት ቁጥር ላይም የተለመደ ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት BC (Before Christ) ተብሎ ከክርስትና ዘመን መነሣት (ከክርስቶስ መወለድ) በፊት ያለውን ጊዜ የሚያመለክት ሲሆን፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ጊዜ AD (Anno Domini ከላቲን የመጣ ሲሆን ‘in the year of the Lord’- በጌታ አመት እንደማለት) ተብሎ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን ተብሎ ከሚታመነው ቀን በኋላ ያለውን ዘመን ይገልጻል፡፡

በአሁን ጊዜ ከላይ ከተገለጹት ጋር የሚስተካከሉ ሌላ አይነት መግለጫዎች ይገኛሉ፡፡ BCE (before Common Era) ከተለመደው ዘመን በፊት እንደማለት ሲሆን የተለመደ የተባለው የክርስትና ዘመን ወይም የክርስቶስ መወለድን መሰረት አድርጎ የሚቆጥረው ዘመን ማለት ነው፡፡ CE (Common Era) የተለመደው ዘመን ማለት ሲሆን ከክርስቶስ መወለድ በኋላ ያለውን ዘመን ይገልጹበታል፡፡ በ BC/BCE/CE ያለው ‘C’ ፊደል Christ ወይም Christian ወይም Common የሚለውን ለመግለጽ ያገለግላል፡፡ BC ከBCE እነዲሁም AD ከCE ይህም ከ BC ጋር ምንም ልዩነት የላቸውም፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ የጊዜ አቆጣጠሮች ለአመታት የምዕራብ ከርሰ ምድር አጥኚዎች(archaeologist) እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ሁሉም የከርሰ ምድር አጥኚዎች ክርሰቲያን አለመሆናቸውን ተከትሎ የተወሰኑት የተለመደው ዘመን የሚለውን መጠቀም ጀመሩ፡፡ ይኸውም ከክርስትና ወይም ክርስቶስ ከሚለው አገላለጽ ጋር ላለመገናኘት ማለት ነው፡፡

ሌላኛው በዚህ ጽሑፍ የሚነሣው የዘመን ጊዜ ማሳያ AUC (ab urbe condita) የሚለው ነው፡፡ ከላቲን የተገኘ ሲሆን ‘from the foundation of the city’ ሮም የተመሰረተችበት አመት መነሻ አድርጎ የሚቆጥር የሮማውያን የጥንት የዘመን መስፈሪያ ዘዴ ነበር፡፡ መነሻው 753 BC በኋላ አንድ በማለት ይሆናል፡: ስለ ምድራዊው የዘመን መለኪያ አይነትና አቆጣጠር እግዚአብሔር ከፈቀደ በሰፊው በሌላ ጊዜ የምመለስበት ይሆናል፡፡

 

ዐመት

የጌታችን የመድኋኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ የተወለደበት ቀን (ዐመት) ብዙ አነጋጋሪና መላምቶች የበዙበት ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል የተለያዩ ጥናቶችና ዘገባዎችን መሠረት አድርገን ለመግለጽ እንሞክራለን፡፡

ሀ. ዝናው የናኘው ትውፊታዊው መላምት ታህሳስ 25 (እ.አ.አ) ዐመቱም AD 1 ወይም (1 CE) ያደርገዋል፡፡

ለ. ሐዲስ ኪዳን ትክክለኛ የተወለደበት ቀን ወይም ዐመት አይሰጠንም፡፡ ቀድሞ የተጻፈው የማርቆስ ወንጌል የሚጀምረው የክርስቶስ የመጠመቁን ዜና በማንሣት ነው ይሄም የጥንት አባቶች (ከሐዋርያት ጀምሮ) የክርስቶስ የትውልድ ቀን ወይም ዐመት የማወቅ ፍላጎት እንዳልነበራቸው የሚያሳይ ይሆናል፡፡

ሐ. የገዳም አበሚኔት የነበረው ሮማዊ መነኪሴ ዲዮናስዮስ ኤክስጂየስ ክርስቶስ የተወለደበትን አመት ወሰነ፡፡ የተጠቀመው ቀመር የሚከተለውን ነበር፡፡

  • ከክርስትና ዘመን በፊት በሮም ዓመታት የሚቆጠሩት ከከተማዋ መገኘት ጀምሮ ነበር፡፡ በዚህም 1 AUC ማለት ሮም የተገኘችበት ዐመት ሲሆን፣ 5 AUC ማለት ሮም የተገኘችበት አምስተኛ ዐመት ማለት ነው፣.. ወዘተ
  • ዲዮናስዮስም በትውፊት የሮማው ንጉስ አውግስጦስ 43 ዓመት እንደገዛና ንጉስ ጢባሪዮስ እንደተካው ተረዳ፡፡
  • በሉቃ 3፥1-23 ላይ ክርስቶስ 30 ዐመት የሞላው ጊዜ የንጉስ ጢባሪዮስ 15 የንግስና ዘመን እንደሆነ ይገልጻል፡፡
  • ስለዚህ ክርስቶስ በጢባሪዮስ ዘመን 30 ዐመት ከሞላው 15 ዓመቱን በንጉስ አውግስጦስ ዘመን ኖሯል ማለት ነው፡፡ የክርስቶስም ልደት አውግስጦስ በነገሠ 28 ዓመቱ ላይ መሆኑ ነው፡፡
  • አውግስጦስ ስልጣን ላይ የወጣው በ 727 AUC ነበር ስለዚህም ዲዮናስዮስ የክርስቶስን ልደት በ 754 AUC አደረገው፡፡
  • ዳሩ ግን ሉቃ 1፥5 የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በንጉስ ሄሮድስ ዘመን እንደሆነ ስለሚገልጽና ሄሮድስም በ750 AUC ስለሞተ ዲዮናስዮስ የክርስቶስን ልደት ከገለጸበት 4 ዐመት ይቀድማል ማለት ነው፡፡

መ. ፕሮፌሰር ዮሴፍ ፊትመር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይፋዊ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ በጻፈበት ወቅት “ምንም እንኳ የክርስቶስ የልደቱ ዐመት በእርግጠኝነት ባይታወቅም በመጀመሪያ ዐመት አልተፈፀመም፡፡ የክርስትና ዘመን የተጀመረው AD 1 ነው ተብሎ የሚገመተው ከ533 በፊት (ca. 533) በዲዮናስዮስ በተጀመረው የተሳሳተ ቀመር መሠረት አድርጎ ነው” በማለት ጽፏል፡፡

ሠ. በሰሜን አፍሪካ በ243 AD አካባቢ የተጻፈ ነው ተብሎ የሚታመነውና ጸሐፊው ያልታወቀ ሰነድ የኢየሱስን ልደት መጋቢት 28 ያደርገዋል፡፡ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅ/ቀሌሜንጦስ (ከAD 215 በፊት ያረፈ) ክርስቶስ በኅዳር 18 እንደተወለደ ያምናል፡፡ ታሪካዊ መረጃዎችን መሠረት አድርጎም ፕሮፌሰር ፊትመር የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በመስከረም 11 ቀን 3 BC እንደሆነ ይገምታል፡፡

ረ. በፓፒረስ ተቀርጾ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የህዝብ ቆጠራ በየ14 ዐመት እንደሚካሄድና በሮማውያን ቅኝ ግዛት ሥር በነበረችው በግብጽ ተካሂዶ የነበረው የሕዝብ ቆጠራ በ AD 104 እንደነበረ ይገልጻል፡፡ ይህ ጽሑፍ እንደሚገልጸው እያንዳንዱ ነዋሪ ለመቆጠር ወደትውልድ መንደሩ እንዲመለስ ይታዘዝ ነበር፡፡ ስለዚህም የሉቃስ 2 የህዝብ ቆጠራ በ 7BC ወይም በ8 BC እንደተካሄደ ይገመታል፡፡

ሰ. ቄሬኔዎስ የሶርያ አገር ገዢ የነበረበት ጊዜ AD 6 ነበር፡፡ ርዕሰ መንግስትነትን በ 9 BC ና በ4 BC መካከል ይዞ እንደ ነበረም ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ሉቃ 2፥2

nativity1 ወርና ቀን

አንዳንድ የወንጌል ተርጓሚዎችና ብዙ አጥኚዎችና ተመራማሪዎች በታህሳስ (December) የመሆን እድሉ ጠባብ ነው በሚለው ይስማማሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “በዚያ ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ” ይላል (ሉቃ 2፥8) ፡፡ አልበርት ባርነስ በወንጌል ሐተታ ላይ በሰጠው ትንታኔ

በሜዳ ላይ መንጋዎችን እየጠበቁ እዛው ማደር የተለመደ ባህል ነው፡፡ ወቅቱ ሙቀት የሚያይልበት ጊዜ በመሆኑ በመንከራተት እንዳይባክኑ ሌሊቱን አብረዋቸው ያድራሉ፡፡ ይሄ ባህል የአይሁዶችም ባህል በመሆኑ መንጋዎቹን ይዘው ወደተራራና ሜዳማ ስፍራዎች ፍለጋ በበጋው ወራት ይወጣሉ፡፡ ቅዝቃዜ እስከሚጀምርበት የጥቅምት ወይም የህዳር ወራት ድረስ እዛው ይቆያሉ፡፡ (አዳም ክለርክ የአይሁዶች መንጋ ይዞ ወደ በረሃ መውረድ ከፋሲካ (pass over) ጀምሮ የመጀመሪያ ዝናብ እስከሚታይበት ጊዜ ድረስ እንደ ሚቆዩ በእነዚህ ጊዜያትም ቀንና ሌሉቱን ያግዷቸዋል በማለት ጊዜውን ያረዝመዋል፡፡ የፋሲካ በአልም በጸደይ (spring) ወራት ስለሚጀምር ከዚህ ወራት የጀመሩ የመጀመሪያ ዝናብ እስከሚታይበት ማርቼዝቫን ወር መግቢያ (በአሁኑ ስያሜ በጥቅምትና ህዳር መሀል የሚገኝ ጊዜ ነው) ድረስ እዛው እንደሚቆዩ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንታኔ ክታቡ ላይ አስፍሮታል)

ክርስቶስ በተወለደበትም ጊዜ እረኞቹ ገና ወደ መኖሪያቸው ያልተመለሱ በመሆኑ ምናልባት የጌታችን ልደት ከታህሳስ 25 ወይም ዛሬ ክሪስማስ ከሚባለው ቀን የሚቀድም ይሆናል፡፡ በዚህን ጊዜ በተለይ በቤተልሔም አካባቢ በሚገኙ ኮረብታዎች ከፍታዎች ብርዳማና ዝናባማ ወቅት ስለሚሆን እረኞቹ በውጭ ሊያድሩ አይችሉም፡፡ ስለዚህም ከመስከረም መጨረሻ ላይዘል እንደሚችል ይገመታል ዳሩ ግን የጌታ የልደት ቀን ያልታወቀና ለማለጋገጥ ምንም መንገድ የለም፡፡

ክለርክ እንደጻፈው የተለያዩ አባቶችና ተመራማሪዎች የቀኑን እርግጠኝነት ለማረጋገጥ ጥረዋል፡፡

“ምንም እንኳ መንፈስ ቅዱስ በዝምታ ውስጥ ለአንዳቸውም የገለጠላቸው ምስጢር ባይኖርም ተመራማሪዎችና የሃይማኖት ቀናያን አባቶች በዚህ ዙሪያ የተለያዩ መላምቶችን በማቅረብ ትንሽም ቢሆን ጥረታቸውን አበርክተዋል፡፡ ፋብሪከስ የጌታን ልደት የተመለከተ ከ 136 ያላነሱ የተለያዩ ሐሳቦች የያዘ ዝርዝር አቅርቧል፡፡ የጌታ ልደት ቀንን በማለት በክርስትናው ያሉ ክፍሎችና ምሁራን የወራቱን የተለያዩ ቀናት ሰይመዋል፡፡ ግብጻውያን ጥር ላይ፣ ዋገንሴይል የካቲት ላይ፣ ቦቻርት መጋቢት ላይ፣ አንዳንድ በእስክንድርያው ቅ/ቀሌሜንጦስ የተገለጹት ሚያዝያ ላይ፣ ሌሎች በግንቦት፣ ኤጲፋንዮስ በሰኔ ላይ ስለሚያከብሩ ሲናገር፣ ሌሎች ሐምሌ ላይ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፣ በየካቲቱ የማይስማሙ ዋገንሴይል ሐምሌ ወርን ሲሰጡት፣ በመስከረም 15 ላይትፉት፣ በጥቅምት ስካሊገር ካሱይበንና ካልቪስየስ በጥቅምት ሲደርጉት የአብያተ ክርስቲያናት የበላይ ሥልጣን የያዘችውና በውሳኔዎቿ ስህተት እንደማይገኝባቸው የምትናገረዋ የሮም (ላቲን) ቤተ ክርስቲያን ታህሳስ 25 ሰይማ ታከብራለች፡፡” በማለት ጽፏል፡፡

ታህሳስ 25 (እ.ኤ.አ) እንዲከበር ለምን ተመረጠ?

ቀድሞ ከጥምቀት በዐል ጋር የጌታ ልደት እንደተከበረ ይገመታል፡፡ በእነዚህ በዐል ወደ ቤተልሔም የተካሄደው የሰብዐ ሰገል ጉዞ፣ የክርስቶስ መጠመቅ፣ መወለዱ ይታሰብ ነበር፡፡ አሁን በምስራቅ ኦርቶዶክስ፣ አንገሊካንና ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት የጥምቀት በዐል የታወቀ ሁኗል፡፡

እስከ ሁለተኛውና ሦስተኛው ክ/ዘመን ድረስ የልደት በዐል ማክበር በክርስቲያኖች ዘንድ ስምምነት የፈጠረ አልነበረም፡፡ እንደ ኦሪገን ያሉት አባቶች ጣኦት አምላኪዎች ለአማልክቶቻቸው የሚያከብሩት ልማድ ነው በማለት ይገልጹ እንደ ነበር ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ እርግጥም የክርስቶስ ትክክለኛ የልደት ቀን አለመታወቅና አለመዘገቡ ለክርክርና ለግምት ትቷቸው ነበር፡፡

አንዳንድ ዘገባዎች የአንቲዎች ቲዎፍሎስ (171-183 አካባቢ) የመጀመሪያው የታህሳስ 25 የልደት ቀን እንዲሆን መለየቱን ይገልጻሉ፡፡ ሌሎች በሶስተኛው ክ/ዘ ሂፖሊተስ (170-236 አካባቢ) የመጀመሪያው ጠቋሚ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

እንደ ግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክና ሌሎች አስተማማኝ ድርሳኖች የሚገልጹት መላምት የመጀመሪያዋ ቤ/ክ የልደት በዐል እንዳላከበረችና የመከበሩ ዜናም ቀድሞ የተገኘው የእስክንድሪያው ቅ/ቀሌሜንጦስ ባስተላለፈው ጽሑፍ ላይ የእርሱ ዘመን ግብጻውያን የጌታን ልደት Nativity ተብሎ በግንቦት 20 እንዳከበሩት ከሚገልጸው መረጃ ነው፡፡ በሶስተኛው ክ/ዘመን ማገባደጃ ላይ የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት ማክበር ሲጀምሩ በሮም ቤ/ክ ግን ተቀባይነት ያገኘው በአራተኛው ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ ነበር፡፡

በዚያን ወቅት ያሉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በዲሴምበር 25 (ታህሳስ 29 በኢትዮጵያውያን የቀን መቁጠሪያ) የኔቲቪቲ (የጌታችን ልደት) በዐል እንዲከበር ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር (AD 273 ቀድሞ እንደሆነ ይገመታል) ፡፡ ይህን እለት የመረጡበት ምክንያትም የጣኦት አምላኪዎች ታላው ክብረ በዐል dies natalis solis invicti (የማይሸነፈው የጸሐይ አምላክ ልደት) በመሆኑና ክርስቲያኖች (በዛን ወቅት እነሱም ያከብሩት የነበረ) ይሄን ቀን ለመውስድ እንደ ሆነ ያስረዳሉ፡፡

Mass of Christ (Christmas)

ክሪስማስ ከየት ተገኘ? ምንስ ማለት ነው?

የክሪስማስ (ገና) በዐል ማክበሪያ ልምዶች ከየት የተገኙ ይሆን?

በቀጣይ እንመለስበታል ይቆየን! መልካም በዐል ይሁልን!!

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑